• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday, 10 February 2016

    ማኅበረ ቅዱሳንን የወለደው፥“እኔ ለቤተ ክርስቲያኔ ምን ማድረግ እችላለኹ” የሚለው ሐሳብ ነው፤ይጥፋ የሚሉት የጥቅም ጋብቻ የፈጸሙ አማሳኞችና የተሐድሶ መናፍቃን ናቸው /ሰብሳቢው/


    ሐራ ዘተዋሕዶ

    ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ

    በማኅበሩ የመጀመሪያው ደንብ ፥ የማኅበሩ ወሰን በሚለው፣ ‹‹ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም›› የሚል ነበረበት፤ ነገር ግን በ1994 ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ተመልክቶ፣ የማኅበሩ በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ አለመግባት ትክክል ነው፤ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳይ ጣልቃ አንገባም ማለት ግን፣ እኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ናችሁ ብለን እያጸደቀን ስንፈልጋችሁ እምቢ ልትሉን ነው ወይ? ስለዚህ ይህ “ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም” የሚለው ንኡስ አንቀጽ መውጣት አለበት አሉን፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ነው መተዳደሪያ ደንቡን፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይበጃል ባሉት መንገድ አሻሽለው ኹሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፈርመውበት ያጸደቁት፡፡ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ቀኖና የመከተል ግዴታ አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያን የበላይ ውሳኔ ሰጭ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ፥ አይ ይበቃል፤ የማኅበሩ አገልግሎት አያስፈልገኝም ካለ ሊዘጋው ይችላል፡፡ አገልግሎት የምንሰጠው ቤተ ክርስቲያናችንን ለመደገፍ ነው፡፡ ስለዚኽ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስነው ነው ተፈጻሚ ሊኾን የሚችለው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔም የማክበር ሓላፊነት አለብን፤ ነገር ግን ፓትርያርኩ ብቻቸውን ማኅበረ ቅዱሳንን ሊዘጉት አይችሉም፡፡የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸውና ከቀዬአቸው ርቀው ወደ ተመደቡበት ግቢ ሲሔዱ፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቶችና ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር የማገናኘት ሥራ እንሠራለን፤ ለተማሪዎቹም አመች ጊዜና ቦታ በማስተካከል ትምህርት እንዲሰጥ እናደርጋለን፡፡ ይህ ጠንካራ መሠረት ይዞና እንደ ባህልም ኾኖ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉበት ቦታ ሁሉ ግቢ ጉባኤያትመኖራቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡የተማረው ኅብረተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እየተማረና ቤተ ክርስቲያንንም በተሻለ ኹኔታ እያወቃት ነው፡፡ ይህም ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች የነበረ ቢኾንም፣ የተማረው ኅብረተሰብለቤተ ክርስቲያን በበጎ ፈቃድ የማገልገል ልምዱ እምብዛም ነበር፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ቤተ ክርስቲያንን በበጎ ፈቃድ እንዲያገለግልማኅበረ ቅዱሳን አርኣያ ኾኖታል ብለን እናምናለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የአገልግሎት ዘርፎች አሏት፤ አገልግሎቷንም በትሩፋት ለመደገፍ ብዙ ማኅበራት ያስፈልጓታል፡፡ማኅበረ ቅዱሳን አንድ ማኅበር ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ከሚያስፈልገው አንድ ሺሕኛውን እንኳ አገልግሎት ሰጥቷል ብለን አናምንም፡፡ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉም የሚበልጡም ብዙ የፈቃድ ማኅበራት ለቤተ ክርስቲያናችን ያስፈልጓታል፡፡ እርግጥ በአገር ውስጥም ኾነ በውጭም አገር ያሉ በርካታ ማኅበራት የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት በተለያየ መንገድ ያግዛሉ፡፡ በተለይ የገዳማትንና የአድባራትን የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ከበርካታ ማኅበራት ጋር አብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ አወቃቀር እንዲሠራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መርጠው ያቀረቧቸውና ቅዱስነታቸው መመሪያ የሰጧቸው የኮሚቴ አባላት ወደ ጥናት ሥራው እንዲገቡ ሲደረግ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የኾኑም በማኅበሩ ተወክለው ባይኾንም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው አባል ኾነው ገብተዋል፤ ጥናቱንም በሚገባ አጥንተው አቅርበዋል፤ ጥናቱም የቅዱስ ሲኖዶስ እንጅ የማኅበረ ቅዱሳን አይደለም፤ የቀረበውም ለቅዱስነታቸው ነው፤ ባለሞያዎቹም መመሪያ የተቀበሉት ከቅዱስነታቸው ነው፡፡ የጥናቱ ትግበራ፣ የግል ጥቅማችንን ይነካብናል ያሉ ጥቂት አለቆች ተቃውሞ አሥነሱ፡፡ ከባለሞያዎቹ የማኅበሩ አባላት መኖራቸው እንደ ጥፋት ተቆጥሮ በቀጥታ ክሣቸውን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ አቀረቡ፡፡ ለጥናቱ መተግበር በይፋ ሲሰጥ የነበረውን የኅብረተሰቡን ድጋፍም አፍነው ለመሔድ ሞከሩ፡፡ ቅዱስታቸውም በመጀመሪያ የነበረው አቋማቸው ተሸርሽሮ የእነዚኽ አካላት ደጋፊ እየኾኑ መጡ፡፡ ለእኛ ግን፣ችግራችኹ ይህ ነው ብለው በቀጥታ ሊነግሩን ወይም በችግሩ ዙሪያ ሊያወያዩን አልፈለጉም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ደጋፊዎቿ አባላቷ ብቻ ናቸው፤ ጥንካሬዋ በሊቃውንቷ የእምነት ጽናት ላይ፣ በምእመናኗ መተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ግን ሰርገው በሚገቡ አካላት እየተቦረቦረ ነው፡፡ የተሐድሶ መናፍቃኑ እንቅስቃሴ ሲያዩት ቀላል ይመስላል እንጂ በብዙ አጥቢያዎቻችን ብጥብጥና መከፋፈል እንዲፈጠር ምክንያት እየኾኑ ነው፡፡ መረጋጋት በቤተ ክርስቲያን እንዳይኖር ተግተው እየሠሩ ነው፡፡ የሥነ ምግባር አለመኖር ኃጢአት እንዳልኾነ የሚያሳይ ልዩ ትምህርት እያስተማሩም ነው፡፡ አንድ ጊዜ በሠራኸው ሥራ ጸድቀሃል በማለት ሰዎች ጥፋትን እንዲለማመዱ ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡ በዚኽም በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የፈለጋቸውን ለሚያደርጉ ጥቅመኞች ሽፋን እየሰጡ ነው፡፡ የሃይማኖት ችግርና የምግባር ችግር ያለባቸው አካላት ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ከባድ ፈተና ነው፤ ለአገልግሎቷም ትልቅ ዕንቅፋት ፈጥሯል፡፡ በካህናቷ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ካህናቱ ተበደልን ብለው የሚጠይቁት እነዚኽኑ በጥቅም የተሳሰሩትን ሰዎች ነው፡፡ ከሥራችን ያባርሩናል ብለው ስለሚሰጉ፣ ደግሞም እያባረሯቸው ስለኾነ ካህናቱ ድምፃቸውን አጥፍተው በስጋት ነው የሚኖሩት፡፡ ይህ እየኾነ በሔደ ቁጥር ምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው እየተቆረቆሩ መጥተዋል፡፡ የምእመናን ቁጣ ሌላ አለመረጋጋትና ችግር ፈጥሮ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሔድ የሚመለከተው አካል ኹሉ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡

    *          *           *

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ፣ በአዲስ አበባ ከሚታተመው የቀለም ቀንድ ሳምንታዊ ጋዜጣ ጋር በማኅበሩ አገልግሎት፤ በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ቃለ ምልልስ አድርገዋል፤ እንደሚከተለው ተስተናግዷል፡፡


    (የቀለም ቀንድ፤ ቅፅ ፫ ቁጥር ፳፰፤ ማክሰኞ፤ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

    ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት በጋዜጣ ደረጃ መዘርዝር ከባድ እንደ ኾነ ይገባናል፡፡ እስኪ ዝርዝር ጉዳዮችን ለጊዜው እናቆያቸውና፣ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን በማገልገል በኩል ሠራቸው የሚባሉትን አንኳር ተግባራት ጠቅለል ባለ መልኩ ይግልጹልን?


