• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 17 November 2015

    ነገረ ቤተክርስቲያን - ክፍል ሁለት

    ምዕራፍ ፩  

    የቤተ ክርስቲያንን የሥራ ሁኔታ የምናይበት ምዕራፍ ሲሆን ሠለስቱ ምዕት በፍትሐ ነገሥታቸው እንደ ጠቀሱት ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቅዶ ካልሆነ እንዳትሠራ እና አገልግሎት እንዳይሰጥባት ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ በዘጠና አራተኛው አንቀጽ ላይ የተመዘገበውን ጠቅሰው እነሱም ተስማምተው አጽድቀውታል፤ አባቶቻችን ሐዋርያትም እንደዚሁ ዲድስቅልያ በተሰኘው ትምህርታቸው በ15ኛውና በ30ኛው ክፍል ላይ እንዳስተማሩት ቤተ ክርስቲያንን የሚሠራ ሰው ያለ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ሠርቷት ቢገኝ እንደ በረት ልትቆጠር ይገባታል እንጅ ቅዱስ ቁርባንን ሊያቀብሉባት አይገባም ብለዋል፤

    ምክንያቱም አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስትሠራ ሊሟሉላት የሚገቡ ነገሮች ያሉ ስለሆነ ነው፡፡

    1.  የሚያገለግሏት ልዑካን ሊሟሉላት ይገባል፡-የልዑካኑ ብዛት ትንሹ ቁጥር ሰባት ሲሆን ትልቁ እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዐቅም ነው፡፡ ይህም አስቀድሞ በነቢይ እንደተጻፈው ‹‹ጥበብ ሐነፀት ቤተ ወአቀመት ላቲ ሰባተ አዕማደ፤ ጥበብ ቤትን ሠራች ሰባት ምሰሶዎችንም አቆመች›› ምሳ 9÷1 ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡

    ጥበብ የተባለችው በነቢዩ ዘንድ ወልድ ናት፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጥበብ ሲናገር ‹‹የእግዚአብሔር ጥበብ››1ቆሮ 1÷24 በማለት የነቢዩን ቃለ ትንቢት ይተረጉምለታል ሌላው ሊቅ ቅዱስ ኢጲፋንዮስም በቅዳሴው ‹‹ጥበብሰ መድኃኒነ ውዕቱ ዘቤዘዎነ በጥብሐ ሥጋሁ ወተሳየጠነ በንዝኃተ ደሙ፤ ጥበብስ ማነው ትሉኝ እንደሆነ በደሙ መፍሰስ፣ በሥጋው መቆረስ ያዳነን መድኃኒታችን ክርስቶስ ነው›› ብሏል፡፡ በሥጋ ተገልጦ ዓለሙ የተሠራበት ጥበብ ስለሆነ ነው፡፡

    ቤት የተባለችውም በጥበበ እግዚአብሔር በክርስቶስ የተሠራችው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ሰባት ምሰሶዎች የተባሉትም ሰባቱ ልዑካኖቿ (ሰባቱ መዓርጋቶቿ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ፣ቆሞስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ንፍቀ ዲያቆን) ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያን በነዚህ ምሰሶነት እንጂ ያለነዚህ የተሠራች ስላልሆነች ምሰሶዎቿ ተባሉላት፤ በመጽሐፍም ስለ መጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ልዑካን የተጻፈው ‹‹አዕማድ መስለው የሚታዩ…..›› ገላ 2÷9 በማለት የአገልጋዮቿን የቤተ ክርስቲያን አዕማድነታቸውን ያስረግጥልናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን መሰብሰቢያ የምትሆነው እነዚህ ምሰሶዎቿ ጥሩ ተሸካሚ ሆነው የተገኙ እንደሆነ ነው፤ ያለ በለዚያ ግን ‹‹ዝናም ዘነመ ነፋስ ነፈሰ…….አወዳደቁም ታላቅ ሆነ›› ማቴ 7÷27 እንደ ተባለው ቤት ጽኑዕ አወዳደቅን ትወድቃለች፡፡ ባለቤቱ ክርስቶስም ቤተ ክርስቲያንን ሲመሠርታት ምሰሶዎቿ የሚሆኑ ሐዋርያትን አቆመላት ከዚያ በኋላ ያለውን ሐዋርያት እንዲሠሩ አዝዞ ነው ወደ ሰማይ ያረገው ማቴ 28÷19

