• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 17 November 2015

    ጥምቀት (Epiphany), ጾመ ገሃድ (Tsome Gehad), እና ቃና ዘገሊላ (Cana Zegelila)


    ጥምቀት

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

    “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርንመንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. 3፡3

    እንኳን ለጥምቀት በአል በሰላም አደረሳችሁ፤ በባሕርዩ ቸርና ሁሉን ቻይ የሆነ አምላቻችን አሁንም የንስሃ ጊዜን ጨምሮልን ለሚቀጥለው ዓመት በሰላም አድርሶን ይህንን በአል ለማክበርና ድንቅ ሥራውን ለመመስከር ያብቃን።

    በዛሬው ትምህርታችን ስለ ሦስት አበይት አርእስት ባጭሩ እንማራለን እነዚህም

    ·         ገሀድ

    ·         ጥምቀት እና

    ·         ቃና ዘገሊላ ሲሆኑ

    ከሦስቱ መካከል በ2ኛው ርእስ ላይ የበለጠ ሰፋ በማድረግ ስለ ጥምቀት ምንነት፤ ታሪክና መልእክት አጭር ትንታኔ እሰጣለሁ እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋሉን ያድለን።

    የመጀመሪያው ርእሳችን ገሀድ ነው። ገሐድ ፡ ከ7ቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ገሐድ ማለት ሰዋስዋዊ ትርጉሙ ግልጽ የሆነ የሚታይ የሚታወቅ ያልተሰወረ፤ የማያጠራጥር ወዘተ ማለት ሲሆን ለምሳሌ “በገሐድ ንገረን! በገሐድ ንገሪኝ” ወይም በገሐድ የተነገረ ነገር” ወዘተ ማለት በግልጽ ሁሉም በሚሰማው መንገድ ማለት ነው። ነገር ግን ሰዋስዋዊ ትርጉሙ ከይዘቱ ወይም ዛሬ ከምንማረው ማለትም  በሰባቱ አጽዋማት ውስጥ የገሐድ ጾም ካለው የሥራ ድርሻ ትርጉም ጋር በቀጥታ አይመሳሰልም። ስለዚህ ገሐድ ማለት በዚህ ትምህርታችን ወይም ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ በመሆኑ በምንሰጠው ትርጉም መሠረት ተለዋጭ ማለት ነው።

     የማን  ወይም የምን ተለዋጭ ለሚለው ጥያቄ የረቡእና የአርብ ተለዋጭ የሚል ይሆናል። ማለትም የጥምቀት በአል ረቡእ ከሆነ የጥምቀት ዕለት መጾም ስለማይገባ በረቡዕ ፈንታ ማክሰኞን ሙሉ ቀን እንጾማለን፤ አርብ ከሆነም እንደዚሁ በአርብ ፈንታ ሐሙስን ሙሉ ቀን እንጾማለን ፤ ረቡእና አርብ ግን የፍስክ ቀናት ሆነው ይውላሉ ማለት ነው። ለዚህም ነው “ተለዋጭ ወይም ምትክ” በማለት ትንታኔ የምንሰጠው።

    የጥምቀት በአል እሁድ ወይም ሰኞ ከዋለ ግንዕሁድና ሰኞ የጾም ቀናት ስላልሆኑ በነዚህ ቀናት ምትክ ቅዳሜና እሁድን መጾም የለብንም ምክንያቱም  1ኛ ቅዳሜና ሰኞ የጾም ቀን አይደሉም፤ በዚህም ምክንያት ተለዋጭ አያስፈልጋቸውም፤ 2ኛው ደግሞ በሰንበት ቀናት መጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን የተከለከለ ስለሆነ በእሁድና በሰኞ ፈንታ ቅዳሜና እሁድ ገሐድ ተብለው አይጾሙም።

    የገሐድ ጾም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ስለሆነና በየአመቱ መቋረጥ ስለሌለበት ግን ቅዳሜን እና ዕሁድን ደግሞ መጾም ስለማይገባ በነዚህ ቀናት ጾመ ገሐድ ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ መሆኑን ለማሰብከሥጋና ከወተት ዘሮች ብቻ እንከለከላለን። ጾማችን ግን አንውልም። ከሦስት ቀናት በኋላ የምናከብረው የዘንድሮው የጥምቀት በአል ሰኞ ስለዋለ እሁድን አንጾምም፤ ከወተትና ከእኅል ዘሮች ግን እንከለከላለን።

