ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
ስለ እመቤታችን ዕረፍትና ዕርገት ቊጥሩ ከ72ቱ አርድዕት አንዱ የሚኾነው ቅዱስ ኢቮዲየስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ስለነበረ በጥር ፳፩ የኾነ የቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍትና በነሐሴ ፲፮ የተከናወነ በዓለ ዕርገቷን በዐይኖቹ የተመለከተውን “የቅድስት ድንግል ማርያም ኅልፈተ ሕይወትና ፍልሰት” በሚል ርዕስ ጽፏል፤ በዐይኑ አይቶ የጻፈውን ይኽነንም የቅድስት ድንግል ማርያምን የዕረፍቷና የዕርገቷ ታሪክ “ነገረ ማርያም በሊቃውንት ክፍል አንድ” በሚለው መጽሐፌ ላይ የጻፉኩት ሲሆን፤ ብዙዎቻችሁ መጽሐፉ አላችሁ፤ ግን መጽሐፉን ማግኘት ያልቻሉ በሌላ ሀገር ላሉት ጓደኞቼ በጥቂቱ ጽፌላችኋለኹና እነሆ፡-
“ድርሳን ዘደረሰ አባ ኢቮዲየስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያ በእንተ ዕረፍታ ወፍልሰታ ለማርያም”
Evodius of Rome, Homily on the Dormition The falling asleep of Mary“An instruction which our holy and in every wise honourable father Abba Evodius, the archbishop of the great city Rome, who was the second after Peter the apostle,…”
(የእኛ ቅዱስ እና በማናቸውም ረገድ ብልኅ እና የተከበረ አባታችን፣ የታላቋ የሮም ከተማ ሊቀ ጳጳስ፣ ከሐዋርያው ጴጥሮስ በኋላ ኹለተኛው በኾነው የቀረበ መመሪያ፡፡ የኹላችንም እመቤት፣ እግዚአብሔርን የተሸከመች ቅድስት ማርያምን አስመልክቶ፤ በእግዚአብሔር ሰላም በግብጻውያን አቈጣጠር በ፳፩ኛው የጦቢ (ጥር) ወር ቅዱስ ሕይወቷን ያበቃችውን እመቤታችን አስመልክቶ የቀረበልን አስተምህሮ አሜን)፡፡
፯. “Now it came to pass at the hour of the light on thetwenty-first of the month Tobi, …” (በጦቢ ወር በ፳፩ በብርሃን ሰዓት ላይ በነጋታው፣ እውነተኛው ቃል ክርስቶስ በኪሩቤል ሠረገላው ላይ ተቀምጦ እልፍ አእላፋት የሚቈጠሩ መላእክት ተከትለውት፣ በዙሪያው የብርሃን ኀይሎች ከብበውት እና ዳዊት በእሳት ሠረገላ ላይ ኾኖ ከፊቱ እየዘመረለት፣ መንፈሳዊ በገናን እየተመታ ከፍ ባለ ድምፅ ለኀያሉ ጌታችን ክብር እንዘምርለት አለ፡፡ መድኀኒታችን በመኻከላችን ቆመ፣ በሮቹ ተዘጉ ወደ ኹላችንም እጆቹን ዘረጋቸው፤ ብዙዎች ደቀ መዛሙርት በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፤ ሰላም ለእናንተ ይኹን አለን፡፡ ኹላችንም በአንድ ላይ ተነሥተን እግሮቹ ሥር ወድቀን የአምልኮት ምስጋናን አቀረብንለት፤ ርሱም በሰማያዊዉ በረከቱ ባረከን፡፡ መላእክቱም አሜን ብለው መለሱ፤ ርሱም ወደ አባቴ ጴጥሮስ በመዞር “በረከት ልሰጣችኊ በመኾኑ መሠዊያዉን ጠብቀው” አለው፤ “በዛሬው ቀን ከእናንተ መኻከል ታላቅ ስጦታ ማግኘት አለብኝ” አለ፡፡ እኛ ግን በእግሮቹ ላይ ተደፍተን አመለክነው እኛም “ከእናንተ መኻከል በዛሬው ዕለት ታላቅ ስጦታ ለመውሰድ እፈልጋለኊ ስትል ምን ማለትኽ ነው” ብለን አጥብቀን ለመንነው፡፡ መድኀኒታችንም ሲመልስልን “ከዓለም ኹሉ አብልጬ የመረጥኋችኊ ክቡራን ኅዋሶቼ ይኽቺ ቀን የአባቴ ዳዊት ትንቢት የሚፈጸምባት ቀን ናት፣ ንግሥቷ በወርቅ በተንቆጠቆጠ አልባሷ አጊጣ እና አሸብርቃ በቀኜ ትቆማለች (መዝ ፵፬፥፱)፡፡
ዛሬ ለዘጠኝ ወራት በምድር ላይ መኖሪያዬ ኾና የቆየችውን ድንግል እናቴን የምቀበልበት እና ከእኔ ጋር ወደ ሰማያት ሰማያዊ ቦታዎች ይዤያት በመውሰድለመልካሙ አባቴ በስጦታ የማስረክባት ቀን ነው፣ ዳዊትም እንኳን “በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፤ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ” (መዝ፵፬፥፲፬) እንዳለ፤ ርሱም በመለኮታዊዉ እና ግሩም ድምፁ የኔ ውድ እናት ሆይ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ (መሓ ፪፥፲)፤ የነፍሴ ደስታ የኾንሽ ወደ እኔ ነዪ (መሓ፪፥፲፫) አላት፤ አንቺ ከቄዳር ልጆችም በላይ ውብ ቆንዦ ነሽ (መሓ ፩፥፭)፤ አንቺ የተመረጥሽ ጎጆ ሆይ የመልካማ ርግብ መኖርያ ነሽ፤ አንቺ የተመረጥሽ የአትክልት ስፍራ ያለምንም ዘር እና የወንድ ሩካቤ መልካሙን ፍሬ ያፈራሽ (መሓ ፬፥፲፪)፤ አንቺ የወርቅ መሶብ ሆይ መናውእውነተኛው መና እኔ እንኳን የተሰወርኹብሽ (ዘፀ ፲፮፥፴፫-፴፬)፤ አንቺ ስዉር ቅርስ እውነተኛው ብርሃን የተሰወረብሽ እና ከአንቺም ውስጥ ወጥቶ በመገለጽ በሰው ልጆች ላይ የተትረፈረፈ ሀብት ያስገኘላቸው፡፡ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ የእኔ ውብ ርግብ ሆይ (መሓ ፮፥፱) የእኔ ቅድስት መርዐት (መሓ ፬፥፰)፣ የእኔ ንጽሕት መስክ፣ ከእኔ ጋር ወደ አትክልት ስፍራው እወስድሻለኊ (መዝ ፸፩፥፮) ከርቤ እና ጣፋጭ ቅመማ ቅመሜን እደረድርልሻለኊ (መሓ ፬፥፲፬) ከበታችሽም እንድታርፊበት ያማረውን ምንጣፍ አነጥፍልሻለኊ፤ ማርያም እናቴ ሆይ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ወደ ምድር ወልደሽ አምጥተሽኛልና፡፡
እኔ ኹሉን መጋቢ የኾንኹትን ያጠቡ ጡቶሽን የተባረኩ ናቸው፡፡ እንዲኹም በከፍታ ቦታዎች ወደሚገኙ ሰማያዊ ስፍራዎች ወስጄሽ በአባቴ በመልካም ነገሮችእመግብሻለኊ፡፡ እስከዚያው በጉልበትሽ ላይ ያስቀመጥሺኝ ድንግል እናቴ ማርያም ሆይ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ በማኖር ከእኔና ከቸሩ አባቴ ጋር ወደ ሰማያት እወስድሻለኊ፡፡ በመጠቅለያ ጨርቆች እንደጠቀለልሽኝ ኹሉ የእኔ ድንግል እናት ማርያም ሆይ በወለድሽኝ ዕለት በከብቶች በረት ከላም እና አህያጋር በአንድ ላይ ከብበውኝ እንዳኖርሽኝ ኹሉ (ኢሳ ፩፥፫፤ ሉቃ ፪፥፯)፤ እኔ ደግሞ ዛሬ ከእኔ ጋር ከሰማያት ባመጣዋቸው በሰማይ መጐናጸፊያ ሰውነትሽን እጠቀልለዋለኊ፤ ከዚያም ከሕይወት ዛፍ ሥር አስቀምጠዋለኊ፣ ኪሩቤልም በሰይፈ ነበልባላቸው እንዲጠብቁት አደርጋለኊ (ዘፍ ፫፥፳፬)፡፡ የተባረከችውን ነፍስሽን የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም መንበር በተሸፈነችበት መሸፈኛዎች እንድትሸፈን አደርጋለኊ፡፡ እኔን በሚያሳድድበት ጊዜ ሥርዓት አልባውን ሄሮድስ በመፍራት ወደ ግብጽ ምድር እንደተሰደድሽው ኹሉ (ማቴ ፪፥፲፫-፲፰)፤ መላእክቶቼ ኹልጊዜም በክንፎቻቸው እያጠሉብሽ እና መልካም ዝማሬያቸውን እንዲዘምሩልሽ አደርጋለኊ)፡፡
፰. “Now when we heard these things, as our Saviour was saying them to His virgin mother,…” (እነዚኽን ነገሮች ስንሰማ፣ መድኀኒታችን ለድንግል እናቱ እንደተናገረው፣ በሥጋ ሊወስዳት እንደፈለገ ኹላችንም ዐወቅን፡፡ ኹላችንም ፊታችንን አዙረን አምርረን አለቀስን፤ የኹላችንም እናት ቅድስት ድንግል ማርያምም ከእኛ ጋር በአንድ ላይ አለቀሰች፡፡ መድኀኒታችንም ለምን ታለቅሳላችኊ አለን? አባቴ ጴጥሮስም “ጌታዬ እና አምላኬ ሥርዓት አልበኞቹ አይሁድ አንተን በሰቀሉኽ ጊዜ በወደቀብን ከባድ ዐዘን የተነሣ ለጥቂት ቀናት አልቅሰን ነበር ግን በኋላ ላይ አንተ ከሞት በመነሣትኽ እጅግ ተደሰትን፤ አንተም ወደ እኛ ቀርበኸን በረከትኽን ለገስኸን፤ በሥጋ የአንተ እናት ብትኾንም የኹላችንም እናት ለኾነችው ወደ ድንግል እናትኽ ማርያም አደራ ጣልኽብን፡፡ አኹን ግን ርሷን ከእኛ የምትወስድብን ከኾነ የሚወድቅብንን ከባድ ዐዘን ለመቋቋም ስለማንችል ርሷን ከመውሰድኽ በፊት እኛኑ አስቀድመን” አለው፡፡ መድኀኔ ዓለምም “የእኔ የተመረጥኽ ጴጥሮስና በእኔ የተመረጣችኊ ሐዋርያቶች ሆይ በሙሉ ትቼያችኊ (ተለይቼያችኊ) እንደማልቀር እና ተመልሼ እንደምመጣ አልነገርኋችኹምን? (ዮሐ ፲፬፥፩-፪) ስለዚኽ ለማርያም ሞት ፈጽሞ ማልቀስ አይገባችኹም፤ ወደ እናንተ በፍጥነት ሳትመለስ በጭራሽ አልተዋትም፡፡
እኔም ራሴን ከእናንተ እንዳልሰወርኹት ኹሉ ድንግል እናቴም ፈጽሞ ራሷን ከእናንተ አትሰውርም፡፡ ስለዚኽ ኹልጊዜም ወደ እናንተ ስመጣ ድንግል እናቴንከእኔ ጋር አብራ እንድትመጣ በማድረግ ነፍሳችኊ እንዲቀደስ አደርጋለኊ” አለ፡፡ እዚኽ ላይ አባቴ ጴጥሮስ እና የተቀሩት ደቀ መዛሙርት ለመድኀኒታችን “አምላካችን እና ጌታችን ከነጭራሹ ፈጽሞ የሞትን ጽዋ እንዳትጋፈጥ ማድረግስ አይቻልም ነበርን?” አሉት፤ መድኀኒታችንም “የእኔ ቅዱሳን ሐዋርያቶች ሆይ ይኼ ንግግር ከእናንተ በመምጣቱ በጣም ድንቅ ነው አላቸው፡፡ በመዠመሪያ የተናገርኹት ቃል ሊታበል ይችላልን? አይችልም አባቴ ከልክሏልና፡፡ ገና ከመዠመሪያውም ኹሉም ሥጋ የለበሰ ሰው ኹሉ ሞትን ማጣጣም ያስፈልጋቸዋል ብዬ ፍርድ ፈርጃለኊ (ዘፍ ፫፥፲፱)፡፡ እኔም የሰዎች ኹሉ ጌታ የኾንኹት በለበስኹት ሥጋ የተነሣ ሞትን ቀምሼ የሞትን ሰቈቃ ያጠፋኊት” አለ (ሮሜ ፭፥፲፯)፡፡ አባቴ ጴጥሮስም በዚኽ ጊዜ ላይ እንደገና. “ከአንተ ጋር እንድነጋገር ፍቀድልኝ” አለው፡፡ ጌታም “ተነጋገር” አለው፡፡ አባቴ ጴጥሮስም “ጌታዬ ለእኛ በማዘን እመቤታችን የምቾታችን (የሐሤታችን) ምንጭ በመኾኗ ለጥቂት ጊዜ በሕይወት እንድትቆይ አድርግልን” አለው፡፡ መድኀኒታችንም ሲመልስለት እያንዳንዱ ሰው በዚኽች ምድር ላይ የተቀመጠለት የቆይታ ጊዜ አለ፤ ጊዜው ሲደርስም ለአንዲት ሰዓትም እንኳን በተጨማሪ ለመቆየት አይቻለውም አለው፡፡ አኹን ስለዚኽ ለእናቴ የተቀመጠላትጊዜ ዛሬ ይፈጸማል፡፡ አኹን ሰውነቷን አኑራ እና ከእኔ ጋር በክብር ወደ ሰማያት መኼድ ይገባታልና፤ የሰማያትን ሥርዓት ተመልከቱ፣ አባቴ የውድ ልጁመቅደስን፤ እኔን ጨምሮ እየጠበቅናት ነውና፡፡ ወደ አባቴ ሳልወስዳት በፊት እራሴ እኔ በቅዱስ መሥዋዕት ከርሷ ጋር እንባርካችኋለንና” አለን)፡፡