          ከዚያ በተጨማሪም ሰባት ቁጥር ፍፁም ቁጥር በመሆኑ እስከ እለተ ምጽዓት ድረስ የማያቋርጡ ልዑካንን እንደሚሰጣት የሚያስረዳ ምሥጢር ስላለው ልታሟላቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ ይህ ሆነ፤ ፍፁም ጸጋውን በእነርሱ በኩል ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን እያቀበለ ለሰው ሲሰጠው የሚኖር ስለሆነ፡፡

    2.  ሊሠራላቸው የሚገባቸው የምዕመናን ብዛት፡-ምዕመናኑ ብዙም ይሁኑ ጥቂት ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን ኅብረት ባለበት ሁሉ ልትሠራ እንዲገባት የታመነ ነው፤ ነገር ግን ምዕመናኑ የአገልጋዮቹን ቤት ሊሠሩ የሚገባቸው መሆኑ የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም አገልጋዮቹ ነቅተውና ተግተው ቤተ እግዚአብሔርን ያገለግላሉ እንጅ ራሳቸውን ወደ ማገልገል ዘወር እንዲሉ አልተፈቀደላቸውምና ነው፡፡ እንኳን አሁን ሕገ ትሩፋት በምትባለው በዘመነ ወንጌል በጥንታዊውዋና ሕገ ርትዕ በምትባለው ፍፁም ባልሆነችው ሕግ ዘመነ ምግብና ሳይቀር ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች ርስታቸው ቤተ እግዚአብሔርን ማገልገል ነበር፤ኢያ 14÷4 ዛሬም በዘመነ ሐዲስ ኪዳን ‹‹በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገር እንዲመገቡ በመሠዊያውም የሚፀኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን››1ቆሮ 9÷13 ተብሎ ነው የተጻፈው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል በትርፍ ጊዜ የሚሠራ ተጨማሪ ሥራ አይደለም እግዚአብሔርን ከማገልገል በላይ ሌላ ሥራ የለምና ሥራዬ ብለው እንዲሠሩት ታዘዋል፡፡ ደመዎዛቸው ምዕመናንን በማገልገላቸው መጠን የሚተመን ነው የእረኞች አለቃ በሚመጣ ጊዜ በአገልጋዮቹ እጅ ያስቀመጣቸው ገንዘቦቹ ምዕመናን ናቸውና ሊተሳሰባቸው በጀመረ ጊዜ በዘመቻ ውሎው ድል እንደቀናው ወታደር እነሆ ብለው የሚያቀርቡት እጅ መንሻቸው ምዕመናን ናቸው፤ ምዕመናን ደግሞ አስራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን (ራሱን በቻለ ምዕራፍ እናየዋለን) ባወጡት መጠን ዋጋቸውን ይቀበላሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሠመረ ጉዞ ይኖራት ዘንድ ሐዋርያትም በዲድስቅልያ መጽሐፋቸው ምዕመናን ይህን እንዲያደርጉ አዝዘዋል፡፡ ዲድ. አንቀጽ 8÷2 ይህን ማድረግ ሲችሉ ቤተ ክርስቲያን እንዲተከልላቸው ታዟል፤ ነገር ግን እንዲህ ስላልን ‹‹ኢይብዝሁ ወኢይህጽፁ፤ አውደልዳዩ አይብዛ አገልጋዩ አይነስ ተብሏል››

    እነዚህንና መሰል ነገሮች መሟላታቸውን አይቶ ሊቀ ጳጳሱ እንዲፈቅድ ይደረጋል፤ በታሪክም ስናይ የመጀመሪያቱን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሲሠሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ጳውሎስና በርናባስ መጀመሪያ የጠየቁት የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስን ነው፡፡ ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር የሚሠራ አንዳች ነገር የለምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንዲያመለክትላቸው ነው እኛም ያለ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ አይሠራም ስንል ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

    ይህ ሰም ነው፡-ወርቁ ግን ቤተ ክርስቲያን ማለት የምዕመናን ኅብረት ማለት ነውና ምዕመናን በኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ ነው እንጅ ያለዚያ መኖር እንዳይገባቸው ያስረዳል፤ ያለ ኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ ተሠርታ ብትገኝ እንደ በረት ትሁን ቁርባንም አያቅርቡባት ተብሎ መነገሩ ያለ ፈቃደ ካህን ያለ ምክረ ካህን የሚኖርን ሰው አጋንንት መሰማሪያ እንደሚያደርጉት ቤተ ክርስቲያንም አውግዛ ከቅዱስ ቁርባን የምትከለክለው እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

