• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 16 November 2015

    ነገረ ቤተ ክርስቲያን-ክፍል ሦስት


    አገልግሎታቸው

    ሦስቱም ክፍላት የየራሳቸው አገልግሎት አላቸው፤ እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ለማየት ያክል፡-
       1.ቤተ መቅደስ፡- መቅደሱ ካህናቱ ህብስቱን ሥጋ አምላክ፣ ወይኑን ደመ መለኮት አድርገው የሚለውጡበት ውስጠኛው ክፍል ነው፡፡

    ወደ ቤተ መቅደስ መግባት የሚፈቀድለት ማነው?

     በዚህ ክፍል ሥልጣነ ክህነት ካላቸው ሰዎች በስተቀር ማንም እንዲገባ አልተፈቀደም፤ ከሊቃነ ጳጳሳት እስከ ዲያቆናት ድረስ ባሉ መዐርጋት ውስጥ ያሉ አገልጋዮች ገብተው ያገለግሉበታል፤ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ(ኤጲስ ቆጶስ)፣ ቆሞስ፣ ካህን፣ ዲያቆን፤ እነዚህ አምስቱ መዐርጋት ያሏቸው እንደ ጥንቱ ቢሆን ኖሮ ነገሥታቱም ክህነትን ከመንግሥ አንድ አድርገው የያዙ ስለነበሩ የእነርሱም መቆሚያ በዚህ ክፍል ነበር፡፡ (በሀገራችን ታሪክ ታቦት የሚሸከሙ ነገሥታት እንደነ አጼ ኢያሱ አድያም ሰገድ ያሉ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናልና፤ ከእሳቸው በፊትም ሌላ ካህን ንጉሥ መኖሩን አዝማሪው በገጠመው ግጥም መረዳት እንችላለን የተገለጠውን የአባቱን ቅስና ኢያሱ ገለጠው ታቦት አነሣና በማለት ከእሱ በፊት የነበረውን የአባቱን ቅስና ይገልጣል) ከዚህ በታች ያሉ ምንም እንኳን በእኛ ቤተ ክርስቲያን የተለመዱ ባይሆኑም በአንብሮተ እድ ሳይሆን በቃል ቡራኬ ብቻ የሚሰጡ የቤተ ክርስቲያን መዐርጋት አሉ ከቤተ መቅደስ ውጭ ባለው ተልዕኮ ካልሆነ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተው መጸለይም ሆነ አገልግሎት መስጠት አይችሉም፡፡ ለምን ከተባለ ይህ ስለክብረ ክህነት ነው፡፡ አምላካችን በዳግም ምጽአቱ የሚያደርገውም ይህንኑ ነው፤ አትናቴዎስ በቅዳሴው እንደተናገረው                    

         በቤተ መቅደስ ውጥ የሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት

    ሥርዓተ አምልኮ ከምንፈጽምባቸው ንዋያተ ቅድሳት ዋኖቹ የሚገኙት በዚህ ክፍል ውስጥ ነው፤ ታቦት፣ መንበር እነዚህ ሁለቱ መሠዊያ ናቸው፤ ጻሕል፣ ጽዋዕ፣ እርፈ መስቀል፣ማኅፈድ፣ አውድ፣ አጎበር፣ እነዚህ ደግሞ የሥጋው የደሙ ማቅረቢያዎች ናቸው፡፡ ጽና፣ መስቀል፣ ልብሰ ተክህኖ እና እነዚህን የመሳሰሉት ሥጋውና ደሙን በማቅረብ ጊዜ የምን ገለገልባቸው ንዋያተ ቅድሳት ናቸው፡፡ (የእያንዳንዳቸውን ምሥጢራዊ ትርጓሜ ስለንዋያተ ቅድሳት በሚናገረው ክፍል እንነጋገራለን)

