• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 17 November 2015

    ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት


    ሐምሌ አሥራ ዘጠኝ ቅዱስ ገብርኤል የራማው ልዑል ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ሕጻኑ ቂርቆስንና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ከሚነደው እቶን እሳት ያዳነበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ቀን ለክርስቲያን ሁሉ የተድላ የፍስሐ በዓል ነው፡፡ የጌታችንን ምሕረትና ቸርነት የመላአኩን አዳኝነት ተራዳኢነት ያየንበት ዕለት ነው፡፡ እኛም ለዕለቱ የሚስማማውን ትምህርት ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ

    ሦስት ዓመት እንኳን ሳይሞላው በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወሩ ታላቅ ሰማዕትነትን የተቀበለው ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ አባቱ ቆዝሞስ (ስምዖን) እናቱ ኢየሉጣ ይባላሉ፡፡ ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ በሕዳር 15 ቀን የተወለደ ሲሆን ሀገሩ በታችኛው እስያ ልዩ ስሙ ሀንጌቤን ይባላል፡፡ ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ነበርና መምለኬ ጣዖት የሆነው ንጉሥ እስክንድሮስ ቅድስት ኢየሉጣን ‹‹ለጣዖቴ ስገጂ›› ብሎ አስገደዳት፡፡ እርሷም ‹‹ሕጻኑ ልጄ መጥቶ ይመስክር›› ብላ ስትናገር ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ ተጠራና ተጠየቀ፡፡ ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስም ‹‹ለጣዖት አንሰግድም፣ ዘላለማዊ የሆነ የማይሻር አምላክ ስላለ ለእርሱ ነው የምንሰግደው›› ብሎ የአምላኩን ክብር በሕፃን አንደበቱ መሰከረ፡፡ ሕፃኑም ይህንን በመሰከረ ጊዜ ዕድሜው ገና ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወሩ ነበር፡፡

    እጅግ በጣም የሚገርመው ቅዱስ ቂርቆስ በከሃዲው ንጉሥ ፊት የጌታችንን ክብር በመሰከረ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ አርባ ጋን ውኃ የሚይዝ በርሜል አስጥዶ አርባ ቀን ሙሉ እሳት አስነድዶ ቅንጭብ፣ ዘይት፣ ዝፍጥና ሌላም በእጅጉ የሚጎዱ ነገሮችን በውስጡ ጨምሮ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን ወደዚያ እቶኑ እሳት እንዲከቷቸው አዘዘ፡፡

    ንጉሡ እስክንድሮስ ጭፍሮቹን “ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ሙጫ፣ እርሳስ፣ ብረትን፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል ጨምሩበት” ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮችም ያዘዛቸውን ከፈጸሙ በኀላ መጥተው “ያዘዝከንን ሁሉ ጨምረንበት ነዶ ፈልቷል” አሉት፡፡ “ድምፁም እንደ ነጎድጓድ ይሰማል፤ ወላፈኑም እንደ ፀሐይ ያንፀባርቃል፡፡ የፍላቱም ኃይል አሥራ አራት ክንድ ያህል እየዘለለ ይወጣል፡፡ በውስጡ የሚጣሉትን ሰዎች እዘዝ” አሉት፡፡ ያንጊዜም ህፃን ቂርቆስንና እናቱን ኢየሉጣን ይዘው ከእስር ቤት አወጧቸው፡፡ በክርስቶስ ስም ስላመኑ በእስር ቤት አግብተው አስረዋቸው ነበርና ፍላቱ ወደ ላይ በሚዘል በብረት ጋን ውስጥ ለመጨመር ሲወስዷቸው በዚያን ጊዜም እልፍ ከአንድ ሺህ አራት መቶ ሰዎች እንዲወጡና በፈላው የብረት ጋን ውስጥ የቅዱሳንን አሟሟት እንዲያዩ ሹሙ አዘዘ፡፡ ቅድስት ኢየሉጣም የፍላቱን ግርማ ባየች ጊዜ ተሸበረች፡፡ ተጠብቆላት ያለውንም ዋጋ ትታ ልትክድ ፈለገች፡፡ ቅዱስ ቂርቆስም ይህን ባወቀ ጊዜ “እናቴ ሆይ ከብረት ጋን ግርማ የተነሳ አትፍሪ፤ ድንጋፄም አይደርብሽ” እያለ ከብሉይና ከሐዲስ እየጠቀሰ እንድትጸና አስተማራት፡፡

