• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 17 November 2015

    የዘመን አቆጣጠር ክፍል ሁለት፤


    መባጃ ሐመር                                                            

        የሁለት ቃላት ጥምር ነው፤መባጃ ማለት መሰንበቻ መቆያ ማለት ነው፣የሚያገለግለውም ለበጋ ነው።ለክረምት “ እንደምን ከርመሃል፤” እንደሚባለው ሁሉ ለበጋ ” እንደምን ባጅተሃል፤  ” ይባላል።ሐመር ማለት ደግሞ መርከብ ማለት ነው፤መርከብ የባሕር ላይ መመላለሻ እንደሆነ ሁሉ መባጃ ሐመርም በዓላትና አጽዋማት በየዓመቱ ለመመላለሳቸው መሪ ነው።መባጃ ሐመርን የምናገኘው የዓመቱን መጥቅዕ እና የመጥቅዕን ዕለተ ተውሳክ በመደመር ነው።ጻድቁ ኖኅ መጥቅዕ / ደወል/ እየመታ መርከቡን እንደሠራ እኛም በዕለተ መጥቅዕ መባጃ ሐመርን እናወጣለን። በመጽሐፈ ኩፋሌ፡፮፥፳፯ ላይ እንደተጻፈው ኖኅ መርከቡን ሠርቶ የጨረሰው በሁለት ኢዮቤል ዩ ነው፤መባጃ ሐመርም በሁለት ክፍለ ዘመን በሐጋይ/ በበጋ/ እና በጸደይ ይፈጸማል። ይኸውም  ጾመ ነነዌ በሐጋይ(በበጋ) ላይ፥ ጾመ ድኅነት(የዓርብ ረቡዕ ጾም) ደግሞ በጸደይ ላይ በማረፋቸው ይታወቃል።

                                                          ጾመ ነነዌ፤                                                        

           ጾመ ነነዌ በመባጃ ሐመር ብቻ ያለ ተውሳክ(ያለ ተጨማሪ) ይወጣል፤የተቀሩት በዓላትና አጽዋማትም የሚውሉበት ወር ይታወቅ ዘንድ መነሻ ሆኖ ያገለግላል። ጾመ ነነዌ የሚውልበት ወር መጥቅዕ በዋለበት ወር መሠረት ይወሰናል። መጥቅዕ ከ፲፬ በላይ ሆኖ በመሰከረም ከዋለ ነነዌ በጥር ትውላለች፥ከ፲፬ በታች ሆኖ በጥቅምት ከዋለ ደግሞ ነነዌ በየካቲት ትውላለች። መጥ ቅዕ ከ፲፬ በላይ ሆኖ ከዕለት ተውሳክ(ተጨማሪ) ጋር ስንደምረው ከ፴ ከበለጠ ነነዌ በየካቲት ትውላለች። መጥቅዕ አልቦ /ዜሮ/ በሚሆንበት ጊዜ መስከረም ፴ የሚውልበት የዕለት ተውሳክ መባጃ ሐመር ይሆናል። በዚህን ጊዜም ጾመ ነነዌ በየካቲት ትውላለች።                                                  

                                 ተውሳክ፤                                                               

             ይህ ቃል፡-“ወሰከ - ጨመረ፤” ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ በመሆኑ ተጨማሪ ማለት ነው።በባሕረ ሐሳብ ስሌት ሁለት ዓይነት ተውሳኰች (ተጨማሪዎች) አሉ፣እነርሱም የዕለታት እና የአጽዋማት በመባል ይታወቃሉ።

    ፩ኛ፡-የዕለታት ተውሳክ (ተጨማሪ)፡-የማይለወጡ የሰባቱ ዕለታት ቁጥሮች ናቸው።አገልግሎታቸ ውም በዓለ መጥቅዕ በዋለበት ዕለት  መሠረት ተጨም ረው መባጃ ሐመርን ማስገኘት ነው።አወጣጣቸውም፡-በዓለ መጥቅዕ ከሚውልበት ዕለት ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ መግቢያ ድረስ ያሉትን ዕለታት ደምሮ በሠላሳ  በመግደፍ (በማጣፋት ወይም ለሠላሳ በማካፈል) የሚገኝ ነው።በዓለ መጥቅዕ ቅዳሜ ቢውል፥እስከ ጾመ ነነዌ መግቢያ ድረስ ፻፳፰ ቀናትን እናገኛለን፤ይኸንን በሠላሳ ብንገድፈው(ለሠላሳ ብናካፍለው) ፬ ጊዜ ደርሶ ፰ ይቀ ራል፤ቀሪው የቅዳሜ ተውሳክ(ተጨማሪ) ይሆናል።እሑድ ቢውል፥ እስከ ጾመ ነነዌ መግቢያ ድረስ ፻፳፯ ቀናትን እናገኛለን፤ይኸንን በሠላሳ ብንገድፈው(ለሠላሳ ብናካፍለው) ፬ ጊዜ ደርሶ ፯ ይቀራል፤ቀሪው የእሑድ ተውሳክ(ተጨማሪ) ይሆናል። ሰኞ ቢውል፥እስከ ጾመ ነነዌ ያሉትን ፻፳፮ ቀናት በሠላሳ ብንገድፈው(ለሠላሳ ብናካፍለው) ፬ ጊዜ ደርሶ ፮ ይቀ ራል፤ቀሪው ፮ የዕለቱ ተውሳክ(ተጨማሪ) ይሆናል።ማክሰኞ ቢውል፥እስከ ጾመ ነነዌ ያሉትን ፻፳፭ ቀናት በሠላሳ ተገድፈው (ለሠላሳ ብናካፍለው) ፬ ጊዜ ደርሶ ፭ ይቀራል፤ቀሪው ፭ የዕለቱ ተውሳክ (ተጨማሪ) ይሆናል።ረቡዕ ቢውል፥እስከ ጾመ ነነዌ ያሉትን ፻፳፬ ቀናት በሠላሳ ብንገድፈው (ለሠላሳ ብናካፍለው) ፬ ጊዜ ደርሶ ፬ ይቀራል፤ቀሪው ፬ የዕለቱ ተውሳክ (ተጨማሪ) ይሆናል።ሐሙስ ቢውል፥እስከ ጾመ ነነዌ ያሉትን ፻፳፫ ቀናት በሠላሳ ብንገድፈው (ለሠላሳ ብናካፍለው) ፬ ጊዜ ደርሶ ፫ ይቀራል፤ቀሪው ፫ የዕ ለቱ ተውሳክ(ተጨማሪ) ይሆናል።ዓርብ ቢውል፥እስከ ጾመ ነነዌ ያሉትን ፻፳፪ ቀናት በሠላሳ ብንገድፈው(ለሠላሳ ብናካፍለው) ፬ ጊዜ ደርሶ ፪ ይቀራል፤ ቀሪው ፪ የዕለቱ ተውሳክ (ተጨማሪ) ይሆናል።                                                 

