ከካህናት ወገን የምትሆን ቅድስት ሐና፥ ከነገደ ይሁዳ ከሆነ ከቅዱስ ኢያቄም ጋር በተቀደሰ ትዳር ሲኖሩ ልጅ አልነበራቸውም። እንደ አብርሃም እና ሣራ፥ እንደ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥ ከመውለድ እጅግ ዘግይተው ነበር። ሁለቱም እግዚአብሔር በሠራው ሕግ ፀንተው የሚኖሩ፥ እግዚአብሔርም የሚወዳቸው ደጋጎች ነበሩ። ልጅ ስለ አልነበራቸው ኑሮአቸው የሐዘን እና የትካዜ ነበር። ዕለት ዕለትም ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ ልጅ እንዲሰጣቸው ልመናቸውን ከዕንባ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ያቀርቡ ነበር። ከገንዘባቸውም ከፍለው ለድሆች እና ለጦም አዳሪዎች፥ ለቤተ እግዚአብሔርም ይሰጡ ነበር። ይኽንንም ያደርጉ የነበረው፥ እግዚአብሔር በትክክል ልጅ እንደሚሰጣቸው ፈጽመው በማመን ነበር። “ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፤” ማር፡፱፥፳፫።
በትዳር ሕይወት ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው። “እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም (በሕጉ በትእዛዙ) የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው። የድካምህን ፍሬ ተመገብ (ትመገባለህ)፤ ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው። እነሆ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲህ ይባረካል።” ይላል። መዝ፡፻፳፯፥፩-፬። አበ ብዙኃን አብርሃም፡- እግዚአብሔር፡- “አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው።” ባለው ጊዜ፥ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፤”ያለው፥ ጸጋ እግዚአብሔር የሆነ ልጅ ለምን ይቀርብኛል ብሎ ነው። እግዚአብሔርም፡- አብርሃም ልጅ እንደሚወልድ፥ ዘሩም እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዛ ነግሮታል። ዘፍ፡፲፭፥፩-፮። በኋላም ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ድንኳን በእንግድነት ተገኝተው፥ “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ወንድ ልጅ ታገኛለች፤” ብለውታል። አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፥ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ዘፍ፡፲፰፥፩-፲፭። “እግዚአብሔርም እንደተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት።ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅ ወለደችለት። አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው፤” ይላል። ዘፍ፡፳፩፥፩-፫። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ።” በማለት አድንቆአል። ዕብ፡፲፩፥፲፩-፲፪።
የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐና መጽናናት እስከ ሚያቅታት ድረስ ዕንባዋን ያፈሰሰችው፥ የጾመችው እና የጸለየችው ስለ ልጅ ነበር። ሐና፡- ሴሎ ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደች፥ በእግዚአብሔር ፊት ልመናዋን አበዛች፥ ድምፅዋ ሳይሰማ ከንፈሯን ታንቀሳቅስ፥ በልቧም ትናገር ነበር፤ ሊቀ ካህናቱ ዔሊም፡- የስካር መንፈስ መስሎት፥ “የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው፤” አላት። ሐናም፡- “ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤ ኀዘኔ እና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ፤” ብላ መለሰችለት። ዔሊም የችግሯን ክብ ደት ተገንዝቦ፡-” በደኅና ሂጂ፥የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ፤” ብሎ መረቃት። እርሷም፡- “በፊትህ ሞገስ ላግኝ፤” አለችው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በፊትዋ ላይ ኀዘን አልታየም፥ እግዚአብሔርም አሰባትና ወንድ ልጅ ወለደች። “ከእግዚአብሔር ለምኜ አገኘሁ፤” ስትል፥ ስሙን፡- “ሳሙኤል” አለችው። ሦስት ዓመት ሲሞላውም ለእግዚአብሔር ሰጥታው በእግዚአብሔር ቤት አደገ፥ ታላቅ ነቢይም ሆነ። ፩ኛ፡ሳሙ፡፩፥፩-፳፰።
