• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 17 November 2015

    “ዘመነ አስተርእዮ”


    በሰመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

    የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።

    ለ2007ኛው የድኅነት ዓመት በሰላምና በሕይወት ጠብቆ ስላደረሰን አምላካችን የተመሰገነ ነው። ብዙውን አይተን፤ ብዙውን አሳልፈን ለዚች ታላቅ ቀን መድረሳችን ብቻ ልዩ የአምላካችን የቸርነት ስጦታ ነው።

    ያለፈውን ዓመት አብረውን ያከበሩ፤ አሁን ግን የሌሉ፤ ለዚች ዕለት መድረስ ያልቻሉና ሞተ ሥጋ የቀደማቸው ብዙዎች ነበሩ ዛሬ የሉም። እኛ ግን እንደእኛ መልካም ሥራ ሳይሆን እንደ አምላክ ቸርነት ብቻ ይቺን ተጨማሪ ዓመት ማየት ችለናል።

    የሕይወት ገጽታው ብዙ ስለሆነ በሕይወታችን የበለጠ አትርፈን፤ ተሳክቶልን፤ ተደስተን፤ ወይም ብዙ ነገር ከስረን ምኞታችን ሳይሳካልን ቀርቶ፤ አዝነን፤ ተክዘን በከባድ ውጣ ውረድ አሁን ካለንበት ደርሰን ሊሆን ይችላል፤

    ነገር ግን ከዚች ዕለት የደረስነው በምንም ይሁን በምን! በደስታም ይሁን በኃዘን፤ በስኬትም ይሁን በውድቀት ከዕድሜያችን ተጨማሪ ጊዜን አግኝተን በሕይወተ ሥጋ መኖራችን ብቻ በጣም ደስተኞች ሊያደርገን ይገባል።

    ምክንያቱም የሰው ልጅ የሚያስብበት፤ የሚያመዛዝንበት ጊዜን፤ የተመሰቃቀለውን ነገር ሁሉ ወይም ሕይወቱን የሚያስተካክልበት ተጨማሪ እድሜን ካገኘ ለተሻለ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ከፍተኛ ዕድል ይኖረዋል። በመሆኑም እግዚአብሔር ሆይ  ተመስገን! እያልን የሰጠንን ተጨማሪውን ጊዜያችንን እንድንሠራበት ያስችለን ዘንድ እንለምነው።

    እንሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማመድኃኒትእርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕጻን ተጠቅሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡ሉቃስ 2፡

    ይህ የያዝነው ወቅት የአምላክ ሰው መሆን የሚታሰብበት ወቅት ነው።ይህ ወቅት የጥምቀትን በአል ጨምሮ በግእዝ ቋንቋ “ዘመነ አስተርእዮ”ይባላል።የመገለጥ ወይም የመታየት ዘመን ማለት ነው።

    የመገለጥ ዘመን ወይም ዘመነ አስተርእዮ የተባለበትም ምክንያት፡

    የማይታየው፤የማይዳሰሰው፤  የማይወሰነው፤ ሰማይንና ሁለንተናዋን፤ ምድርንና መላዋን፤ በአጠቃላይ የሰው ልጅ ጥበብ የደረሰበትን እና ያልደረሰበትንም፤ የሚታየውንም የማይታየውንም ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ፤  ለሊቀ ነቢያት ሙሴ “ያለና የሚኖር ላከኝ ትላቸዋለህ” በማለት ራሱ እንደነገረው ለመኖሩ መጀመርያ፤ ለዘመኑም መጨረሻ የሌለው ሕያው አምላክ በፍጹም ተዋሕዶ የሰውን ሥጋ ለብሶ አምላክ ወሰብእ ወይም ሰውና እግዚአብሔር በመሆን የተወሰነበት፤ የተዳሰሰበት፤ የታየበት ወይም የተገለጠበት ዘመን ስለሆነ“የመገለጥ ዘመን ወይም ዘመነ አስተርእዮ”ይባላል።

    በመሆኑም

     ስለዚህ በአል ወይም ስለ አምላክ ልደት በምንማርበት ጊዜ ለግንዛቤ ያመቸን ዘንድ በሁለት አበይት አርእስት እንከፍለዋለን።

    አንደኛው  ክፍል የስሙን ወይም የስያሜውን ሰዋስዋዊ ትርጉም ወይም ፍች እና ታሪካዊውን አመጣጥ በጊዜ እየለካን፤ በቦታ እየወሰን በመከፋፈል በታሪክነቱ እንማረዋለን  ወደፊትም ቢሆን እናስተምረዋለን።