    ፪ኛ፡-የበዓላትና የአጽዋማት ተውሳክ(ተጨማሪ) ከመባጃ ሐመር ጋር እየተደመሩ በዓላቱ የሚውሉበትን ፥ አጽዋማቱም የሚገቡበትን ወርና ቀን ያስገኛሉ። አወጣጣቸውም ከነነዌ መግቢያ ማግስት ጀምሮ (የነነዌን ማግስት አንድ ብሎ በመቁጠር) እስከ በዓላቱና እና አጽዋማቱ መግ ቢያ ድረስ የሚገኙትን ቀናት ብዛት ካገኘን በኋላ ከሠላሳ የሚበልጡ ከሆነ በሠላሳ በመግደፍ(ለሠላሳ በማካፈል) ነው። ከሠላሳ በታች ከሆኑ ግን እንዳሉ እንተዋቸዋለን። ሀ፡-የዐቢይ ጾም ተውሳክ (ተጨማሪ) ፲፬ ነው፥ምክንያቱም ከጾመ ነነዌ ሳኒታ (ማግስት) ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም የሚገኙት ቀናት ፲፬ ናቸው። ለ፡-የደብረ ዘይትን ተውሳክ ለማውጣት፥ ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ደብረ ዘይት ስንቆጥር ፵፩ ቀናትን እናገኛለን፤ይህንንም በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፲፩ የበዓሉ ተውሳክ(ተጨማሪ) ይሆናል።(፵፩ን ለ፴ ስናካፍል ፩ ጊዜ ደርሶ ፲፩ ይቀራል)። ሐ፡-የሆሣዕናን ተውሳክ ለማግኘት ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ሆሣዕና የሚገኙትን ቀናት ቆጥረን የምናገኘውን ፷፪ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፪ የሆሣዕና ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው። (፷፪ን ለ፴ ስናካፍለው ፪ ጊዜ ደርሶ ፪ ይቀራል)። መ፡-የስቅለትን ተውሳክ ለማውጣት ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ስቅለት ያሉትን ቀናት ቆጥረን የምናገኘውን ፷፯ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፯ የስቅለት ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው።(፷፯ን ለ፴ ስናካፍለው ፪ ጊዜ ደርሶ ፯ ይቀራል)። ሠ፡-የትንሣኤን ተውሳክ ለማውጣት ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ትንሣኤ ያሉትን ቀናት ቆጥረን የምናገኘውን ፷፱ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፱ የትንሣኤ ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው። (፷፱ን ለ፴ ስናካፍለው ፪ ጊዜ ደርሶ ፱ ይቀራል)። ረ፡-የርክበ ካህናትን ተውሳክ ለማውጣት ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ርክበ ካህናት ቆጥረን የምናገኘውን ፺፫ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፫ የርክበ ካህናት ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው።(፺፫ን ለ፴ ስናካፍለው ፫ ጊዜ ደርሶ ፫ ይቀራል)። ሰ፡-የዕርገትን ተውሳክ ለማውጣት ከጾመ ነነዌ እስከ ዕርገት ቆጥረን የምናገኘውን ፻፰ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀ ረው ፲፰ የዕርገት ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው። (፻፰ን ለ፴ ስናካፍለው ፫ ጊዜ ደርሶ ፲፰ ይቀራል)። ሸ፡-የጰራቅሊጦስን ተውሳክ ለማውጣት ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ጰራቅሊጦስ ቆጥረን የምናገኘውን ፻፲፰ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፳፰ የጰራቅሊጦስ ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው። (፻፲፰ን ለ፴ ስናካፍለው ፫ ጊዜ ደርሶ ፳፰ ይቀራል)። ቀ፡-የጾመ ሐዋርያትን ተውሳክ ለማውጣት ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ጾመ ሐዋርያት ቆጥረን የምናገኘውን ፻፲፱ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፳፱ የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው።(፻፲፱ን ለ፴ ስናካፍለው ፫ ጊዜ ደርሶ ፳፱ ይቀራል)። በ፡-የጾመ ድኅነትን ተውሳክ ለማውጣት ከጾመ ነነዌ ሳኒታ እስከ ጾመ ድኅነት ቆጥረን የምናገኘውን ፻፳፩ን በሠላሳ ገድፈን የሚቀረው ፩ የጾመ ድኅነት ተውሳክ(ተጨማሪ) ነው።(፻፳፩ን ለ፴ ስናካፍለው ፬ ጊዜ ደርሶ ፩ ይቀራል)።                                                                                   ኢይወርድ ወኢየዐርግ፤                                                                      