    ለበለጠ ማብራርያ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከአባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ጳጳስ” መጽሐፍና እና ሐብታችንና ሥርዓቱ የተሰኘውን መጽሐፌን ይመልከቱ። ሊንክ

    ጥምቀት፡

    የጥምቀት ትርጉም፦ ጥምቀት ማለት ቀጥታ በቋንቋነቱ ሲተረጎም በተከማቸ ውሃ ውስጥ መነከር ማለት ሲሆን ይዘቱን በተመለከተ በእምነታችን ሲገለጥ ግን በተጸለየበት ውሃ ውስጥ በሥላሴ ስም ተጠማቂውን ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አድርጎ የማውጣቱ ሂደት ጥምቀት ይባላል።

    ሁላችሁም እንደምታውቁት በየአመቱ የጥምቀትን በአል ታቦታት ከየመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ወንዝ ወይም ውሃ ወዳለበት ቦታ በመሄድ በውኃ ዳር ያድራሉ። ውሀ በሌለበት አካባቢም በልዩ ልዩ መሣሪያዎች ወይም ዕቃወት ውኃው እንዲከማች ይደረጋል። የተከማቸውም ውኃ  ከተጸለየበት በኋላ ለምእመናን ይዳረሳል። ቦታው የዮርዳኖስ ወንዝን፤ ውኃው የዮርዳኖስ ውሀን የሚተካ ነው።

    የታቦታት ወደ ወንዝ መውረድና የውሐው ምሳሌ

    1.      ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በወንዞች ወይም ውሀ ባለበት አካባቢ የሚያድሩት ምክንያትም ታቦት የጌታ ማደሪያ ስለሆነ  ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በትኅትና የመሄዱን ምሳሌ ለማሳየት፤ ትኅትናውን ለማሰብና ለመግለጽ ነው።

    2.     ውኃው በጸሎት ተባርኮ ለምእመናን የሚረጭበትም ምክንያት ጌታችን የባረከውን ውኃ በመከፋፈል የእርሱን በረከት ለማግኘት ነው። በዚህ ጌዜ የሚጸለየው ጸሎት ሁሉ በዚያን ጊዜ በዮርዳኖስ የተፈጸሙ ታሪኮችና በነቢያት ስለጥምቀትና ስለዮርዳኖስ ወንዝ ወይም ውሃ የተነገሩ ወይም የተተነበዩ ትንቢቶች ናቸው።

    ጥምቀት

    ·         ከመገለጥ በአላት አንዱ ነው ማለትም አምላክ ራሱን ለዓለም ከገለጠባቸው መንገዶች አንዱ የጥምቀት በአል ነው።

    ·         ለሰው ልጆች ወደ ክርስትና ሕይወት ለመግባት የመጀመሪያው በር ነው

    ·         በአዳምና በሔዋን ምክንያት ያጣነውን የእግዚአብሔርን ልጅነት መልሰን የምናገኝበት መንገድ ነው

    ·         በአዳም ምክንያት ከተላለፈብን ኃጢአትና ከጊዜ በኋላ ራሳችን ከምንሠራው ኃጢአት የምንነጻበት ነው

    ·         ያልተጠመቀ ሰው የመዳን ዕድል የለውም “”

    ·         ሰው ሲጠመቅ ሁለተኛ ተወለደ ይባላል።

    ጥምቀት ሁለተኛ ልደት የተባለበትም ምክንያት አንደኛ ልደት ከአባትና ከእናት በሥጋ መወለድ ሲሆን ሁለተኛው በማይመረመር የአምላክ ጥበብ በውሃ ተጠምቀን በመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ስለምንወለድ ነው። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርንመንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. 3፡3

