• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 17 November 2015

    ነገረ ቤተ ክርስቲያን ክፍል አንድ


     ነገር የሚለው ቃል ሲተረጎም ፡- ወግ፣ ታሪክ፣ መልዕክት፣ ሥርዓት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፤ ነገረ ቤተ ክርስቲያንም ስንል የቤተ ክርስቲያንን ጉዞ የሚገልጽ ወግ፣ ታሪክ፣ መልዕክት፣ ሥርዓት፣ ሕግ የሚነገርበት ትምሕርት ማለታችን ነው፡፡ በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለሦስት ነገሮች እንነጋገራለን፤ ስለሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ካሕናት አገልግሎትና ስለ ምዕመናን እንመለከትበታለን፤ ቤተ ክርስቲያን የሚለውንም ቃል ስንተረጉመው እነዚህን ሦስት ትርጉሞች ነውና የሚሰጠን፡፡

          በዚህም ርዕሰ ጉዳይ ውስጥ ከሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አተካከል ጀምሮ ምዕመናንና ካህናት አንድ ሆነው የሚወርሷት፣ እኛ ሁላችንም ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት እስክትሰጠን ድረስ ያለውን የሰው ልጆች ሥርዓተ አምልኮ አፈጻፀም በተመለከተ አባቶቻችን የነገሩንን፣ በመጻሕፍት ጉያ ውስጥ የተደበቀውን መንፈሰ እግዚአብሔርን ገላጭ በማድረግ እያወጣን እንነጋገራለን፤

          ለዚህም ጽሑፋችን በዋናነት ፍትሐ ነገሥትን ቋሚ ምስክር የምናደርግ ሲሆን ፈውስ መንፈሳዊንና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት በምንጭነት እንጠቀማለን፤ መልካም ንባብ፡፡

         በእንተ ሕንጼሃ ለቤተ ክርስቲያን   

    በዚህ ንዑስ ርዕስ ውስጥ ማየት የምፈልገው የቤተ ክርስቲያንን የአተካከል ነገር ነው፤ 
    መምህራችን ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሲመላለስ በነበረበት ጊዜ ፍጹም አንድነቷ ከሁሉ በላይ የሆነች ምዕመንን ከተበተነችበት ሰብስቦ አንድ መንጋ እንዳደረጋት እናውቃለን ምዕመናን ከመሰብሰብ አስቀድሞ የሠራው ሌላ የቤተ ክርስቲያን ሥራ የለም፤ ከሰማያዊነት ወደ ምድራዊነት ያመጣውም የምዕመናን ከልጅነት በረት ወጥቶ በምድረ በዳ እረኛ እንደሌላቸው መንጋዎች ተበትነው የአራዊት ንጥቂያ የጠላት መሳለቂያ መሆናቸው ነውና፤ ስለዚህም የመጀመሪያውን ሥራውን የጠፉትን በጎች ፍለጋ አደረገ፡፡ በዚህ የጠፉትን የመፈለግ ወቅት የሰበሰባቸውን ምዕመናን የሚያከማችበት ስፍራ አልነበረውም፤ ምክንያቱም ለዚህ ለእግዚአብሔር መንጋ የሚሆን ንጹሕ ስፍራ ባለመኖሩ ነው፡፡

          ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ፣ እንደ ሰው በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በሰው መካከል እየተመላለሰ የሚሠራቸው ሥራዎችን ጨርሶ ወደ ቀደመ አነዋወሩ የሚመለስበት ጊዜ ሲደርስ ለምዕመናን መሰብሰቢያ የሚሆን ቤትን አሳይቷቸው መሄድ ስለነበረበት ያደረገውን ተመልከቱ፤ አይሑድ ለገዛ ራሳቸው ጥቅም የማይገባ ሥራ እየሠሩበት ወደ ሚገኘው ቤተ መቅደስ ገብቶ ቤተ መቅደሱን አስተካከለ፤ ከዚህ አስቀድሞ ጌታችን በተወለደበት ዕለት ለማደሪያ የሚሆን ቦታ የላቸውምና ድንግል የበኵር ልጇ ክርስቶስን የወለደችው በከብቶች በረት ነው ሉቃ 2÷7 የአባቱን ቤት ወንበዴዎች ወርሰውት የውንብድና ሥራ እየሠሩበት ነበርና በዚያ እንዳይወለድ ሥራቸውን ስለተጸየፈ ለመወለጃው የከብቶችን በረት መረጠ፤ እንደእውነቱማ ከሆነኮ በመለኮቱ፡- ሰማያዊ አባቱ የሚመሰገንበት በዚያም ተገኝቶ የሰው ልጆችን ጸሎት ሊቀበል ቃል የገባበት ቅዱስ ቦታ ነው  1ነገ 7÷16፤ በምድርም አባቱ ሰሎሞን የሠራው በሰማይም በምድርም የአባቱ ቤት ነው በዚህ ሊወለድ በተገባ ው ነበር፤ ዳሩ ግን ምን ይሆናል የአባቱን ቤት የያዙት ሌሎች ናቸውና ያንን ስፍራ ለመወለድ አልመረጠውም፡፡