    በቀጥታ ትርጉሙ፡- ከዚህ በላይ አይወጣም፥ከዚህ በታች አይወርድም ማለት ነው። ይህም በዓላቱ እና አጽዋማቱ የሚገቡበትን እና የሚወጡበትን ጊዜ የሚወስን ነው።ለምሳሌ፡-የወር ቀናት መመላለሻ፥የጨረቃ ዓመት መጀመሪያ የሆነው የአበቅቴ መነሻ (ልደተ አበቅቴ) ከነሐሴ ፰ በታች አይወርድም፥ከጳጉሜ ፭ በላይ አይወጣም ። ስለዚህ የአበቅቴ ኢይወርድ እና ኢየዐርግ ይባላል። በዚህ ዓይነት በዓላቱና አጽዋማቱ በዓመቱ ውስጥ የሚውሉበት ቀናት የታጠሩበት የታችኛውና የላይኛው ድንበሮች ታሕታይና ላዕላይ ቀመር (ቁጥር) ይባላሉ። ሂደታቸውም የጾመ ነነዌን ከፍተኛ እና ዝቅተኛ ቁጥር በመከተል በ፴፭ ቀናት ውስጥ ይመላለሳሉ።                                    

    መጥቅዕ የሚውልበት ዝቅተኛው የዓመቱ ቀን (ታሕታይ ቀመሩ) መስከረም ፲፭ ነው፤ከዕለታት ተውሳክ(ተጨማሪ) ደግሞ አነስተኛው የዓርብ ሲሆን እርሱም ፪ ነው።በእነዚህ ድምር የሚገኘው መባጃ ሐመር የጾመ ነነዌ የዓመቱ ዝቅተኛው ቁጥር (ታሕታይ) በመሆን ያገለግላል። ስለዚህ የሁለቱ ድምር ፲፯ በመሆኑ፥ ነነዌ ከጥር ፲፯ በፊት አትውልም።መጥቅዕ በሚውልበት ከመስከረም ፲፭ - ፴ ባለው ክፍለ ጊዜ መሠረት የሚገኙት ነነዌን ጨምሮ ሌሎቹም በዓላትና አጽዋማት በታሕታይ ቀመራቸው ይውላሉ።                                                     