፱. “The women therefore that went with her, even thevirgins that followed her, turned their face away, andall wept bitterly…” (ከርሷ ጋር በአንድነት ይኼዱ የነበሩትም ሴቶች ተከትለዋት የነበሩትም ደናግል ፊታቸውን አዙረው ኹሉም አምርረው በሲቃ ድምፅ አለቀሱ፤ ቅድስት ድንግል ማርያምም አብራቸው አለቀሰች፡፡ ቸሩ መድኀኒታችንም “ማርያም ድንግል እናቴ ሆይ ስለምን ታለቅሺያለሽ? አላት፤ አኹን ልቅሶሽን በመተው ለዘላለም ነዋሪ ወደኾነው ደስታ መኼድ አለብሽ አላት፤ ሐዘን እና ለቅሶሽን በመተው በሐሤት እና በደስታ ለዘላለሙ መኖር ይገባሻል፤ የምድር ነገሮች በሙሉ ትተሽ የሰማያት የኾኑትን መውረስ ይገባሻልና”፤ ድንግል ማርያምም ለመድኀኒታችን ስትመልስለት “ጌታዬ፣ አምላኬ እና ልጄ እንዴት ዐላዝን እና በልቤስ አላለቅስ? በጣም ብዙ ጊዜያት በሰው ልጆች ሞት በጣም ብዙ ቅርፆች እናዳሉት፣ሊወስዳቸው ከመጣ በኋላም አስፈሪ እና አሰቃቂ ነገር እንዳለው ሲነገር ሰምቻለኊ፤ እነዚኽ ነገሮች ከኾኑ፣ እንዴት አላለቅስ እንዴት ብዬስ አስፈሪውንቅርፁን ልመልከተው?” አለች፤ ጌታችን ኢየሱስም “ውዷ እናቴ ማርያም ሆይ ሞትን ፈጽሞ እንዳትፈሪው፣ ማንኛውንም የሞት ኀይል ለማውደም የሚችለው ከአንቺ ጋር አይደለምን? አላት፤ ብዙ ቅርጽ ያለው ጣዕረ ሞትን የዓለም ኹሉ ሕይወት እስትንፋስ የያዘው ከአንቺ ጋር እያለ እንዴት ትፈሪዋለሽን?” አላት፤ ጌታም በራሱ ራርቶ ራሱን ወደ ድንግል እናቱ አስጠግቶ እንባዎቿን ጠራርጎላት በመለኮታዊ ከናፍሮቹ ሳማት፡፡ ከዚያም ጌታ ኢየሱስ በመሠዊያዉ ላይ በመኾን ኹላችንንም ባረከን፣ የሰላም ሰላምታውን አቅርቦልን፣ አባቴን ጴጥሮስን “ፍጠን ወደ መሠዊያዉ ተመልከትና አባቴ ከሰማይ የላከልኝን ንጹሓት አልባሳትን አምጣልኝ ድንግል እናቴን ላልብሳት ምክንያቱም የርሷን ቅዱስ ሰውነት በምንም ዓይነት ከምድር የተገኘ ጨርቅ መሸፈን አይገባውምና” አለ፡፡ ከዚያም አባቴ ጴጥሮስ ያማረውን ውብ ሸማ፣ ንጹሕ፣ ቅዱስ፣ በጣም ውድ እና ጣፋጭ መዐዛ የሚረጨውን ይዞ መጣ፤ እጅግ ደማቅ ብርሃን የሚለቀውን ያማረ ሸማ ስንመለከት ኹላችንም በጣም ተደነቅን፡፡ መድኀኔ ዓለምም ያማረውን ሸማ ከአባቴ ጴጥሮስ ላይ ተቀብሎት በራሱ መንገድ ዕጥፋቶቹን በመዘረጋጋት፤ ድንግል እናቱን ጠርቷት፣ ተነሺ የእኔ ብራማ ርግብ ክንፎችሽ በወርቅ የተንቈጠቈጡት ወደ እኔ ነዪ አላት (መዝ ፰፯፥፲፫)፤ የእኔ ንጽሕት እና እንከን የለሽ ጠቦት ወደ እኔ ነዪ” አላት (መዝ ፷፰፥፴፩))፡፡
፲. “And she arose, the queen of all women, Mary the Virgin, the mother of the King of kings, to go unto her beloved Son, our Lord Jesus Christ…” (የሴቶች ኹሉ ንግሥት፣ ድንግል ማርያም፣ የነገሥታት ንጉሥ እናት ወደ ተወዳጁ ልጇ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመኼድ ተነሣች፡፡ ኹላችንም ከተቀመጥንበት ተነሥተን እጆቿን እና እግሮቿን እያነባን ሰላምታን ሰጠናቸው፤ ከዚያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውድ ልጇ ሰላምታ አቅርቦላት “ወደ ዘረጋኹልሽ አልባሳት ውስጥ ግቢ እና ፊትሽን ወደምሥራቅ መልሺ እና ጸሎት አቅርቢ፤ ከዚያ በኋላ መጐናጸፊያው ላይ ጋደም በይ እና በምድር ላይ ለተወለዱ ሰዎች በሙሉ ጸሎትሽን አሟይ” አለ፤ የሴቶችኹሉ ልዕልት፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የነገሥታት ኹሉ ንጉሥ እናት ከተቀመጠችበት ተነሥታ መድኀኒታችን በእጆቹ ወደ ዘረጋላት መሸፋፈኛ መኻከል ገባች፡፡ በቆመችበት ፊቷን ወደ ምሥራቅ አግጣጫ አዙራ በሰማይ ነዋሪዎች ቋንቋ ጸሎቷን አቀረበች፡፡ ጸሎቷንም እንደጨረሰች አሜን አለች፤ እኛም ኹላችንም ከተቀመጥንበት ተነሥተን አሜን ብለን መልስ ሰጠናት፡፡ ከዚኽ በኋላ በመሸፋፈኛ አልባሳቱ ላይ ጋደም ብላ እጆቿን ተደግፋ ወደ ምሥራቅ አግጣጫ ፊቷን አዞረች፡፡
