• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday 18 November 2015

    ጌታችን ለምን በመስቀል ላይ ተሰቀለ?


    “እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!” በማለት ዓምደ ተዋሕዶ ጦማር ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በሙሉ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

    ጌታችን ለምን በመስቀል ላይ ተሰቀለ?

    ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶልናል፥ ክቡር ደሙን አፍስሶልናል፥ ክብርት ነፍሱንም በፈቃዱ አሳልፎ ሰጥቶልናል። ይህንንም ያደረገው በቤዛነቱ እኛን ከእርግማን ሊዋጀን ነው። ምክንያቱም የሰው ልጆች በጠቅላላ በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ ተይዘን ነበርና። በመሆኑም በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም፥ በሞተ ሥጋ ላይም ሞተ ነፍስ ተፈርዶብን ከእርግማን በታች ወድቀን ነበር። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን “እንደ ወጡ ሳይመለሱ፥ እንደወደቁ ሳይነሱ ይቅሩ፤” ሳይል እኛን ለመፈለግ ከሰማየ ሰማያት ወረደ። /ማቴ. 18፥12-14/። በመንፈስ ቅዱስ ግብር በማኅፀነ ድንግል ማርያም ተፀነሰ። /ሉቃ. 1፥35/። ከእመቤታችንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። /ሉቃ. 2፥7/። በተዋሕዶ ሰው አምላክ፥ አምላክ ሰው ሆነ። /ማቴ. 16፥13፣ 1ኛ ዮሐ. 1፥1-2፪፤ 5፥20/። ቀስ በቀስም አደገ። /ሉቃ. 2፥40/። ሠላሳ ዓመት በሞላውም ጊዜ በፈለገ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾመ። /ማቴ. 3፥13-17፣ ሉቃ. 3፥21-23፣ ማቴ. 4፥2/። ከዚያም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ሰባ ሁለቱን አርድዕትና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት መረጠ። /ሉቃ. 10፥1፣ የሐዋ. 1፥15/። አዲስ ሕግ ወንጌልንም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር አስተማረ። በመጨረሻም ሰለእኛ እርግማን /ኃጢአት/ ተላልፎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ። /ማር. 15፥23-37/። የሞተውም በፈቃዱ ነው። /ዮሐ. 10፥11፤ 15፥13/። በዚህም የዕለት ፅንስ ሆኖ በእመቤታችን ማኅፀን ጀምሮት የነበረውን የማዳን ሥራ በመስቀል ላይ ፈጸመው። /ዮሐ. 19፥30/።

    እንግዲህ ጌታችን ወደዚህ ዓለም መጥቶ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ የሞተው ከላይ እንደተጠቀሰው ስለ እኛ እርግማን ተላልፎ ነው። እርሱ በመስቀል ላይ እርግማናችንን /ኃጢአታችንን/ ሰለተሸከመልንም እኛ ከእርግማን /ከመርገመ ሥጋ፥ ከመርገመ ነፍስ/ ነፃ ሆነናል። ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፥ ሕመማችንንም ተሸክሟል፤ … እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፥ ስለበደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣፅ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።” ሲል አስቀድሞ የተናገረው ለዚህ ነው። /ኢሳ. 53፥4-5/። ቅዱስ ጳውሎስም ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና፥ ክርስቶስ ስለ እርግማን ሆኖ /ስለ እኛ ኃጢአት ተላልፎ በመስቀል/ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤” ብሏል። /ገላ. 3፥13/።

    በቆሮንቶስ መልእክቱም “የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆን እኛን ጻድቃን ያሰኘን ዘንድ ስለ እኛ ኃጢአት ተላልፎ ራሱን ኃጥእ አሰኝቷልና፤” ብሏል። /2ኛ ቆሮ. 5፥21/። ከዚህም ሌላ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ይኸውም ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፤” ብሏል። /ፊል. 2፥7-8/። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በበኩሉ “እርሱ ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፥ ኃጢአታችንን /እርግማናችንን/ በእንጨት /በመስቀል/ ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ፤” ብሏል። /1ኛ ጴጥ. 2፥22-24/።