    መጥቅዕ የሚውልበት ከፍተኛው የዓመቱ ቀን (ላዕላይ ቀመሩ) ጥቅምት ፲፫ ነው፥ከዕለ ታት ተውሳክ(ተጨማሪ) ደግሞ ከፍተኛው የቅዳሜ ሲሆን እርሱም ፰ ነው። ተደምሮም መባጃ ሐመሩን እናገኛለን፥ይህም የጾመ ነነዌ የዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ኢየዐርግ ሆኖ ያገለግላል። ስለዚህ የሁለቱ ድምር ፳፩ በመሆኑ፥ነነዌ ከየካቲት ፳፩ በላይ አትወጣም።መጥቅዕ ጥቅምት ፲፫ ሆኖ ቅዳሜ ላይ ቢወድቅ የላዕላይ ቀመር ድንበር ይገኛል።በዚህ አካሄድ በዓለ መጥቅዕ ከ፪ - ፲፫ ሆኖ ጥቅምት ወር ላይ በሚወጣበት ጊዜ በዓላትና አጽዋማት በላዕላይ ቀመራቸው ይውላሉ። ጾመ ነነዌ ከጥር ፲፯ - የካቲት ፳፩ ባሉት ፴፭ ቀናት እየተመላለሰች ስትወጣ፥ሌሎቹም በዓላትና አጽዋማት እንደ ሰንሰለት ተያይዘው፥ከታችኛው ድንበራቸው ሳይወርዱ ከላይኛውም ድንበራ ቸው ሳይወጡ በ፴፭ ቀናት ውስጥ ሲመላለሱ ይኖራሉ።                                                                            ሀ፡-ከላይ እንደገለጥነው የጾመ ነነዌ ኢይወርድ ጥር ፲፯ ሲሆን ኢየዐርጉ ደግሞ የካቲት ፳፩ ነው። ትርጉሙም የነነዌ ጾም ከጥር ፲፯ በታች ወርዳ ጥር ፲፮ አትውልም፥ከየካቲት ፳፩ በላይም ወጥታ የካቲት ፳፪ አትውልም። ከጥር ፲፯ እስከ የካቲት ፳፩ ባሉት ዕለታት ውስጥ ስትመላለስ ትኖራለች። የሌሎቹም ከተወሰነላቸው ቀናት በታች አለመውረዳቸውና አለመውጣታ ቸው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው።ለ፡-የዓቢይ ጾም ኢይወርድ የካቲት ፩ ሲሆን፥ኢየዐርጉ ደግሞ መጋቢት ፭ ነው።ሐ፡-የደብረ ዘይት ኢይወርድ የካቲት ፳፰ ሲሆን፥ ኢየዐርጉ ደግሞ ሚያዝያ ፪ ነው።መ፡-የሆሣዕና ኢይወርድ መጋቢት ፲፱ ሲሆን ፥ኢየዐርጉ ደግሞ ሚያዝያ ፳፫ ነው።ሠ፡-የስቅለት ኢይወርድ መጋቢት ፳፬ ሲሆን፥ኢየዐርጉ ደግሞ ሚያዝያ ፳፰ ነው። ረ፡-የትንሣኤ ኢይወርድ መጋቢት ፳፮ ሲሆን፥ ኢየዐርጉ ደግሞ ሚያዝያ ፴ ነው። ሰ፡-የርክበ ካህናት ኢይወርድ ሚያዝያ ፳ ሲሆን፥ ኢየዐርጉ ደግሞ ግንቦት ፳፬ ነው።ሸ፡-የዕርገት ኢይወርድ ግንቦት ፭ ሲሆን፥ ኢየዐርጉ ደግሞ ሰኔ ፱ ነው።ቀ፡-የበዓለ ሃምሣ ኢይወርድ ግንቦት ፲፭ ሲሆን፥ ኢየዐርጉ ደግሞ ሰኔ ፲፱ ነው ።በ፡-የጾመ ሐዋርያት ኢይወርድ ግንቦት ፲፮ ሲሆን፥ኢየዐርጉ ሐምሌ ፬ ነው።የጾመ ሐዋርያት መነሻ ቢለያይም መድረሻው ሐምሌ ፬ አይለወጥም። የጾመ ሐዋርያት ረዥሙ የጾም ቀናት ከግንቦት ፲፮ - ሐምሌ ፬ ያሉት የ፵፱ ቀናት ጾም ሲሆን፥ አጭሩ ደግሞ ከሰኔ ፳ - ሐምሌ ፬ ያሉት የ፲፭ ቀናት ጾም ነው። ተ፡-ጾመ ሐዋርያት ሰኞ ቀን ሲጀመር ፥ጾመ ድኅነት(የረቡዕ እና የዓርብ ጾም) አብሮ ይጀመራል።ጾመ ሐዋርያት ሐምሌ 4 ቀን ሲያበቃ፥ጾመ ድኅነት ግን በበዓለ ሃምሣ ምክንያት እስኪበላ ድረስ ይቀጥላል።                                                        አዕዋዳት፤                                                               

    አዕዋዳት ለብዙ የሚነገር ሲሆን፥ “ዖደ - ዞረ፤”ከሚለው ግስ የተገኘ ነው፣ዙሮ የሚመጣ(ዞሮ የሚገጥም)ማለት ነው። የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የሚጀምረው ከጥንት ነው።ጥንትነቱም ከፍጥረተ ዓለም፥ከፍጥረተ ፀሐይ፣ጨረቃና ከዋክብት ነው። ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበት ዕለተ እሑድ ጥንተ ዕለት ይባላል። ግብር እምግብር ማለትም እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት መነሻነት የተፈጠሩ ፍጥረታት መቆጠር የጀመሩበት ዕለተ ሠሉስ(ማክሰኞ) ጥንተ ቀመር ይባላል። ለምሳሌ ቀድማ ከተፈጠረች መሬት፥አትክልት፣አዝርዕት እና ዕፅዋት በዕለተ ሠሉስ ተፈጥረዋል። ዘፍ፡፩፥፲፩። ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የተፈጠሩበት ዕለተ ረቡዕ ደግሞ ጥንተ ዖን(ዮን) ይባላል።ትርጉሙም ጥንተ ብርሃን ማለት ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሳድሲቱ ዐምሲት፥ዐምሲቱ ራብዒት፥ራብዒቱ ሳልሲት፥ሳልሲቱ ካልዒት፥ካልዒቱ ኬክሮስ፥ኬክሮሱ ዕለት፥ ዕለታቱ ሳምንት፥ሳምንታቱ ወር፥ወራቱ ዓመት፥ዓመታቱ ዘመን፥ዘመናቱ አዝማናት እየሆኑ ከዛሬ ደርሰናል።በዘመን አቆጣጠራችን ከዕለት በታች የምንቆጥርባቸው ስድስት መለኪያዎች አሉ። ፩ኛ፡-ስድሳ ሳድሲት አንድ ዐምሲት ነው፤ ፪ኛ፡- ስድሳ ዐምሲት አንድ ራብዒት ነው፤ ፫ኛ፡- ስድሳ ራብዒት እንድ ሳልሲት ነው፤ ፬ኛ፡- ስድሳ ሳልሲት አንድ ካልዒት ነው፤ ፭ኛ፡- ስድሳ ካልዒት አንድ ኬክሮስ ነው፤ ፮ኛ፡- ስድሳ ኬክሮስ አንድ ዕለት ነው።ዓለም ከተፈጠረ ፥ዘመን ከተቆጠረ 7507 ዓመተ ዓለም ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው 5500 ዓመት ነው፥ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኵነኔ ይባላል። ይኸውም ከአዳም እስከ ኖኅ 2250 ዓመት፥ከኖኅ እስከ ሙሴ 1588 ዓመት፥ከሙሴ እስከ ሰሎሞን 599 ዓመት፥ከሰሎሞን እስከ ልደተ ክርስቶስ 1063 ዓመት ነው።ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው 2007 ዓመት ነው፤ ዓመተ ሥጋዌ፥ዓመተ ምህረት ይባላል።     