ከዚያም መድኀኒታችን ከርሷ ጋር በቤተ መቅደስ ሲያገለግሉ ከነበሩትና መድኀኒታችንን እስከ እግረ መስቀል ሲከተሉ ከነበሩ ደናግል ጋር በአንድ ላይ እንድንጸልይ ለጸሎት እንድንቆም አደረገን፡፡ ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ ሴቶቹ ተከትለዋት መጥተው ነበር፡፡ እኛም በቤተ መቅደስ ለምን ማገልገል እንዳቆሙ ስንጠይቃቸው? እነርሱም የእግዚአብሔር አብ ቃል ክርስቶስ በተሰቀለበት ቀን ኹሉም ቦታዎች ሲለወጡ ተመልክተን ነበር አሉን፡፡ ፀሓይ ጨልማነበር፣ ጨረቃ ደም መስላ ነበር ከዋክብትም ከሰማያት ወደ ምድር ወድቀው ነበር፡፡ እኛም በጣም ፈርተን የቅዱሳን ኹሉ ቅዱስ ወደኾነው የጌታ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሸሽተን ገባን በሩንም ጥርቅም አድርገን ዘጋነው፡፡ ወዲያውኑም ኀይለኛ መልአክ ከሰማይ በታላቅ ቁጣ በእጁ ውስት የሚያብለጨልጭ ሰይፍ ይዞ ወደ ምድር ሲወርድ ተመለከትን፣ በያዘው ሰይፍም መጋረጃውን መኻል ለመኻል ከላይ ወደታች እኩል በእኩል ቀደደው (ማቴ ፳፯፥፶፩)፡፡ ከዚያም ታላቅ ድምፅ “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ ርሷ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድኊ! አልወደዳችኹምም እነሆ ቤታችኊ የተፈታ ኾኖ ይቀርላችኋል” (ማቴ ፳፫፥፴፯) የሚል ሰማን እንደገና ስንመለከት ለመሠዊያው ተመድቦ የነበረው መልአክ በመሠዊያው በላይ ሰይፉን ይዞ በታላቅ ቁጣ ሲበርር ተመለከትን፤ እነዚኽ ነገሮች በሙሉ ሲኾኑ ባየን ጊዜ፣ ጌታ በሰዎቹ በጣም እንደተቆጣና በርግማን ሥር እንዳንወድቅ በማሰብ ከእኛ ጋር ወደነበረችው እናቱም በፍጥነት እንደመጣን ዐወቅን፣ ይኽነንም መጋረጃውን ከቀደደው የጌታ መልአክ አፍ ሰማን” አሉ (ማቴ ፳፯፥፶፩)፡፡
፲፩. “The twelve virgin s therefore and all the women also who were with us, were all weeping with us together,…” (ዐሥራ ኹለቱ ደናግል እና ከእኛ ጋር የነበሩት ሴቶች በሙሉ ድንግል ማርያምን በዙርያዋ ከብበን የተማርነውን የሰማያዊ ምስጋና መዝሙር ስንዘምር ቆመን ስናለቅስ ነበር፡፡ ክርስቶስም ለእናቱ ክብር እጆቹን በጉንጮቿ ላይ አድርጎ ከጐኗ ተቀምጦ ነበር፡፡ ለረዥምጊዜ በዝማሬ ላይ ሳለን ክርስቶስ ለእናቱ ሰላምታ አቅርቦላት ወደ ውጭ ይዞን ወጣ፡፡ ድንግልም “ኢየሱስ ሆይ እውነተኛው ያለምንም ነውር ነቀፋ የወለድኹኽ ልጄ፣ የኀያሉ እግዚአብሔር ልጅ እና ውዱ ልጄ ልለምንኽ፣ የወለድኻትን እናትኽን እንዳትረሳት፣ ጌታዬ ሆይ፣ የሞት ጥላ እንዳይቀርበኝ፤ ውዱ ልጄ ሆይ የአምባገነኑ የሞት ኀይሎች እና የድቅድቁ ጨለማ ሥልጣናት ይርቁ ዘንድ፡፡ የብርሃን መላእክት ይቅረቡኝ እንጂ ሞትን የማያውቁት ትሎች እንዳሉ ባሉበት ይኹኑ፡፡ የውጭው ጨለማ ብርሃን ይኹን፡፡ የሐሰት ከሳሾች አፍ ይዘጋ፡፡ በጥልቁ እንጦርጦስ የሚገኘው እሳት የሚተፋው ዘንዶ ወደ አንተ ስመጣ ሲመለከት አፉ የተዘጋ ይኹን፡፡ ውዱ ልጄ ሆይ የጥልቁ እንጦርጦስ አዛዦች ከእኔ እንዲሸሹ እና ነፍሴን እንዳያስፈራሯት እዘዛቸው፡፡ በእነዚኽ መንገዶች የሚገኙት አደናቃፊ ድንጋዮች ከፊቴ ይውደሙ፡፡ በመጥፎ ዐይኖቻቸው የሚያዩኝን በቀለኞችን ከልለኝ፡፡ ልክ እንደ ባሕር ማዕበል የሚናወጠው የሚንቀለቀለው የእሳት ወንዝ፣ ጻድቃን እና ኀጥኣንን ለኹለት የሚከፍለው በማልፍበት ጊዜ ነፍሴን ፈጽሞ እንዳይነካት፤ ምንም ኀፍረት በሌለበት ፊቴ አመልክኻለኹና ከዘመናት እስከ ዘመናት ኀይል እና ክብር የአንተ ናቸው” አሜን)፡፡
፲፪. “And our Lord Jesus Christ said to His mother with His gentle voice, Be of good cheer, O Mary my mother…” (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን ድንግል ማርያም ለስለስ ረጋ ባለ አስደሳች አንደበቱ ማርያም እናቴ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አላት፡፡ እነዚኽ ኹሉ ነገሮች በአንቺ ውስጥ ፈጽሞ ቦታ ስለሌላቸው ከአንቺ አርቄ አባርርልሻለኊ፤ በእነርሱ ፈንታ ለዘላለሙ ማረፊያሽ የኾኑትን የሰማያዊ ማረፊያ ቦታዎች እና በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም የሚገኙትን መልካሞች ነገሮችን አዘጋጅቼልሻለኊ፡፡ አካልሽ በውስጡ የሚሸፋፈንበት ከገነት የመጣውን ሰማያዊ መሸፈኛ እና እጅግ ያበቡትን የዘንባባ ዝንጣፊዎች አዘጋጅቼልሻለኊ፡፡ ቅዱስ ነፍስሽን ከእኔ ጋር ወደ ሰማይ በመውሰድ ለመልካሙ አባቴ በስጦታነት አበረክታታለኊ፣ እኔን የወለድሽኝ አንቺ ቅድስት ሆይ ከስጦታዎች ኹሉ እጅጉን ከፍ ያልሽ ስጦታ ነሽና” አላት፤ ጌታችን ሐዋርያቱን “እኔ የዓለም ሁሉ ሕይወት እስትንፋስ ባለኹበት ሞትን ማየት ስለማይገባት የውድ እናቴ ነፍስ መሰናበቻዋ ጊዜ በመቃረቡ ለጥቂት ጊዜያት ወደ ውጭ እንውጣ” አላቸው፡፡ እነሆ አኹን እኛን በመጠበቅ በአንድ ላይ ኹሉም የሰማያት ኀይሎች ኹሉ ተሰብስበዋልና፤ ስለዚኽ ርሷ ጋደም ብላ እንዳለች ትተናት ጌታን ተከትለን ኹላችንም ወደ ውጭ ወጣን፤ ከርሷ ጋር የተሰበሰቡት ደናግል ዮሐና እና ሰሎሜ እንዲኹም ኹሉም ታማኝ ሴቶች ሊያገለግሏት በውስጥ ቀሩ፡፡ ጌታችን በመግቢያው በር ላይ በውጭ በሚገኝ አንድ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ ሳለ ኹላችንም ከብበነው በዙሪያው ቆምን፡፡
ወደ ሰማይ ተመልክቶ በከፍተኛ ድምፅ “ሞት ሆይ መኖሪያኽ በስተደቡብ በሚገኙት የማከማቻ ስፍራዎች የኾነው ድል ነሥቼኻለኊና ሥጋ በለበሱ ፍጡራን ላይም በሙሉ ሥልጣን ሰጥቼኻለኊ እና ወደ ድንግል እናቴ ና፣ ቅረባት ትመልከትኽ ግን ማርያም እናቴ ምንም ልታይኽ እስከማትችልበት ጊዜ ድረስ ማቃጠልኽ እና አሸናፊነትኽ ይውደም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን (እናቴ ካረፈች በኋላ) ለዘላለሙ የምትለብሰውን አስፈሪ ቅርጽ እና ማቃጠልኽን እንዲኹም አሸናፊነት መልሰኽ ተጐናጸፍ፡፡ በአፍታ ቅጽበት እና በዐይን ብልጭታ ከሰው ልጆች ኹሉ ስሙ እጅግ አስፈሪ የኾነው ሞት ቀረበ፡፡ ልክ በዐይኖቿ እንዳየች ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታ ልጇ ተቀምጦበት ወደነበረው ቦታ መጥታ በዕቅፉ ውስጥ ወደቀች፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም በነበርንበት ቦታ ከመኻከላችን ተቀምጦ ሳለ ሰማይ እና ምድርን መላቸው፡፡ እንደ በረዶ ጸዐዳ የኾነውን የድንግል ማርያምን ነፍስ በዕቅፉ ውስጥ እንደያዘ ለነፍሷ የከበረ ሰላምታውንሰጥቶ ባማረው ሸማ ጠቅልሏት ለሊቀ መልአኩ ለቅዱስ ሚካኤል በብርሃናማ ክንፎቹ እንዲሸከማት ሰጠው፣ ይኽም ለቅዱስ አካሏ ማኖሪያ ቦታ እስኪያዘጋጅ ድረስ ነበር፡፡ ኹሉም በዙሪያዋ ከበው የነበሩት ሴቶች ዕረፍቷን በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ዐዝነው አለቀሱ፡፡ ሰሎሜም ወደ ውጭ ወጥታ በጌታዋ እግር ላይተደፍታ “ጌታዬ አምላኬ ተመልከት ውድ እናትኽ ዐርፋለች” ብላ አመለከችው፡፡ ዛሬ ታላቅ ዐዘን እና መነጠል የወደቀብን ለእኛ ወዮውልን፡፡ አንተ በአጠገቧ ብትኖር ኖሮ አትሞትም ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስም “እናቴ ድንግል ማርያም አትሞትም ይልቁንም ለዘላለም ትኖራለች፤ የእናቴ ሞት ሳይኾን የዘላለም ሕይወት ነው እንጂ” አለ፡፡ ቅዱሱ አመስጋኝ ዳዊትን በመንፈሳዊ በገናው ጮኾ በመዘመር “በጌታ ፊት የቅዱሳኑ ሞት እጅግ የከበረ ነው” (መዝ ፻፲፭፥፲፭) የነገሥታት ኹሉ ንጉሥ የኾነው የክርስቶስ እናት ማርያም ደስ ይበልሽ፤ ይኽ ስለ እውነተኛዋ ንግሥት ማርያም የተናገርኩት ትንቢትየተፈጸመበት ቀን ነው” (መዝ ፵፬፥፱) በማለት ዘመረ)፡፡
፲፫. “And our Saviour arose from the stone, and went into the house,…” (መድኀኒታችንም ኹላችንም ከርሱ ጋር በአንድ ላይ እያለን ከተቀመጠበት ድንጋይ ተነሥቶ ወደ ቤት ውስጥ ገባ፡፡ የድንግል ፊት እንደ ፀሓይ እያበራ እና ሰውነቷ አስደሳች የሽቱ መዐዛን ሲረጭ አየን፡፡ በለቅሶ አኹን በእናቱ ድንግል ማርያም አካል ላይ አድርጎ “የእኔ እናት ማርያም ሆይ እግዚአብሔርን (እኔን) የሳምሽባቸው ከናፍሮችሽ የተባረኩ ናቸው፤ ወደ ምድር ሲመለከት መሠረቶቿ እንዲናጉናእንዲሸበሩ ለማድረግ የሚችለውን ከኀሊውን ልጅሽንና አምላክሽን (እኔን) ያየሽባቸው ዐይኖችሽ የተባረኩ ናቸው፤ ከሰማያት ነዋሪዎች ጋር በመላእክት ቋንቋዎች ስነጋገር የሰማሽባቸው ዦሮዎችሽ የተባረኩ ናቸው፤ አንቺ ሆይ በቃሉ ኀይል ምድርን የተሸከማትን የተሸከሙት የኖርኹባቸው ታናናሾች ክንዶችሽ የተባረኩ ናቸው፡፡ የእኔ ድንግል እናት ማርያም ሆይ ፍጥረትን ኹሉ የምመግበውን የመገቡት እና ያጠቡት ጡቶችሽ የተባረኩ ናቸው፡፡ በኀያሉ ዙፋን ላይበክብር የምቀመጠውን እኔን በፍቅር ያስቀመጡኝ ጉልበቶችሽ የተባረኩ ናቸው፡፡ ለዘጠኝ ወራት የተሸከሙኝ ማሕፀኖችሽም የተባረኩ ናቸው፡፡ በመለኮታዊነቴብርሃን ብሩሃት የኾኑት ሥጋሽና ነፍስሽ የተባረኩ ናቸው” አላት)፡፡
