• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 5 November 2015

    ነገረ ቅዱሳን መላእክት ክፍል ፪


    መላእክት (ካለፈው የቀጠለ)

    ባለፈው ጽሁፋችን ስለቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮ ተመልክተናል በመቀጠልም በእያንዳንዱ ሰማይ የተፈጠሩትን ነገደ መላእክት እንመለከታለን፡፡

    1. ኢዮር

    ኢዮር ከሰባቱ ሰማያት ውስጥ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ እግዚአብሔር በዚህች ከተማ ላይ ዐርባውን ነገደ መላእክት አስፍሯቸዋል፡፡ ሲያሰፍራቸው ለዐራት ከፍሎ ዐራት ዐለቆችን ሾሞላቸዋል፡፡ እነዚህንም ሲፈጥራቸው በ10ኛው ሰዓት ሌሊት ኢዮርን እንደፎቅ ላይ ቤት፣ ታች ቤት፣ ምድር ቤት አድርጐ ፈጥሯቸዋል፡፡

     

    1.1 አጋእዝት

    የመጀመሪያዎቹን በኢዮር ያሰፈራቸውን የመላእክት ነገዶች አጋእዝት ብሎ ጠራቸው፡፡ አለቃቸውን ሳጥናኤልን አድርጐ ሾመላቸዋል፡፡ በኋላም ሣጥናኤል አምላክነትን ሽቶ ከክብር በመውረዱ ቅዱስ ሚካኤል ተረክቦታል፡፡

    ሣጥናኤል ማለት ቅሩበ እግዚአብሔር አኃዜ መንጦላእት፣ አቅራቤ ስብሐት ማለት ነው፡፡

    1.2 ኪሩቤል

    በሁለተኛው ከተማም ዐሥሩን ነገደ ኪሩቤል ብሎ ከሰየማቸው በኋላ ኪሩብ የተባለውን መልአክ አለቃ አድርጐ ሾመላቸው፡፡ እነዚህም የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ ሕዝ 1÷6-7

    ሕዝ 10÷1 ‹‹እኔም አየሁ፣ እነሆም በኪሩቤል ራስ ላይ ባለው ጠፈር በላይቸው እንደ ስንፔር ድንጋይ ያለ እንደዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ›› እንዲል፡፡

    እነዚህንም ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጐ ፈጥሯቸዋል፡፡ እነዚህም 4 ገፅ ይባላሉ፡፡ ገፀ ሰብእ፣ ገፀ አንበሳ፣ ገፀ ንስር፣ ገፀ እንስሳ (ላም) ይባላሉ፡፡ ከእግራቸው እስከ ራሳቸው በዓይን የተሸለሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ኪሩቤል እንደነብር ዡንጉርጉር አንድም እንደመስታወት ብሩህ ናቸው፡፡

    1.3 ሱራፌል

    በሦስተኛው ከተማም ዐሥሩን ነገደ ሱራፌል ብሎ ሰየማቸው፡፡ እነዚህም የዲያቆኖት አምሳያ ናቸው፡፡ አፈጣጠራቸውም ስድስት ክንፍ አድርጐ ፈጥሯቸዋል፡፡ ኢሣ 6÷2 ‹‹ሱራፌል ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፡፡ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር›› እንዲል የእነኚህም አለቃቸው ገፀ ንስር፣ ገፀ እንስሳ ነው ስሙም ሱራፊ መልአክ ይባላል፡፡

    1.4 ኃይላት

    በዐራተኛው ከተማም ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን ኃይላት አላቸው፡፡

    እነዚህ የሥላሤ ሰይፍ ጃግሮች፣ ሰይፋ ያዦች ናቸው፡፡

    የኃይላት አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ሲሆን እነዚህንም ከነአለቃቸው በኢዮር በዐራተኛው ሰማይ አስፍሯቸዋል፡፡

    2. ራማ

    ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በ10ኛው ሰዓት ከሰባቱ ሰማያት በስድስተኛዋ ሰማይ በራማ ያሉትን መላእክት በ3 አለቃ አድርጐ ለሦስት ከፍሎ አሰፈራቸው፡፡ ሲያሰፈራቸውም ራማን እንደ ላይና ታች ቤት፣ እንደምድር ቤት አድርጐ በ3 ከተማ አስፍሯቸዋል፡፡ እነዚህም