    ሀ፡-ከሰኞ እስከ እሑድ የሚገኙት ዕለታት በየሳምንቱ  እየተመለሱ ወይም እየዞሩ ስለሚ መጡ ዓውደ ዕለት ይባላል። ዕለታቱ እየተመላለሱ ወይም እየዞሩ በመምጣት ሳምንታትን ይፈጥ ራሉ፣ሳምንታቱም አራት ሲሞሉ ወርን ይፈጥራሉ።                                                                                                                 

              ለ፡- ወር፡-በየሠላሳ ቀኑ እየተመለሰ ወይም እየዞረ ስለሚመጣ ዓውደ ወርኅ ይባላል። ወራት ዓውድ በማድረግ (እየዞሩ በመምጣት) ዓመትን ይፈጥራሉ።በፀሐይ አቆጣጠር አንድ ወር ፴ ቀናት ነው፤በጨረቃ ሲሆን ግን አንድ ወር ፳፱ በሌለኛው ወር ደግሞ ፴ እያደረገ ይቆጥራል።መስከረም ፳፱፣ጥቅምት ፴፣ኅዳር ፳፱፣ታኅሣሥ ፴፣ወዘተ…።                                      

              ሐ፡- አንድ ዓመት በፀሐይ አቆጣጠር ፫፻፷፭ ቀን ከአስራ አምስት ኬክሮስ ነው።ሄኖ፡ ፳፩፥፵፱።አሥራ ሁለቱን ወር በ፴ ቀናት አባዝተን አምስቱን የጳጉሜን ቀናት ስንደምርበት ፫፻፷፭ ይሆናል።አስራ አምስቱ ኬክሮስ ደግሞ በየአራቱ ዓመት ተጠራቅሞ ፳፬ ሰዓት ( አንድ ቀን ) ይሆንና የዘመነ ሉቃስን ጳጉሜን ስድስት ያደርጋታል።ምክንያቱም ፩ ኬክሮስ ፳፬ ደቂቃ ነው፣በመሆኑም አስራ አምስቱን ኬክሮስ በ፳፬ ደቂቃ ስናባዛው ፮ ሰዓት ይሆናል።ይህም በ፬ ዓመት ውስጥ ፳፬ ሰዓት ይሞላና ፩ ቀን ይፈጥራል።                              