    በዚህ  በአንደኛ ታሪካዊ ክፍል፡የሚጠቃለሉ አበትይ አርእስት

    በዚህ ክፍል የስሞችን ትርጉም  ባጭሩ እንረዳለን ለምሳሌ ልደት፤ ዘመነ አስተርእዮ፤ አብ፤ ወልድ፤ አማኑኤል፤ ክርስቶስ፤ ኢየሱስ፤ መድኃኔዓለም፤  የሚባሉት እና ሌሎችም ተመሳሳይ ስሞች የሚሰጡን ትርጉም ምን እንደ ሆነና የስያሜ ምክንያታቸውንም የምንማርበት፤ ነው።

    እንዲሁም

    ·         አምላክ ማነው?፡

    ·         አምላክ እንዴት ተወለደ?፡  

    ·         አምላክ መቼ ተወለደ ?

    ·         በየት ተወለደ ?

    ·         ከማን ተወለደ ?

    ·         ለምን ተወለደ ?

    በሚሉት ንዑሳን አርእስት ስር ደግሞ ጊዜንና ቦታን መሠረት በማድረግ በቅደም ተከተላቸው እንመለከታቸዋለን።

    ምክንያቱም የድኅነታችን ታሪክ ስለሆነ የስያሜውን ትርጉምና የታሪካችንን ጉዞ ማወቁ የኅሊና እርካታ ከመሆኑም አልፎ የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ ለምናደርገው ጥረትም ይረዳናል።

     ምክንያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ“ እንግዲህ ያላመኑትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።” ሮሜ 10፡14 እንዳለው ሁሉ ካልተማርን አናውቅም፤ ካላወቅን መሥራት አንችልም፤ ካልሠራንም መዳን አንችልም ማለት ነው። ይህም የበአሉ ታሪካዊ ክፍል ይባላል።

    ሁለተኛውና ዋናው ግን የታሪኩ ባለቤት፤ የታሪኩ ተካፋይ ወይም የታሪኩ ተራኪ ብቻ ሆነን እንዳንቀር ከታሪኩ ተጠቃሚዎች መሆን ስላለብን ከታሪኩ ዘላቂ ተጠቃሚዎች ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ነው። ይህም የትምህርቱ መንፈሳዊው ክፍል ወይም መልእክቱ ሲሆን ራሳችንን የምናይበት መንገድ ነው።

    በሁለተኛ መንፈሳዊ ክፍል ወይም መልእክት፡ የሚጠቃለሉ አበይት አርእስት

    መንፈሳዊ ክፍል ወይም መልእክት በሚለው ክፍል ሥር ደግሞ በዚህ በአል ታሪክ ውስጥ የእኛ የሥራ ድርሻ ምን ነበር ድርሻችንንስ ተወጥተናል? ወደፊትስ በምን ዓይነት መልኩ ነው ድርሻችንን መወጣት የምንችለው? የታሪኩን መልእክት በተግባር በመተርጎም የምናገኘው ጥቅምስ ምንድነው? የሚሉትንና የመሳሰሉትን እንማርበታለን።

    በአጠቃላይ መልኩ ግን በዚህ የልደት በአል ስለ ኃያሉ አምላካችን ሁሉን ቻይነትና አለመወሰን፤ የባሕርዩ መገለጫዎች የሆኑት ስሞቹም የሚሰጡትን ትርጉምና እንዲሁም በማይወሰነውና ኢምክንያታዊ በሆነው ፍቅሩ እንዴት ወደ ዓለም እንደመጣና እንዳዳነን በመጠኑ እናያለን።

     እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋሉን ያድለን

    ትንታኔ

    ዓለምን ለማዳን በቤተልሄም የተወለደው የእግዚአብሔር ወልድ  ወይም የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስሞች፡

    ቃል፡ አንደበት መናገሪያ ማለት ሲሆን ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ በኩነት ወይም በመሆን ግብሩ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ስለሆነ ቃል  ወይም እግዚአብሔር ቃል ይባላል።

    ወልድ፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ይባላል፤ ወልድ ማለትም ልጅ ማለት ሲሆን የወልድም አካላዊ ግብሩ መወለድ ነው። ማለትም የአብ የባሕርይ ልጅ ስለሆነ እግዚአብሔር ወልድ ይባላል።