          በዚያ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሆነው ደጅ የሚጠኑት የእርሱን መምጣት ነው ሆኖም ግን ደጅ የሚጠኑት መምጣቱን፣ በሌላ ስፍራ መወለዱንም ሳያውቁ ቀሩ፤ እነርሱ በእግዚአብሔር ቤት ይኖራሉ እንጅ የእግዚአብሔር ሰዎች አልነበሩምና እግዚአብሔርም ሊሠራውን ያሰበውን ታላቁን የመዳን ምሥጢር እንዳያዩ ዐይኖቻቸውን ከደነባቸው፡፡ ይህም ሳያንስ ለቤተ መቅደስነት የሠሩት ቤታቸውን ናቀባቸው ቀኑ ደርሶ እስኪያስተካክለው አንዳንድ ጊዜ በቀዳማዊ ልደቱ ከሕግ በላይ የተወለደው ጌታ በደኃራዊ ልደቱ ከሕግ በታች ተወልዷልና ሕገ ኦሪትን ለመፈጸም በእናቱ እቅፍ በሕጻናት ልማድ በተወለደ በዐርባኛው ቀን ጀምሮ በሆሣዕና በአህያይቱና ውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ እስከገባበት የመጨረሻ ው ቀን ድረስ ወደዚህ ቤተ መቅደስ እየገባ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን መሥራቱ ተጽፎ የምናገኘው እውነት ነው፡፡ ሉቃ 2÷24፣42፣ ዮሐ 8÷1 - 12 ፣ ማቴ 24÷1 ፣21÷13 ለአብነት ያክል እነዚህን መመልከቱ በቂ ነው፡፡

          በሌሎቹ ቀናት ወደ ቤተ መቅደስ የገባው ከሕዝቡ ጋር እንደ ሕዝባዊ ሆኖ ነበር የሆሣዕናው ግን ከሁሉም ልዩ ነው እንደ አባቶቹ ነቢያት የሰላሙ ዘመን እንደደረሰ ሊያበሥራቸው በአህያ ላይ ተቀምጦ ነው የመጣው፡፡ አባቶቹ ነቢያት ዘመነ ሰላም መሆኑን ያስረዱ የነበረው እንደዚህ ባለ ሁኔታ ነበርና ፤ ከኋላውና ከፊቱ የሚከተሉት ሕዝቡ ሁሉ እያመሰገኑት በምስጋና የተገለጠበት ወቅት ነበር፤ ሌላ ጊዜ በምኵራብ ተገኝቶ ሲያስተምራቸው ያደንቁት የነበሩ የካህናት አ፤ልቆች በዚህ ቀን ባደረገው ሥራ ግን ደስተኞች አልነበሩም ማቴ 13 ÷54 ምክንያቱም ይህ ቀን የቤተ መቅደስ የመታደስ ወራት ስለነበር በአይሑድና በሊቃነ ካሕናት አድረው ክፉ ሥራን ያሠሩ ለነበሩ አጋንንት የጥፋታቸው ዘመን ስለሆነ እጅግ አጥብቀው ይቃወሙት ዘንድ ግድ ነበር፤

          ምንም እንኳን አይሑድና አለቆቻቸው ድርጊቱን የተቃወሙት ቢሆንም ወደ ውስጠኛው የመቅደሱ ክፍል ዘልቆ መቀጣት ያለባቸውን በጅራፉ ቀጥቶ፣ መሾም ያለባቸውን የቢታንያ ድንጋዮች ሹሞ፣ ለደቀ መዛሙርቱም ምንያክል ለቤቱ እንደሚቀና አሳይቶ ነው የወጣው፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ ቤተ መቅደስ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለምና ሜዳ ላይ አይደለም ሊሠራው ያሰበው፤ ከኦሪት የተወለደ የኦሪት ትርጓሜ በመሆኑ የኦሪቱን ቤተ መቅደስ አዲስ አድርጎ በዚያው ላይ ለመሾም ገብቶ ቤተ መቅደሱን አስተካከለ፡፡ የርግብ ሻጮችን መቀመጫቸውን፣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታቸውን ገለበጠ፡፡ አስተውሉ ቤተ መቅደሱን ያፈረሰው አይደለም ቤተ መቅደሱን አደሰው እንጅ፤ በነበረው አገልግሎት ባለመደሰቱ አገልግሎቱንና አገልጋዮችን ነው የለወጠው እንጅ የቦታ ለውጥ ያደረገ አይደለም፤ እንዲያውም ለአይሑድ በመጨረሻ የነገራቸው ቃል ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የወንበዴ ጋሻ፣ የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት ነው ያላቸው፤