    መ፡-ዓውደ አበቅቴ(ንዑስ ቀመር)፡-በየ፲፱ ዓመቱ እየተመላለሰ ወይም እየዞረ የሚመጣ ነው።ፀሐይና ጨረቃ ሁለቱም በዕለተ ረቡዕ በአንድ ኆኅት(መስኮት)ውስጥ ተፈጥረው፥ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዑደት(ዙረት)ያደርጋሉ።ሁለቱም ተለያይተው ሲዞሩ ይቆዩና በ፲፱ ዓመት አንድ ጊዜ በተፈጠሩበት ኆኅት(መስኮት)ይገናኛሉ፥ዓውደ አበቅቴ የሚባለው ይህ ነው።በሌላ አገላለጥ ጨረቃ በምትወለድበት ዕለትና ሰዓት ተመልሳ በዚያው ዕለትና ሰዓት እንደገና የምትወለደው ከ፲፱ ዓመት በኋላ ነው።በሳይንሱም ቢሆን የሜቶን ዑደት በመባል ይታወቃል።ጥንተ አበቅቴ የሚባለው ደግሞ በፀሐይና በጨረቃ መካከል ያለው የ፲፩ ቀናት ልዩነት ነው።በፀሐይ አቆጣጠር በዓመት ውስጥ ፫፻፷፭ ቀናት ሲኖሩ በጨረቃ ግን ፫፻፶፬ ቀናት ናቸው።በመሆኑም  ከ፫፻፷፭ ላይ ፫፻፶፬ ሲቀነስ ፲፩ ይቀራል።                                                                                                        ሠ፡-ዓውደ ፀሐይ፡-በየ፳፰ ዓመቱ እየዞረ የሚመጣ ነው።ይኸውም ፀሐይ የተፈጠረችበት ዕለተ ረቡዕና የወንጌላውያን መጀመሪያ ቅዱስ ማቴዎስ የሚገናኙበት ስለሆነ ነው።ሊቃው ንቱ ረቡዕ ማቴዎስ ይሉታል።ለምሳሌ ዘመነ ማቴዎስና ረቡዕ መስከረም ፩ ቀን የተገናኙት በ፪ሺ ዓ.ም. ነው።ከዚህ በኋላ እንደገና የሚገናኙት ከ፳፰ ዓመት በኋላ በ፪ሺ፳፰ ዓ.ም. ነው።ሌሎቹም ወንጌላውያን በዘመን መለወጫ የገቡበትን ዕለት እንደገና የሚያገኙት ከ፳፰ ዓመት በኋላ ነው። ለምሳሌ መስከረም ፩ ቀን ፪ሺ፰ ዓ.ም. ዘመነ ዮሐንስና ቅዳሜ ተገናኝተዋል።እንደገና የሚገናኙት ከ፳፰ ዓመት በኋላ ነው።ይህንንም በቀላሉ ለማግኘት ሰባቱን ዕለታት በአራቱ ወንጌላውያን ስናባዝ ፳፰ን እናገኛለን።                                                                                                        ረ፡-ዓውደ ማኅተም(ማዕከላዊ ቀመር)፡-በየ፸፮ ዓመቱ እየተመላለሰ ወይም እየዞረ የሚመጣ ነው።ይኸውም የአበቅቴ ፍጻሜ ፲፰ እና የወንጌላውያን ፍጻሜ ቅዱስ ዮሐንስ የሚገናኙበት ስለሆነ ነው።ከላይ እንደተገለጠው፥ የቀመር (የቁጥር)መጀመሪያ ማክሰኞ ሲሆን የወንጌላውያን መጀመሪያ ማቴዎስ ነው።ምክንያቱም፡-እሑድ አሥራወ ፍጥረታት (የፍጥረታት መሠረቶች) ከተፈጠሩ በኋላ፥ ከእነርሱም ከማክሰኞ ጀምሮ ግብር እምግብር እየተፈጠሩ መቆጠር ስለጀመሩ ነው።ግብር እምግብር ማለት፡-እሑድ ከተፈጠሩት የፍጥረታት መሠረቶች የተገኙ (የተፈጠሩ) ፍጥረታት ማለት ነው።እሑድ የተፈጠሩት ስምንት ፍጥረታት፡-እሳት፣ውኃ፣ ነፋስ፣መሬት፣ጨለማ፣ሰባቱ ሰማያት፣ መላእክት  እና ብርሃን ናቸው።የቀመር(የቁጥር) መጨረሻ  ሰኞ፥ የወንጌላውያን መጨረሻ ደግሞ ዮሐ ንስ ነው።(ዕለታት ከማክሰኞ ጀምሮ ሲቆጠሩ ሰኞ የመጨረሻ ይሆናል፥ወንጌላውያን ደግሞ ከማቴ ዎስ ጀምሮ ሲቆጠሩ ዮሐንስ የመጨረሻ ይሆናል።)                                                                                   

    ሰ፡-ዓውደ ዓቢይ ቀመር ፭፻፴፪ ዓመት ነው።በዚህን ጊዜ፥ ፩ኛ፡-የአበቅቴ ፍጻሜ የሆነው ፲፰ አበቅቴ፤ ፪ኛ፡-የወንጌላውያን ፍጻሜ የሆነው ዮሐንስ፤ ፫ኛ፡-የቀመር(የቁጥር)ፍጻሜ የሆነው ሰኞ፥ሦስቱ ይገናኛሉ።ከ“ሀ” እስከ “ሰ” እንዳየነው አዕዋዳት ሰባት ናቸው።አንድ ጊዜ ተፈጽመው ወይም ታይተው የሚቀሩ ሳይሆን በየተወሰነላቸው ዘመን ዞረው የሚመጡ ስለሆነ አዕዋዳት ተብለ ዋል።ትልቁ መስፈሪያ(መቁጠሪያ) ፭፻፴፪ ዓመት ስለሆነ ዓቢይ ቀመር ተብሏል። መካከለኛው መስፈሪያ ፸፮ ዓመት ስለሆነ ማዕከላዊ ቀመር ተብሏል።ትንሹ መስፈሪያ ደግሞ ፲፱ ዓመት ስለሆነ ንዑስ ቀመር ተብሏል።                                                                               

             ዓመተ ወንጌላውያን፤                                                             በብሉይ ኪዳን  የዘመን አከፋፈል በአርባዕቱ እንስሳ ማለትም መንበሩን በሚሸከሙ በኪሩ ቤል ነበር።በአራቱም መልክ፡-ዘመነ ብእሲ፥ዘመነ አንበሳ፥ዘመነ ላህም፥ዘመነ ንስር ይባል ነበር።በዘመነ አዲስ ደግሞ እነዚህ ምሳሌዎች ሆነው፡-ዘመነ ማቴዎስ፥ዘመነ ማርቆስ፥ዘመነ ሉቃስ፥ዘመነ ዮሐንስ ይባላል።የዓመቱን ወንጌላዊ የምናውቀው ዓመተ ዓለምን ወይም ዓመተ ምሕረትን ወይም የሁለቱን ድምር ለአራት አካፋለን በቀሪው ነው።አንድ ከቀረ ቅዱስ ማቴዎስ፥ሁለት ከቀረ ቅዱስ ማርቆስ፥ሦስት ከቀረ ቅዱስ ሉቃስ፥እኩል ተካፍሎ ቀሪ ከሌለው ቅዱስ ዮሐንስ ይሆናል።                                         

