• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 16 November 2015

    የመንቃት ዘመን


    የሰው ልጆች አባት አዳም ከተፈጠረ በስምንተኛው ቀን ላይ ከባድ እንቅልፍ ውስጥ እንደነበረ በታላቁ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ እናነባለን፤ በተፈጠረ ማግስት የነበረውን ታላቁን ሰንበት ካከበረ በኋላ እንዲሠራ የታዘዘውን ሠርቶ ሲጨርስ አዳም ብቻውን እንዳይሆን የፈለገው አምላክ ‹‹ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም …›› በማለት ብቻውን ዓለምን እንደ ማይሠራት አስቦ የምትረዳውን ሔዋንን በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ሳለ ፈጠረለት፡፡ እንቅልፍ ምሳሌው የሆነ ሞትን የምታመጣ ሔዋን በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ከነበረው አዳም ጎን እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ተፈጠረች፡፡ የእንቅልፍን ታሪክ ያወቅነው ከዚህ ጀምሮ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለባሕርያችን የሚስማማ ሆኖ እንድናርፍ በተሰጠን ሌሊት ውስጥ እንቅልፍን ከዚህ ክፉ ዓለም ወጥተን ሌሎች በልባችን ያሰብናቸውንም ሆነ ያላሰብናቸውን የምናይበት አንዳንድ ጊዜም ያላወቅነውን የምናውቅበት ሌላ ጊዜም ወደ ፊት በሕይወታችን ውስጥ ሊሆን በእግዚአብሔር የታሰበልንን ከመሆኑ አስቀድሞ የምናይበት ነው፡፡

        እግዚአብሔር ሥራው ግሩም ነውና የምንወደውን ብርሃን ወስዶ በጨለማ ያሳርፈናል፤ እያየን እየሰማን ሊያደርግ ያልፈለገውን ነገር በእንቅልፍ ውስጥ ሳለን ያደርግልናል፤ በሌላ አነጋገር ሌሊት ቀን የምንሠራውን የምናቅድበት እንቅልፍም የሕይወታችንን መስመር የምናይበት የሕይወታችን አንድ ጠቃሚ ክፍል ነው ማለት ነው፤ የቀደሙት አባቶቻችን ታላቁን የክርስቶስን ሰው የመሆኑን ነገር ያዩት በሦስት መንገድ ነው፡-

    §  በራእይ

    §  በሕልም

    §  ግልጥ ሆኖ ከእግዚአብሔር በሚመጣ መልእክት ነው

    ያለ እንቅልፍ ሕልም የለም፤ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ባያንቀላፋ ኖሮ ከምድር እስከ ሰማይ በተዘረጋው መሰላል ላይ የተቀመጠውን ንጉሥ እንዴት ማየት ይችል ነበር፤ ‹‹ዛቲ ይእቲ ሆኅታ ለሰማይ ዝዬ ይትሐነጽ ቤተ እግዚአብሔር፤ ይህች የሰማይ ደጅ ናት በዚህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ይሠራል›› ብሎ መናገርን እንዴት ሊያገኝ ይችላል፤ በእንቅልፉ ውስጥ ያዕቆብ ወደ ፊት የሚሆነውን አይቶ ተናገረ ከአርባ ስምንቱ የአይሁድ ምኩራባት አንዱ እሱ በተኛባት ስፍራ በቤቴል እንደሚሠራ መሰከረ፤ ነቢይነቱ ከእንቅልፍ በኋላ ተጀመረ፤

        አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እንቅልፍ እግዚአብሔር ልጆቹን ከመከራ የሚሰውርበት  የደኅንነት ድንኳን ሆኖ ሊያገለግልም ይችላል፤ ስሳ ስድስት ዓመት የተኛውን አቤሜሌክን ሦስት መቶ ሰባ ሦስት ዓመት የተኙትን ሰባቱን ሕጻናት ከሞት የሰወረበት መንገድ ስለሆነ ነው፡፡ ብቻ በዚያም አለ በዚያ እንቅልፍ ከእግዚአብሔር ሲሆን የጤና ምልክት መሆኑ ነው፡፡