    Ø  አሠራሯን በተመለከተ በሀገራችን የተለመዱና እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም የማይነቀፉ ሦስት አይነት የቤተ እግዚአብሔር አሠራሮች አሉ፡፡

    1. ዋሻ

    2. ሰቀላማ(ምኵራብ)

    3. ቤተ ንጉሥ (ክብ)ናቸው

    ዋሻ የምንለው በሰው ሥራም ሆነ በተፈጥሮ የሚገኝ ሲሆን ልክና መጠኑ እንዲህ ነው ተብሎ ላይነገር ይችላል የውስጥ አሠራሩም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ሁሉ ላያሟላ ይችላል፡፡ የተወሰደው ከአዳም ጀምሮ የተነሡ አበው አግዚአብሔርን ለማገልገል እንዲህ አይነት ቦታዎችን ይጠቀሙ ነበርና ከዚያ የተወረሰ ነው፤ አባታችን አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ መሥዋዕት ያቀርብ የነበረውና ይኖርም የነበረው በዋሻ ውስጥ ነው፤ ከዚያ ሲያያዝ መጥቶ መልከ ጼዴቅም እንደዚሁ ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ የነበሩ የአስሩን አበው አጽም እንደ ታቦት፣ ዋሻዉን እንደ ቤተ መቅደስ አድርጎ በመሓላ በጸናው ክህነቱ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ በዚያ ዘመን ማንም ሊያቀርበው ያልቻለውን በኋላ መድኃኒታችን ክርስቶስ ብቻ ያቀረበውን ለወንጌል መምጣት ፊታውራሪ የነበረውን ወንጌላዊ መሥዋዕት ለአብርሃም ያቀረበዉ፣ አብርሃምም ለመልከጼዴቅ አስራቱን በኵራቱን የሰጠዉ በዋሻ ውስጥ በተፈጸመ አገልግሎት ነው፡፡ ከዚያም በኋላ የዋሻ ቤተ መቅደስ የጥንት ክርስቲያኖች ይገለገሉበት ከነበረው ካታኮምብ(ግበበ ምድር) የተወሰደ ነው፤ በዘመኑ ወንጌል ሰፍታ መነገር ስትጀምር ሁለት ዋና ዋና ፈተናዎች ገጥመዋታል፡፡

              ሕገ ኦሪት እና ሕገ ጣኦት ናቸው፤ እነዚህ ሁለቱም ሕገ ኦሪት በሕገ ወንጌል ፍፁም ልትሆን፣ ሕገ ጣኦትም በሕገ ወንጌል ሊጠፋ ሲገባው አሕዛብ ለጣኦታቸው፣ እስራኤል ለኦሪታቸው በሚያሳዩት ቅንዓት ምክንያት ሕገ ወንጌል በምድራችን ላይ በዝታ ልትነገር አልቻለችም ነበር፡፡ ሲጀመርም መምህራችን ክርስቶስ በጨለማው ዓለም ውስጥ በጨለማ ነበርና ያስተማራቸው፡፡ ማቴ 10÷27 ‹‹በጨለማ የነገርኳችሁን በብርሃን ንገሩት›› እንደተባሉት በብርሃን እንዳይሰብኳት የጨለማው ዓለም ገዥ ቄሳሮች አይደረግም በማለታቸው ከነርሱ ብዙዎቹ እንደ ሳጥናኤል ፀሐይ ሊያቀልጠው በማይችል ጨለማ እንደ ተሸፈኑ እለተ ሞታቸው ደረሰ፤ ቤተ ክርስቲያንም በሰገነት ላይ ልትወጣ የሚገባት የሰማዩ ንጉሥ እጮኛ ንጽሕት ሙሽራ ስትሆን ጫጉላዋን በመሬት ልብ ውስጥ አደረገችው፡፡ ለጊዜው ከቄሳሮች ቁጣ ለመዳን አባቶቻችን የተጠቀሙበት ጥበብ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን በምድር ሆድ ውስጥም ለወዳጆቹ ማደሪያ እንደ ሚያዘጋጅና በፍቅሩ የተማረኩ ክርስቲያኖች በየትኛውም አይነት ፈተና ውስጥ ሆነው እንደሚያመልኩት ያስረዳበት ጥበብ ነው፡፡ እነ ቅዱስ ጳውሎስ በአቴንሱ የጥበብ ስፍራ በአርዮስ ፋጎስ፣ በግሪክ ሕዝብ ዘንድ እንደ አማልክት በሚቆጠሩት ታላላቅ ጠቢባን በነዲዮናስዮስ ፊት በሰገነት ላይ ወጥተው እስኪሰብኳት ድረስ በምድር ውስጥ ባለ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር፤