    የቅዱስ መስቀል ትሩፋት

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ቅዱስ ሥጋውን በመቁረሱ ክቡር ደሙን በማፍሰሱ ያገኘናቸው ትሩፋቶች ምንድን ናቸው? ተብለው ለሚነሡ ጥያቄዎች ምላሽ ይዘን ቀርበናል፡፡

    ሕይወትን አግኝተናል፤

    በኃጢአት ምክንያት ሞት ገዝቶን ሞት ነግሦብን ነበር። ኃጢአት በዘር እየተላለፈም ሁላችንም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እንሞት ነበር። በመሆኑም ሞት ከአዳም እስከ ሙሴ /እስከ ክርስቶስ/ ድረስ ነገሠ። /ሮሜ. 5፥12-14/። ከክርስቶስ በኋላ ግን በክርስቶስ ቤዛነት ሞት ስለተሻረ አጥተነው የነበረውን ሕይወት አግኝተናል። ለዚህም ነው “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፤” የተባለው። /1ኛ ቆሮ. 15፥22/። በተጨማሪም “እኛ ሁላችን ደግሞ፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር እንደሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር /በክርስቶስ ቤዛነት/ ሕይወትን ሰጠን።” ተብሏል። /ኤፌ. 2፥3-5/። ምክንያቱም ጌታችን በሞቱ ሞትን ሽሯልና። /2ኛ. ጢሞ. 1፥10/።

    የሕይወትን ምግብ አግኝተናል፤

    ኃጢአት ወደ ዓለም ገብቶ ሞትን ያመጣብን በመብል ምክንያት ነው። /ዘፍ. 3፥1-24/። ምክንያቱም አዳምና ሔዋን የዕፀ በለስን ፍሬ በልተው ጐትተው ያመጡት ሞትን ነውና። ኢዮርብአምን እንዲገሥጽ ተልኮ የነበረውም የይሁዳ ሰው አትብላ የተባለውን በመብላቱ ያተረፈው ሞትን ነው። /1ኛ ነገ. 13፥20-25/። እስራኤል ዘሥጋም በምድረ በዳ የተመገቡት መና ከሞት አላዳናቸውም። /ዮሐ. 6፥49/። ስለዚህ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ሥጋውን የሕይወት እንጀራ አድርጎ በመስቀል ላይ ሰጠን። ይህንንም “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ /የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን/ ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤” ሲል አረጋግጦልናል። /ዮሐ. 6፥53-54/። በመሆኑም ዕለት ዕለት በቤተ ክርስቲያን የሚሠዋውና በሃይማኖት የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን አማናዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና አማናዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ምክንያቱም ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኰት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኰት ይሆናልና። /ማቴ. 26፥26-29/። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና፤” ያለው። /1ኛ ቆሮ. 11፥27-30/።

    ሰላምን አግኝተናል፤

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፤” ብሎ እንደተናገረ ፍጹም የሆነውን ሰላም የሰጠን በመስቀል ላይ ነው። ይህንንም፦ ሞትን በኃይሉ ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። /ዮሐ. 14፥27፤ 20፥19/። ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና፤” በማለት የቆላስይስን ሰዎች አስተምሯል። /ቆላ. 1፥19-20/። የኤፌሶንን ሰዎችም “አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና /ሰላማችን የተገኘው በእርሱ ቤዛነት ነውና/፤” ብሏቸዋል። /ኤፌ. 2፥13-14/።

    አዲስ ሰው ሆነናል፤

    በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ አርጅቶ የነበረው ሰውነታችን አዲስ የሆነው በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን /ሰውነታችን/ ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን።” ያለው /ሮሜ. 6፥6/። ዳግመኛም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ “ስለዚህ ማንም ቢሆን በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል፤” ብሏል። /2ኛ ቆሮ. 5፥17/። ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው፦ ጌታችን እኛን በቤዛነቱ አዲስ አድርጎናል፥ አዲስ ሕግ ወንጌልንም ሰጥቶናል፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር መንግሥተ ሰማያትንም አዘጋጅቶልናል። /ማር. 1፥15፣ 2ኛ ጴጥ. 3፥13፣ ራእ. 21፥1/።