    አማኑኤል፡ አማኑኤል ማለት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚተረጉመው “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። ይህም ማለት በተዋሕዶ አምላክ ሰው ሰውም አምላክ በመሆኑ አምላክ ወሰብ ማለት ነው።

    ኢየሱስ፡ መድኃኒት ማለት ነው  መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “ለሰው ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ፤ የምሥራች፤ እነግራችኋለሁ ዛሬ በዳዊት ከተማመድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። በማለት መድኃኒት ሲል ይጠራዋል።

    ክርስቶስ፡ ቅቡዕ ወይም የተቀባ ማለት ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና በመሰሎቿ አብያተ ክርስቲያናት “የተዋሐደ” በመባል ይተረጎማል።

    መድኃኔ ዓለም፡ የዓለም መድኃኒት ማለት ነው ምክንያቱም ዓለምን ስላዳነ መድኃኔ ዓለም ይባላል።

    አምላክ ማነው?፡ አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ አምላክ ፈጣሪ ነው፤ ሰማይንና ሁለንተናዋን፤ ምድርንና መላዋን፤ የሰው ልጅ አእምሮ የደረሰበትንም ሆነ ያልደረሰበትን ሁሉ በአጠቃላይ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ ሕያውና ዘላለማዊ ነው። መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም ማለትም ጊዜና ቦታ አይወስኑትም።በሁሉ የመላ፤ በሁሉ የሚገኝ፤ የነበረ፤ ያለና ለዘላለም የሚኖር ነው። ይህንንም ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚከተለው ይገልጹታል።

    “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስወዴት እሸሻለሁ? 
    ወደ ሰማይ ብወጣ፥አንተ በዚያ አለህ።ወደሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። 
    እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥እስከባሕር መጨረሻም ብበርር፥ 
    በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህምትይዘኛለች። 
    በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊትበዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤ 
    ጨለማ በአንተ ዘንድአይጨልምምና፥ሌሊትም እንደቀን ታበራለችና፤እንደጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋነው።”መዝሙር 139 ፡7-12 

    “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ፤ ለእስራኤል ልጆች ያለና የሚኖር ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህአለው”። ዘጸ.3 ፡14

    አምላክ እንዴት ተወለደ?፡ ልደቱስ ምን ዓይነት ነው?አምላክ ሁለት ልደቶች አሉት እነዚህም ሁለት ልደቶች በተፈጥሮ ሕግ መመርመርና መታሰብ የለባቸውም። ምክንያቱም በተፈጥሮ ሕግ ሊፈጸሙ የማይችሉና ከሰው ልጅ ምርምር ውጭ የሆኑ አምላካዊ ሥራዎች ናቸው። እነዚህም

     1ኛ ቅድመ ዓለም ወይም ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ያለእናት ከባሕርይ አባቱ ከአብ የተወለደው ልደት ሲሆን ይህ ልደት በዘመን የሚወሰን አይደለም። እግዚአብሔር ወልድ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ተለይቶ ያልነበረበት ጊዜ የለም፤ በፍጡራን እንደ ተለመደው ልጅ ከአባት በኋላ እንደ ሚገኘው አይደለም አብና ወልድ በጊዜ አይቀዳደሙም።

     “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም አንዳችስ እንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” ዮሐ. 1፡1

    እንዲሁም በዚሁ ወንጌል ምእራፍ 8 ላይ “ከአብርሃም ትበልጣለህን?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” በማለት ለመኖሩ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው መሆኑን እናያለን።

    2ኛ ድኅረ ዓለም ወይም ከዓለም በኋላ (ፍጥረት ከተፈጠረ በኋላ) ያለአባት የመወለዱ ነገር-

    ከመወለዷ ከ700 ዓመታት በፊት በቅዱሳን ነቢያት ትንቢት ከተነገረላት ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተወለደው ልደትና አሁን የምናስበው ነው። “ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እንሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤ ” ኢሳ.7፡14 ይህንን ነቢዩ ኢሳይያስ ከ700 ዓመታት በፊት የተነበየውን ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎች እንደሚከተለው እየጠቀሰ ቅዱስ ዮሴፍን ሲያስተምርበት እናያለን። “ በነቢይ ከጌታ ዘንድ እንሆ ድንግል ትጸንሳለች ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው” ማቴዎስ 1