    አራቱም ወንጌላውያን የተሾሙበትን ዓመት የሚጀምሩበትና የሚጨርሱበት ቀን ከነሰዓቱ የተጠበቀ ነው።ቅዱስ ማቴዎስ ዓመቱን የሚጀምረው በዋዜማው ሠርክ ፲፪ ሰዓት (6pm) ሲሆን፥ ዓመቱን ጨርሶ የሚወጣው ደግሞ መንፈቀ ሌሊት ፮ ሰዓት (12PM) ነው።ቅዱስ ማርቆስ ዓመቱን የሚጀምረው መንፈቀ ሌሊት  ሰዓት (12pm) ሲሆን ፥ዓመቱን ጨርሶ የሚወጣው ደግሞ ነግህ ፲፪ ሰዓት (6AM) ነው።ቅዱስ ሉቃስ ዓመቱን የሚጀምረው ነግህ ፲፪ ሰዓት(6AM) ሲሆን፥ ዓመቱን ጨርሶ የሚወጣው ደግሞ ቀትር ፮ ሰዓት (12AM)ነው።ቅዱስ ዮሐንስ ዓመቱን የሚጀምረው ቀትር ፮ ሰዓት (12AM) ሲሆን፥ዓመቱን ጨርሶ የሚወጣው ደግሞ ሠርክ ፲፪ ሰዓት (6PM) ነው።                                                                                                                                                          ወንበር፤                                                            በዓላትንና አጽዋማትን ለማውጣት ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ መጥቅዕ ነው።በዓላትና አጽዋማት የሚያድሩባቸውን ሌሊት የሚያሳውቀን ደግሞ አበቅቴ ነው።አበቅቴና መጥቅዕ በየዘመኑ ስለሚቀያየሩ፥በየዓመቱ አበቅቴንና መጥቅዕን ማውጣት ይኖርብናል።እነዚህን የምናወጣበት ቁጥር ወንበር ይባላል።ወንበር መባሉም ለበዓላትና ለአጽዋማት መውጣት ወሳኝ የሆኑት አበቅቴና መጥቅዕ የሚገኝበትና ዓመቱን ሙሉ በቋሚነት የሚያገለግል ቁጥር በመሆኑ ነው ።                                                                            ወንበር እንዴት ይወጣል?                                                   በመጀመሪያ ዓመተ ፍዳን እና ዓመተ ምሕረትን ደምረን የምናገኘው ውጤት ዓመተ ዓለም ወይም የዓለም ዕድሜ ይባላል። ቀጥለንም ድምሩን በየቤቱ ተንትነን፥በዓቢይ ቀመር፥ በማዕከ ላዊ ቀመርና በንዑስ ቀመር በመግደፍ(በማካፈል) የዘመኑን ወንበር እናገኛለን።በዚህም መሠረት 5500ን እና 2007ን ስንደምራቸው 7507 እናገኛለን። ይህም በየቤቱ ሲተነተን፡-፩ኛ/ 7000፤  ፪ኛ/ 500፤  ፫ኛ/ 7፤  ይሆናል።በቅድሚያ 7000ን ለዓቢይ ቀመር ለ532 ስናካፍለው13 ደርሶ ቀሪ 84 እናገኛለን።ቀሪውን ከ500 ጋር እንደምረውና የምናገኘውን ውጤት 584ን ለማዕከላዊ ቀመር ለ76 ስናካፍለው 7 ደርሶ ቀሪ 52እናገኛለን።አሁንም ቀሪውን ከ7 ጋር ደምረን የምናገኘውን 59ን ለንዑስ ቀመር ለ19 ስናካፍለው 3 ደርሶ ቀሪ 2 እናገኛለን። በመጨረሻም ከቀሪው ላይ አንድ ቁጥር ቀንሰን የሚቀረን አንድ የ2007 ዓ.ም. ወንበር ይባላል።በመጨረሻ ከሚገኘው ውጤት ላይ አንድ የምንቀንስበት ምክንያት “አሐደ አዕትት ለዘመን፥አንዱን ለዘመን ስጥ ወይም አስቀር፤” ስለሚል ነው። ይኸንንም፡- ዘመኑ አንድ ተብሎ ስለተጀመረ ተቆጠረ፥ስላልተፈጸመ ደግሞ ታተተ ወይም ተቀነሰ በማለት ይገልጹታል።ለምሳሌ፡-2006 ዓ.ም. ልክ እንደተፈጸመ አንድ ደቂቃም ብትሆን ወዲያውኑ 2007 ዓ.ም. ተብሎ ይቆጠራል። በመሆኑም የዘመኑን ወንበር ሁለት ካልን በኋላ፥ተጀመረ እንጂ መቼ ተፈጸመ ብለን አንድ እንቀንሳለን።                                                                                      

                             

