• በቅርብ የተጻፉ

    Monday, 18 January 2016

    የተኩላው ለምድ ሲገፈፍ ክፍል ሁለት



    ክፍል ሁለት

    የተኩላው ለምድ ሲገፈፍ

    እነዚህ ክፉ ሠራተኞች በእውነተኞቹ መምህራንና ዘማርያን ስም የሚያታልሉ አገልጋይ ነን ባዮች የዲያብሎስ መልእክተኞች መሆናቸውንም በንግግራቸውና በጽሑፋቸው አረጋግጠዋል ‹‹እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይ የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ (ራዕ 13፡6) ተብሎ እንደተጻፈ ቤተክርስቲያንን እናድሳለን ብለው የተነሱት እነዚህ ተጠራጣሪዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ኢየሱስ ክርስቶስ አልተሰበከም ብለው በድፍረት ከመናገራቸው ባሻገር ፣ የፈጣሪ ማደሪያ ሁለተኛ ሰማይ የሆነችውን.፣ ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆነውን አምላክን የወለደችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲሁም እግዚአብሔር ያከበራቸውን ቅዱሳን መላዕክትን ጻድቃንና ሰማዕታትን በመሳደብ ፣ በሚገባ የጠላት ሰይጣን ማደሪያዎች ታማኝ አገልጋዮቹ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡ ቅዱሳንን ለጆሮ በሚቀፍና በሚዘገንን ስድብ ከአብጠለጠሉ በኋላ ስለራሳቸው ማንነት ሲገልጡ ግን የበቁና የነቁ የፈጣሪን ማንነት ጠንቅቀው ያወቁ እንደሆኑ አድርገው በትዕቢት ይናገራሉ፡፡

    በእነሱ ቋንቋም አሮጊቷ ሣራ፣ የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ እነሱን በሚያስገርም ሁኔታ እንዳስገኘች አድርገው በስብከታቸው ሳይቀር ይናገራሉ፡፡ ያልተረዱትና ምስጢሩ የተሰወረባቸው ነገር ግን ምሥጢርን ከምስጢር አራቀው የሚያስተምሩትን አበው ሊቃውንትንና በጥዑመ ዜማ ለእግዚአብሔር ክብር የዘመሩትን እነ ቅዱስ ያሬድንና አባጊዮርጊስ ዘጋስጫን የወለደች ተዋሕዶ በእውነት እነሱን አልወለደችም በፍጹም!!!ፍጹም!!ፍጹም፡፡ እንዲያውም እነሱ አባታቸውን ሉተርንና ግብረ አበሮቹን ስለሚመስሉ የዘር ሐረጋቸውን ከዚያ ሊቆጥሩ ይችላሉ፡፡ አባቶቻችን የለየለት ጠላት ከወዳጅ እኩል ነው እንዲሉ ሥውር ሴራቸውንና ተልኳቸውን ትተው ራሳቸውን በመግለጥ እዚያው ከቢጤያቸው ጋራ በነፃነት የሚፈልጉትን ማድረግ ሲችሉ የበግ ለምድ ለብሶ ማደናገሩ ይብቃችሁ እንላለን፡፡ ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀትም ሳይሆን ጤነኛ አዕምሮ ላለውና ማገናዘብ ለሚችል በኅሊና ዳኝነትም ለሚፈርድ እግዚአብሔር ለእመቤታችን፣ ለቅዱሳን መላዕክት ፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ስለቅድስናቸውና ስለንጽህናቸው እንደ መሰከረላቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ ተአምር፣ ገድልና ድርሳን ይመሰክራል፣ ይህም ብቻ ሳይሆን ዛሬም እንኳን በዘመናችን ብዙ ተጠራጣሪዎች እንደ ክረምት አግቢ በበዙበት ዘመን፣ በቅዱሳን ቃል ኪዳን የተማጸኑ ፈጣሪያቸውን ያመኑ ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ሲፈወሱ በዓይን የሚታይ በጆሮ የሚደመጥ ተአምር ነው፡፡ እነዚህ ተኀድሶአውያን ሰባኪያንና ዘማርያንም ሳያውቁ አውቀናል ሳይበቁ በቅተናል ፣ ፈጣሪ ሳያዛቸው ታዝዘናል፣ መንፈሳዊ ሥልጣን ሳይኖራቸው ተሹመናል ላሉት ሰዎች ግን እግዚአብሔር አልመሰከረላቸውም ለመሆኑ የትኛው ሐዋርያ ነው የእግዚአብሔር የሆኑትን እየተቃወመ ስለራሱ ክብር የተናገረው በመጎናጸፊያው (በልብሱ) ሳይቀር ተአምር ያደርግ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ወይስ በጥላው ድውያንን የፈወሰው ቅዱስ ጴጥሮስ?