    ጥምቀት በስንት ይከፈላል?፡

    ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀት፡-

    ጥምቀት አንዲት ናት፤ ሆኖም ግን የንስሐ ጥምቀት የሚባልም ስላለ የልጅነት እና የንስሐ በመባል በሁለት ይከፈላል። መጽሐፍ ቅዱስና የሃይማኖት ጸሎት “በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ሲሉ የልጅነት ጥምቀትን መጥቀሳቸው ነው። ብዙ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት ልጅነትን ስለምታሰጥ ጥምቀት ስለሆነ የሚናገሩት ጥምቀት አንዲት ናት ይላሉ።“..አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት…” ኤፌ.4፡5

    የንስሐ ጥምቀት፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ጥምቀቶች የሚል ብዛትን ወይም ከአንድ በላይ መሆናቸውን  ጽፏል። ምክንያቱም የንስሐን ጥምቀት በመጨመር በብዙ ቁጥር መናገሩ ነው። “…እርሱም  ከሞተ ሥራንስሐና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችናእጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው…” ዕብ 6፡ 2

    ስለ ንስሐ ጥምቀት ዋና ምሳሌ ከሚሆኑን ጥቅሶች መካከል መጥምቁ ዮሐንስ ሲያጠምቀው የነበረው ጥምቀት አንዱ ነው። “እኔስ ለንስሐ በውኃአጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድየማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትምያጠምቃችኋል፤ ” ማቴ.3፡11

    እንዲሁም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደ ሚከተለው ጳውሎስ የተናገረውን ጠቅሶ ጽፏል። “…እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ?አላቸው። እነርሱም ።በዮሐንስ ጥምቀትአሉት። ጳውሎስም። ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላበሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀአላቸው…”። የሐዋርያት ሥራ፡ 19፡3

    የጥምቀት ምድብ ወይም አመዳደብ፡-

    ጥምቀት ከ5ቱ አእማደ ምሥጢር አንዱ ምሥጢር ሲሆን በ3ኛ ተራ ቁጥር ይገኛል። አምስቱ አእማደ ምሥጢር የሚባሉት

    1.      ምሥጢረ ሥላሴ (የሥላሴ ወይም የሦስትነት ምሥጢር)

    2.     ምሥጢረ ሥጋዌ(ሰው የመሆን ወይም የተዋሕዶ ምሥጢር)

    3.     ምሥጢረ ጥምቀት(የጥምቀት ወይም የመጠመቅ ምሥጢር)

    4.     ምሥጢረ ቁርባን እና(የቁርባን ወይም የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምሥጢር)

    5.     ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው።(የትንሣኤ ሙታን ወይም ከሞተ ሥጋ በኋላ የመነሣት ምሥጢር)

    ከ7ቱ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትም ደግሞ አንዱ ጥምቀት ሲሆን በ1ኛ ተራ ቁጥር ይገኛል።

    7ቱ የቤ/ክ ምሥጢራት የሚባሉት ደግሞ

    1.      ምሥጢረ ጥምቀት (የጥምቀት ምሥጢር)

    2.     ምሥጢረ ሜሮን(የሜሮን ወይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሚተላለፍበት ቅባት ምሥጢር)

    3.     ምሥጢረ ንስሐ( የንስሐ ወይም በሠሩት ኃጢአት ተጸጽቶ በመመለስ ከኃጢአት የመንጻት ምሥጢር)

    6.     ምሥጢረ ቁርባን (የቁርባን ወይም የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምሥጢር)

    4.     ምሥጢረ ክህነት( የሥልጣነ ክህነት ምሥጢር)

    5.     ምሥጢረ ተክሊል (የተክሊል ወይም ሁለት ተቃራኒ ጾታዎች  በጸሎት አንድ የሚሆኑበት ምሥጢር) እና

    6.     ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው። (የቀንዲል ወይም ሰዎች ከልዩ ልዩ ህመም የሚድኑበት ቅባት ምሥጢር)

    እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሁሉ ምሥጢር የተባሉበት ምክንያት ምስጢር ማለት ስውር በአይን ሊታይ በእጅ ሊዳሰስ የማይችል ረቂቅ ማለት ሲሆን በነዚህ ምሥጢራት ወይም የጸሎት ክፍሎች አማካኝነት በሚታዩ ካህናት ጸሎት እና በሚታዩ ንዋያተ ቅድሳት የማይታይ የእግዚአብሔር ጸጋ ስለሚገኝባቸው ነው።

    ክርስቶስ ለምን ተጠመቀ?