    የወንጌል ሰገነቱ የሰው ልብ እንጂ ከፍባለ ቦታ ላይ የተሠራ ውብ የነገሥታት መናፈሻ አይደለምና ምንም እንኳን በምድር ውስጥ ያለች ቢሆንም ከተማውን ከሞሉት ከነ አርጤምስ ቤተ መቅደስ በተሻለ ሁኔታ በመላው ዓለም መንፈስ ቅዱስ ቀጥሎ ቀጥሎ በሚደረግ ተዐምር እያገዛት እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰች፤ ተራራ ላይ ወጥታ ከመሠራቷ በፊት በሰው ልብ ውስጥ የተሠራውን የጣዖት ቤተ መቅደስ እያፈረሰች በሰው ልብ ውስጥ ተሠራች መቅደም ያለበት ይህ ነበርና፡፡

    ከዋሻ መውጣት ስትጀምር በወንጌል አምነው የተጠመቁ ምዕመናን የሚሠሯቸው አብያተ መቃድሳት ከላይ የጠቀስናቸውን ሁለቱን አይነት ቅርፆች የሚይዝ ሲሆን አንዱ ሰቀላማ ቅርጽ ያለው ነው፤ የተወሰደውም ከጥንቱ የሙሴ ድንኳን ጀምሮ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ምኵራባትና እንዲሁም ከታላቁ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአራቱም የዓለም መዓዝናት የምትሠራ መሆኑን ለመግለጥ ባለአራት መዐዝን አድርገው ይሠሩት ነበር፤ ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባታቸው የማይቀር ነውና በሮቹም በአራቱም ማዕዝን የተከፈቱ ናቸው እንጅ እንደ ክቡ ቤተ ክርስቲያን በሦስቱ ፆታ ምዕመናን ልክ ሦስት ብቻ ሆነው የተሠሩ አይደሉም፤

          የጥንቱ ቤተ መቅደስ ምንም እንኳን ባለ አራት ማዕዘን ሆኖ መሠራቱ የማይካድ ቢሆንም ከአንድ አባት ከያዕቆብ የተወለዱ እስራኤላውያንን ብቻ ይቀበል የነበረ በመሆኑ አንድ በር ብቻ ነው ያለው፤ ነገር ግን አይሁድ በክፋታቸው ምክንያት አልገባቸው ብሎ እንጅ አንድ አባት ቢኖራቸውም አራት እናቶች ነው ያሏቸው፤ ለምን ከአራቱም እናቶች ማኅፀን አስገኝቶ የአንድ አባት ልጆች እንዳደረጋቸው ባለማወቃቸው ከዓለመ ጣዖት፣ ከዓለመ ኃጢአት ኮብልሎ የሚመጣውን ሁሉ እስራኤላዊ ደም የለህም በማለት በእግዚአብሔር አማኝ ሲከለክሉበት ኖረዋል፡፡ አባታቸውን አንድ አድርጎ እናቶቻቸውን አራት ማድረጉኮ ከአራቱም የዓለም መዐዝናት የተበተኑ የሰው ልጆች በሙሉ አንድ ድምጽ አውጥተው ‹‹አቡነ ዘበሰማያት ›› የሚሉበት ዘመን እንደሚመጣ አመላካች ነበር፤ ታዲያ ቀኑ ሲደርስ ይህ እንዲተረጎም ቤተ መቅደሱ ከአዳም አብራክ፣ ከሔዋን ማኅፀን ለተገኘ ሥጋዊ ደማዊ ፍጥረት ሁሉ እንዲሆን በአራቱም የዓለም መዐዝን ልክ አራት በር እንዲኖረው አደረገ፤ አንድ አባት ያለን ነገር ግን በአራቱ መዐዝን ተዘርተን የምንኖር፣ ጊዜው ሲደርስ በአንድ ጎተራ የምንሰበሰብ የእግዚአብሔር ምርቶች መሆናችንን የሚያሳይ ምሥጢር አለው፡፡ ማቴ 3÷12