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እናድሳለን ብለው የተነሱት ቢጽ ሐሳውያንም ሆነ ተኀድሶ የለም በማለት በስውር የሚንቀሳቀሱት ተንኮለኞች ሠራተኞች በአርባና በሰማንያ ቀን ጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ ተወልደን፣ የሥላሴ የጸጋ ልጆች በመሆን የምንበቃባት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደማታውቀው አድርገው ዓለም ያወቀውን ግልጽ ምስክርነት ልባቸው እያወቀው ለመመጻደቅ ለጉራ፣ ለውዳሴ ከንቱና ለገንዘብ ብለው ክደዋል፡፡

    ለመሆኑ እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማን ያውቀዋል፡፡ ለዚህም ምስክር ከሆኑት አስተምህሮዋ መካከል ጌታችን ‹‹ስለእናንተ የሚስጠው ሥጋዬ ይህ ነው ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› በማለት ባዘዘው ትዕዛዝ መሠረት (ሉቃ 22፡19) የሐዋርያቱን ፈለግ ተከትላ (1ቆሮ 11፡21-34) በየገዳማቱና በየአድባራቱ በየዕለቱ ለሚመጡ ምዕመናኖቿ የዓለም መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስን እየሰበከች አማናዊው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምታቆርብ ከመሆኑም በላይ፣ ኢየሱስ ያደረገውን ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል (ዮሐ 21፡15) ተብሎ እንደተጻፈ ተአምረ ኢየሱስን፣ ድርሳነ ማኅያዊን፣ መልክአ ኢየሱስን ፣ግብረ ሕማማትን ጽፋና ጠርዛ የምታነብና የምትተረጉም ብቸኛዋ ቤተክርስቲያን እንደሆነች አላወቁ ይሆን፡፡

            ዳሩ በመጽሐፍ (ኢዮ 8፡8) አባቶችህ ለመረመሩት ነገር ትጋ ተብሎ ተጽፎ ትውፊትንና ታሪክን ባለመመርመር ለምንፍቅናና ለአውሬው ማደሪያ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ እነዚህ ቢጽ ሐሳውያን (ተኀድሶ) የጥፋት ልጆች ኢየሱስን ለመቀበል ድንግል ማርያምንና ቅዱሳን መላዕክትን እንዲሁም ጻድቃን፣ ሰማዕታትን ከልብህ አውጣ በማለት በተለያየ ጊዜ በጉባዔያቸው መናገራቸው ተረጋግጧል፡፡ እንግዲህ ተጠራጣሪዎች በድፍረት መንፈስ ተሞልተው ቅዱሳንን መንቀፋቸው፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት አለመሆኑን ለመግለጥ እንወዳለን፡፡ ትርጉሙን ሳይረዱ ኢየሱስ ክርስቶስን እንሰብክበታለን ብለው የተሸከሙት መጽሐፍ ቅዱስ ግን ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፣ እኔን የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል›› ይለናል መታሰቢያቸውንም ማድረግ እንደሚገባም ሲገልጥ ‹‹ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀመዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም (ማቴ 10፡40-42) ይላል፡፡

    በተጨማሪም እግዚአብሔር የቅዱሳንን ዋጋ እንደማይረሳ መታሰቢያቸው እንደሚዘከር አስቀድሞ በነቢዩ ተናግሯል ‹‹እግዚአብሔርም ሰንበቱን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጀንደረቦች እንዲህ ይላልና፡- በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፡፡ (ኢሳ 56፡4-5)

    የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ክብርና ምልጃ በቃና ዘገሊላ፣ ቅዱሳን መላዕክት ጥበቃና አገልግሎታቸው በብሉይ ኪዳን ሎጥን ከክፉ መቅሰፍት ከገሞራ ጥፋት ………….. እስራኤልን ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን አምድ መምራታቸው ነቢዩ ኤልሳን ከደፈጣ ተዋጊዎች በማዳናቸው በዘመነ ሐዲስ ቅዱስ ጴጥሮስን ከእስር ቤት ማውጣታቸው የጎላ የተረዳ ታሪክ መሆኑን እናስታውሳለን፡፡(ዘፍ19:1፣   ዘጸ 14ና15:   2ነገ6፣16:   ማር16፣16  :  ዮሐ2፣1_11 :    ሐዋ12፣6_11)

    በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን በሞት ከተለዩ በኋላ ተአምር እንደሚሰሩ ‹‹ኤልሳም ሞተ ቀበሩትም ከሞዓብ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳ መቃብር ጣሉት የኤልሳንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ በማለት ያረጋግጥልናል (መጽ ነገ 13፡20-21) ገድለ ቅዱሳንን መቀበል እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል (ማቴ 26….) ተኀድሶአውያን መናፍቃን በተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ከሚፈጸመው ሥርዓት መካከል አንዱ የሆነውን መስቀል መባረክም ተገቢ አለመሆኑን ያስተምራሉ፣ በዚህም የመስቀል ጠላት መሆናቸውን ራሳቸው ይመሰክራሉ፣ በተለያየ ጊዜ በስብከታቸውም እያጣጣሉ ይናገራሉ፡፡ እኛ ግን አባቶቻችን እንዳስተማሩት አጥብቀውም እንዳሳሰቡን መስቀልን የሚጠላ ሰይጣን መሆኑን ሰምተናል፣ እኛም ይህንኑ በዘመናችን በዓይናችን ጭምር ያየነውን በእምነት ልናረጋግጥ ይገባል፣ አጋንንት ያደረባቸው ሰዎች በመስቀል ሲታሹ መስቀል ሲሳለሙ ሕመማቸው እንደሚታገስላቸው እንደሚድኑም እናውቃለን፡፡ በመሆኑን መስቀልን የሚጠላ የማን ወገን እንደሆነ ለመፍረድ አያዳግትም፡፡