ካህኑ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥም ፈጽመው እስከሚያረጁ ድረስ የጸለዩት ስለ ልጅ ነበር። “ሁለቱም በጌታ ትእዛዝ እና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ሁለቱም በዕድሜአቸው አርጅተው ነበር፤” ይላል። የመውለጃ ዘመናቸው ካለፈም በኋላ ጸሎታቸውን አላቋረጡም ነበር።ጻድቁ ካህን ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ሲያገለግል፥ በመሠዊያው በስተ ቀኝ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጠለት።ዘካርያስ፡- ልቡ ፈራ፥ ኅሊናው ደነገጠ፥ ጉልበቱ ተንቀጠቀጠ። መልአኩም፡- “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንደ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፤” አለው። ለጊዜው፡- “እኔ ሽማግሌ ነኝ፥ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለች፥ ይህን በምን አውቃለሁ? (ምልክት ስጠኝ )፤” አለ። መልአኩም፡- “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድ ሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፥ መናገርም አትችልም፤” አለው።እንደተባለውም ሆነ፥ ከዚህም በኋላ ኤልሳቤጥ ፀነሰች። እርሷም፡- “ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል፤” ስትል ራስዋን ለአምስት ወራት ሰወረች። ጊዜው ሲደርስም መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን ወለደች፥ የዘካርያስም አንደበት ተፈታ። ሉቃ፡፩፥፭ -፳፭፣፶፭። በዘመነ ኦሪት ልጅ አለመውለድ ያስነቅፍ ነበር።
ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐናም ትልቁ ሐዘናቸው ልጅ ማጣታቸው ነበር። ወደ ተክል ቦታ ገብተው ሲጸልዩ፥ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሎአቸው ሲጫወቱ አይተው በራሳቸው አዘኑ፤ ኀዘናቸውም ፍጹም እና ከባድ ስለ ነበር አንቀላፍቶአቸው ተኙ። በህልማቸውም ምሥጢሩ አንድ የሆነ የተለያየ ነገር አዩ። ቅዱስ ኢያቄም፡- ነጭ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ ወርዳ ከቅድስት ሐና ራስ ላይ ስታርፍ፥ በቀኝ ጆሮዋም ገብታ ከማኅፀንዋ ውስጥ ስትተኛ አየ። ቅድስት ሐናም በበኵሏ፡- ቅዱስ ኢያቄምን ነጭ ጸምር ሲያስታጥቁት፤በትሩም ለምልማ፣ አብባ ስታፈራ፥ ታላቅም ዛፍ ስትሆን፥ከጥላዋ ስርም ብዙዎች ሲጠለሉ እና ፍሬዋን ሲመገቡ አየች። ያዩትንም ከተጨዋወቱ በኋላ ወደ መፈክረ ሕልም ዘንድ ሄዱ፥እርሱም ደግ ልጅ እንደሚወልዱ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን “ጊዜ ይፍታው፤”ብለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ሕልሙን ያዩት ሐምሌ ሠላሳ ቀን ነው፥ከዚያን ዕለት ጀምሮ ጾም ጸሎት ያዙ፤ ከጾም ጋር የሆነ ጸሎትም ቅድመ እግዚአብሔር ይደርሳል።ነቢዩ ዳንኤል፡- ከሥጋ እና ከቅቤ፥ ከደረቅ እንጀራም ተለይቶ ጾም ጸሎት በመያዙ ልመናው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶለታል። “በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋ እና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስከ ሚፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። . . . እርሱም (በሚያስፈራ እና በሚያስደነግጥ ግርማ የተገለጠልኝ ቅዱስ ገብርኤል) ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ ካደረግህበት (ጾም ጸሎት ከጀመርክበት) ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ፥ አለኝ፤” ብሎአል። ዳን፡፲፥፩-፲፪።
ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና መኝታቸውን ለይተው ጾም ጸሎት በያዙ በሰባተኛው ቀን፥ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ፡- “በሕልም እንደተረዳችሁት፥ መፈክረ ሕልምም እንደተረጐመላችሁ፥ ደግ ልጅ የምትወልዱበት ጊዜ ደርሶአልና መኝታችሁን አንድ አድርጉ፤” አላቸው። እነርሱም የታዘዙትን አደረጉ፥ ፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑም ነሐሴ ሰባት ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀነሰች። ይኽንንም አባ ሕርያቆስ፡- “ድንግል ሆይ፥ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፥ በሕግ በሆነ ሩካቤ (ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ጋብቻ ክቡር፥ መኝታውም ንፁሕ ነው እንዳለ) ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፤” በማለት በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ ተናግሮታል። ቅድስት ሐናም፡- “የሰጠኸኝን ልጅ ጊዜው ደርሶ ሲወለድ፥ መልሰን መብዓ አድርገን ለአንተ እንሰጥሃለን፤” ብላ ተሳለች።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን እያለች አያሌ ተአምራትን አድርጋለች። የቅድስት ሐና ዘመድ የምትሆን አንዲት ዓይነ ስውርት ሴት ነበረች። እርስዋም የሐናን መፅነስ ሰምታ በመደነቅ ሆድዋን ዳሰሰቻት፥ በዳሰሰችበት እጇም ዓይንዋን ብትነካ በርቶላታል። ቅድስት ሐናንም፡- “ብፅዕት መባል ይገባሻል፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እንደ አንቺ በማኅፀኑ ዓይን ያበራ የለምና፤” አለቻት። ይኽንንም አብነት አድርገው ሕሙማን ሁሉ ማኅፀን ዋን እየዳሰሱ የሚፈወሱ ሆነዋል። ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል የአጎትዋ ልጅ ሙቶ፥ እንደ ባህሉ የአልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስትአለቅስ፥ የሐና ጥላዋ ቢያርፍበት፥ አፈፍ ብሎ ተነሥቶ፥ “ሰማይ እና ምድርን ለፈጠረ እናቱ ለምትሆኚ ለአንቺ ሰላምታ ይገባሻል፤” በማለት በማኅፀን ላለች ለድንግል ማርያም ምስጋና አቅርቦአል።
ቅድስት ሐና በማኅፀንዋ ያለች እመቤት ድንግል ማርያም በምታደርገው ተአምር የተነሣ፥ ዘመዶችዋ ሁሉ ሰገዱላት፥ ዝናዋም በየአገሩ ተሰማ። ይኽንን ድንቅ ነገር የሰማ ሁሉ፥ “በማኅፀን ሳለ ሕሙም የፈወሰ በተወለደ ጊዜ እንደምን ይሆን?” አለ። መቼም በማኅፀን መቀደስ መኖሩን ከቀደሙ ነቢያት ከቅዱስ ኤርምያስ ተምረናል። “የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፡- በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፤” ይላል። ኤር፡፩፥፬። በአዲስ ኪዳን መግቢያ ላይ ደግሞ በቅዱስ ዮሐንስ አውቀናል። “በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል፤” ይላል።ሉቃ፡፩፥፲፭። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ትምህርቱ፥ “በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች (ቅዱሳን) ሆነው የሚወለዱ አሉ፤” ብሎአል። ማቴ፡፲፱፥፲፭። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ፡- ማኅደረ መለኰት፥ወላዲተ አምላክ በመሆንዋ ከእነዚህ ሁሉ ትበልጣለች። በመሆኑም በማኅፀን ሆና ተአምር ማድረግዋ ያንስባታል እንጂ አይበዛባትም። ደግሞም ለባሪያዎቹ የተሰጠ ጸጋ፥ ምልዕተ ጸጋ ለሆነች ለእናቱ አልተሰጣትም፥ ማለት ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም።
0 comments:
Post a Comment