    አምላክ መቼ ተወለደ ? ቅድመ ዓለም ያለእናት ከባሕርይ አባቱ ከአብ የተወለደው ልደት ከዘመን ውጭ የሆነና ዘመን የማይቆጠርለት ልደት እንደ ሆነ 1ኛ ልደት በሚለው ንኡስ ክፍል አይተነዋል። ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደው ግን ከዛሬ 2007 ወይም 2014 ዓመታት በፊት ታህሳስ 29 ወይም መስከረም 29 ቀን ነው። (ትክክለኛ የልደት ቀን የሚባለውን ለማወቅ የዘመኑ ታሪክ የሚለውን መጽሐፍ ያንቡ) በመሆኑም “ዓመተ ምህረትን” ወይም  አዲስ የምህረት ዓመትን የጀመርንበት ቅጽበትም የሚቆጠረው ከተወለደባት ከዚች ቅጽበት ጀምሮ ነው።

    በየት ተወለደ ? አሁንም ቅድመ ዓለም ለነበረው ልደቱ ቦታ አይወሰንለትም። ድኅረ ዓለም የተወለደው  በትንቢቱ መሠረት በእሥራኤል አገር ከደቡባዊ ኢየሩሳሌም 6 ማየልስ ያህል ርቃ በመትገኘው በቤተልሄም በከፍቶች በረት ተወለደ። ቤተ ልሔም ማለት ሰዋስዋዊ ትርጉሙየእንጀራ ቤትማለት ነው። “የሕይወት እንጀራ” የሆነው መድኃኔ ዓለም በዚሁ ቦታ ተወለደ።

     ከማን ተወለደ ? ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ከአብ፤ ያለ እናት፤ ድኅረ ዓለም ደግሞ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ያለ አባት ተወለደ። “ ” ኢሳ. 7፡14፤ ማቴዎስ 1 ፤ ሉቃስ 2.

    ለምን ተወለደ ? አሁንም ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ የተወለደውን ልደት በምሥጢረ ሥላሴ መሠረት “የወልድ ወይም የልጅ ውስጣዊ የአካል ግብሩ ወይም ሥራው መወለድ ስለሆነ ብለን ከማለፍ በስተቀር የማይመረመር አምላካዊ ምሥጢር ነው።

     ድኅረ ዓለም ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተወለደበት ምክንያት ግን አዳምን ወይም እኔን እና እናንተን ወይም መድኃኒት ያልተገኘለትን ሕመምተኛ ዓለም በሞቱ   ከዘላለም ሞት ማለትም ከኃጢአት ለማዳን ነው። “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ ” 1ኛ ጤሞ.1፡15ታሪካዊውና ሰዋስዋዊው ክፍል ባጭሩ ይህንን ይመስላል ።

    ሁለተኛ መንፈሳዊ ክፍል ወይም መልእክት፡

    በልደት ታሪክ ውስጥ የእኛ ድርሻ ባጭሩ “

    የእኛ ድርሻ መወደድ ሳይገባን እኛን ፈልጎ፤ በፍቅራችን ተገዶ ወደ እኛ የመጣውን አምላክ በደስታና ልባዊ በሆነ ፍቅር መቀበል ነው። ከእርሱ የተቀበልነውንም ፍቅርና ሰላም እኛም በበኩላችን ያለምክንያት ወይም ያለምንም ውለታ ለሌሎች በነጻ መስጠት ነው።

    እግዚአብሔር ዓለሙን ወይም እኛን የወደደን እንዲሁ ያለምንም ምክንያት ነው፡

    በሥራችን አይደለም፤ ምክንያቱም ሥራችን የተጠላ ነበር፤ በሥልጣናችን፤ በመልካችን፤ በሐብታችን፤ በምንም አይደለም። የሚወደድ ያወም ሕያውን አምላክ የሰውን ሥጋ የሚያስለብስ ከዚያም አልፎ የመስቀል ሞትን የሚያስከፍል አንድም ተወዳጅ ሥራ አልነበረንም ።

    የሠራንለት አንድም ወለታ አልነበረም፤ እንዲያውም፣ እንኳን ውለታ ልንሠራለት ይቅርና በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮ፤ ሥልጣንንና ጥበብን ሰጥቶ፤ ሐብትን አድሎ፤ ገነትን የምታክል ቤተ መንግሥት ፈጥሮ በክብር ቢያስቀምጠን በአምላክነቱ ተነሣን፤ ከጠላት ዲያብሎስ ጋርም ተመካከርንበት። በአጠቃላይ ውለታ ቢሶችና የተሰጠንን ሁሉ የዘነጋን ነበርን።