         በቤተ መቅደስ የሚፈጸመው አገልግሎት

    በዚህ ክፍል ውስጥ ለጸሎት ብቻ ካልሆነ በስተቀር መግባት እንዳይቻል የሥርዓት መጽሐፋችን ይከለክላል፡፡ ቤተ መቅደሱ የቀራንዮ ምሳሌ ነው፤ በቤተ ልሔም ዲያቀኑ ያዘጋጀው ህብስት ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል፤ በዚህም ክርስቶስ በቤተ ልሔም ተወልዶ በቀራንዮ መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡን ቤተ ክርስቲያን ሥዕላዊ በሆነ መንገድ የምታስተምርበት ነው፡፡ ህብስቱ ከቤተ ልሔም ወደ ቤተ መቅደስ ሲመጣ ሁለት ዲያቆናትና አንድ ካህን አክብረው ይዘውት ይመጡና ለሚያርደው ለሚያወራርደው በቤተ መቅደስ ላለው ካህን ያቀብላሉ፤ ይህም ጌታችን በተወለደበት ስፍራ ቤተ ልሔም እመቤታችን፣ ዮሴፍና ሰሎሜ ናቸው እንጅ ሌላ ምን ነበረ፤ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበባት ቀራንዮ ላይ ግን ከሊቃነ ካህናት እስከ ተራው አይሁዳዊ ድረስ ሁሉም ነበሩ፤ ቤተ ክርስቲያናችን ከቤተ ልሔሙ ይልቅ ቤተ መቅደሱን ከፍአድርጋ የምታንጽ ለምን ይመስላችኋል፤ በቤተ ልሔም የተፈቀደላቸው ሰዎች ብቻ ዋሻውን ከፍተው አይተውት ይሆናል እንጅ ለሁሉም የተገለጠ አልነበረም፤ ቀራንዮ ላይ ግን እንዲህ አይደለም ሁሉም እንዲያየው ልብስ እንኳን ሳይጥሉበት ከፍ አድርገው ሰቀሉት፤ ቤተ መቅደስም ከገባ በኋላ ካህናቱም ምዕመናኑም ከህብስትነት ወደ ሥጋ አምላክነት፣ ከወይንነት ወደ ደመ መለኮትነት እንዲለወጥላቸው ደጅ ይጠኑታል፤ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ እንዲሆን ተግተው ይጸልዩበታል፡፡ በመቅደሱ ውስጥ ያሉት ሥርዓቱን ይመራሉ፣ በሌሎቹ ክፍላት የሚገኙት ደግሞ ይከተላሉ፤ እስከ ፍጻሜ እንዲሁ ይቀጥላሉ፤ ይህ አንዱ የመቅደሱ ሥርዓት ሲሆን
         1.1 ሥዩማነ ቤተ መቅደስ ካህናት ሥጋወደሙን ይቀበሉበታል፡- እንደ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መዐርገ ክህነት ያለው ማንኛውም ሰው በዚህ ክፍል ነው ሥጋው ደሙን ሊቀበል የሚገባው፤
         1.2 ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ካህናት የስንብት ሥርዓት ይካሄድበታል፤ በፍት.መን. አን 22 በተደነገገው መሠረት ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ሲሞት ስንብት ሊደረግለት የሚገባው በሕይወት ሳለ ሥጋውን ደሙን ይቀበልበት ከነበረው ስፍራ ላይ አስከሬኑ ከተቀመጠ በኋላ ነው፡፡ ሰማያዊት ርስቱን የሚወርሰው በዚህ ስፍራ ቆሞ በጸለየው ጸሎት፣ በቆረበው ቁርባን ነውና፡፡ በዚህ ስፍራ ካስቀመጡ በኋላ ሊቀጳጳስ ካለ ከሁሉ በፊት ከሌለ ደግሞ ከካህናት በመዐርግ የሚበልጠው በድን ርኵስ የምትል ሕገ ኦሪት እንደ ተሻረች ለማጠየቅ በድኑን ስሞ ይሰናበተዋል ከእርሱ ቀጥለው ሕዝቡም እየሳሙት ይሰናበቱታል፤

       2.ቅድስት፡-

    በቤተ መቅደሱና በቅኔ ማኅሌቱ መካከል የሚገኝ መካከለኛ ክፍል ሲሆን የመንግሥት ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ክፍል በቤተ መቅደስና በቅኔ ማኅሌት መካከል እንደሆነ ሁሉ መንግሥተ ሰማያትም በሦስቱ መቅደሳተ እግዚአብሔር(መንበረ ስብሐት፣ሰማይ ውዱድ፣ጽርሐ አርያም) እና በመላእክት ዓለም መካከል ነው ያለው፤

          አገልግሎቱም፡- ምዕመናን ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉበት፣ ሲሞቱ የመጨረሻውን የስንብት አገልግሎት የሚያገኙበት ስፍራ ነው፤ ቅድም በቤተ መቅደሱ ክፍል ላይ እንደተናገርነው አድርገው የመጨረሻ ውን ጸሎት አድርገውላቸው ወደ መካነ መቃብር ያደርሷቸዋል፡፡