    በመጀመሪያ ልትጠይቁን በመምጣታችሁ አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ሊቋቋም የቻለው፣ መጀመሪያ የተለያዩ አካላት በየአካባቢው ቤተ ክርስቲያንን ሲወቅሱ እንሰማ ነበር፡፡ እኛም በቤተ ክርስቲያናችን የምናያቸውና አንዳንዴ እንዲህ ባይኾኑ ኖሮ የምንላቸው ነገሮች አሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እንዲህ ቢደረጉ ብለን የምንመኛቸው ነገሮችም ነበሩ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እነዚህን ነገሮች ማን ነው የሚሠራቸው ሲባል ኹሉንም ጠቅልሎ ቤተ ክህነቱ ብቻ ይሥራቸው ብሎ ማሰብ ተገቢ ስላልኾነ ቤተ ክርስቲያን የኹላችንም በመኾኗ ማድረግ የሚገባን ምንድን ነው? ብለን አስበን እነ እገሌ ለምን ያን አይሠሩም ከምንል ለምን እኛስ አንሠራም? እንዴትስ ነው የምንሠራው? የሚል መነሻ ነው ማኅበረ ቅዱሳንን እንዲወለድ ያደረገው፤ አስተሳሰቡንም ጨምሮ “እኔ ለቤተ ክርስቲያኔ ምን ማድረግ እችላለሁ፤” የሚለው ነው፡፡

    ምን ማድረግ እንችላለን ብለን ስናስብ፣ በጊዜው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ስለነበርን የሰንበት ትምህርት ቤቶች እኛ ፈልገናቸው ካልሔድን በስተቀር ቀጥታ እኛን የሚደርሱበት ዕድል አልነበረም፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ለማግኘት እኛ መፈለግ ነበረብን፡፡ በሌላ መልኩ ግን የሌሎች እምነት ተቋማትን ስናይ ግን እዚያው ቀጥታ ከአካባቢው የእምነት ተከታዮቻቸው ጋር የሚገናኙበት ኹኔታ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ቁጭቶች ናቸው ማኅበረ ቅዱሳን እንዲጀመር ያደረገው፡፡

    ስለዚህ በመጀመሪያው ጊዜ እንደነበረው፣ዓላማችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያውቁ፤ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንዲረዱ ማስቻል ከዚያም ባለፈ ካወቁ በኋላ ራሳቸው በሕይወታቸው እንዲወስኑ ማድረግ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ስለ ቤተ ክርስቲያን ሳያውቁ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚተቹ ዐውቀው እንዲወስኑ ማስቻል ነው፡፡

    ብዙዎቹ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸውና ከቀዬአቸው ርቀው ወደ ተመደቡበት የትምህርት ቦታ/ግቢ ሲሔዱ፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቶችና ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር የማገናኘት ሥራ እንሠራለን፤ ለተማሪዎቹም አመች ጊዜና ቦታ በማስተካከል ትምህርት እንዲሰጥ እናደርጋለን፡፡አኹን አኹን ግን ይህ ጠንካራ መሠረት ይዞና እንደ ባህልም ኾኖ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉበት ቦታ ሁሉ ግቢ ጉባኤ መኖሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የተማረው ኅብረተሰብ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጣ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህም ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡

    ኹለተኛው ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው፡፡ ይህ የብዙዎችን ድጋፍ የሚጠይቅ፣ ሁሉም በያለበት ሊሠራው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ አንድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የተቋቋመ የስብከተ ወንጌል መምሪያ፣ አልያም በአጥቢያ ያለ አንድ የስብከተ ወንጌል ክፍል ብቻ የሚፈጽመው አገልግሎት አይደለም፡፡ ኹሉም የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ተደጋግፈው የሚሠሩት ሥራ ነውና ከዚህ አንጻር ማኅበሩም በተለያዩ ቦታዎች የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲዳረስ አድርጓል፤ እያደረገም ነው፡፡

    ለምሳሌ ብዙዎች የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎቻችን በሚመደቡበት የገጠር አጥቢያ ሒደው በሚችሉት ኹሉ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በብዙ ቦታዎች እንኳን ሰባኬ ወንጌል ማግኘት ቀርቶ የሚቀድስ ካህን እንኳን ማግኘት የተቸገሩ አጥቢያዎች ብዙ ነበሩ፤ አሁንም ወደ ገጠሩ ክፍል እንዲኹ ዓይነት ችግር ያለባቸው ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከየግቢ ጉባኤያቱ የተመረቁ ወጣቶች የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱና ሰባካ ጉባኤ እንዲመሠረት አድርገው በራሳቸው ገንዘብ ካህን ቀጥረው የአካባቢው ምእመን አገልግሎት እንዲያገኝ ያስቻሉባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አካል ነው፡፡

    ቀደም ሲል በየገጠሩ ባሉ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምር መምህርና የማስተማሪያ መሣሪያ እጥረት ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ችግሩን ለመፍታት ከየግቢ ጉባኤው ተመርቀው ወደ የሰንበት ት/ቤቶቹ ሲሔዱ ለማስተማር የሚረዳቸውና የዘመኑ ሰው ለሚጠይቃቸው ጥያቄ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ጽሑፎችን በማባዛት ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች መላክ ጀመርን፡፡ ይህን ለምን ወደ መጽሔት እና ጋዜጣ አናሳድገውምበማለት የሐመር መጽሔት እና የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ኅትመቶችን ማሳተም ጀመርን፡፡ ከዚያም አልፈን ዘመናዊውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን በድምፅ እና በምስል ስብከተ ወንጌል እና መዝሙር እያዘጋጀን እናሰራጫለን፡፡ በድረ ገጾችም የተለያዩ ትምህርቶች ይለቃቃሉ፡፡ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችንም ጀምረን ነበር፤ ወደፊትም እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንቀጥልበታለን፡፡

    ከዚኽ በተጨማሪም በጠረፍ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችን እያስተማርን ራሳቸውን እንዲደግፉ እያስቻልን ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነት አካባቢዎች ፈቃደኛ የኾኑ ወጣቶችን መሠረታዊ በኾኑ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ላይ ሥልጠና እየሰጠን በአካባቢያቸው፣ በባህላቸውና በቋንቋቸው ሒደው እንዲያስተምሩና ስብከተ ወንጌልን እንዲያስፋፉ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ኢአማንያን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ተጨምረዋል፡፡