     ነቢዩ ዳዊት የሰውን ልጅ የመጀመሪያ ክብርና በኋላ የመጣበትን መዋረድ ሲያነጻጽር “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ”ሰው የተከበረ፤ ከፍ ያለ፤ ልዩ ሆኖ ተፈጥሮ ነበር፤ ነገር ግን የተሰጠውን ስጦታ ወይም ተሰጦ አላወቀም፤ ሕይወቱን፤ ተሰጦውን አላወቀበትም። ስለዚህ እንደ እንስሳ ሆነ ይላል።

     የዚህ ዓለም ማለትም የሰው ልጆች ወይም የእያንዳንዳችን ችግር ከወላጆቻችን ከአዳምና ከሄዋን ጋር ተመሳሳይ ችግር ነው፤ መልኩን ለውጦ ይምጣ እንጂ ልዩነትም የለውም።

    በነፍሳችን ወይም በመንፈሳዊው ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን በሥጋዊው ሕይወታችን ጭምር ችግራችን እግዚአብሔር በተፈጥሮም ሆነ ከጊዜ በኋላ የሰጠንን ተሰጦ፤ የሰጠንን ስጦታ አለማወቅና አለማክበር፤ የተሰጠንን ሁሉ አክብረን አለመያዝ ነው። ባለን ሁሉ አለመርካት፤ የተሰጠንን ታላቅ ነገር እንደ ኢምንት በመቁጠር ያልተሰጠንን አሻግረን ስንመለከት በመዳፋችን ውስጥ የነበረንና የያዝነው ልዩ ሐብት፤ ልዩ እድል፤ ከእጃችን አምልጦ ይወድቃል። ከዚያም  በባዶ እጅ እንቀራለን።

     ይህ ነበር በአዳምና በሔዋን የደረሰው። ይህ ነበር ከአምላካቸው የለያቸው፤ ከዚያም አልፎ መድኃኒት ያልተገኘለትን የኃጢአት ደዌ ለአለም አወረሱት።

    የዚህ ዓይነት ችግር ነበር በአዳምና በሔዋን የደረሰው “ አምላካቸው ከሰጣቸው ተቆጥሮ የማያልቅ ጸጋ ይልቅ ዲያብሎስ በተንኮል ያቀረበላቸው አንድ ሩቅና የማይገባ ነገር ሐሳባቸውን ለወጠው። ለአምላካቸው የገቡትን ቃልም አስረሳቸው። ታዲያ ያንን የሕልም እንጀራ የሆነ አምላክነትን ለማግኘት ሲንጠራሩ የተትረፈረፈው ሙሉ ጸጋ ከእጃቸው አፈትልኮ ወደቀ። እነሱም ከክብራቸው ሁሉ ተራቆቱ፤ ባዶም ሆኑ።

    ታዲያ የሰው ባሕርይ እንደዚህ ክፉና አስቸጋሪ ከሆነ አምላክን ለዚህ በተዋሕዶ ሰው የመሆን ምሥጢር ያበቃው ምክንያቱ ምን ነበር? ቢባል መልሱ ኢምክንያታዊ የሆነ  ፍቅር ብቻ ነው የሚል ይሆናል።“ እስመ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለአለም እስከ መጠወ ወልዶ ዋሕደ ከመ ይህየው ኩሉ”ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ

    በእርሱ የሚያምን ሁሉየዘላለም ሕይወትእንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋእግዚአብሔር አንድያ ልጁንእስኪሰጥ ድረስዓለሙንእንዲሁ ወዶአልናዮሐንስ 3፡ 16።እንዲሁ የሚለው ቃልም የሚነግረን ያለምንም ምክንያት፤ ያለምንም ውለታ እንዲሁ ነጻ ፍቅር ማለት ነው።

    በዚያን ጊዜ ያለምክንያት የተሰጠን ፍቅርና የተገኘው ድኅነት ግን ከዘመነ ሥጋዌ ወይም ከቀራንዮ የቤዛነት ሥራ በኋላ ለምንፈጽመው በደል በውርስነት የሚያልፍ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን የሚጠይቅ ነው።