    ታርቀናል፤

    በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተን እንኖር ነበር። ይሁን እንጂ እኛ በበደልን እርሱ ክሶ በቤዛነቱ መልሶ ታርቆናል። ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን፤” ሲል ገልጦታል። /ሮሜ. 5፥10-11/። በተጨማሪም “በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና፤” ብሏል። /ቆላ. 1፥20/። በኤፌሶን መልእክቱም “ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛት ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድ አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር /ከራሱ/ ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፤” ብሏል። /ኤፌ. 2፥14-16፣ 2ኛ ቆሮ. 5፥17/።

    መስቀል ለተዋሕዶ ክርስቲያኖች ምናችን ነው?

    ከላይ የጠቀስናቸው ትሩፋቶች የተገኙበት ቅዱስ መስቀል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ምናችን ነው?

    ኃይላችን ነው፤

    “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፤” /1ኛ ቆሮ. 1፥18/ ተብሎ እንደተነገረ፥ የእግዚአብሔር ኃይሉ የተገለጠበት ኃይለ እግዚአብሔር ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የፈጸመው በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ነው። በመሆኑም የጌታችን ቅዱስ ሥጋው የተፈተተበትና ክቡር ደሙም የፈሰሰበት መስቀል ስለ ክርስቶስ የከበረ ነው። ለምሳሌ የሆሳዕና አህያ በተጓዘችበት ጐዳና ሁሉ የተነጠፈላትና የተጐዘጐዘላት ስለ ክርስቶስ የከበረች በመሆኗ ነው። /ማቴ. 21፥8/። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የከበረውና የማዳን ኃይሉም የተገለጠበት መስቀል፥ ወልድ ዋህድ ብለን በኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ለምናምን ሁሉ ዲያብሎስን የምንቀጠቅጥበት ኃይላችን ነው። ምክንያቱም ጌታችን አስቀድሞ “እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤” ተብሎ እንደተነገረ ዲያብሎስን የቀጠቀጠው በመስቀሉ ነውና። /ዘፍ. 3፥15/። ይህንን በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸመ ምሳሌ አለ። የነቢያት አለቃ ሙሴ እጆቹን በመስቀል አምሳል ግራና ቀኝ ዘርግቶ በሚጸልይበት ጊዜ እስራኤል ኃይል አግኝተው ጠላቶቻቸውን ድል አድርገዋል። እኛም እስራኤል ዘነፍስ የምንባል ምዕመናንም ጠላቶቻችንን አጋንንትን በኃይለ መስቀሉ ድል እናደርጋቸዋለን። የአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል አባት ቅዱስ ያዕቆብም እጆቹን ባመሳቀለ ጊዜ ኃይል አግኝቶ በዮሴፍ ልጆች ላይ በረከትን አሳድሯል። /ዘፍ. 48፥13-20/። እኛም በመስቀሉ ኃይል በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን እናገኛለን።


    ነቢዩ ዳዊት “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ፤” ብሎ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረ፥ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዲያብሎስ ቀስት /ጦር/ እናመልጥና እንድን ዘንድ በደሙ ቀድሶና አክብሮ የሰጠንን ምልክት መስቀልን አጥብቀን መያዝ አለብን። /መዝ. 59፥4-5/። እንደ ቅዱስ ጳውሎስም “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት /ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት ከሆነበት/ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት /እኔም በዓለም ዘንድ ሙት ከሆንኩበት/ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” እያልን በመስቀሉ መመካት አለብን። /ገላ. 6፥14/። መስቀልን በምልክትነቱ ብቻ የሚቀበሉት ሰዎች አሉ፤ ለእኛ ግን መስቀል ኃይላችን፥ መድኃኒታችን፥ የሚያድነን፥ ቤዛችንና የነፍሳችንም መዳኛ ነው።

    ይቆየን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ጌታችን ለምን በመስቀል ላይ ተሰቀለ? Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top