    የተማረው ኅብረተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እየተማረና ቤተ ክርስቲያንንም በተሻለ ኹኔታ እያወቃት ነው ያለው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በስብከተ ወንጌል በኩል እየተሠራ ያለው ነው፡፡

    ሌላው የቤተ ክርስቲያናችን ገዳማት የነበሩበትን ኹኔታ ለመቃኘት የዳሰሳ ጥናት ስናካሒድ ያወቅነው፣ አብዛኛዎቹ ገዳማት ራሳቸውን ችለው የሚኖሩበት ገቢ እንደሌላቸው ነው፡፡ ጥናቱ በተዘጋጀበት ወቅት፣ አብዛኛዎቹ ጥንታውያንና ከእይታ ራቅ ብለው የተገደሙ ገዳማት ውስጥእንዲሁ ከዚኹ እንሙት ያሉ ታላላቅ አባቶች ብቻ የቀሩባቸው ነበሩ፡፡ ለእነርሱም ቢኾን ጾም ውለው በሰዓት እንኳ የሚመገቡት ማግኘት አዳጋች ነበር፡፡ ብዙ ምእመናን ለገዳማት ርዳታ ቢሰጡም የሚሰጡት ግን መረጃው ላላቸው ገዳማት ወይም ችግራቸውን ለሰሙት ቦታ ብቻ ነበር፡፡ ችግሩ፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚጥቅሙ ብዙ መናንያን ያሉባቸው ቦታዎች እየከሰሙ እንዲሔዱ የሚያደርግ በመኾኑ አሳሰበን፤ ከዚህም አንጻር የተለየ መርሐ ግብር መንደፍ ነበረብን፡፡

    ብዙ ጊዜ በእኛ አገር ልማት ሲባል በበለጸጉ ሀገሮች ያሉ አካላትን ጠይቆ መሥራት ነው የተለመደው፡፡ እኛ ግን በራሳችን ምእመናን ዐቅምና አስተዋፅኦ ላይ ተመሥርተን መሥራትን ነው የመረጥነው፡፡ ርግጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ የአገልግሎት ዘርፍ ኾኖ የተቋቋመው የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አለ፤ ይህ ኮሚሽን አብዛኛውን ገንዘቡን የሚያገኘው ከውጭ በጎ አድራጊዎች ከሚላክ ገንዘብ ነው፡፡ የውጭ ረጅዎች ደግሞ ለአጠቃላይ ማኅበረሰባዊ ጥቅም የሚውል እንጅ ለገዳማት ብቻ ተብሎ የሚሠራ ሥራን ለመርዳት ይውል ዘንድ ብዙም አይፈቅዱም፡፡ በመኾኑም ለገዳማቱና ለአድባራቱ በኮሚሽኑ በኩል የሚደረጉ የልማት ሥራዎች ቢኖሩም ችግሩን ለመፍታት ግን በቂ አልነበሩም፡፡

    በዚኽ ምክንያት በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ ምእመናን በጋራ በመተባበር ገዳማቱ ራሳቸውን እንዲችሉና በውጤታቸውም ምርታማ እንዲኾኑ መሬት ያላቸው መሬታቸውን አርሰው እህልና ፍራፍሬ እንዲያመርቱ፣ ወይም ንብ እንዲያንቡ፣ አልያም ከብት እንዲያደልቡ፤ የመሬት እጥረት ላለባቸው ደግሞ የእህል ወፍጮ እንዲኖራቸው  እንዲሁም የሽመናና የጥልፍ ሥራዎችን እንዲሠሩ የማመቻቸት ለአንዳንዶቹም የከተማ ቦታ ላላቸው የሚከራይ ቤት ተሠርቶላቸው እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነደፍን፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳንላለፉት ዐሥራ ስምንት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡

    የአብነት ትምህርት ቤቶችን ስንመለከት ደግሞ፤ቀደም ባለው ጊዜ ለአብነት ተማሪዎች በነዋሪው ኅብረተሰብ የትምህርት ዕድል (Scholarship) እየተሰጠ ነው ሲማሩ የነበሩት፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት በምዕራባውያኑም ይደረግ እንደነበረው ኹሉ የትምህርት ድጋፍ ይሰጥ የነበረው ለተማሪዎችም ለመምህራንም ሲኾን ኅብረተሰቡ የእህል መዋጮ እያደረገ ኹሉንም ያኖር ነበር፡፡ ተማሪዎቹ እህሉን አስፈጭተውና አብስለው መመገቡ አስቸጋሪ ስለሚኾንባቸው የበሰለ እህል እየተሰጣቸው ነው ሲማሩ የነበሩት፡፡ ተማሪዎቹ በተመደቡበት ሠፈር በመሔድ በእንተ ስማ ለማርያም ብለው ይጠይቃሉ፤ ባለቤቶቹም ወላጆች ባይኖሩ እንኳ ቀሪዎቹ የቤተሰቡ አካላት ተማሪ ሲመጣ ስጡ ስለሚባሉ ለተማሪዎቹ ምግቡ ይሰጣል፡፡

    በዚያ መልኩ ትምህርቱ ሲከናወን ቢቆይም አኹን ግን ዘመናችን እየተቀየረ በመምጣቱ፤ ከአንዳንድ አካባቢዎችም ሕዝቡ በተፈጥሮ አደጋዎች እና በሰፈራ ምክንያት አካባቢውን ሲለቅ የገንዘብ አቅማቸው የተሻለ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችም በአብዛኛው ወደ ከተማ እየገቡ ሲመጡ፣ ትምህርት ቤቶቹ ግን እዚያው ቀደም ሲል የነበሩበት አካባቢ ቀሩ፡፡ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያለው ኅብረተሰብም ትምህርት ቤቶችን ለመርዳት ያለው አቅም እየተዳከመ መጣ፡፡ በተቀሩት የሀገራችን ክፍሎች ደግሞ የነበሩት ትምህርት ቤቶች እየከሰሙ ካህን ለማገኘት እንኳ አስቸጋሪ ኹኔታ እየተፈጠረ መጣ፡፡

    ይህ ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን ስጋት በመኾኑና በሀገር ደረጃም ቢኾን ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ማሸጋገሪያና ማበልጸጊያ የኾኑት እነዚሁ የትምህርት ማዕከላት ስለነበሩ“የባህል ትምህርቶች ናቸው” ብለን ሳንተዋቸው የትምህርቱንም ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ነገር መሥራት ግዴታችን ነበር፡፡ ስለዚኽ ኹለት ነገሮችን መሥራት ነበረብን፡፡

    አንደኛው፡- በሰሜን በኩል ያሉና ብዙ ደቀ መዛሙርት ሲያፈሩ የኖሩ ትምህርት ቤቶች መምህራን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ወይም ከሀገረ ስብከታቸው የምትመደብላቸው በጣም አነስተኛ መደጎሚያ ነበረች፡፡ እኛ ጥናቱን ስናካሒድ እንዲያውም በወር 50 ብር ብቻ የሚሰጣቸው መምህራን ነበሩ፡፡ 50 ብር ለቤተሰብ ማስተዳደሪያ፣ ለልብስ፣ ለቀለብና ለማናቸውንም ወጪ መሸፍኛ ኾና ኑሮን ለመግፋት በፍጹም አታስችልም፡፡ ስለኾነም መምህራኑ የሚኖሩት ተማሪዎች ለልመና ወጥተው በሚያመጡት ነገር ተደጉመው ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን የኑሮ ኹኔታ ለማሻሻል ለመምህራን መጠነኛ ድጎማ ማድረግ እንዲኹም ለተማሪዎች ለምግባቸውና ለልብሳቸው የሚኾነውን መደጎም የእኛ ድርሻ ነው ብለን ስላሰብን ፕሮጀክት ነድፈን ለኅብረተሰቡ አስተዋወቅን፡፡ ኅብረተሰቡም ደስተኛ ኾኖ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንደገና እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡

    ኹለተኛው፥ በምሥራቅ፣ በምዕራብና በደቡብ የአገራችን ክፍል ክፍሎች ስንሄድ ግን፤ እምብዛም ያልነበረ ተቋምን እንደገና መመሥረት ይጠበቅብን ነበር፡፡ ስለዚህ በእንተ ስማ ለማርያም ብሎ መጠየቅ ኹሉ የተለመደ ስላልኾነ ለመምህራንም ለተማሪዎችም መኖሪያ እና መማሪያ የሚኾኑ ግንባታዎችን መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ ምግብ ከዚያው መሠራት አለበት፤ መምህራንም በአዲስ ተቀጥረው መሔድ ነበረባቸው፡፡ ከየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳትና ሓላፊዎች ጋር በመነጋገርና አብረን በመሥራት አዲስ የአብነት ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ የአካባቢው ወጣቶች በቅርባቸው ባለ አጥቢያ የአብነት ትምህርት ቤት በመማር የቤተ ክርስቲያናቸውን አገልግሎት በብቃት እንዲረከቡ ለማድረግ በሞከርነው አነስተኛ ጥረት ትልቅ ፍሬ እያየንበት ነው፡፡

    ከዚኽ ኹሉ በተጨማሪ፣ ምንም እንኳ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች የነበረ ቢኾንም፣ ለቤተ ክርስቲያን የተማረው ኅብረተሰብ በበጎ ፈቃድ የማገልገል ልምዱ እምብዛም ነበር፡፡ማኅበረ ቅዱሳን ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ቤተ ክርስቲያንን በበጎ ፈቃድ እንዲያገለግል አርኣያ ኾኖታል ብለን እናምናለን፡፡ ለአንዳንዶችም ማኅበሩ የበጎ ፈቃደኛ አገልግሎትን በማስተዋወቅ አርኣያ ኾኗል ብለን እናምናለን፡፡

    በአጠቃላይ የተማረው ኅብረተሰብ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያገለግል፣ የአብነት ትምህርት የመማር ፍላጎት እንዲያዳብር፣ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጎለብቱ፣ አጥቢያዎች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ስብከተ ወንጌል በኹሉም እንዲስፋፋ ለማስቻል በአቅማችን የምንችለውን እያደረግን ነው፡፡

    እንግዲህ ይህን ኹሉ ሥራ ስንሠራ፣ ማኅበሩ ምን ያህል ኣባላት አሉት? ለተባለው፣ ባለፉት 23 ዓመታት አገልግሎታችንን ስናከናውን በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ስንት ናቸው ብሎ ማስላት ነው? ነው፡፡ በዚኽ ዓመት ብቻ በግቢ ጉባኤ በመማር ላይ ያሉ ወደ 250 ሺሕ ተማሪዎች አሉ፡፡ በርግጥ ከተመረቁት ውስጥ ኹሉም ወደ አገልግሎቱ አልመጡም፡፡ አንዳንዶቹ የማኅበሩን የአባልነት ፎርም ባይሞሉም በአገልግሎት ግን ደጋፊዎች ናቸው፡፡ በማኅበሩ በቀጥታ በመዝገብ የያዝናቸውና በአገልግሎት የሚሠማሩ ከ500 ሺሕ በላይ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን የማኅበሩ አባላት እነዚኽ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አኹን ቁጥራቸውን ይህን ያክል ነው ብሎ ለመናገር ቢያዳግትም የአገልግሎታችን ደጋፊዎቻችን እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

    ማኅበሩ በመጀመሪያዎቹ ዘመናቱ የነበረው እንቅስቃሴው በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ብዙ ወጣቶች በግቢ ጉባኤ አማካይነት የማኅበሩ አባላት እየኾኑ ራሳቸውን ማነፅና በኅብረተሰቡ ዘንድ ሳይቀር በዕውቀታቸውና በምግባራቸው የተመሰገኑ መኾን የቻሉ ቢኾንም፣ ቀጣይነት ያለው አይመስልም፡፡ አኹንም ጎልተው የሚታዩት የመጀመሪያው ትውልድ ሊባሉ የሚችሉት አባላት ይመስላሉ፡፡ ማኅበሩ ዕድገቱ ተገትቷል፤ ባለበት እየረገጠ ነው ወይስ እያደገ ነው?


    ይኽን ጉዳይ ለማዬት በጨለማ ውስጥ መጀመሪያ አንድ ሻማ ለመለኮስ ክብሪት ስትጭር የምታየው የብርሃን መጠንና ሻማውን ከለኮስከው በኋላ ያለው የመብራቱ የድምቀት መጠን አንድ አይደለም፤ የመጀመሪያው፣ ብርሃን ካልነበረበት ኹኔታ መውጣት ስለነበር ትንሹም ደምቆ ይታያል፤ ቆይቶ ግን ያን ስንለምደው የደበዘዘ ይመስለናል፡፡ ለእኔ ይህ ጥያቄ ከዚኽ ኹኔታ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡

    መጀመሪያ ጊዜ ማንም በሌለበት የተሰባሰቡትን ሰዎች ኹሉም ሰው እንደ አዲስ ያያቸዋል፤ ኹሉም ክብር ይሰጣቸዋል፤ የተለየ አድርጎም ይገምታቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ያሉትን በተጫረው ብርሃን ምክንያት የመጣ ስለኾነ አዲስም ስላይደለ ይለመዳል፡፡ የአባላቱም መጠን ስለሚጨምር ለይቶ እገሌ ለማለት አይቻል ይኾናል እንጅ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎትም፣ ሰው የማፍራት ሒደቱም እንደቀጠለ ነው፡፡ በቁጥር ብናየው እንኳ አባላቱ እጅግ እየጨመሩ እንጅ እየቀነሱ አልመጡም፡፡ እንዲያውም ለማኅበራችን ፈታኝ የነበረው የመጀመሪያዎቹ የምሥረታ ጊዜያችን ላይ የነበሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥርና ተማሪዎች ትንሽ ነበሩ፤ በኋላ ግን የተማሪዎችም፣ የትምህርት ተቋማቱም ሥርጭትና ብዛት በአንድ ጊዜ ሲመነደግ ኹሉንም ቦታ የመድረስ ሓላፊነት የማኅበረ ቅዱሳንነበር፡፡ ስለዚኽ በአንድ ጊዜ ሲመነደግ ቁጥሩና ሥርጭቱ ሲያድግ ማኅበራችንም በዚያው ልክ ዐቅሙንም ማሳደግ ነበረበት፡፡