        እኔ ግን ዛሬ ስለ እንቅልፍ ላወራችሁ ፈልጌ ሳይሆን ከእንቅልፍ ስለመንቃት ነው፤ ምክንያቱም ዘመኑ የመንቃት ዘመን ነውና፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የብሉይም ሆነ የሐዲስ ኪዳን መግቢያ ምእራፍ ብትመለከቱት የእንቅልፍ ታሪክ አለበት የመጀመሪያው በአዳም ሁለተኛው ደግሞ በዮሴፍ የተመዘገበ የእንቅልፍ ታሪክ ነው፤ ልዩነቱ በአዳም እንቅልፍ ውስጥ ራእይ የሌለ ሲሆን በዮሴፍ እንቅልፍ ውስጥ ደግሞ ራእይ አለበት፤ የአዳም እንቅልፍ ሞትን የሚያስከትል በመሆኑ ራእይ አልባ ሆነ የዮሴፍን እንቅልፍ ተከትሎ ባለው ዘመን ግን የሚቀጥለው ዘመን የትንሣኤ ነውና ዮሴፍ በእንቅልፉ ውስጥ ሲነቃ የሚያደርገውን አየ

        ባለ ራእይ ሰው በእንቅልፉም ውስጥ እንደሞተ ሰው አይደለምና ነገን ያይበታል፤ ቀጣይ ሕይወቱን ይተነብይበታል የነቃ ትውልድ በእንቅልፍ ጽናት ማዕበል አይሰጥምም የነቃ ትውልድ አፉ ባይናገርም በኅሊናው ዝም አይልም ዐይኖቹ እንጅ ኅሊናው አያንቀላፋምና፡፡ አፈ ወርቅ ቅዱስ ዮሐንስ ይህን የዮሴፍን የእንቅልፍ ታሪክ (ወነቂሆ ዮሴፍ እምንዋሙ ዮሴፍም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ......) ማቴ 1÷24 የሚለውን ሲተረጉም ዘመኑ የመንቃት ዘመን ነበረ ብሎ ተርጉሞታል፡፡

        በእኛም ዘንድ ይህ አሁን ያለንበት ዘመን እባካቸችሁ የመንቃት ዘመን እንዲሆን ጸልዩ ካልነቃን እንደምን በመኝታችን ላይ ያየነው ራእያችን ይፈጸማል እንዴትስ ያሰብነውን መስራት እንችላለን፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደተባለ ዮሴፍ በእግዚአብሔር መላክ የታዘዘውን ማድረግ የቻለ ከአንቅልፉ ከነቃ በኋላ ነው፤ ማቴ 1÷25‹‹ወነቂሆ ዮሴፍ እምንዋሙ ገብረ በከመ አዘዞ መላከ እግዚአብሔር፤ዮሴፍም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ የእግዚአብሔር መላክ እንዳዘዘው አደረገ›› ተብሎ ስለ እርሱ ተጻፈለት፡፡ ያልነቃ ትውልድ እንዴት ይታዘዛል ሳይነቃስ እንዴት የታዘዘውን ያደርጋል አሁን ዘመኑ የመንቃት ዘመን ነው፤ በተለይም ያለንበት ወቅት አዲሱን ዓመት የምንጀምርበት በመሆኑ ምን አልባት ያሳለፍነው ዓመት የእንቅልፍ ዓመት ከነበረ ይሄኛው ግን የመንቃት ዘመን ሊሆንልን ይገባል፤