    1ኛ አምላክነቱን ለማሳየት ወይም ለመግለጥ ሲሆን አገላለጹም እንደ ሚከተለው ይሆናል።

    ·         እግዚአብሔር ወልድ ድምጹን በማሰማት አሰማእነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስየሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ” ማቴ.3፡17

    ·         እግዚአብሔር ወልድ በአካል በዮሐንስ እጅ እየተጠመቀ በመታየት ተገለጸ “...ያን ጊዜ ኢየሱስበዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃወጣ.. ማቴ.3 13፣16

    ·         እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በእግዚአብሔር ወልድ ላይ አረፈ እነሆም፥ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ” ማቴ. 3፡16

    በመሆኑም ከዚህ በላይ በተፈጸሙት ተአምራት የእግዚአብሔር ሦስትነት ወይም የሥላሴ ምስጢር ተገለጠ የክርስቶስ በተዋሕዱ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ መሆን ተረጋገጠ፤ ማለት ነው።

    2ኛ እሱ ተጠምቆ ምሳሌውን ወይም አርአያውን ለእኛ ለመስጠትእና

    3ኛ ጥምቀትን ባርኮ ለእኛ ጥምቀት ኃይልን ለመስጠት የሚሉት ናቸው።

    ጥምቀት ይደገማል ወይስ ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው?ልጅነትን የምንቀበልባት ጥምቀት አንድ ብቻ ናት። አትደገምም ነገር ግን የንስሐ ጥምቀት የሚባለው ብቻ ሊደጋገም የሚችል ነው።

    አጥማቂው ማነው?

    ጥምቀት በሁለቱ የክህነት ደረጃዎች ብቻ ይፈጸማል በኤጲስ ቆጶስና ( ኤጲስቆጶስ የሚባለው ጳጳስ ነው) በቄስ ብቻ፤ ዲያቆናትና ምእመናን እንዲሁም ሥልጣነ ክህነት የሌላቸው መነኮሳት  ግን ማጥመቅ አይችሉም። ምክንያቱም ክርስቶስ እንዲያጠምቁ ያዘዛቸው ሐዋርያትን ነው፤ ሐዋርያትም የኤጲስቆጶስነት ወይም የቅስና ሥልጣን ነው የነበራቸው።

    ተጠማቂዎቹ እነማን ናቸው?

    ማነኛውም በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ወንድ፤ሴት፤ ሕጻን፤ ሽማግሌ፤ ነጭ፤ ጥቁር፤ በአጠቃላይ ለሰው ዘር ሁሉ የተፈቀደ ሲሆን መመዘኛው ማመን ብቻ ነው። “…በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅየሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።  ፊልጶስም።በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው።መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅእንደ ሆነ አምናለሁ አለ።  ሰረገላውም ይቆም ዘንድአዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃወረዱ፥ አጠመቀውም…” የሐዋርያት ሥራ 8፡ 36-38። 

    የጥምቀት ዕድሜ፡

    ለመጠመቀ  የዕድሜ ክልልህ አልፏል ወይም አልደረሰም ስለዚህ መጠመቅ አትችልም የሚል ሕግ የለም። በማነኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሁሉ መጠመቅ ይችላል። የክርስቲያን ልጆች ከሆኑና የመጠመቅ ዕድል ካገኙ ወንድ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት በተወለደች በ80 ቀኗ በክርስትና አባት ወይም እናት ኃላፊነት በተወካዮቻቸው በኩል እምነታቸውን እየመሠከሩ መጠመቅ አለባቸው።

    ለምን በ40 እና በሰማንያ ቀናት እንጠመቃለን (የክርስቲያን ልጆች)?