    ማኅበሩ ያለው የሰው ኃይልና ሀብት በዚኽ ልክ ዕድገት ስላልነበረው እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ የግቢ ጉባኤያቱንና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን የማስተሳሰር ሥራውን የሠሩት አባሎቻችን ናቸው እንጅ ሌላ ከየትም የመጣ አካል አይደለም፡፡ አኹን በአንድ ግቢ ጉባኤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ50 እስከ 100 መርሐ ግብር አለ፤ በአጠቃላይ ወደ 390 የሚጠጉ የግቢ ጉባኤያት አሉ፡፡ እንግዲህ አባሎቻችን ይህን ኹሉ መሸፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ የማኅበሩ አባላትና አገልግሎት ምን ያህል እንደጨመረ ያሳያል፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንቀጣይት ያለው ሥራ እያከናወነ ነው፡፡

    ምናልባት መጀመሪያ የነበሩት አባላት አገልግሎት በእይታ ደረጃ አኹን ያሉትን አባላት አገልግሎት ወጥቶ እንዳይታይ ሸፈነው ካላልን በስተቀር አገልግሎታችን እየሰፋ እንደኾነ በርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የማኅበሩ አገልግሎት ዘርፍም እንዲኹ ሰፍቷል፡፡ ለዚህ ለሰፋው አገልግሎቱ ደግሞ ብዙ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ስብከተ ወንጌልን ለመፈጸም በሚቻላቸው ሁሉ ገጠር እየገቡ ያገለግላሉ፡፡ በሞያቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉት አባሎቻችን ኹሉ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱም ሰፍቷል፤ ዕድገቱም አልተገታም፡፡

    ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ከእርሱ ውጪ ሌሎች ማኅበራትና ስብስቦች እንዳይገቡ ይከላከላል፤ የሌሎችን ማኅበራት መኖር አይደግፍም የሚል አስተያየት አለ፡፡ አስተያየቱ በእናንተ በኩል እንዴት ይታያል?


    እውነት ለመናገር ይህ ትክክለኛ መረጃ ነው ብለን አናምንም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አንድ ማኅበር ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ከሚያስፈልገው አንድ ሺሕኛውን እንኳ አገልግሎት ሰጥቷል ብለን አናምንም፡፡ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉም የሚበልጡም ብዙ የፈቃድ ማኅበራት ለቤተ ክርስቲያናችን ያስፈልጓታል፡፡እርግጥ ነው ካህናቱም በፈቃድ ነው ሲያገለግሏት የኖሩት፤ ግን በማኅበር ደረጃ ተደራጅቶ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራት ቁጥር ውስን ነበሩ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ሕግና ደንብ ወጥቶለት በቅዱስ ሲኖዶስም ተፈቅዶለት ተቋቁሟል፡፡ ሌሎችም ማኅበራት የእኛን አርኣያ እንዲከተሉ እንፈልጋለን፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚወቅሱ አካላት ለምን ማኅበረ ቅዱሳን ያልሠራውን ክፍተት ሞልተው አያሳዩንም? ማኅበረ ቅዱሳን የሚያስፈልጓትን ለማሟላትና ክፍተቶች ካሉ ለቤተ ክርስቲያናችን አካላት እገዛ ለማድረግ ኹልጊዜ ይጥራል፤ የሚቻለውንም ያደርጋል፤ ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበር እንዲያደራጃቸው፣ ገንዘብና ለአገልግሎት የሚኾን ቦታም እንዲሰጣቸው የሚሹ አንዳንድ ሰዎች ያሉ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ለማድረግ ማኅበሩ ሓላፊነትም ኾነ ዐቅም የለውም፡፡ ይህን ለማድረግ አለመቻላችን ግን አለመደገፍ ተደርጎ ሲወሰድ እንሰማለን፤ ይኼ ያሳዝነናል፡፡

    ኹለተኛው፡- በማኅበራት ስም ተደራጅቶና የቤተ ክርስቲያን አካል መስሎ የሚፈልጉትን የቅሰጣ ሥራ ለመሥራት እንዲያመቻቸው ተሐድሶዎቹ የጀመሩት አንዱ ስልታቸው ነበር፡፡ በመኾኑም ማኅበር መሥርተው ብዙ የሔዱ እንዲህ ያሉ ወገኖች መኖራቸውን ባለን መረጃ መሠረት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ማሳወቃችን እንደ አሉታዊ ኹኔታ ተቆጥሮ ተሐድሶዎቹ ያስወሩትን ሌሎች ወገኖችም በማስተጋባት አሉታዊ ምስል ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ መጀመሪያ ያስወሩት ተሐድሶዎቹ ናቸው፡፡

    በዚህም ምክንያት “ማኅበሩ የሌሎች ማኅበራትን መመስረትም ሆነ ማደግ አይፈልግም”  እየተባለ ትክክል ባልኾነ መልኩ መወራት ጀመረ፡፡ ይህ በእውነቱ ያሳዝነኛል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን የቤተ ክርስቲያናችንን ሕግና ደንብ ተከትለው ከተቋቋሙ ማኅበራት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የዐቅማችንንም ያኸል ለመደገፍ ኹልጊዜም ዝግጁ ነን፤ እንዲያውም ለምንድን ነው የተለያዩ ማኅበራት ቢኖሩም ለአንድ ዓላማ እስከተቋቋምን ድረስ የጋራ የውይይት መድረክ የማይኖረን እያልን እንጠይቃለን፡፡

    በ1980ዎቹ በበጎ ፈቃድ ተነሣሥተው የተጀመሩ ብዙ የኅትመት ውጤቶች ነበሩ፡፡ በጣም ጥሩ ነበሩ፡፡ እነዚያ ጥረቶች ግን በጥቂት ሰዎች ድካም ላይ የተመሠረቱ ስለነበሩ ሰዎቹ የሚችሉትን አደረጉ፤ የሚያግዛቸው በቂ ሰው ባለመኖሩ አገልግሎታቸው እየከሰመ ሔደ፤ ኋላም ቆመ፡፡ ለረጅም ጊዜ መዝለቅ የቻለው የጽርሐ ጽዮን አንድነት የኑሮ ማኅበር ነው፡፡ እነርሱም አሁን ድረስ መለከት መጽሔትንና የተለያዩ በራሪ ጽሑፎችን በማሳተም፣ ከየጠረፉ የሚመጡትን ወጣቶች ለማሠልጠን የሚያስችልየስብከተ ወንጌል ማሠልጠኛ ማእከል በመክፈትና ሥልጠናውንም ለተከታታይ ዓመታት በማከናወንለቤተ ክርስቲያን በርካታ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፤ እኛም ከእነርሱ ጋር በጋራ በመተጋገዝ እንሠራለን፡፡

    ቤተ ክርስቲያን በርካታ የአገልግሎት ዘርፎች አሏት፤ አገልግሎቷንም በትሩፋት ለመደገፍ ብዙ ማኅበራትም ያስፈልጓታል፡፡ እርግጥ በአገር ውስጥም ኾነ በውጭም አገር ያሉ በርካታ ማኅበራት የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት በተለያየ መንገድ ያግዛሉ፡፡ በተለይ የገዳማትንና የአድባራትን የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ከበርካታ ማኅበራት ጋር አብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡

    ማኅበሩ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር የሠመረ ግንኙነት የለውም ይባላል፡፡ ምክንያቱ ምን ይኾን?


    ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የተደራጀ የበጎ ፈቃድ ማኅበር ነው፡፡ ፈቃድም የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን መነሻው የማኅበሩ አባላት በፈቃዳቸው በዚህ መልክ ልናገለግል እንፈልጋለን ብለው መቅረባቸው ነው፡፡ አገልግሎታችን የተሻለና የሠመረ የሚኾነው በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ብንኾን ነው ብለን ስላመንን የራሳችን መተዳደሪያ የሚኾን ሕገ ደንብ አውጥተን፣ ዕወቁን ብለን የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ጠየቅን፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱም አስተዳደር በየደረጃው እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ያቀረብነውን መነሻ አይቶና መርምሮ ግንቦት 1 ቀን 1984 ዓ.ም. ዕውቅና ሰጥቶናል፡፡ ኾኖም ግን የማኅበሩ ምሥረታ ሒደት ከ1970ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ነው፡፡

    በኋላም የማኅበሩ አግልግሎት እየሰፋና እየሠመረ ሲሔድ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ1991 ዓ.ም. አይተው ሕገ ደንቡም ዳግመኛ ተሻሽሎ የበለጠ የሚያሠራ እንዲኾን ኾኖ እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተመራው ኮሚቴ አይቶ መርምሮ ይህን ጨምሩ ይህን ቀንሱ ብሎ በ1992 ዓ.ም. በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ደረጃ የጸደቀ ደንብ ተሰጠን፡፡

    በኋላም ሊቃነ ጳጳሳት ይህ የማኅበሩ አገልግሎት እኮ በየሀገረ ስብከቱ እየሰፋ ስለኾነ በአጠቃላይ ደረጃ ሊታይ ይገባዋል በማለታቸው በአምስት ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ፣ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብ መርምሮ ነው የደንቡን ማሻሻያ ያጸደቀው፡፡ ለምሳሌ ማኅበሩ ባረቀቀው የመጀመሪያው ደንብ ላይ፥ የማኅበሩ ወሰን በሚለው ውስጥ፣ ‹‹ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም››የሚል ነበረበት፤ ነገር ግን በ1994 ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ተመልክቶ፣ የማኅበሩ በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ አለመግባት ትክክል ነው፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳይ ጣልቃ አንገባም ማለት እኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ናችሁ ብለን እያጸደቀን ስንፈልጋችሁ እምቢ ልትሉን ነው ወይ? ስለዚህ ይህ “ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም” የሚለው ንኡስ አንቀጽ መውጣት አለበት አሉን፡፡

    በዚኽ ዓይነት መንገድ የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይበጃል ባሉት መንገድ አሻሽለው ኹሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፈርመውበት ነው ያጸደቁት፡፡ ርግጥ ነው እንደየትኛውም ዓለም አሠራር መጀመሪያ መነሻ የኾነውን መተዳደሪያ ደንብን አዘጋጅቶ ያቀረበው ማኅበሩ ነው፡፡ ስለዚኽ በማኅበሩ እና በቅዱስ ሲኖዶስ መካከል መቼም ቢኾን ችግር ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ኹልጊዜም እንደ ልጅነታችን የመታዘዝ ግንኙነታችን የሠመረ ነው፡፡ ፈቃዱን የሰጠን ቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ኾነ ድረስ ከዚህ በኋላም የማኅበሩ አገልግሎት አያስፈልገኝም ካለም ቅዱስ ሲኖዶስ ማኅበሩን እንዲከስም ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር የሠመረ ግንኙነት ባይኖረንማ ማኅበሩን ወዲያውኑ ሊሰርዘው ይችል ነበር፡፡

    ነገር ግን በአኹኑ ወቅት በሚያሳዝን ኹኔታ ግንኙነታችን የሠመረ ሊኾን ያልቻለው ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ነው፡፡ ቅዱስነታቸው ገና ወደ መንበሩ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ቡራኬ ለመቀበል፣ እየታዘዝን አብረናቸው ለመሥራት ዝግጁ እንደኾን አሳውቀናል፤ ጠይቀናልም፡፡ በደብዳቤም፣ በአባቶችም፣ በአካልም ሔደን ብዙ ጊዜ ጠይቀናቸዋል፡፡ ግን ጊዜ ሰጥተው ሊያናግሩን አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ምን እንደኾነ እስካኹን ሊገባን አልቻለም፡፡ በአንጻሩ ቤተ ክርስቲያን የነበረችበት የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር የከፋ በመኾኑ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለቤተ ክርስቲያን ባለድርሻ አካላት ኹላችኁም ርዱኝብለው ጥሪ ሲያቀርቡ እኛም ለመርዳት፣ ለመታዘዝ ዝግጁ እንደነበርን አሳውቀናል፡፡ ኾኖም ግን በዚያ ደረጃ ስላልተጠየቀ ማኅበሩ በቀጥታ ሠርቶ ያቀረበው ነገር አልነበረም፡፡

    ይህ በእንዲህ እያለ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ አወቃቀር እንዲሠራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መርጠው ያቀረቧቸውና ቅዱስነታቸው መመሪያ የሰጧቸው የኮሚቴ አባላት ወደ ጥናት ሥራው እንዲገቡ ሲደረግ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የኾኑ ሰዎችም በማኅበሩ ተወክለው ባይኾንም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው የኮሚቴው አባል ኾነው ገብተዋል፡፡ ጥናቱንም በሚገባ አጥንተው አቅርበዋል፡፡ ይህ ጥናትም የቅዱስ ሲኖዶስ እንጅ የማኅበረ ቅዱሳን አይደለም፤ የቀረበውም ለቅዱስነታቸው ነው፡፡ ጥናቱንም የሠሩት ባለሞያዎች መመሪያ የተቀበሉት ከቅዱስነታቸው ነው፡፡

    ነገር ግን የጥናቱ ግኝት በተለይ በአዲስ አበባ አድባራት ያሉ አንዳንድ አለቆች የግል ጥቅማችንን ይነካብናል ብለው በማሰባቸው ይመስለናል ተቃውሞ አሥነሱ፡፡ ጥናቱን ከሠሩት ባለሞያዎች መካከል የማኅበሩ አባላት መኖራቸው እንደ ጥፋት ተቆጥሮ በቀጥታ ክሣቸውን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ አቀረቡ፡፡ ለጥናቱ መተግበር በይፋ ሲሰጥ የነበረውን የኅብረተሰቡን ድጋፍም አፍነው ለመሔድ ሞከሩ፡፡ ቅዱስታቸውም በመጀመሪያ የነበረው አቋማቸው ተሸርሽሮ የእነዚኽ አካላት ደጋፊ እየኾኑ መጡ፡፡ ለእኛ ግን፣ ችግራችኹ ይህ ነው ብለው በቀጥታ ሊነግሩን ወይም በችግሩ ዙሪያ ሊያወያዩን አልፈለጉም፡፡

    ይህም ቢኾን እንኳ እኛ አባታችን ናቸውና ከቅዱስነታቸው ፊት ቀርበን መመሪያ ለመቀበልና ጉዳዮቻችንንም ለማስረዳት በደብዳቤ ብቻ እንኳ ለስድስት ጊዜ ያክል ጠይቀናቸዋል፤ መልስ እንኳ አልሰጡንም፡፡ በአካል እየሔድን፣ ተራ እየጠበቅን ቀጠሮ እንዲያዝልን ብዙ ሞክረናል፤ ብፁዓን አባቶችንና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትንም እንዲኹም የተለያዩ አካላትን እንደ ሽማግሌ እየላክን አቅርበው ያነጋግሩን ዘንድ አስጠይቀናል፤ ግን ሊያገኙን አልፈለጉም፡፡ 