        ባለፈው ጊዜ እግዚአብሔር ያዘዘንን ማድረግ ሳንችል የቀረነው ለምን ይመስላችኋል ተኝተናልና ሳናደርገው ቀረን እግዚአብሔር ደግሞ የተኙትን ማንቃት ልማዱ ነውና ወደ ተኙት ሰዎች ሂዶ ያነቃቸዋል፡፡ በእንቅልፍ ውስጥ ስለነበረው አልዓዛር የተባለው ነገር  ምንኛ ድንቅ ነው፤ ‹‹አልዓዛር አርክነ ኖመ ወባሕቱ አሐውር አንቅሆ፤ ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል ነገር ግን ላነቃው እሔዳለሁ›› ዮሐ 11÷11   የተኙትን  ሳይቀር በጥላው ስር እንዲጠለሉ ያደርጋቸዋል፤ የሚተኛ ሁሉ ‹‹ አንሰ ሰከብኩ ወኖምኩ ፤ እኔ ግን በሰላም ተኛሁ አንቀላፋሁም መዝ 3÷5 ብሎ ያንቀላፋል ይህ ግን ጠባይዐዊ እንቅልፍ ተብሎ ይጠራል፤ ጠባይዐዊ እንቅልፍ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ የታዘዘ በመሆኑ እንደሚገባ ብንተኛ የሚያስነቅፍ አይደለም በእርግጥ በባሕታውያን ዘንድ የእንቅልፍ ጾም የታዘዘ በመሆኑ ሌሊቱንና ቀኑን በጾምና በጸሎት ያሳልፉትና በስግደት ለደከመው ሰውነታቸው ‹‹ኦ ሀካይ ሥጋዬ ንሳዕ መክፈልተከ፤ አንተ ሰነፍ ሥጋዬ ድርሻህን ውሰድ›› ብለው ለጥቂት ሰዓት ብቻ ያንቀላፋሉ እንዲያውም አባ አርሳንዮስ በትጋት ውስጥ ላለ መነኩሴ ከአንዲት ሰዓት በስተቀር መተኛት አይገባውም ይሉ ነበር፤ በዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ግን ለጸሎት ከተመደቡ ጥቂት ጊዜያት በስተቀር ቢተኙ ኃጢአት ሊሆን አይችልም፡፡

        ከዚያ ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገር እንዳንነቃቃ የሚያደርገን የኃጢአት እንቅልፍ በእግዚአብሔር ዘንድ  የከፋ ነው፤ ምንም ራእይ የማታይበት ሰው ከሞት በከበደ አዚም ውስጥ የሚቆይበት ክፉ እንቅልፍ ነው፤ በእንቅልፍ ውስጥ ያሉትንማ አየናቸው እኮ የምድሩን አይደለም የሰማዩን ምሥጢር በእንቅልፋቸው አዩ በኃጢአት አዚም ውስጥ ያሉት ግን ሌላውን ሳይሆን ራሳቸውንም ማየት አይችሉም ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን በማቴዎስ 25 ላይ የጠቀሳቸውን የአምስቱን ሰነፍ ደናግል ታሪክ በተረጎመበት ትምህርቱ ‹‹አኮ ንዋም ጠባይዐዊ አላ ኃዲገ ምግባራት ወትሩፋት መንፈሳውያት፤ እንቅልፋቸው ጠባይዐዊ አይደለም ከትሩፋት መራቅ ከመንፈሳዊ ተግባር መለየት ነው እንጅ›› በማለት የክርስቶስን መምጣት በትጋት መጠበቅ የተሳናቸውን ሰነፎች ይገስጻቸዋል፡፡

        እስከ መቼ እንተኛለን ዮሴፍ እንዳደረገ ነቅተን የታዘዝነውን ልናደርግ ይገባናል፤ የማይተኛ የለም ከሞተ ሰው በስተቀር የማይነሣም የለም፤ እኛም ተኝተናል እንጅ አልሞትንምና አሁን ለመንቃት ጊዜአችን ነው፡፡ አሁን እኮ ‹‹አንተ የምትተኛ ንቃ ክርስቶስም ያበራልሀል›› ተብሎ ዐዋጅ የተነገረበት ዘመን ላይ ነን፤ ተስፋ አንቆርጥም የተኙትን አሥነስቶ ሥራ ሲያሠራ አይተናልና፡፡ እናምናለን አንድ ቀን ‹‹..... እግዚአብሔር ደግፎኛልና ተነሣሁ›› መዝ 3÷5 ብለን እንዘምራለን ያም ቀን ዛሬ ነው፡፡

                              የመንቃት ዘመን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የመንቃት ዘመን Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top