፲፬. “Now when out good Saviour had said these things…’’ (አኹን ቸሩ መድኀኔ ዓለም ስለ እናቱ እነዚኽን ነገሮች ሲል እያነባ ነበር እኛም ኹላችንም ስናለቅስ ነበር፡፡ ከተቀመጠበትተነሥቶ ሰማያዊ አልባሳቶቹን በማንሣት ቅዱስ አካሏን ሸፈነው፤ ርሱ፣ ጴጥሮስ እና ዮሐንስ፣ አልባሳቶቹን ከአካሏ ጋር በደንብ ታስረው ነበር፡፡ መድኀኒታችንም ለሐዋርያቱ “ተነሡ ለእኔ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የኾነውን የእኔ ውድ እናት ቅዱስ አካሏን ወደ ላይ አንሥታችኊ እና የኀያሉ አልባሳት የተጠቀለሉበት እና የሰማያዊ ቦታዎች ዘንባባ ዝንጣፊዎች ያረፉበትን በዠርባችኊ ተሸከሙት” ብሎ ተናገራቸው፡፡ “በእኔ የተመረጥኽ ጴጥሮስ ሆይ ራሷንበትከሻኽ ተሸከም፣ ዮሐንስም እግሮቿን ተሸከም፤ እናንተ ወንድሞቼ እና ቅዱሳን አባላቶቼ (ኅዋሶቼ) ናችኹና፤ የተቀራችኹት ሐዋርያቶቼ በፊቷ ዘምሩላት፤ ኹላችሁም ከትንሽ እስከ ትልቅ ሳትሉ ወደ ምሥራቃዊቷ ኢየሩሳሌም ኢዮሳፍጥ ዐብራችኋት ኺዱ በዚያም እንደደረሳችኊ ከዚኽ በፊት ማንም ሰው ያላረፈበት ዐዲስ መቃብር ታገኛላችኊ፡፡ ቅዱስ አካሏን በዚያ ውስጥ ያርፍ ዘንድ አለውና ለሦስት ቀናት ተኩል ትጠብቁታላችኹና፡ ፈጽሞ እንዳትፈሩ እኔም ከእናንተው ጋር ነኝና” አለ፤ አኹን መድኀኒታችን የቡራኬ ንግግሩን አድርጎ እንደጨረሰ ዘማሪው ቅዱስ ዳዊት “ሃሌ ሃሌ ሉያ በኋላዋ ደናግሉንለንጉሥ ይወስዳሉ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ” በማለት ዘመረ (መዝ ፵፬፥፲፬)፡፡ ከዚኽ በኋላ ጌታ ኢየሱስ የሰላም ሰላምታውን ሰጠን ኹላችንም አመለክነው፡፡ እንደገናም ዳዊት “ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ አቤቱ ወደ ዕረፍትኽ ተነሥ አንተና የመቅደስኽ ታቦት ይኽቺውም ነውር ነቀፋ የሌለባት ንጽሕት ማርያም ናት” (መዝ ፻፴፩፥፰) በማለት አመሰገነ)፡፡
፲፭. “Straightway our Saviour rode upon His chariot of Cherubim,…” (በቀጥታ መድኀኒታችን በኪሩቤል ሠረገላ ላይ ኾኖ፣ ኹሉም የሰማያት ሥልጣናት በዝማሬያቸው ተከትለውት ሳለ አየሩበጣፋጭ መዐዛ ተትረፍርፎ ነበር፡፡ የእናቱን ነፍስ በዕቅፉ ተቀብሎ፣ ባማረ መጐናጸፊያ ጠቅልሎት፣ የብርሃን ብልጭልጭታን በመላክ ኹላችንም እየተመለከትነው ወደ ሰማያት ኼደ፡፡ ከዚያም ወዲያውኑ የድንግልን አካል ወደ ላይ በማንሣት አባቴ ጴጥሮስ ራሷን፣ ዮሐንስ እግሮቿን ተሸክመው ሳለ የተቀሩት ሐዋርያት በእጆቻቸው የዕጣን ማዕጠንት ይዘው በአንድ ላይ ከእኛ ጋር እየዘመሩ ኹሉም ደናግል ከኋላችን ተከትለውን በምሥራቃዊቷ ኢየሩሳሌም ኢዮሳፍጥ መስክ ተብላ ወደምትታወቀው ኼድን፡፡ ርጉማን የአይሁድ ሕዝቦች ጌታችንን ዐምፀው ወደ ገደሉባት ስንደርስ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት በታላቅ ድምፅ ሲጸልዩ ድምፅ ሰሙ፤ ከዚያም ርስ በርሳቸው “በዚኽ ከተማ ዛሬ በቀን የሞተው ማን ነው” ተባባሉ፡፡ አንዳንዶቹም “እኛ በመስቀል ላይየሰቀልነው የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ናት እነሆ ወደ መቃብሩ እየወሰዷት ነው” ብለው መለሱ፡፡ ከዚያም ርስ በርሳቸው ተመካክረው ሰይጣን ልባቸውን አደንድኖት በሰይጣናዊ ዕብሪት ተነሣስተው እኛን ገድለው የድንግል ማርያምን አካል ለማቃጠል ዐስበው ወደ እኛ መጡ፤ ይኽነንም ከዚያ በኋላ ለእኛ እንደተናዘዙልን፡፡ ወደ እኛ እየቀረቡ ሲመጡ እነሆ እኛንም እነርሱንም የእሳት ግድግዳ ከበባቸው ዐይኖቻቸውም በድቅድቅ ጨለማ ተዋጠ፡፡ ጌታም ከዚኽ በፊት ልክ በግብጻውያን ላይ አድርጎት እንደነበረው ማንም ሊሰማው በሚችል ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ዋጣቸው (ዘፀ ፲፥፳፪-፳፫)፡፡ ግን የድንግልማርያምን አካል ሐዋርያቱ እንደተሸከሙት በመድኀኒታችን ቃል መሠረት በመቃብር ውስጥ አስቀመጡት እና ጥበቃ ለማድረግ ሦስት ቀን ከተኩል በዚያው ቆዩ)፡፡