    ወደ ዕለቱ ወንጌል  እንመለስና  በበዚህ ዕለት ከተፈጸሙት ታሪኮች በመነሣት  ሕይወታችንን እንመልከት። መድኃኒታችን በቤተልሄም የከብቶች በረት በተወለደ ጊዜ

    ·         የጥበብ ሰዎች ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ይዘው መጥተዋል

    ·         የመንጋ ጠባቂዎች በዚሁ ቦታ ተገኝተዋል

    ·         ሰዎችና መላእክት በአንድ ላይ የሰላምን “መዝሙር ዘምረዋል።

    እነዚህ የጥበብ ሰዎች የሚባሉት ስንት አገር አቋርጠው ወደ ቤተልሄም የመጡት እንዲሁ አይደለም። 1ኛ (አንደኛ) በትንቢቱ መሠረት በቤተልልሄም የሚወለደው የዓለም መድኃኒት መሆኑን ስላወቁ ይህንን መድሃኒት በዐይናቸው አይተው ንጹህና ልባዊ የሆነ ስጦታን ስጥተው እነሱም የዘላለምን ስጦታ ተቀብለው ለመመለስ ከልብ በመነጨ ፍላጎት ነበር። በመሆኑም የፈለጉትን አግኝተው መስጠት የፈለጉትንም ሰጥተው ተመለሱ።

    በእለቱ መንጋቸውን ሲጠብቁ የነበሩት ጠባቂዎችም በቤተልሄም የተወለደው ለዓለም ሁሉ ለሰው ዘር ሁሉ ፍጹም ደስታ የሆነ የምሥራች ነው እና ሂዳችሁ ማየት አለባችሁ ተብለው በመላእክት ሲነገሩ በልባቸው ጥልቅ ፍላጎት አደረባቸው  በዚህም ምክንያት “እግዚአብሔር የገለጠልንን ነገር ማየት አለብን” እያሉ ወደ ቤተልሄም መሮጥ ጀመሩ። የተነገራቸውም ሁሉ እውነት ሆኖ አገኙት ። በመሆኑም የፈለጉትን አገኙ ማለት ነው።

    ማነኛውም ሰው የሚፈልገውን ካወቀ፤ የሚፈልገው ነገር ከማንና እንዴት መገኘት እንደሚችል ከተረዳና ለፍለጋ ሥራው በቂ ዝግጂትን ካደረገ የሚፈልገውን ይፈልጋል። ያገኛልም። መጽሐፍ ቅዱስም የሚለን ይህንኑ ነው ማንም ሰው እግዚአብሔርን ወይም ከእግዚአብሔር በፍጹም ልቡ ከፈለገ የሚፈልገውን ያገኛል።

    በትንቢተ ኤርምያስ 29 ፡13 ላይ “በፍጹምልባችሁም ከሻችሁኝታገኙኛላችሁ”። ይላል፤

    መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ለምኑ ይሰጣችኋል፤ በሩንም አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የለመነ ያገኛል፤ በር የሚያንኳኳ ይከፈትለታል። በማለት ነበር  ለፈለጉት ሁሉ ቅርብና የሚገኝ መሆኑን በማይታበለው ቃሉ የተናገረው። (ስለ ጸሎት በሌላው ትምህርታችን እንማራለን)

    ታዲያ ይህ ቀን ምን ዓይነት ቀን ነው?

    ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅምተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎይጠራል። ኢሳ.9፡6

    ቃሉ እንደሚለው የተወለደው መድኃኒት ነው (የሚያድን፤ የሚፈውስ ነው፤) ይህ መድኃኒት ዓለም ሁሉ ወይም የሰው ዘር ሁሉ ሊደሰትበት የሚችል ልዩ የምሥራች መልካም ዜና ነው። ደስታውና የምሥራቹ ለእኔ እና ለእናንተ ጭምር ነው።

    ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱሕዝቡንከኃጢአታቸውያድናቸዋልና ስሙንኢየሱስትለዋለህ። 

    የእግዚአብሔር ቃል በቤተልሔም የተወለደው ሕጻን የሰውን ዘር ሁሉ ከኃጢአት የሚያድንመድኃኒት ነው ይላል። ይህ ለዓለም የተሰጠው ድኅነታዊ የምሥራች ከልብ የገባቸውናለዘመናት ተለያይተው የነበሩ ሰዎችና መላእክት በአንድ ላይ የሰላምን መዝሙር ዘመሩከዓለም የማይገኘ ዓለም ሊሰጠን የማይችል የዘልዓለም ሰላም ለሰው ልጅ ተሰጠ። ከሁሉም በላይ  የዘላለም መንግሥትን የሚያወርስ የምሥራች ነበር፤

