• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday, 25 February 2016

    ፓትርያርኩ:ደንባዊ ህልውናውን የካዱት ማኅበረ ቅዱሳን፣ በስምዐ ጽድቅ ላወጣው የፀረ ተሐድሶ ኑፋቄ ጽሑፍና በደብዳቤ ለሰጣቸው ምላሽ በአምስት ቀናት ውስጥ ይቅርታ እንዲጠይቅ መመሪያ ሰጡ

    ማኅበሩ መመሪያውን በግልጽ ተቀብሎበደብዳቤ ይቅርታ ካልጠየቀና ይህንኑም በኹሉም ሚዲያዎቹ ካልገለጸ“የማስተካከያ ሥራ ለመሥራት የምንገደድ መኾኑን በጥብቅ እናስታውቃለን፤” ብለዋል“የማስተካከያ ሥራ” ያሉት፥ የማኅበሩን የኅትመት ሚዲያዎች ማገድ፤ በኮሌጆቹ የስም ማጥፋት ወንጀል ክሥ እንዲመሠረትበት ማድረግና ሌሎችንም አስተዳደራዊ ጫናዎችንና ማነቆዎችንእንደሚጨምር ተጠቁሟልበመመሪያዎቻቸው፣ “ማኅበረ ቅዱሳን የተባለ ማኅበር” እያሉ በመጥራት፤የመተዳደርያ ደንብ እንዳይኖረው አድርገው በአየር ላይ እንዳስቀሩት በመግለጽ ደንባዊ ህልውናውን ክደዋል፤ በቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ድምፅ በጸደቀው መተዳደርያ ደንቡ መሠረት ክፍሎችን አዋቅሮ የሚፈጽመው አገልግሎት፣ የብዝበዛና ቤተ ክርስቲያን የማታውቀው እንደኾነ ገልጸዋል

    *                *               *

    መመሪያው፥ ፓትርያርኩ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲኹም በቋሚ ሲኖዶሱ፣ ማዕርገ ክብራቸውንና ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩየተሰጣቸውን ምክር እና አስተያየት ባለመቀበል ያለመዋቅር በተጽዕኖ በጠሩት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ስብሰባ ተጠቅመው ያስተላለፉት ነው፡፡
    በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌዎች፣ ፓትርያርኩ የሚሰበስቧቸውና በርእሰ መንበርነት የሚመሯቸው ስብሰባዎች፥ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ቋሚ ሲኖዶስና የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደኾኑ ሰፍሯል፤ ፓትርያርኩ፣ በመጀመሪያ ደረጃም ኾነ በይግባኝ የሚቀርቡ ጉዳዮች ታይተው ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረግ ያለባቸው፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ወይም ምክትላቸው በሚመሩት ጠቅላይ ቤተ ክህነት አልያም በቋሚ ሲኖዶስ ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መኾን ይገባዋል፡፡ፓትርያርኩ የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎችን በሰበሰቡበት ወቅት፥ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢው፣ “እኛን የሚሰበስቡን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ወይም ምክትሉ ናቸው፤ ከባድ ችግርም ሲፈጠር ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠርቶ የሚመለከታቸው ኹሉ ባሉበት መወያየት እንጂ ጉዳዩ ብቻዎትን የሚያዩት አልነበረም”ሲሉ የአካሔዳቸውን አድሏዊነትና መዋቅራዊ ስሕተት ጠቁመዋቸው ነበር፤ ፓትርያርኩ ግን ከስብሰባው ቀደም ብሎ አካሔዳቸውን እንዲያስተካክሉ የመከሯቸውን ብፁዓን አባቶች፣ “ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ፤ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ፤ ኹሉም አልታዘዝ አሉኝ፤ ሊቃነ ጳጳሳቱን አብረውኝ እንዲኾኑ ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን ሊመጡልኝ አልቻሉም፤”በማለት ነበር ሊያሳጧቸው የሞከሩት፡፡ ማኅበሩም እንዲያወያዩት በተደጋጋሚ ጠይቆ ምላሽ በማጣቱ ለመጻፍ የተገደደውን ደብዳቤ፣ “ሕገ ወጥና ሥርዓት አልባ ደብዳቤዎችን አሻቅቦ ወደላይ በመጻፍ መሪዎችን መቃወም እያስፋፋና እያስለመደ መጥቷል” ሲሉ ነው በመመሪያቸው ያጣጣሉት፡፡ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን የሚፈጽመው፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር እንደመኾኑ፣ ጉዳዩ ከኹሉም በፊት በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ እና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ በኩል እንዲታይ መደረግ ነበረበት፤ፓትርያርኩ ግን፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም ኾኑ ምክትላቸው ባልተገኙበት፣ የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን በተጽዕኖ ሰብስበው ያስተላለፉትን መመሪያ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም ኾነ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እንዲያውቁት ያደረጉት በደብዳቤው ግልባጭ ነው፡፡