    በአዲስ አበባ አንዳንድ አለቆች እንዲሁም ከነዚህ ላይ ተጨምሮ በተሐድሶ ኑፋቄ ተከታይነታቸው የሚጠረጠሩ አንዳንድ ግለሰቦች በሚሰጧቸው መረጃ ብቻ፣ ማኅበሩ መጥፋት አለበት የሚሉት አካላትን የሚደግፉ የሚመስሉበት ጊዜ አለ፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ከቅዱስነታቸው ጋር ከዚኽ የተለየ የማያግባባ ነገር አለን ብለን አናምንም፡፡ ኹላችንም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነው የምንተጋው፤ የምንሠራውን የምናውቅ ሰዎች ነን፡፡ ያጠፋነው ጥፋት ካለ እንኳ ጠርተውን ሊጠይቁንና ሊመክሩን ይገባል ነው የምንለው፡፡ ቅዱስነታቸው፣ የቤተ ክርስቲያን ርእሰ መንበር እንደመኾናቸውና የኹሉም አባት ስለኾኑ እንዲህ ዓይነት አመራር ቢከተሉ ነው የሚሻለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋርም ኾነ ከየትኛውም የቤተ ክርስቲያን አካል ጋር ምንም ዓይነት የጎላ ችግር የለብንም፡፡

    የቅዱስነታቸውን ደብዳቤ እንዳየነው፣ ፓትርያርኩ ማኅበሩ እንዲፈርስ ይፈልጋሉ፡፡ የፓትርያርኩ ሐሳብ (ውሳኔ)ና እምነት ተፈጻሚ ቢኾን የማኅበሩ ዕጣ ፈንታ ምን ይኾናል?


    ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ቀኖና የመከተል ግዴታ አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያን የበላይ ውሳኔ ሰጭ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ፥ አይ ይበቃል፤ የማኅበረ ቅዱሳን አግልግሎት አያስፈልገኝም ካለ ሊዘጋው ይችላል፡፡ አታስፈልገኝም ካለው ማኅበሩም በግዴታ አስፈልግሃለሁ አይልም፡፡ ያሉትን ክፍተቶች በትሕትና ከማስረዳት አልፎ ለምንድን ነው የማላስፈልገው ብሎ መከራከር ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡ አገልግሎት የምንሰጠው ቤተ ክርስቲያናችንን ለመደገፍ ነው፡፡ ስለዚኽ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስነው ነው ተፈጻሚ ሊኾን የሚችለው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔም የማክበር ሓላፊነት አለብን፤ ነገር ግን፣ ፓትርያርኩ ብቻቸውን ማኅበረ ቅዱሳንን ሊዘጉት አይችሉም፡፡ ቅዱስነታቸው ቅዱስ ሲኖዶሱን በርእሰ መንበርነት የሚመሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ናቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ብቻቸውን ሊሽሩ አይችሉም፡፡

    የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ወቅት የገጠማት ፈተና ምንድን ነው? ፈተናውን ለመጋፈጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልታደርገው ይገባል የሚባለውስ ምንድን ነው?


    ቤተ ክርስቲያን የተቋቋመችው ዛሬ በኛ ዘመን አይደለም፡፡ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ሲኖዶስ አቋቁማ በራሷ ፓትርያርክ መመራት ከጀመረች ገና የአንድ ሰው ዕድሜ ያክል እንኳ ባይኾንም ብዙ ተመክሮዎች ግን አሏት፡፡ እንግዲህ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ ተቋቁሞ፣ በራሷ ፓትርያርኮች እየተመራች መሔድ ከጀመረች አጭር ጊዜ ቢኾንም በነዚህ አጭር ዓመታት ውስጥ በሀገራችን የተለያዩ ማኅበረሰብ አቀፍ ለውጦች ተካሒደዋል፡፡ መንግሥት ተቀይሯል፤ የፖለቲካ ፍልስፍና ተለዋውጧል፤ አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡ ይህ በቤተ ክርስቲያንም ላይ በበጎም ኾነ በአሉታዊ መልኩ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ 

    በነዚኽ ዓመታት ውስጥ በሊቃውንቱ እና በአባቶች ያላሰለሰ ጥረት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ብዙ ለውጥ የታየባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፥ ብዙ አህጉረ ስብከት ተቋቁመዋል፤ ደረጃቸውን የጠበቁ መንበረ ጵጵስናዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ ከሌላውም ጊዜ በተሻለ መልኩ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቁጥር በመጨመሩ በየአካባቢው ያሉ ምእመናን አገልግሎቱን በቅርብ እያገኙ መጥተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን የነገረ መለኰት ትምህርት የሚያስተምሩ መንፈሳዊ ኮሌጆች ተቋቁመዋል፡፡ በየአጥቢያው የሰበካ ጉባኤ በመቋቋሙ ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን ዐውቀው ለማገልገልና የቅርብ ተሳታፊ እንዲኾኑ ለማድረግ ተችሏል፤ በስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ዘርፍም ዕንቅፋቶች ቢያጋጥሙም የተሻለ ለውጥ ይታያል፡፡ በበጎ ጎን የሚታዩ ሌሎችም እጅግ ብዙ ለውጦች ተከናውነዋል፡፡  

    ይህም ኾኖ ግን ፈተናዎች ከውስጥም ከውጭም መምጣታቸው አልቀረም፡፡ አኹን ግን የውጩን ብቻ እያየን ከውስጣችን ያለውን ፈተና ከዘነጋን ችግሯን መቅረፍና አደጋውን መቋቋም አንችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ሊያፈርሱ የሚተጉ አካላት ውስጥ ለውስጥ ያለውን ክፍፍል ነው የሚጠቀሙት፡፡በተለይ በመካከለኛው ዘመን የካቶሊክ መልእክተኞች በጊዜው በነበረው ዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት መጥተው አገራችን ውስጥ ፈጠሩት ከሚባሉት ችግሮች መካከል የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ዋና ሥራቸው የሆነውን ስብከተ ወንጌልን ትተው እርስ በርሳቸው እንዲከራከሩና እንዲጨቃጨቁ፣ እርስ በርስም እንዳይተማመኑ ማድረግ ነበር፡፡ በዚያ መሃል ነው፣ እነርሱ ውስጥ ገብተው ነገሥታትን ጭምር በሃይማኖት መቀየር የቻሉት፤ በዚህም ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት በርካታ ምእመናን በእርስ በርስ ጦርነት እንዲያልቁ ምክንያት ኾኑ፡፡

    አኹንም ቢኾን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ዓይነት ነገር እንዲገባ ተግተው የሚሠሩና የዋሃንንም በማታለል የክፉ ተግባራቸው ሰለባ የሚያደርጉ አሉ፡፡ የቀድሞዎቹ መናፍቃን ሐሳባቸውን በይፋ ስለሚናገሩ ኹሉም ያውቃቸው፣ መከራከርም ሲያስፈልግ ሐሳቤ ይህ ነው ብለው ለመቅረብ የሚችሉ ነበሩ፡፡ በአኹኑ ዘመን ያሉትእናድሳለን ባዮች ግን እኔ ብለው በይፋ ወጥተው መናገር የማይደፍሩ፣ ሲጠየቁ እኔ አላልኩም ብለው ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለው የሚምሉ በመኾናቸው እንቅስቃሴያቸው በአብዛኛው በሰርጎ ገብ መልኩ ነው፡፡