     “ለሰው ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ፤ የምሥራች፤ እነግራችኋለሁ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒትእርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።

    በመሆኑም ይህ ቀን የሰላም ቀን ነው፤ ይህም ሰላም ዓለም ለዓለም እንደሚሰጠው ያለ በቅጽበት መልሶ የሚጠፋ ሰላም ሳይሆን “የሰላም አለቃ” ተብሎ ከተጠራው ከዘላለም አምላክ የተሰጠ የዘላለም ሰላም ነው። በመሆኑም ይህ ዕለት ዓለም ሊሰጠው የማይችለው ዘላለማዊ ሰላም የተገኘበት ዕለት ነው፤ ሰላማችን የእግዚአብሔር ቃሉና ልጁ የዓለም መድኃኒት፤ የዓለም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እለት ስለሆነ  ዛሬ

    በጨለማ የኖረው ዓለም ልዩ ብርሃንን ያየበት ዕለት ነው፤  “በጨለማ የሄደ ሕዝብብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩብርሃን ወጣላቸው” ። ኢሳ.9፡2

    ልደት የሰላም ቀን፤

    የፍቅር ቀን፤

    የደስታ ቀን  ነበር አሁንስ?

    በእኛ ውስጥ፤ ልደቱን በምናከብር በእያንዳንዳችን ልቡና ውስጥ እነዚህ ነገሮች ቦታ አግኝተዋል ወይስ አላገኙም? ሰላምን፤ ፍቅርን፤ ደስታን፤ ስማቸውን ብቻ የሚጠራቸው በጣም ብዙ ነው። ነገር ግን የሚኖራቸው ወይም የውጤታቸው ተጠቃሚ የሆነው ሕዝብ ስንት ነው? የእኛስ ምድብ ከየትኛው ነው?

    እስኪ እንደገና ወደ ቤተልሔም እንመለስ፤ በእግረ ኅሊናም እንጓዝ፤ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት አስደናቂና መልካም ነገሮች ሌላ በቤተልሔም ውስጥ የተፈጸሙ ተቃራኒ ድርጊቶችም ነበሩ። ከብዙዎቹ መካከል አንዱን እንመልከት፡

    ሁላችንም ልንወያይበት የሚገባ ልናስብበት የሚገባ ራሳችን ልንመረምርበት የሚገባ የያንዳንዳችንን ሕይወት ሊዳስሥ የሚችል አንድ ታላቅ ችግር በቤተልሄም ውስጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡

    ይህም ችግር ዓለምን ያስደነቀ፤ አለም የሚወያይበት፤ እኔ እና እናንተም አዘውትረን የምንጠቅሰው፤ ዝነኛ እና አስደናቂ አስገራሚም ችግር ነው።

    ችግሩም በቤተልሄም ውስጥ፤ በቤተልሄም ዙሪያ ነጻ የሆነ ወይም ያልተያዘ ቤት አለመኖር ነው፤

    “በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራስላልነበራቸው በግርግምአስተኛችው”። ሉቃስ 2፡7

     ሁሉም ቤቶች ሙሉ ነበሩ፤ ከየአለማቱ በመጡ ሰዎች ተሞልተው ስለነበረ “ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን የዓለም መደኃኒት ሊገባበት ወይም ሊዳበልበት የሚችል ቤት አልተገኘም። አልነበረም።  ቤት አልነበረም ። የሰዎች ቤት ስለጠፋ አምላክና የአምላክ እናት፤ እንዲሁም ለዚህ ታላቅ የሥጋዊ ታሪክ የተመረጡ የአምላክ ተከታዮች ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ በከብቶች በረት ውስጥ ማደር ነበረባቸው። ምክንያቱም ባዶውን የነበረው ያ የከብቶች በረት ብቻ ነው። ባዶውን ስል በውስጡ ሰዎች አልነበሩም ለማለት ነው እንጂ ለዚህ ቅዱስ አገልግሎት የተመረጡ አስደናቂ ፍጥረታትስ ነበሩ። ሌላው ግን በሌላ የተሞላ ነበር። አምረውና ተውበው የታነጹት ቤቶች በእንግዶች ተሞልተው ስለነበሩ በቤተልሄም የተወለደውን መድኃኒት መጨመር አይችሉም ነበር።