    መሳሳትን ልማዳቸው ያደረጉት ፓትርያርኩ፥ ሳያነቡ ይተቻሉ፤ ሳይመዝኑ ይወስናሉ፤ ሳያረጋግጡ ይመሰክራሉ!! በመዝባሪዎች አለቃ፣ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የክፋትና የተንኰል ምክር !!

    በስብሰባው ላይ ፓትርያርኩ፥ “ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ከመጣኹ በኋላ ምንም ዓይነት መጽሐፍ አንብቤ አላውቅም፤ ሰዎች ከሚሉኝ ነው የምሰማው፤ ይኼ የሚባለውንም ሰምቼ ነው፤ ስለተነገረኝ የሰማኹት ነው፤ አላነበብኩትም፤ እንዲኽ እንዲኽ ብለው በነገሩኝ ነው፤” ሲሉ የክሥ እና የቅስቀሳ መመሪያ ያስተላለፉበትን የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣን ጽሑፍ እንዳላነበቡት ተናግረዋል፤ ይህም በአንድ በኩል የበርካታ ስሕተቶቻቸውን ምንጭና መንሥኤ በሌላ በኩል ምን ያኽል በአማካሪዎቻቸው ተጽዕኖ ውስጥ እንደወደቁና የተንኰላቸውንም ክፋት በግልጥ አሳይቷል!! የሊቃውንት ጉባኤው ሰብሳቢም በወቅቱ፣ “ከብፁዓን አባቶች ጋር በአንድነት እየሠሩ አይደለም፤ አማካሪዎችቤተ ክርስቲያንን የሚያጠፉ ሌቦች የደብር አለቆች ናቸው፡፡ እርስዎንና አስተዳደርዎን ተቆጣጥረዋል፤ይህን ያስተካክሉ፤ ውጭ ያለውን ቅር ያሰኛል፤ ለሥራም የሚያበረታታ አይደለም፤” ሲሉ ነበር ኹኔታውን በከፍተኛ ቅሬታ የገለጹት፡፡ማኅበረ ቅዱሳን፥ የቀድሞ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕን፣ በቅድስና ደረጃ ሠይሞ ታቦት እንደቀረጸላቸውና ቤተ ክርስቲያንም በስማቸው እንዳነጻላቸው ተደርጎበአማካሪዎቻቸው የተነገራቸውን አምነው በስብሰባው ወቅት፣ ለአቡነ ጎርጎርዮስ ሲኖዶስ ቅድስና ሳይሰጣቸው ቅድስና ሰጥተዋቸዋል፤ ታቦት አስቀርጸው ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸዋል፤ በቅድስና ደረጃ ብፁዕ ወቅዱስ ተብለው ቅድስና ተሰጥቷቸው እየተገለገለ ነው፤ ሲሉ መጥቀሳቸው፣ ፓትርያርኩ ይኹነኝ ተብሎ ስለ ማኅበሩ የሚደርሷቸውን መረጃዎች ሳያጣሩና ሳይመዝኑ አቋም እንደሚይዙና ውሳኔ እንደሚሰጡ በማያወላዳ መልኩ አረጋግጧል፡፡በሕገ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከሢመተ ፕትርክና በኋላ የተቀበሉትን ሓላፊነት በመዘንጋት ሊሳሳቱ እንደሚችሉ (fallible) ተመልክቷል፡፡ ከዚኽም በላይ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መጣሳቸው፤ በተሾሙበት ቀን የፈጸሙትን ቃል አለመጠበቃቸው፤ በአጠቃላይ ታማኝነታቸውና መንፈሳዊ አባትነታቸው በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት አጥቶ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ተግባር መፈጸማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ በተጨባጭ ከተረጋገጠ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱሊወሰንም ይችላል፡:

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ፓትርያርኩ:ደንባዊ ህልውናውን የካዱት ማኅበረ ቅዱሳን፣ በስምዐ ጽድቅ ላወጣው የፀረ ተሐድሶ ኑፋቄ ጽሑፍና በደብዳቤ ለሰጣቸው ምላሽ በአምስት ቀናት ውስጥ ይቅርታ እንዲጠይቅ መመሪያ ሰጡ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top