    ባጭሩ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሲሆን መሠረቱን እንደሚከተለው እንመልከት።

    1ኛ በዘመነ ብሉይ እሥራኤላውያን ወንድ ከወለዱ በ40 ቀኑ፤ ሴት ከወለዱ በ80 ቀኗ ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው በስማቸው መሥዋዕት ያቀርቡላቸዋል፤ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሟቸዋል በመሆኑም ከዚያች ዕለት ጀምረው ከእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ይቆጠራሉ ማለት ነው። ዘጸ. 12፡1፤ ዘጸ. 4፡22፡፤ ይህ ሥርዓት ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስም ተከናውኖለታል። ሉቃስ፡2፡22

    2ኛ በመጽሐፈ ኩፋሌ ተጽፎ እንደሚገኘው፡ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ፤ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ አምላካቸው እግዚአብሔር በጸጋው ከወለዳቸው በኋላ ብርሃንን አልብሶ ብርሃንን አጎናጽፎ ወደ ገነት አስገብቷቸዋል። “… ለአዳም 40 ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ወደ ገነት አስገባነው፤ ሚስቱንም በ80 ቀን አስገባናት…”ኩፋሌ 4፡9። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቲያን ልጆች በክርስትና አባትና እናት ሐላፊነት በ40 እና በ80 ቀናት እንዲጠመቁ ታዛለች።

    መጽሐፍ ቅዱስ በማርቆስ ወንጌል 16፡ 15-16 “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። 

    ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግንይፈረድበታል ስለሚል ሰው መጠመቅ ያለበት ተምሮ፤ አምኖ እራሱ እምነቱን እየመሠከረ መሆን አለበት በማለት የ40 እና የ80 ቀን ጥምቀትን የሚቃወሙ አሉ። ሆኖም ግን “ አምኖ እምነቱን እየመሠከረ መጠመቅ አለበት” የሚለውን ቤተ ክርስቲያናችን በሚገባ ትቀበለዋለች፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው። በ40 እና በ80 ቀናት መጠመቅ አይገባም የሚለውን ግን ቤተክርስቲያን አትቀበለውም።

     ምክንያቱም  መጽሐፍ ቅዱስ በ40 እና በ80 ቀናት መጠመቅ አይገባም አላለም፤  ስለ እምነታቸው ተምረው፤ እምነታቸውን እየመሠከሩ መጠመቅ ያለባቸው 1ኛ በልዩ ልዩ ምክንያት በ40 በ80 ቀናት ወይም ከዚያም በኋላ የመጠመቅ ዕድል ሳያገኙ የቆዩ ከሆኑ፤ 2ኛ ከእስልምናና ከሌሎች የእምነት ድርጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኦርቶዶክስ እምነት ለመመለስ ወስነው የሚመጡ ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች አስተማሪ ተመድቦላቸው ተምረው አውቀው እምነታቸውን እራሳቸው እየመሰከሩ ይጠመቃሉ። የክርስቲያን ልጁች ግን እምነታቸውን ራሳቸው የመመስከር ችሎታ እስከሚኖራቸው የእድሜ ክልል ድረስ መጠበቅ የለባቸውም።

    ይህም የሆነበት ምክንያት፡

    1ኛ፡ ከላይ በዘጸአትና በመጽሐፈ ኩፋሌ እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌነት አለው። መጽሐፍ ቅዱስም የ40 እና የ80 ቀናት ጥምቀትን አልከለከለም።

    2ኛውና ዋናው ግን  “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰውዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርንመንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. 3፡3 

    ስለሚል ሁለተኛ መወለድ ማለት ድግሞ መጥመቅ ማለት ነው። ስለዚህ ዕድሜያችን ለትምህርት ደርሶ እምነታችን እየመሠከርን ለመጠመቅ ከመቻላችን በፊት በሞተ ሥጋ ብንለይ ከመንግሥቱ ተለይተን እንዳንቀር በማሰብ በ40 እና በ80 ቀናት እንጠመቃለን።

    አሁንም ሕጻናት ለሞት ሊያደርስ በሚችል ሕመም መያዛቸው ከታወቀ በማነኛውም የዕድሜ ገደብ ማለትም ከ40 ከ80 ቀናትም በፊት መጠመቅ እንደሚችሉ ቤተ ክርስቲያን ታዛለች። ፍትኃ ነገሥት አንቀጽ 3።

    በማን ስም እንጠመቃለን?

    “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድናበመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁእያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. 28፡ 20ላይ ቅዱሳን ሐዋርያትን ባዘዛቸው መሠረት በሥላሴ ስም እንጠመቃለል።

    ክርስቶስ የተጠመቀው በ30 ዓመቱ ስለሆነ ለምን እኛ በ30 አመታችን አንጠመቅም ?