          ይህንም ተናግሮ ከዚያው ሳይወጣ እውሮችና አንካሶችን እንደፈወሰ እናያለን ማቴ 21÷14 የቤተ መቅደሱ ትክክለኛ አገልግሎት ድውያነ ነፍስን በትምህርት ፣ ድውያነ ሥጋን በተዓምራት መፈወስ ነበርና ወደ ትክክለኛ ሥራው እንዲመለስ አድርጎታል፤  አገልጋዮችም ለዚህ ቤተ መቅደስ ክብር የሚመጥኑ አልነበሩምና የቢታንያን ድንጋዮች ጠርቶ ለቅዳሴ አሰለፋቸው ሉቃ 19÷40 አስቀድሞ በነቢይ የአብርሃም ልጆች በመሆናቸው ይንጠራሩ ለነበሩት አይሑድ እንደነገራቸው እግዚአብሔር ከነዚያ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጅን አሥነሳለት፤ ማቴ 3÷9 እነሱ በልባቸው አብርሃም አባት አለን በማለታቸው ከሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያላቸው ይመስላቸው ነበርና የቢታንያን ድንጋዮች በማስነሣት እንደ ድንጋይ የፈዘዘ አዕምሮ ያላቸውና ድንጋዩን አለዝበው ፣ እንጨቱን ጠርበው ያመልኩ የነበሩ አሕዛብ ቀድመዋቸው ገነት መንግሥተ ሰማያት እንደ ሚገቡ አስረዳቸው፡፡

          አሁን ጊዜው የሕፃናትና በአናጢዎች ዘንድ ለተናቁት ድንጋዮች በመሆኑ እነዚህን ሲመርጥ አይሑድና አለቆቻቸውን የሥልጣን ዙፋናቸውን ሻረባቸው፤ ሥርዓታቸውን ለወጠባቸው፤ እንዲያውም ከዚያ በኋላ በነገራቸው ምሳሌያዊ ትምህርቱ ከነርሱ ይልቅ ኃጢአተኞችና ጋለሞቶች ለእግዚአብሔር መንግሥት መታጨታቸውን አስረዳቸው ሉቃ 20÷9-18 ሕንጻው ምን አጠፋና ሕንጻውን ይለውጠዋል፤ ጥፋቱ የነበረው የሰው ልጆች ላይ እንጅ ቤተ መቅደሱ ላይ ስላልነበረ የሰው ልጆችን ወደ ማስተካከሉ አዘነበለ፤ የሰው ልጅ ከተስተካከለ ሁሉም ነገር መስተካከሉ አይቀርምና፡፡

          ቃና ዘገሊላ የተባለው መንደር ውስጥም በተገኘ ጊዜ ያደረገው ይህንኑ ነው ጋኖችን ሳይሆን የለወጠው አይሑድ ያጠምቁባቸው በነበሩት በነዚያው የድንጋይ ጋኖች የወይን ጠጁን ነው የለወጠላቸው፤ ችግሩ የነበረው ወይን ጠጁ ላይ እንጅ ጋኖቹ ላይ አልነበረምና ወይንጠጁን ብቻ ነው የለወጠው፤ እንደዚሁም ሁሉ የብሉይ ኪዳኑን አገልግሎት እንጅ ማሳለፍ የፈለገው የብሉይ ኪዳኑን ቤተ መቅደስ አይደለምና በቤተ መቅደስ ተገኝቶ እንደ ባለቤትነቱ ቤቱን አስተካከለ፤ ደቀ መዛሙርቱም እርሱን አብነት በማድረግ ከእርገት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ በመውጣት ይጸልዩ እንደነበረ መጽሐፍ ምስክር ነው፡፡ሥራ 3÷1