፲፮. “Now the Jews, when they saw the great anger which…” (አይሁድ አኹን ከጌታ የወረደባቸውን ታላቅ ቁጣ ሲመለከቱ ጮኸው በማልቀስ እንዲኽ በማለት ተማጸኑ፣ “የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ማርያም ሆይ ርጂን፡፡ ከአንቺ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ እኅታችን ማርያም ሆይ ከዘር ሀረጋችን ትመዘዥያለሽና እና ምሕረትን ለምኝልን፡፡ ለአፍታም እንኳን ምንም ጥፋት አጥፍቶ በጭራሽ የማያውቀውን ክርስቶስ ልጅሽን በድለናል፡፡ ስለዚኽ እኅታችንማርያም ሆይ ምሕረትን አውርጅልን እና የዐይኖቻችንን ብርሃን ለግሺን” አሉ፡፡ ወዲያውኑም ዐይኖቻቸው ተከፍተው ብርሃን አዩ፤ ቢፈልጉም የድንግልን ቅዱስ አካል አላገኙትም (ወደ ገነት ከዮሐንስ ጋር በመነጠቁ)፡፡ በኾነው ድንቅ ተአምር እጅግ ተደምመው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ጮኸው “አንድዬ ልጁን ወደ ዓለም የላከው ርሱ የእስራኤል አምላክ ነው፤ በእውነት ታላቅ ኀጢአት በመፈጸም ጥፋተኞች ነን” አሉ)፡፡
፲፯. “Now when they had reached mid-day on the fourth day, the apostles being gathered together with one another…” (በአራተኛው ቀን እኩለ ቀን እየተቃረበ ሲመጣ ሐዋርያቱ አንዳቸው ለአንዳቸው ከደናግል ጋር የድንግልን ሥጋ ሊያኖሩበት በነበረው በመቃብሩ ስፍራ በመሰብሰብ ለድንግል ማርያም ክብር ዝማሬ እና የምስጋና ዜማ አቀረቡ፤ እነሆ ልክ እንደ መለከትያለ ድምፅ በከፍተኛ ኹኔታ ከሰማይ መጣ “እስከ ሰባተኛው ወር ድረስ ወደቦታው ኹላችኹም መኼድ ይኖርባችኋል፡፡ እነሆ የካህናት አለቆችን እና የኹሉንም አይሁዶች ይኽነን ቦታ ከዚኽ በኋላ እንዳያዩት ወይም እንዳያውቁት ወይም አካሏን ከእኔ ጋር ወደ ሰማይ እስክወስደው ድረስ የድንግልን አካልለማግኘት እንደይፈልጉ ልባቸውን አደንድኜዋለኊ፡፡ ከእናንተ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርቶች እና ደናግል በሙሉ በዐሥራ ስድስተኛው ወር ሚዞሪ (ነሐሴ ፲፮) እናቴን ድንግል ማርያምን ነፍሷን ወደ ሥጋዋ መልሼላት ልክ በምድር ከእናንተ ጋር ትኖር እንደነበረው ከእኔ ጋር ወደ ሰማይ ስወስዳት እንድትመለከቱ ትንሣኤ ለኹሉም ሥጋ መኾኑን ኹላችኹም በልባችኊ እንድታምኑ ዘንድ ትመጣላችኊ”፤ ይኽነን ድምፅ እንደሰማን እግዚአብሔርን እያመሰግን ነበር፤ ከተቀመጥንበት ተነሥተን ጸለይን፣ ወደምንኖርበት ቤትም ተመለስን፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመለየታችን በታላቅ ዐዘን እና ልቅሶ ውስጥ ወደቅን እግዚአብሔር የልባችንን ዐዘን እንዲያቀልልን እና ርሷን ደግሞ እንዲያሳየን በየቀኑ ስንጸልይ ቆየን፡፡ እግዚአብሔርን የተሸከመች ቅድስት ድንግል ማርያም ነፍሷ ከሥጋዋ ከተለየችበት የሚዞሪ (ከጥር) ወር ዠምሮ ሰባተኛው ወር (ነሐሴ) ላይ ደረስን፣ በዚኽ በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ላይ የድንግል አካል ወደነበረበት መቃብር ስፍራ ተሰበሰብን፣ ደናግልም ከእኛ ጋር በአንድ ላይ ነበሩ፡፡ ሌሊቱን በሙሉ ስናይ እና ስንዘምር፣ የዕጣን መሥዋዕት ስናቀርብ፣ ደናግልም መብራት ሲያበሩ ዐደርን)፡፡
፲፰. “Now at the hour of the light on this same night, which is the morning of the sixteenth of the month Mesore,…” (በዐሥራ ስድተኛው ሚዞሪ (ነሐሴ) ጠዋት በተመሳሳይ ምሽት በብርሃን ሰዓት ላይ፣ በምንኖርበት ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ እኛ መጣ፣ “ቅዱሳን ሐዋርያቶቼ ሰላም ለእናንተ ይኹን የአባቴ ሰላም ከእናንተ ጋር ይኹን” አለን፡፡ እኛም ተደፍተን አመለክነው፣ ርሱም ኹላችንንም ባረከን፣ እንዲኽም አለን፣ “በዚኽ ታላቅ ዐዘን፣ የልብ ስብራት እና ጥልቅ ለቅሶ ውስጥ ናችኹን?”፤ አባቴጴጥሮስም “ጌታዬ እና አምላኬ እንዲኽ ጥልቅ ዐዘን ውስጥ የወደቅነው በእናትኽ ድንግል ማርያም እና በኹላችን እመቤት አካላዊ ሞት የተነሣ እና ከሞተችበት ጊዜ ዠምሮ ቃል እንደገባኽልን ደግመኽ ስላላሳየኸን ነው” አለው፡፡ ጌታም “የውድ እናቴ አካል እነሆ፣ በአባቴ ትእዛዝ መሠረት በመላእክቶቼ እና በእናንተ ይጠበቃልና ምክንያቱም የልጁ የእኔ ቤተ መቅደስ ነውና፤ ሰውነቷ ግን በሰማይ ሰማያዊ ቦታዎች ላይ በከፍተኛ ቦታዎች ላይ በሚገኙ መላእክት ዝማሬ ታጅቧል፡፡ እዚኽ ላይ በተውኹላችኊ ነገሮች ፈንታ በገባኹላችኊ ቃል ኪዳን የአኗኗሯን ክብር ለመግለጽ ወደዚኽ ወዳላችኹበት እንድትመጣ ልኬባታለኍ”፡፡