    በተለያዩ የብዕር ስሞች በሚጽፏቸው መጻሕፍት፣ አሳታሚያቸው በውል በማይታወቁ መጽሔቶችና ጋዜጦች፣ በራሪ ጽሑፎች፣ እንዲኹም በድረ ገጾች እና የማኅበራዊ መገናኛዎች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ያብጠለጥላሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ አገልግሎት ኹሉ በእጅጉ ይነቅፋሉ፡፡ ጽሑፋቸውን ሲጽፉም ግእዝ ስለሚጠቅሱ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች መስለው አንዳንድ የዋሃንን ለማታለል ይሞክራሉ፡፡ ራሳቸውን ደብቀው ስለሚንቀሳቀሱም በሊቃውንቱም ኾነ በምእመናኑ መካከል ጥርጣሬና መለያየትን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

    ኹለተኛው፡- ቤተ ክርስቲያን የምንኖርበትን ዘመን ባገናዘበ መልኩ አደረጃጀቷ የተሻለ መኾን ነበረበት፡፡ ስሕተትን ቶሎ ማረም የሚያስችልና ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችል አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያስፈልጋታል፡፡ የአመራር ሥርዓቷ በደንብ የተሰናሰለና ለሌውም በአርኣያነት የሚጠቀስ መኾን አለበት፡፡ ይህን ስንል ግን ቀኖናዊ ሥርዓቷ ቀርቶ ዘመናዊ የአስተዳደር ዘይቤ ብቻ የምትከተል ትኹን እያልን አይደለም፡፡ የካህናት አስተዳደርና በውስጧ ያሉትን ኹሉ በሥርዓት የምታስተዳድርበት የአስተዳደር መርሕ በውስጧ አለ፡፡ የካህናት አስተዳደር፣ አባቶቻችን ከሐዋርያት ተቀብለው እስከ አኹን በትውፊት ይዘነው የነበረው ወደፊትም የሚቀጥለው የአስተዳደር ሥርዓታችን ነው፡፡ ኾኖም ግን በሐዋርያትም ዘመን ቢኾን የአስተዳደሩ ጉዳይ ዋናውን ተልእኮአቸውን እንዳያስተጓጉልባቸው አስተዳደሩን የሚያግዙ ሰዎችን ከተመሰከረላቸው አማንያን መካከል መርጠው ሾመው ነበር፤ ይኸው አጠቃላይ ሥርዓት አኹንም አለ፡፡

    በሌላ በኩል ደግሞ፣ የዘመኑን ትውልድ አሳምኖ ለመምራት የሚያስችል፣ አርቆ የሚያይና ዘመኑን የሚዋጅ ዘመናዊ አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያናችን ያስፈልጋታል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ለኹሉም ነገር ጠንቃቃ የኾነ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አስተዳደራዊ ሥርዓት ያስፈልጋት ነበር፤ ግን ገና የለንም፡፡ ሦስተኛው በፕላን የመመራት ችግርአለባት፡፡ ዘመኑ በጣም በፍጥነት የሚጓዝ ነው፡፡ የጥፋት ተልኳቸውን ለማሳካት ተፈታታኝ የኾኑ አካላት እኩል ነው እየተጉ ያሉት፡፡ ይህን መመከት የሚችል የረጅም ዘመን ዕቅድ ያስፈልጋታል፡፡ ቀድሞ ማሰብ የሚችልና ዘመናዊውን መሥመር የሚያሳይ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡

    አኹን ግን፣ በየዓመቱ በሚታቀድ፣ ከእጅ ወደ አፍ በኾነ ባልተሰናሰለ ዕቅድ እየተመራች ነው፡፡ በዚህ ላይ የእናድሳለን ባዮቹ ተጽዕኖ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ ሌሎች ተቀናቃኞቿ የውጭ ደጋፊ አካላት አሏቸው ማለት ይቻል ይኾናል፤ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ግን ደጋፊዎቿ አባላቷ ብቻ ናቸው፡፡ ጥንካሬዋ በሊቃውንቷ የእምነት ጽናት ላይ፣ በምእመናኗ መተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

    ይህም ግን ሰርገው በሚገቡ አካላት እየተቦረቦረ ነው፡፡ የተሐድሶ መናፍቃኑ እንቅስቃሴ ሲያዩት ቀላል ይመስላል እንጅ በብዙ አጥቢያዎቻችን ብጥብጥና መከፋፈል እንዲፈጠር ምክንያት እየኾኑ ነው፡፡ መረጋጋት በቤተ ክርስቲያን እንዳይኖር ተግተው እየሠሩ ነው፡፡ የጥሩ ሥነ ምግባር አለመኖር ኃጢአት እንዳልኾነ የሚያሳይ ልዩ ትምህርትእያስተማሩም ነው፡፡ አንድ ጊዜ በሠራኸው ሥራ ጸድቀሃል በማለት ሰዎች የበለጠ ጥፋትን እንዲለማመዱ የማድረግ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ በዚኽም በቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ የፈለጋቸውን ለሚያደርጉ ጥቅመኞች ሽፋን እየሰጡ ነው፡፡

    የሃይማኖት ችግር ያለባቸውና የምግባር ችግር ያለባቸው አካላት ኹለቱ የጥቅም ትስስር ያለበት ትልቅ ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ከባድ ፈተና ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ትልቅ ዕንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ ታች አግልግሎት ላይ ያሉ ካህናት ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ካህናቱ ተበደልን ብለው የሚጠይቁት እነዚኽኑ በጥቅም የተሳሰሩትን ሰዎች ነው፡፡ ይህ በመኾኑ፣ ስለኑሯቸውና ከሥራችን ያባርሩናል ብለው ስለሚሰጉ፣ ደግሞም እያባረሯቸው ስለኾነ ካህናቱ ድምፃቸውን አጥፍተው በስጋት ነው የሚኖሩት፡፡ይህ እየኾነ በሔደ ቁጥር ምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው እየተቆረቆሩ መጥተዋል፡፡ የምእመናን ቁጣ ሌላ አለመረጋጋትና ችግር ፈጥሮ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሔድ የሚመለከተው አካል ኹሉ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለን እናምናለን፡፡

    ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ፣ ለኹለት ጊዜ ያክል በዚኽ ጉዳይ ላይ በሰፊው ተወያይቶ ውሳኔ ሰጥቷል፤ ግን ውሳኔውን ማስፈጸም አልተቻለም፡፡ ያ የሚያሳየው ጥቅመኞቹ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ እንደ ኾነ ነው፡፡ ይህን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተፈጻሚ ለማድረግ ኹላችንም ሓላፊነት አለብን፡፡ እንደየድርሻችንም የቤተ ክርስቲያን አንድነት ይመጣ ዘንድና ዕድገቷ ምእመናኗን ኹሉ ለበለጠ አገልግሎት በሚያሳትፍ መልኩ ይኾን ዘንድ ልንደግፋት፤ የበኩላችንን ድርሻም ልንወጣ ይገባል፤ እላለኹ፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ማኅበረ ቅዱሳንን የወለደው፥“እኔ ለቤተ ክርስቲያኔ ምን ማድረግ እችላለኹ” የሚለው ሐሳብ ነው፤ይጥፋ የሚሉት የጥቅም ጋብቻ የፈጸሙ አማሳኞችና የተሐድሶ መናፍቃን ናቸው /ሰብሳቢው/ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top