       3.ቅኔ ማኅሌት

    ከስሙም እንደምንረዳው ካህናት በእየዕለቱ አዲስ አዲስ ምስጋና ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡበት ስፍራ ነው፡፡ በአብዛኛው በዚህ ክፍል አገልግሎት ሲሰጡ የምናገኛቸው ካህናትን ብቻ ነው፤ በጥንቱ ዘመን ግን ነገሥታቱም ገብተው ቅኔ ይቀኙበት እንደ ነበረ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ለምሳሌ አጼ በእደ ማርያም ‹‹ድኅረ ተሰብረ አጽንኦ ለሰብእናነ ልኅኵት፤ ለብሐዊ ክርስቶስ በማየ ሐዲስ ጥምቀት፤ሸክላ ሠሪው ክርስቶስ ገንቦ ባሕርያችን በኃጢአት ከተሰበረ በኋላ በሐዲስ የጥምቀት ውኃ አፀናው›› ብለው ተቀኝተዋል፡፡ አጼ ዮሐንስ ሣልሳይም ‹‹…..አዕላፈሂ ጊዜያተ እመ መከሩ አዕላፍ አንተ ዘወሰንኮ ወዘሀለይኮ ኢይተርፍ፤ እልፍ ሆነው እልፍ ምክር ቢመክሩም አንተ ይሁን ያልኸው ሳይሆን አይቀርም›› ብለዋል ይባላል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ በልዩ ልዩ ጊዜያት የተመዘገበ ታሪክ አላቸው፡፡ ምንም እንኳን አገልግሎት መስጠት ባይችሉም ሴቶችም ቀርበው ያዳምጡ ስለነበር እማሆይ ገላነሽ አባታቸው በቅኔ ማኅሌት ይቀኙት የነበረውን ቅኔ ‹‹…በታቦርሂ አመ ቀነፀ መለኮትከ ፈረስ›› ብለው ሲጀምሩ እማሆይ ነጠቁና ‹‹ኢክህሉ ስሂቦቶ ሙሴ ወኤልያስ›› ብለው ጨረሱት ይባላል፡፡

        ቅኔ ማኅሌት እንዲህ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ቆመው የሚያገለግሉበት ክፍል ሲሆን የዓለመ መላእክት ምሳሌ ነው፡፡ በመላእክት ዓለም ከበሮውን ጸናጽሉን ሌሎችንም የዜማ መሣሪያዎች ይዘው እንደ ሚያገለግሉ አትናቴዎስ በቅዳሴው ይመሰክራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ከበሮውን ጸናጽሉን ሌሎችንም የዜማ መሣሪያዎች ይዘው ሲያገለግሉ ይታያሉ፡፡ ትጋታቸው እንደ መላእክት፣ አቋቋማቸውም በጽናት የሆነ ያለዕረፍት ሌሊትና ቀን ሲያገለግሉ የምናውቃቸው አባቶቻችን የሚቆሙበት ቦታ ነው፡፡ ከቁመታቸው መብዛት የተነሣ አንዳንዶቹ እግራቸው እስከማበጥ ይደርሳል፤ ልቡናቸው እንደ ንስር በርሮ፣ እንደ መንኰራኵር ተሸከርክሮ እስከ ጽርሐ አርያም ጣራ ድረስ ስለሚወጣ ያሉበትን የዚህን ዓለም ድካም ይረሳሉ፡፡

    በነገራችን ላይ በዚህ ስፍራ ዓመት እስከ ዓመት አገልግሎት የሚቋረጥበት አንዳችም ጊዜ የለም፤ ቤተ መቅደሱን ያየን እንደሆነ ቢያንስ የሰሙነ ኅማማት ግዴታ መቋረጡ  አይቀርም ቅኔ ማኅሌት ግን አንዳችም የሚቋረጥበት ጊዜ የለውም፡፡ እንደ ዓለመ መላእክት ያለ ድካም ዜማ ሌሊትና ቀን ይቀርብበታል፤ በዚህ ስፍራ ለብዙ ጊዜያት ያለ መብልና መጠጥ ማገልገል የሚችሉ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሰዎችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ የልብን በር ሰብሮ የኅሊናን ጓዳ በርብሮ ቀልብን የሚገዛ አንዳች ምሥጢራዊ ኃይል ከእነርሱ ይወጣል፤ ጳውሎስና ሲላስ እንዳደረጉት የወኅኒውን በር ብቻ ከፍቶ እጃቸው ላይ ያለውን ሰንሰለቱን ብቻ ፈትቶ የቀረ አይደለም የሮማውን ወታደር ልቡን አላልቶ የክርስትናን ፀዳል አብርቶ የመለሰ ዜማ ነበር፤ በማኅሌታችን የሚሰማውም ዜማ ድውያንን የሚፈውስ አጋንንትን የሚያርቅ ዜማ ነው፡፡

    በኅብረት ሆነው የሰው ልጆች የሚያሰሙት የምስጋና ድምፅ በመሆኑ እግዚአብሔር ወዶ ፈቅዶ የሚቀበለው መሥዋዕት ነው፡፡ ከእለታት በአንድ ቀን አንድ ባሕታዊ በቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ ብቻውን ሆኖ ይጸልያል ካህናቱ ደግሞ ማኅሌት ቆመዋል፤ ባሕታዊው እግዚአብሔር የጎበኘው ሰው ስለነበር እመቤታችን በቅኔ ማኅሌት ተገኝታ የካህናቱን በድካም የወዛ ፊታቸውን ስትጠርግላቸው እንዳያት ታሪክ ያስረዳናል፤ በፍቅር ሆነን በኅብረት የምናቀርበው ማንኛውም አገልግሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ፈጥኖ ይሰማል፡፡

                                        ይቀጥላል……

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ነገረ ቤተ ክርስቲያን-ክፍል ሦስት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top