                   አበቅቴ እና መጥቅዕ፤                                                       

    አበቅቴ የሚለው ቃል “አፖክቴ” ከሚለው የግሪክ ቃል የወጣ ነው።ትርጉሙም ተረፈ ዘመን፥ ስፍረ ሌሊት፥ ቁጥረ ሌሊት ማለት ነው።የዘመኑን አበቅቴ ለማግኘት ከላይ ያገኘነውን ወንበር በጥንተ አበቅቴ ማባዛት ነው።ውጤቱ ከሠላሳ ከበለጠ በሠላሳ ገድፈን ቀሪውን እንይዛለን።ቅዱስ ድሜጥሮስ ሱባዔ ገብቶ ጥንተ አበቅቴ ፲፩፥ጥንተ መጥቅዕ ደግሞ ፲፱ መሆኑ ተገልጦለታል።በዚህም መሠረት የ፪ሺ፯ ዓመተ ምሕረትን አበቅቴ ለማግኘት፥ የዘመኑን ወንበር በጥንተ አበቅቴ እናባዛ ለን።የ፪ሺ፯ን ወንበር ፩ን በጥንተ አበቅቴ በ፲፩ ስናባዝው ፲፩ ይሆናል፥ይህም የዘመኑ አበቅቴ ይሆናል።                                              መስከረም ፩ ቀን፥ ከሰኞ እስከ እሑድ የሚውልበት ዕለት እንዴት ይታወቃል?                         
    መስከረም ፩  የሚውልበትን ዕለት ለይቶ ለማውጣት በሦስቱም ጥንታት ተጠቅመን ማው ጣት እንችላለን። ፩ኛ፡-ዓመተ  ዓለምን፥ ከዓመተ ምሕረት እና ከሁለት ዕለተ ጠቢባን ጋር በመደመር  ውጤቱን ለ፯ ካካፈልን በኋላ በቀሪው ዕለቱን እናገኛለን።ቀሪው ፩ ከሆነ እሑድ፥፪ ከሆነ ሰኞ፥፫ ከሆነ ማክሰኞ፥፬ ከሆነ ረቡዕ፥፭ ከሆነ ሐሙስ፥፮ ከሆነ ዓርብ፥ያለ ቀሪ ከተካፈለ ደግሞ ቅዳሜ ይሆናል።ለምሳሌ ያለፈውን ዓመት የ፪ሺ፯ን እንመልከት።5500+2007+2=7509 ይሆናል። ይኸንን ለ 7 ስናካፍለው 1072 ጊዜ ደርሶ 5 ይቀራል።በሕጉ መሠረት ቀሪው 5 ከሆነ መስከረም1 ቀን 2007 ዓ.ም. የዋለው ሐሙስ ነው። ሁለት ዕለተ ጠቢባን የተባሉት እግዚአብሔር ፍጥረታትን መፍጠር የጀመረባት ዕለተ እሑድና ግብር እምግብር (ከተፈጠሩት ፍጥረታት መልሶ መፍጠር) የጀመረባት ዕለተ ሠሉስ (ማግሰኞ) ናቸው። እግዚአብሔር እም ኀበ አልቦ (ከምንም) እና ግብር እምግብር (ከምንት) የመፍጠር ጥበቡን ያሳየባቸው ዕለታት በመሆናቸው ዕለተ ጠቢባን ተብለዋል። 2ኛ፡-በጥንተ ቀመር ማለትም በማክሰኞ መነሻነት ዓመተ ዓለምን እና ዓመተ ምሕረትን በመ ደመር ለ፯ ማካፈል ነው። ቀሪው ፩ ከሆነ ማክሰኞ፥ቀሪው ፪ ከሆነ ረቡዕ፥ቀሪው ፫ ከሆነ ሐሙስ ፥ ቀሪው ፬ ከሆነ ዓርብ፥ቀሪው ፭ ከሆነ ቅዳሜ፥ቀሪው ፮ ከሆነ እሑድ፥ያለ ቀሪ ከተካፈለ ደግሞ ሰኞ ይሆናል።ምሳሌ፡-5500 + 2007 =7507 ይሆናል።ይኸንን ለ7 ስናካፍለው 1072 ጊዜ ደርሶ 3 ይቀራል። በሕጉ መሠረት ቀሪው 3 ከሆነ መስከረም 1 ቀን  2007 ዓ.ም. የዋለው ሐሙስ ነው።                                                          

    ፫ኛ፡-በጥንተ ዖን ማለትም በረቡዕ መነሻነት  ከዓመተ ዓለም  እና ከዓመተ ምሕረት ድምር ላይ 1 ከቀነስን በኋላ ውጤቱን ለ7 በማካፈል በቀሪው እናገኛለን።ቀሪው ፩ ከሆነ ረቡዕ፥ቀሪው ፪ ከሆነ ሐሙስ፥ቀሪው ፫ ከሆነ ዓርብ፥ቀሪው ፬ ከሆነ ቅዳሜ፥ቀሪው ፭ ከሆነ እሑድ፥ቀሪው ፮ ከሆነ ሰኞ፥ያለ ቀሪ ከተካፈለ ደግሞ ማክሰኞ ይሆናል።ምሳሌ፡-5500 + 2007 - 1 = 7506 ይሆናል።ይኸንን ለ7 ስናካፍለው 1072 ጊዜ ደርሶ 2 ይቀራል።በሕጉ መሠረት ቀሪው 2 ከሆነ መስከረም 1 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚውለው ሐሙስ ነው፥ዘመኑም ዘመነ ሉቃስ ነው።ቅዱስ ሉቃስ ከዚህ በኋላ ሐሙስ የሚውለውን መስከረም እንድን የሚያገኘው ከ28 ዓመት በኋላ ነው።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የዘመን አቆጣጠር ክፍል ሁለት፤ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top