    እያንዳንዳችን ለአምላክ ማደሪያነት የተፈጠርን ወይም ተውበን የተሠራን፤ በደሙ የተገዛን፤ ወይም የተገነባን በእርሱ ቤዛነት የታነጽን ቤቶች ነን።  ቤት ማለት ማደሪያ ማለት ነው። ለምሳሌ ቤተ መቅደስ ማለት የመመስገኛ ወይም የማመስገኛ ቦታ፤ ወይም የእግዚአብሔር ማደሪያ ማለት ነው። ስለዚህም  የእያንዳንዳችን አካል ቤተ መቅደስም ይባላል።

    “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁየእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁአታውቁምን? ” 1ኛ ቆሮ. 3፡16 ቤተ መቅደሱ ለባለቤቱ ለልዑል እግዚአብሔር ብቻ የተጠበቀ መሆን እንደ ሚኖርበት ሁሉ የእያንዳንዳችን አካልም ለአምላካችን የተጠበቀ ካልሆነ እና በሌሎች (በተንኮል፤ በቂም፤ በሐሰት፤ በዝሙት፤ በስርቆት፤ በክህደት፤ በጥላቻ) የተመላ ከሆነ፤ እነዚህ መጥፎ ሥነ ምግባራትም የዲያብሎስ መሣሪያዎች ስለሆኑ  በአካል ቤቶቻችን ውስጥ ዲያብሎስ እስከ መሣሪያዎቹ ከትሞበት ከሆነ፤ ከዛሬ 2000 ዓመታት በፊት በቤተልሄም አካባቢ እንደ ነበሩት ቤቶች መሆናችን ነው። እግዚአብሔርን ማስተናገድ አንችልም።  እግዚአብሔር ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት እንግዶች ጋር መዳበል አይወድም፤ እኛ የአምላካችን ማደሪያ ቤቶች መሆን የምንችለው ለአንድ ጌታ ብቻ የተዘጋጀን ስንሆን ብቻ ነው።

    ለሁለት ጌቶችመገዛት የሚቻለውማንምየለም፤ ወይም አንዱንይጠላልሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደአንዱይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ለእግዚአብሔርና ለገንዘብመገዛትአትችሉም። ማቴ 6፡ 24

    አሁን፡ሁላችንም ራሳችንን እንመርምር፡

    በቤተልሄም የተወለደው አምላክ ወደእኛ ቢመጣ ወደ ቤታችን ቢመጣ፤ ቤታችን ለእርሱ ብቻ የተዘጋጀ ነው ወይስ አይደለም? በቤታችን ውስጥ ወይም በአካላችን ውስጥ የሚገኙት ኢምክንያታዊ ፍቅር፤ ሰላም፤ ቅንነት፤ እውነት፤ ታማኝነት፤ ከሆኑ በእውነትም ከነዚህ ጋር መድኃኔ ዓለም መስተናገድ ይችላል፤መዳበል ይችላል።

    ነገር ግን በተቃራኒው ቤታችን የተመላው በተቃራዊው ከሆነ የቤተ ልሄም ቤቶች ነን ማለት ነው፤ ሕያውን አምላክ ማስተናገድ አንችልም። በእንግዶች አማልክት ተመልተናል ማለት ነው።

    የልደት ትርጉም በወቅቱ የተሰበከውን ለዓለም የተሰጠውን ኢምክንያታዊ ፍቅርና ሰልም በንጹህና በቅን ልቡና መቀበልና ለሌሎችም መስጠት ነው፤ ይህ ነው የልደት ትርጉም፤ የምንሰጠው ስጦታ ሁሉ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ያስቀደመ ካልሆነ ልደታዊ ትርጉም አይኖረውም።

    ታሪክን ተራኪዎች፤ በታሪክና ለሌሎች በሆነው ነገር የምንመካ ብቻ ሳንሆን ታሪክ ሠሪዎችም እንድንሆን፤ በዳዊት ከተማ የተወለደውንመድኃኒት፤ ለሰው ሁሉ የሚሆነውን ታላቅ ደስታ በሕይወታችን ማብሠር፤ ወይም መናገር እንድንችል  አምላካችን ይርዳን። 

    መልካም የልደት በአል።

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    አሜን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: “ዘመነ አስተርእዮ” Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top