          ምንም እንኳን እንዲህ አድርጎ ቤተ መቅደሱን እንዳስተካከለ ብናውቅም አይሑድ ግን እሺ በጄ ብለው ሊያስተካክሉት ፈቃደኞች አይደሉም ባለማወቃቸው ለእግዚአብሔር የሚገባውን ስፍራ እነርሱ ይዘውት ነበር እንጅ፤ አንዳንድ ጊዜ ባለማወቃቸው የእግዚአብሔር ስፍራ ላይ እሚቀመጡ ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔረን ምስጋና የሚመሰገኑ፣ የእግዚአብሔርን አምልኮ የሚመለኩ፣ ክብሩን የሚነጥቁ ይህንም ባለማወቃቸው በመከራ ጉድጓድ የሚወድቁ ሰዎች አሉ፡፡ አይሑድንም የገጠማቸው እንዲሕ አይነቱ ነገርነው፤ በዚህ ምክንያት በኦሪት ተስፋ ወንጌልን ትጠባበቅ በነበረችው ምድር በኢየሩሳሌም ሳይሆን ለመጀመረቲያ ጊዜ ቤተ መቅደሱ በሰዎች እጅ የተሠራለት በአሕዛብ ምድር በመቄዶንያ ዋና ከተማ በፊልጵስዩስ ነው፡፡ ቦታ አልሰጠው ባሉ ቁጥር እግዚአብሔር ከተማቸውን ለቆ ተሰደደ፤ በምድር ላይ ያለውን ቤተ መቅደሱን እንዳያድርበት ከልክለውታልና በሰማይ ያለች ቤተ መቅደሱን ለሌሎች አሕዛብ ሰጠባቸው፤ ያን ጊዜ ያ ባለተስፋ ነቢይ በመካከላቸው ቆሞ እያለቀሰ ያወጣው የኃዘን ሙሾ በእነርሱ ላይ ተፈጸመ እንዲህ ነበር ያለው‹‹ ርስታችን ለእንግዶች ቤቶቻችንም ለሌሎች ሆኑ›› ሰቆ 5÷2

          እንደተጻፈው ሁሉም በእነርሱ ተፈጸመባቸው፤ ዮሐንስ እንዳየው ራዕ 21÷12 የአስራ ሁለቱ አባቶቻቸው ስሞች በበሮቿ ላይ የተጻፈባት የአባቶቻቸው ርስት የእግዚአብሔር መንግሥት ለለሌሎች እንግዶች አብርሃም ላልወለዳው እግዚአብሔር በጸጋ ለወለዳቸው ልጆች ለአሕዛብ ተሰጠችባቸው፤ አሕዛብ ለእግዚአብሔር ክብር ከእስራኤል ይልቅ ተገብቷቸው ስለተገኙ ለክብሩ መገለጫ የሚሆን ቤትን በመካከላቸው ሠራላቸው፤ ይህን ቤት በተመለከተ ለጊዜው አባቶቸቻችን ሐዋርያት የሠሩት ሥርዓት ብዙ አይደለም ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ተሰብስበው ሥርዓት የሠሩበት ጊዜ ያለ ቢሆንም ሥራ 15÷6-29 አብዝተው ይተጉ የነበረው ግን ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ እንጅ ሥርዓት ለማስቀመጥ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ከእነርሷ በኋላ እነርሱን መስለው የተነሡ አበው ሥርዓት እንዲሠሩ ተገብቷቸዋል፤ እነርሱም በፍትሐ ነገሥት መቅድም ላይ እንደተናገሩት ቀጥለው የሚነሡት አበው እንደ ጊዜው ዘመኑን የዋጀ ሥርዓት እንዲሠሩ ፈቅደውላቸዋል ታዲያ ከዚህ በኋላ የምናየው የቤተ ክርስቲያንን አሠራር በተመለከተ የተቀመጠው ሥርዓት ከክርስቶስ እስከ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት እስከ ሐዋርያውያን አበው፣ ከሐዋርያውያን አበው እስከ ሊቃውንት ድረስ የተፈቀደላቸው አባቶቻችን ያስቀመጡትን ይሆናል ማለት ነው፡፡

    ይህ እስካሁን ድረስ ያየነው መግቢያ ሲሆን ምዕራፍ በክፍል ሁለት እንመለስበታለን እስከዚያው ሰላም ያቆየን፡፡

    ማሳሰቢያ በዚህ ተከታታይ ርዕስ ላይ የሚጻፉ ጽሑፎች በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ የሚለቀቁ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ወቅታዊ ጽሑፎችና አንዳንድ ቁም ነገር ያላቸው መልዕክቶች ሲኖሩን በየመሀሉ የምናስገባ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    1 comments:

    Item Reviewed: ነገረ ቤተ ክርስቲያን ክፍል አንድ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top