    2.1 አርባብ

    የመጀመሪያዎቹን የራማ የላይኞቹን ዐሥሩን የመላእክት ነገዶች አርቦብ ብሎ ሰየማቸው፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር ፊት ቋሚዎች አጋፋሪዎች ናቸው፡፡

    ሉቃ 1÷19 ‹‹እኔ እግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ›› እንዲል፡፡

    የአርባብ አለቃቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

    2.2 መናብርት

    በራማ ያሉትን ሁለተኛዎቹን ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን መናብርት አላቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡

    እነዚህም የሥላሴ ጋሻ ጃግሮች ናቸው፡፡ የመብረቅ ጋሻ፣ የእሻት ጦር ይዘው ለዘለዓለም እንደነፋስ ሲበሩ ይኖራሉ፡፡ እነዚህንም በራማ ሁለተኛው ከተማ ላይ አስፍሯቸዋል፡፡

    2.3 ስልጣናት

    ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በራማ ያሉትን ሦስተኛዎቹን ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን ስልጣናት አላቸው፡፡ አለቃቸው ሱርያል መልአክ (ቅዱስ ዑራኤል) ነው፡፡

    እነዚህም የሥላሴ ነጋሪት መቺዎች፣ መለከት ነፊዎች ናቸው፡፡ መላእክትን ለቅዳሴ፣ ለስባሔ ሲያነቁ፣ ሲያተጉ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነዚህንም በራማ በሦስተኛው ከተማ አስፍሯቸዋል፡፡ 1ኛ ጴጥ 3÷22

    3. ኤረር

    ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ በ11ኛው ሰዓት ሌሊት በሰባተኛዋ ሰማይ በኤረር ያሉትን መላእክት በ3 አለቃ በ30 ነገድ አድርጐ ኤረርን እንደ ላይ ቤት፣ ታች ቤት፣ ምድርቤት አድርጐ ከፍሎ አስፍሯቸዋል፡፡ እነዚህም

    3.1 መኳንንት

    የመጀመሪያዎቹን በኤረር ያሉትን ዐሥሩን ነገደ መላእክት መኳንንት ብሎ ከሰየማቸው በኋላ አለቃቸውን ሰዳክያል መልአክ አድርጐ ሾመላቸው፡፡

    እነዚህም የሥላሴ ቀስተኞች ናቸው፡፡ ተራራ የሚንድ ድንጋይ የሚሰነጥቅ የእሳት ፍላፃ የእሳት ቀስት ይዘው ሰውን ሁሉ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ የሚጠብቁ ናቸው፡፡

    በተጨማሪም በትንሣኤ ዘጉባኤ የሰውን ሁሉ አጥንት የሚሰበስቡና ምድርን ለምጽአት እንዲያዘጋጁ የሚላኩ ናቸው፡፡

    3.2 ሊቃናት

    ከዚህ በኋላ በኤረር ያሉትን ሁለተኛዎቹን ዐሥሩን ነገደ መላእክት ስማቸውን ሊቃናት አላቸው፡፡ አለቃቸውም ሰላትያል መልአክ አድርጐ ሾመላቸው፡፡

    እነዚህም የሥላሴ የፈረስ ባልደራስ ናቸው፡፡ በእሳት ፈረስ ተቀምጠው የእሳት ልብድ ተለብደው፣ በከዋክብት አምሳል የብርሃን ሰላጢን ይዘው በልባቸው የሚሳቡ፣ በእግራቸው የሚሽከረከሩትን፣ በክንፋቸው የሚበሩትን በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡

    3.3 መላእክት

    ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ በኤረር ያሉትን በሦስተኛ ከተማ አድርጐ ዐሥሩን ነገድ መላእክት ብሎ አስፍሯቸዋል፡፡ አለቃቸውም አናንኤል መልአክ አድርጐ ሾመላቸው፡፡

    እነዚህ እንደ ብረት የጸና የእሳት ነጐድጓድን ወደምድር የሚወነጭፉ፣ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ ከዋክብትን፣ እዝርዕትን፣ አትክልትን፣ እፅዋትን ከምድር በላይ ከሰማይ በታች የተፈጠሩትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ኩፋሌ 2÷6-8 በ3ቱ ሰማያት ያሉት አስር አለቆችና መቶ ነገድ እነዚህ ናቸው፡፡ ሄኖክ 20÷38-42

    ይቀጥላል

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ነገረ ቅዱሳን መላእክት ክፍል ፪ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top