    ስለሰዎች የጥምቀት ዕድሜ  መጀመሪያ ላይ“የጥምቀት ዕድሜ” በሚለው ርእስ አይተናል ። የክርስቶስ በ30 ዓመት መጠመቅ ግን ምሳሌነቱ ለጥምቀት ዕድሜ ሳይሆን ለክህነት አገልግሎት ነው።

    ምክንያቱም ወዲያውኑ እንደተጠመቀ ወደ ጾምና ወደጸሎት በመሄድ 40 ቀንና 40 ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ የክህነት አገልግሎቱን ሐዋርያትን በመምረጥ ጀመረ። በመሆኑም በዚህ ምሳሌ መሰረት ቅስና የሚቀበል ሰው ዕድሜው ከ30 ያነሰ መሆን እንደሌለበት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተሠራ።

    በጥምቀት የሚገኘው ጥቅም፡

    1.      ከእግዚአብሔር መወለድ

    2.     ከአዳም እና በግላችንም ከሠራነው ኃቲአት መንጻት

    3.     በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን መጠን የአባታችንን የዘላለም መንግሥት ለመውረስ ዕድል ማግኘት

    4.     አዲስ ስምን ማግኘ፤ ትክርስቶሳውያን መሆን እና በክርስቶስ “ክርስቲያን” የሚለውን የዜግነት ስም ማግኘት

    ·         የክርስትና አባት ወይም እናት ማግኘት ማነኛውም ተጠማቂ የክርስትና አባት ወይም እናት ያስፈልገዋል፡፡

     ለቅዱሳንና ለእግዚአብሔር እንሰጣለን የሚሉ ወላጆች መስጠት ቢችሉም አሁንም ቅዱሳንን ወይም እግዚአብሔርን ወክሎ ስለ እምነት የሚወከል ስለሚያስፈልግ በእለቱ የሥርዓተ ጥምቀቱን ጸሎት የሚያደርሱ ካህናት መወከል ይችላሉ።

    ነገር ግን በፍትሐ ነገሥት መሠረት ያላገባ ዲያቆን ሴት ልጅን ክርስትና ማንሳት አይችልም። ስለዚህ ቄሱ ወይም ዲያቆናዊት ሴት መወከል ይችላሉ።

    ከጥምቀት በኋላ ምን ማድረግ አለብን?

    ከጥምቀት በኋላ አምላካችን በሰጠን ዕድል መሠረት በውሃና በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን ሁለተኛ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል፤ ስለዚህ ወደ ኋላችን ሳንመለስ በደሙ አጥቦ ቀድሶ ከኃጢአት ንጹሐን አድርጎ አዲስ ፍጥረት አድርጎ እንዳከበረን ክብራችንን ጠብቀን በክርስትና ሥነ ምግባር ጸንተን መኖር ነው። “ስለዚህ ማንምበክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገርአልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” ። 2ኛ ቆሮ. 5፡ 17

    “…በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስምፈንታ አትስጡት።  የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህአይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለውየሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምንእየሠራ ይድከም…” ኤፌ.4፡27-28።

    እንደ ሰውነታችን ነገሮች ከጠበቅናቸውና ከአቅማችን በላይ ሆነውብን በኃጢአት ስንወድቅም በልባዊ ንስሐ እየተመለስን የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ማፍራት መቻል አለብን። ስምን ብቻ ተሸክመን  ታሪክን እየተረክን፤ በታሪክና በባለታሪክ እየተመካን ለውጥ በሌለው ንስሐ፤ ፍሬ በሌለው ክርስትና ተደብቀን የምንኖር ከሆነ ግን የስም ክርስቶሳዊነት የአምላክን መንግሥት ሊያወርሰን አይችልም።

    “ እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬአድርጉ፤  በልባችሁም። አብርሃም አባት አለንእንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለትእግዚአብሔር ይችላል።  አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥርተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል”። ማቴ. 3፡8-10 

    ማለትም እግዚአብሔር መንግሥቱን ሊያወርሰን ወይም ለአብርሃም ያደረገውን ሁሉ ሊያደርግልን የሚችለው የአብርሃምን ታሪክ በመተረካችን ሳይሆን የአብርሃምን ሥራ በመሥራታችን ብቻ ነው ማለት ነው።