    ታማኞቹ መላዕክትም በከተማቸው በሰማይ ታላቅ ሰልፍ ሆኖ ውጊያ በተደረገ ጊዜ በቅ/ሚካኤልና ቅ/ገብርኤል መሪነት ዲያብሎስን ተከራክረው የረቱት በትዕምርተ መስቀል መሆኑታውቋል፣ በብሉይ ኪዳን የወንጀለኛ መቅጫ መሣሪያ የነበረው መስቀል በመድኀኒታችን ስቅለት ከብሯል፣ በሐዲስ ኪዳን መስቀል የሞት ሳይሆን የሕይወት፣ የውርደት ያይደለ የልዕልና የድላችን ዓርማ የነፃነታችን ምልክት መሆኑ ታውቋል፡፡ (መዝ 59፡4፣ …………) የመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ካህናት ቅዱሳን ሀዋርያትም የመስቀሉን ነገር ከልባቸው የፋቁትን ከኅሊናቸው ያወጡትን ክርስቲያኖች መገሰጻቸውን እንጂ የመስቀሉ ምልክት ይጥፋ ሲሉ አልተሰማም፡፡ ‹‹የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር በእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? (ገላ 3፡1)

    ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክዕት ከእኔ ይራቅ›› (ገላ 6፡14-15) ያለውን ሐዋርያ ተከትላ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በዘወትር ጸሎት ‹‹ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት ለመስቀልም እሰግዳለሁ መስቀል ኃይላችን ነው ኃይላችን መስቀል ነው የሚያጸናን መስቀል ነው፣ መስቀል ቤዛችን ነው ፣ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን ያመነው እኛም በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም›› በማለት ስለ ክቡር መስቀሉ ትመሰክራለች ዛሬም ትንቢቱ መፈጸም ስላለበት መስቀል ጨብጠው የመስቀሉን ኃይል በካዱ ቢጽ ሐሳውያን የክህደት ትምህርት አትሸበርም፣ ክቡር መስቀሉንም ከአንገታችን አንበጥስም ከእጃችን አንጥልም፣

    በመሆኑም የተዋሕዶ ልጆች ሁሉ መንፈሳውያን መስለው ከመጡ ሥጋውያን፣ እውነተኞች መስለው ከተነሱ ሐሰተኞች እንድትጠብቁ በአክብሮት እያሳሰብኩ የማይኖሩበትን የተዋሕዶ ካባ አጥልቀው መስቀል ጨብጠው የመጡ ነቢያተ ሐሰት ስላሉ፣ የአበውን መለያ ምልክት ስላደረጉ ብቻ የጠመጠመና ቆብ ያደረገውን በየዋህነት በመከተል ወደ ክህደት እንዳትሄዱ ምክራችንን እንለግሳለን፡፡

    የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኖች ነቢያት ተጠንቀቁ. ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ (ማቴ 7፡15) ተብሎ ተጽፏልና፡፡

    ማኅቶተ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ክታቡ ጊዜ የወለደውን፣ ዘመን የወደደውን የስህተት ትምህርት እንዳንከተል፣ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው በማለት መክሮናል (ዕብ 13-19) ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስም በመልዕክቱ፣ ‹‹ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ፣ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም ስለመምጣቱ መልክትና ስለዓለም ፍጻሜ ደቀመዛሙርቱ ለጠየቁት ምላሽ ሲሰጥ የሐሰተኞች መምህራን (አስተማሪዎች) አንዱ ምልክት እንደሆነ ከመግለጡም ባሻገር ቢቻላቸው የተመረጡትንም ያስታሉ በማለት አስገንዝቦናል፡፡ (ማቴ 24፡11)

    እንግዲህ ቤተክርስቲያንን እናድሳለን በሚል የተነሱ ክፍሎች ምንም እንኳን እስከዛሬ ድረስ ማንነታቸውን ሳይገልጹ በድብቅ ሲንቀሳቀሱ ምዕመናንም ከእውነተኞች መምህራንና ከአባቶች ጋር ሲያጣሉና ሲያካስሱ ቢቆዩም የቤተክርስቲያን መሠረትና ጉልላት የሆነው ወልድ ዋሕድ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድንቅ በሆነ ጥበቡ ሥራቸውንና ተንኮላቸውን እየገለጠባቸው ነው፣ በመሆኑም ሁላችንም በንቃትና በማስተዋል ሆነን ሃይማኖታችን እናጽና አበው ያስተማሩንንም ትውፊት (ወግ) እንጠብቅ፡፡

    ይቆየን፡፡

    በክፍል (3) የተኀድሶአውያን መለያ ጠባይ ምን ይመስላል የሚለውን እናያለን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የተኩላው ለምድ ሲገፈፍ ክፍል ሁለት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top