    “ነገር ግን እናቴ ሆይ አናንያንና አዛርያን፣ ሚሳኤልንም እግዚአብሔር ከዕቶን እሳት እንዳወጣቸው እወቂ፤ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ውስጥ ሊያድነን ይችላል፡፡ እናት ሆይ ከሚያልፈው ከዚህ ዓለም ጭንቅ ልታመልጭ በሚያልፈው በዘለዓለም እሳት ልትቀጭ ትሻለች፡፡ እናት ሆይ ይህን አትሺ፤ ይቅርብሽ አሁን እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ ሶስናን ከሀጢያተኞች እጅ ያዳናት እኛንም ከብረት ጋን ያድነናል፡፡ ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ ያዳነ እርሱ ያድነናል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችን ልንፈፅም ፈቅዶም እንደሆነ የኢዮብን ነፃነት (ትእግስት) ልናገኝ ይገባናል፡፡ እርሱ ልጆቹንና ሚስቱን ያገኘው ገንዘብ ሁሉ አጥቶ በመጨረሻው ሰውነቱን አጥቶ ነበርና ምንም ምንም የቀረበለት አልነበረምና እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ ከማለት በቀር ያለው ነገር የለም እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ወሰደ አለ፡፡ የእግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለም ይመስገን አለ፡፡ እኛም ይህንን መከራ ልንታገስና የተጠበቀልንን ልንከተል ይገባናል…” እያለ አብዝቶ መከራት፡፡ ነገርግን በዚህም ምክር እናቱን መመለስና ለሰማዕትነት ማዘጋቸት አልቻለም፡፡ ከዚህ በኋላ ቂርቆስ ዓይኖቹን ወደሰማይ አቅንቶ መጸለይ ጀመረ፡፡ “እግዚአብሔር ሆይ ይህች ባርያህ ከምትክድ ከህይወት መፅሐፍ እኔን ፋቀኝ አለ፡፡ አቤቱ ይህነን ነገር ልታደርግ አይገባህም፤ አቤቱ እርሻውን ልታቃጥል ፍሬውንም ልትባርክ ትወዳለህን፡፡ አቤቱ እንጨቱን ቁረጡና አንድዱት ቅጠሉን ጠብቁ ብለህ ልታዝ አይገባህም፡፡ እንጨቱንም ቅጠሉንም ጠብቁ ብለህ እዘዝ እንጂ ይህ አይገባህም ያመነብህ ሁሉ ይህን ያየ ዘንድ፡፡ ማዳን የሚችል አምላክ ኑሮአቸው ቢሆን ከዚህ ከእሳት ባልሸሹም ነበር ብሎ እንዳይጠራጠር፡፡ ዲያብሎስ ከባለስልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ ቅዱሳኑም ድል ነሳኋቸው ብሎ እንዳይመካ፣ ከመንጋውም አንድ በግ ቀማሁ እንዳይል አቤቱ የኃይል መንፈስ ለእናቴ ስጣት አበርታት…” ብሎ ጸለየ፡፡
    በዚያን ጊዜ ዲያብሎስ ከእርሷ ሸሽቶ ሄደ፡፡ ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ እንዲህ አለች፡- በመንግስተ ሰማያት አባት የሆንከኝ ልጄ ሆይ ጌታህ ኃይል ስጠኝ፡፡ የሚጠብቀንን ገድላችንን እንፈፅምና ድል እንነሣ” አለችው፡፡ የብረት ጋኑን ሲነድ ሳየው በምንጭ ላይ በዝቶ እንደሚወርድ ጠል ሁኖ አየዋለሁና፡፡ ቅዱሳንም ይህንን ሲነጋገሩ አንስተው ከብረት ጋኑ ውስጥ ጨመሯቸው፡፡ በውስጡም አንገትን የሚቆለምም ልብን የሚያጣምም ሆድን የሚሰነጥቅ ሥርንም የሚበጥስ መሣሪያ ነበረበት፡፡ ወዲያውም የራማው ልዑል ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ ከሰማይ ወረደና የብረት ጋኑን እሳት ፈጽሞ አበረደው፡፡ ከቅዱሳንም አንዱን እንኳን ሳይነካው የብረት ጋን ማቃጠሉና መፍላቱ ፀጥ አለ፡፡ እንደ ውኃም ሆነ፡፡