    ልዑል እግዚአብሔር ሰምተን ለመማር ወይም ለማወቅ አውቀን ለመሥራት ሠርተንም ለመዳን እንድንችል በቸርነቱ ይርዳን ።

    ቃና ዘገሊላ፦

    ቃና ዘገሊላ ከጥምቀት በኋላ በማግሥቱ ማለትም ጥር 12 ቀን የሚውለውን በአል የምንጠራበት ስም ነው። ትርጉሙን በተመለከተ ግን ቃና ዘገሊላ ማለት ሁለቱም ቃላት (ቃና እና ገሊላ) የቦታ ስሞች ሲሆኑ  ቃና ዘገሊላ ማለት ወይም ስንል በገሊላ ውስጥ የምትገኝ ቃና የተባለች ቦታ ወይም ከተማ ማለት ሲሆን በዚች ቦታ የተፈጸመውን ታሪክ የምናስብበት ዕለት ነው።

    ይህ ቦታና ይህ ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ለዓለም ያሳየበትና አምላክነቱንም የገለጸበት ዕለት ነው። ታሪኩንም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደሚከተለው ጽፎታል።

    \

    “ በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤  ኢየሱስም ደግሞደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።  የወይንጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅእኮ የላቸውም አለችው። 

    ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።  እናቱምለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። 

     አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙነበር።  ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸውአላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። 

    አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ሰጡትም። 

    አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውንየቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪውሙሽራውን ጠርቶ።  ሰው ሁሉ አስቀድሞመልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላመናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከአሁን አቆይተሃል አለው።

    ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃናአደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱምበእርሱ አመኑ ”። ዮሐንስ 2፡ 1-11

    ቃሉ እንደሚለን ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ድንግል ማርያም፤ ጌታችን፤ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ዚህ ሰርግ ቤት ታድመው ወይም ተጋብዘው ስለነበረ በዚያ ተገኝተዋል።  ሆኖም ግን ባለሠርጎቹ እንደ ሰውነታቸው  ጥሪ ቢያስተላልፉም  ሁኔታው ግን አምላካዊ እቅድ ነው።

    በዚህ ላይ ግን ማተኮር የምንፈልገው

    በእመቤታችን፤ በጌታ እና ሠርጉን በደገሱት ሰዎች መካከል በተካሄዱት ውይይቶች እና በውጤታቸው ላይ ይሆናል።

    1.      ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ወደ አምላኳና ወደ ልጃ በመሄድ  የወይን ጠጅ እኮ  የላቸውም አለቺው

    2.     ጌታም አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገናአልደረሰም አላት።  

    3.     እመቤታችንም  ተመልሳ  የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው

    4.     ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው።

    5.     ሰርገኞቹ እመቤታችን በነገረቻቸው መሠረት ጌታ ያላቸውን አደረጉ

    6.     ውሃውም የወይን ጠጅ ሆነ

    አሁን በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚታየው በማላጅና በተማላጅ መካከል የተካሄደ የምልጃ ክንውን ነው

    ማላጅ ማለት ሁለት ክፍሎችን የሚያስታርቅ፤ ወይም ከተማላጁ አንድ ነገርን ጠይቆ ለሚማልድለት ክፍል መስጠት፤ ወይም የምልጃውን ውጤት ለሚማልድለት ክፍል ማድረስ ነው።

    ተማላጁ እሽ ካለ እሽታውን እንቢ ካለም እንቢታውን ለሚማልድለት ክፍል ያደርሳል። በመሆኑም እመቤታችን ልጇና አምላኳ ልመናዋን ተቀብሎ እንደሚፈጽምላት በአምላካዊ ትበቡ አስታውቋታል፤ ማለትም ልመናዋን ተቀብሏል፤ በመሆኑም ያቀረበችለትን የምልጃ ልመና ለመፈጸም ለሠርገኞቹ የሚያዛቸውንም ጭምር ታውቅ ስለነበረ  ወደ ሠርገኞቹ ተመልሳ “የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው። እርሱም (ጌታም) እመቤታችን  እንዳለቺው አንድ ነገርን አላቸው ይኸውም  “ ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው”

     እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ልጇና አምላኳ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልመናዋን እንዳልተቀበላት ብታውቅ ኖሮ የሚላችሁን አድርጉ ሳይሆን ልትል የምትችለው እንዳልተቀበላት መናገር ወይም ዝም ማለት ነበር ። በመሆኑም በእመቤታችን ምልጃ መፈጸሙን የምናውቀው

    ለጌታ ምልጃዋን ወይም የሚፈለገውን ነገር ጠቅሳ በመናገሯ፤

    ተመልሳም ለሰርገኞቹ የሚላችሁን አድርጉ በማለቷ፤

    ጌታም ልክ እሷ እንደተናገረች “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” በማለቱ እና

     ከሁሉም በላይ ያቀረበቺው የምልጃ ጥያቄ ሳይለወጥ በሥራ ላይ መዋሉ ወይም መፈጸሙ ነው። ባይቀበላት ኖሮ ግን ያቀረበቺው ጥያቄ የለመነቺው ልመና ሳይቀየር እርሱው ራሱ አይፈጸምም ነበር። ማለትም የለመነቺው ሰርገኞቹ ወይን እንዲያገኙ ነበር ያንኑ አደረገላቸው።

    አምላካችን መድኃኒታችን መድኃኔ ዓለም ስለናቱ ስለቅድስተ ቅዱሳን ስለወዳጆቹ ቅዱሳን ሁሉ ብሎ በደላችን ይቅር ይበለን፤ የንስሐ ዘመን ይጨምርልን፤

    ከአባታችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሳንወጣ በፈቃዱ እና በትእዛዙ መመራት እንድንችል፤

    በስማችን ብቻ ሳይሆን በሥራችን፤ በጠባያችን፤ በአጠቃላይ በሕይወታችን ሁሉ የአባታችንን ፈለግ ለመከተል እንበቃ ዘንድ አባታችንና አምላካችን ጽናቱን ይስጠን።

    እኛም እንደ ሰውነታችን ድካም ቢበዛብንም ወድቀን የምንቀር ሳንሆን ፈጥነን የምንነሣ፤ በንስሐ የምንመለስ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ የምናደርግ መሆን ይጠበቅብናል። በዚህ ጊዜ ተስፋችን ይበዛል፤ ከሁሉም በላይ በዘላለም መንግሥት ድሆች ሳንሆን ሐብታሞች እንሆናለን፡

    በፈቃዱ  ከተጓዝን የአባታችን የሆነው ሁሉ የእኛ ስለሆነ የማያልፈውን የአባታችንን መንግሥት፤ የማያልቀውን የአባታችንን ሐብት የመውረስ መብት ይኖረናል።

    ለአባታችን የማንታዘዝ፤ በባሕርያችን፤ በሥራችን በሕይወታችን ሁሉ አባታንን የማንመስል ከሆን ግን አባታችን ያለውን ሁሉ  የመውረስ መብታችንን ሊነፍግገን ይችላል። መልካም ልጅና ለአባቱ የሚታዘዝ ልጅ እንጅ የተወለደ ሁሉ የወላጁን ሐብት የመውረስ መብት አይኖረውም። ማለትም በ40 ወይም በ80 ቀናት ወይም ከዚያም በላይ ባለው ዕድሜ የተጠመቀ ሁሉ ሳይሆን ጥምቀቱን በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ያስመሰከረ ብቻ የጸጋው ተካፋይ የምንግሥቱም ወራሽ ይሆናል።

    በመሆኑም በክርስቲያናዊ ሥነምግባር ጸንተን በአምላካችንና በአባታችን በመድኃኔ ዓለም ፈቃድ ኖረን የአባታችንን መንግሥት ለመውረስ እንበቃ ዘንድ የአምላካችን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፤ የንስሐ ጊዜንም ጨምሮልን ለሚቀጥለው ዓመትም ይህንን በአል ለማክበር ያብቃን ።

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    አሜን

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    2 comments:

    Item Reviewed: ጥምቀት (Epiphany), ጾመ ገሃድ (Tsome Gehad), እና ቃና ዘገሊላ (Cana Zegelila) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top