          በሐዲስ ኪዳኑ ቤተ መቅደስ ይህ ምሥጢራዊ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲተረጎም ቤተ ክርስቲያኑ ባለ አራት በር ሆኖ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ እንዲህ ግን ስለሆነ ከውጭ ስንገባ ቤተ ክርስቲያን ከምሥራቅና ምዕራብ ከሰሜንና ደቡብ ለሚመጣው ሕዝብ የተሠራች የመንፈስ ቅዱስ ጉባኤ መሆኗን ይነግረንና ከውስጥ ስንገባ ደግሞ የቤተ መቅደሱ በሮች ሦስት በመሆናቸው፣ የውስጡም መጋረጃ አንድ በመሆኑ ሃይማኖታችንን ይሰብክልናል፤ እኛ አንድ ሲሆን ሦስት፣ ሦስት ሲሆን አንድ ብለን የምናምነውን አምላክ በአንድ ቤተ መቅደስ ላይ ሦስት በሮችንና አንድ መጋረጃን ከፊት ለፊት በማድረግ እንገልጠዋለን፤ አንድነቱ የማይነጣጠል፣ ሦስትነቱ የማይጠቀለል ነውና ሁል ጊዜ ለአንዱ ቤተ መቅደስ ሦስት በሮች እንዲኖሩት አድርገን እንሠራለን፤ ህንጻችንም ሃይማኖታችንን ሊገልጥ ይገባዋልና ማንም ቢሆን ደስ እንዳለው ሳይሆን እንደ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ትርጉም ባለው መንገድ ሊያንጽ ይገባዋል፡፡

    ·         ወደ ሦስተኛው የቤተ ክርስቲያን የአሠራር አይነት ስንመጣ ክብ (ቤተ ንጉሥ) ተብሎ ይጠራል በሥርዓተ

    ቤተ ክርስቲያን በጣም የሚደገፈው የአሠራር አይነት ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ሦስቱንም ፆታ ምዕመናን(ካህናት፣ወንዶችና ሴቶች) በየነገዳቸው ለይቶ ለይቶ በማስቀመጡ ረገድ ከሦስቱም የቤተ ክርስቲያን አይነቶች የተሻለ ስለሆነ ነው፡፡ እስካሁን የጠራናቸው የአሠራር አይነቶች ስናያቸው ብዙ ሕዝብ በመያዛቸው የሚመሰገኑትን ያክል በመጋረጃ የሚከፋፈሉ እንጅ በግድግዳ የማይከፋፈሉ በመሆናቸው ወንድና ሴቱን፣ ካህንና ደብተራውን ቀላቅለው በማቆማቸው የሚነቀፍ ነገር አላቸው፡፡ ምን አልባት ዛሬ ዛሬ እየተሠሩ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ስንመለከት በስፋት የምንመለከተው ቅድም ካልነው ምክንያት ጋር ተያይዞ ጥንታዊውንና ክቡን አሠራር ሳይሆን ሰቀላማውን አሠራር ነው፡፡ እንደኔ ግን ወደ ፊት የሚመጣው ትውልድ ሴቱ ከወንዱ፣ ወንዱ ከሴቱ አንድ ሆኖ በፕሮቴስታንቱ ዓለም እንደምናየው እንዳያስቸግር ፍርሃቱ አለኝ፡፡ በዚያውም ላይ የዚህን ዘመን አለባበስ እንደምታውቁት ከትከሻ የሚወርድ ነጠላ ለብሰው ለጸሎት የሚቆሙ እህቶቻችንን ማግኘት አስቸጋሪ  የሆነበት ነውና የምስጋና መሥዋዕታችንን እንክርዳዳዊ ሃሳብ ተጨምሮበት የቃኤል መሥዋዕት እንዳያደርግብን እሰጋለሁ፡፡

          ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ጥንታዊው የቤተ መቅደስ አሠራር ነውና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እጅግ የሚደገፍ ሥራ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታችን ካረገ በኋላ በአስራ ዘጠኝ ዓመት ገደማ በፊልጵስዩስ ከተማ ሥትሠራ ክብና ባለ ሦስት ክፍል፣ ሃያ አራት ክንድ ቁመትና አስራ ሁለት ክንድ ስፋት እንዳላት በታሪክ እንረዳለን፡፡ ሦስቱ ክፍሎቿ ቅድስት፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማኅሌት ናቸው፤

    አገልግሎታቸው

    ክፍል ሦስት

    ይቀጥላል

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ነገረ ቤተክርስቲያን - ክፍል ሁለት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top