መድኀኒታችን ከእኛ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለም ከፍ ባለ ቦታ ላይ የምስጋና መዝሙር ሰማን፡፡ ወዲያው ስንመለከት አንድ ትልቅ የእሳት ሠረገላ ተመለከትን፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም በላዩ ላይ ተቀምጣበት በኪሩቤል መንኰራኲር እየተሳበና ከፀሓይ እና ከጨረቃ ዐሥር ሺሕ እጥፍ እያበራች መጥታበመኻከላችን ቆመች (መሓ ፮፥፲፤ ራእ ፲፪፥፩)፡፡ እኛም በከባድ ፍርሃት ወድቀን በፊታችን ተደፍተን አመሰገንናት፤ ርሷም እጆዎችዋን ወደ እኛ ዘርግታ ኹላችንንም በመባረክ የሰላም ሰላምታዋን አቀረበች፡፡ እንደገናም በታላቅ ደስታ እና መቀደስ ውስጥ ኾነን አመሰገንናት፤ እዚኽ ላይ እምነት የለሽ በኾኑት የሰው ልጆች የተነሣ የማንናገራቸው ታላቅ እና ድብቅ ምስጢራትንም ነገረችን፡፡ (ዳግመኛ ለማሳየት) ጌታም ወደ መቃብሩ በመጣራት የድንግል እናቱን አካል በማስነሣት ነፍሷንም እንደገና ወደ ሥጋዋ በማስገባት ልክ ቀድሞ በሥጋ እንደምናውቃት በሕይወት አየናት፡፡ መድኀኒታችንም እጆቹን ዘርግቶ ከርሱ ጋር በሠረገላው ላይ አስቀመጣት መድኀኒታችን ለስለስ ባለ ድምፅ “እነኋት ውድ እናቴን” አለን፡፡ በዚኽች ምድር ለ፱ ወራት በማሕፀኗ የተሸከመችኝ እና ከማር የሚጣፍጡትን ጡቶቿን ለ፫ ዓመታት ያጠባችኝ ርሷ ነበረች አለን፤ እነኋት ፊት ለፊትም እይዋት፣ በእኔ አማካይነት ከሞት ተነሥታ ኹላችኹንም ባርካችኋለች አላቸው፡፡ አኹን ስለዚኽም ተጋድሏችኹን እስክታጠናቅቁ ድረስ ፈጽሞ ከእናንተ አልለይም፡፡ አኹንም ተነሡ ወደ መላው ዓለም ኼዳችኊ በየደረሳችኹበት ኹሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሰዎችን አጥምቁ ኹሉንም ያስተማርኋችኹን ነገሮች እንዲያከብሩ አስተምሯቸው” አለን (ማቴ ፳፰፥፲፱)፤ መድኀኒታችን እነዚኽን ነገሮች እየነገረን ቀኑን ሙሉ ከእናቱ ድንግል ማርያም ጋር ከእኛ እና ጋር ዐሳልፏል፡፡ ከዚያ በኋላ የሰላም ሰላምታውን ሰጥቶን መላእክት በፊቱ እየዘመሩለት በክብር ወደ ሰማያት ዐረገ)፡፡
፲፱. “This is [the end of] the life of the Lady of us all, the holy God-bearer Mary, on the twenty-first of Tobiand her assumption on the sixteenth of Mesore….” (ይኽ የኹላችንም እመቤት አምላካችንን የተሸከመች ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍተ ሥጋዋ በኻያ አንደኛው የጦቢ ወር (ጥር ፳፩) ሲኾን በዐሥራ ስድስተኛው የሜዞሪ ወር (ነሐሴ ፲፮) በሥጋ ተነሥታ ዐርጋለች፡፡
እኔ ኢቮዲየስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የአባቴ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙር በዚኽ ጽሑፍ ውስጥ ከተነገሩት ሐዋርያት ጋር በአንድ ላይ በመኼድ፤ እነዚኽ ኹሉ ነገሮች ሲኾኑ ተመልክቼያለኊ፡፡ እነዚኽን ክስተቶች የሚነግራችኊ ሌላሰው ሳይኾን እኔው ራሴ ነኝ፤ ግን እነዚኽን ነገሮች በራሴው ዐይኖች ያየኋቸው እንዲኹም በዦሮዎቼ የሰማኋቸው ናቸው፤ እነዚኽ ክስተቶች ያልረከሰችው ነውር ነቀፋ ፈጽሞ የሌላት የአምላካችን የክርስቶስ እናት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት የነገርኋችኍ ናቸው፡፡ ትክክለኛው ዳኛ በሕያዋን እና በሙታን ላይ የሚፈርደው እግዚአብሔር በእነዚኽ ቃላት ላይ ምንም እንዳልቀነስኊ ወይም እንዳልጨመርኊ ምስክሬ ነው፡፡ የኹላችን እመቤት ቅድስቲቱ የእግዚአብሔር እናት ማርያም ክብረ በዓሏን እስከዛሬም ድረስ የምናከብርላት በእውነት የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ የእኛ አምላክ ከኾነው ከተወደደው ልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ታማልደን፤ ለተቸገሩ ድኾች ሰዎች አምላክን በወለደች በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ምፅዋትን እንስጥ፣ በባዕድ ሀገር እንዳንሰቃይ ታማልደን፣ ጌታችን እና አምላካችን እግዚአብሔር ምሕረት እንዲሰጠን እና ይቅር እንዲለን ታማልደን፤ አርምሞ ጽርዐት በሌለው ጸሎት በመዓልትም በሌሊትም ጮኽ ብለን ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ይቅርታኽን በእኛ ላይ አኑር ከባሕርይ አባትኽ ከአብ ከአንተ ጋር በተካከለ ሕይወትንበሚሰጥ ከባሕርይ ሕይወትኽ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር ጽንዕ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን እያልን እንዘምር)፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰሙሉውን “ነገረ ማርያም በሊቃውንት ክፍል አንድ” ከሚለው መጽሐፍ አንብቡ::
ጌታችን ሆይ የእናትኽን በረከት አሳድርብን አሜን፡፡
0 comments:
Post a Comment