    ንጉሡም እሳቱ እንዳልጎዳቸው ሲያውቅ ከዚያ አውጥቶ በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ አፍና አፍንጫ መርዝ ከተተበት፣ ነገር ግን መርዙ ምንም አልጎዳውም እንዳውም ምግብ ሆነው፡፡ ዳግመኛም ጨውና በርበሬ በዐይኑ አነደደበት፡፡ አሁንም ምንም አልነካውም፡፡ ከዚህም በኀላ ሹም እስክድሮስም አስራ አራት የተሳሉና የጋሉ ብረቶች ያመጡ ዘንድ ዳግመኛ አዘዘ፡፡ ሰባቱን በእናቱ አካል ሰባቱን በሱ አካል ውስጥ ይተክሉ ዘንድ ከነዚሁም ሁለቱን በጆሮዎቹ ሁለቱን በዓይኖቹ ሁለቱን በአፍንጫዎቹ አንዱን በልቡ ይተክሉ ዘንድ አዘዘ፡፡በሕፃኑም ላይ ሹሙ እንዳዘዘው አደረጉበት፡፡ አሁንም ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና ፈወሳቸው፡፡
    ዳግመኛም የሕጻኑን እራስ ከነቆዳው ገፈው በእሳት ውስጥ ይጨምሩ አንድ ሹም አዘዘ፡፡
    እንዲሁም አደረጉበት፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ ገብርኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ መጥቶ ይህንን መከራ ከሕፃኑ አራቀለት፡፡ ዳግመኛም ሹሙ በመቃን ውስጥ ጨመረው በገመድ እንዲሰቅሉት አዘዘ፡፡ ከዚህም መከራ መልአኩ አዳነው፡፡ በዛሬዋ ዕለት ሐምሌ 19 ቀን በዓሉን በታላቅ ድምቀት የምናከብረው ይህንን ሁሉ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት በማሰብ ነው፡፡

    ንጉሡም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በብዙ ጭንቅና ሥቃይ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ለ3 ዓመታት አሠቃያቸው፡፡ እነርሱም መከራን እየተቀበሉ በከሀዲው ንጉሥ ፊት የአምላካቸውን ስም እየጠሩ መሰከሩ፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ክብሩን ይመሰክሩለት ዘንድ የቢታንያን ድንጋዮችና የበለዓምን አህያ አንደበት ከፍቶ ያናገረ አምላክ ሦስት ዓመት እንኳን ባለሞላው በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር ሕፃን ልጅ ላይ አድሮ በወቅቱ የነበሩ ዓላውያን ነገሥታት ክብሩን እንዲያውቁ አደረገ፡፡

    በመጨረሻም ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር 15 ቀን በ3 ዓመት ከ1 ወር ከ3 ቀኑ አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ሰማዕትነትን ተቀብሏል፡፡ ሲሰየፍም ከአንገቱም ደም፣ ውኃና ወተት የወጣ ሲሆን ሦስት አክሊላትም ወርደውለታል፡፡ ጌታችንም የመከራውን ጽናት የትዕግስቱን ብዛት አይቶ ከመከራ ሊያሳርፈው ፈቀደና ተገልጾለት ‹‹ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ቂርቆስ›› አለው፡፡ ‹‹ሰላም ላንተ ይሁን፤ የመከራህን ጽናት፣ የትዕግስትህን ብዛት አይቼ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍህ መጣሁ›› ብሎ ብዙ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ ‹‹…ስምህ በተጠራበት፣ ቤተመቅደስህ በታነጸበት፣ ስዕልህ ባለበት ቦታ ሁሉ የሕፃናት እልቂት፣ የከብት በሽታ፣ የእህል እጦት ርሀብ፣ ቸነፈር አይደርስም›› የሚል አስደናቂ ቃልኪዳንም ገብቶለታል፡፡ ሕፃኑም በምድር ላይ አልተቀበረም ይልቁንም ጌታችን በኤልያስ ሰረገላ ሥጋውን አሳርጎለታል፡፡ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣም በጥር 16 ቀን ሰማዕትቷን በክብር ፈጽማለች፡፡

    ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በአማላጅነታቸው የምታመን ሁላችንን
    የብርሃናዊውን መልአክ የቅዱስ ገብርኤልን፣ የሕጻኑ ቂርቆስንና የቅድስት ኢየሉጣን ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን፡፡ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top