የተሐድሶ መረብ አድማስና የትኩረት አቅጣጫዎች
ክፍል ሦስት
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች ተሐድሶ መናፍቃን በምን ዐይነት መንገድ ምእመናንን እየነጠቁ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ቀጥለን በምናወጣቸው ተከታታይ ጽሑፎች ደግሞ የተሐድሶ አድማሱ የት ድረስ እንደሆነ ለአንባቢያን ግንዛቤ የሚሰጥ መረጃ የምናቀርብ ይሆናል፡፡
የተሐድሶ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፋዊ መልክ ያለውና በዓለም ላይ ባሉ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በፕሮቴስታንት የእምነት ተቋማት የተቃጣ ስውር ሴራ ነው፡፡ እንቅስቃሴው ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የመጣ ስለሆነ የተሐድሶው አቀንቃኞች በአሳብ፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ ወዘተ ከሚያግዟቸው በልማት ስም ከተቋቋሙ ድርጅቶች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች እና ከፕሮቴስታንት ቸርቾች በሚበጀት በጀት፣ ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ አገር በተዘረጋ መዋቅር፣ ቤተ ክርስቲያንን ከተቻለ ሙሉ በሙሉ ለመረከብ ፕሮቴስታንት ለማድረግ ካልሆነም ለሁለት ለመክፈል በሚያስችል ስልት እየሠሩ እንደሆነም ተመልክተናል፡፡
በአገር ውስጥ ያሉት ሠላሳ የሚደርሱ የተሐድሶ ማኅበራት የቤተ ክርስቲያን ምንጮች በሆኑት የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ገዳማት፣ መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ላይ እንዲሁም መዋቅራዊ ድጋፍ ለማግኘት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ይሠራሉ፡፡ የተለያዩ መመዘኛዎችን በመጠቀም ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ መነሻቸውን አዲስ አበባ ላይ አድርገው በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ዕትም ጀምሮ በተከታታይ ጽሑፎች ከመነሻቸው ከአዲስ አበባ ጀምረን ትኩረት ሰጥተው በሚሠሩባቸው አካባቢዎች ያለውን እንቅስቃሴ እንመለከታለን፡፡
አዲስ አበባን ማእከል ያደረገው የተሐድሶ መረብ
አዲስ አበባ የተሐድሶ እንቅስቃሴው ማእከል ነው፡፡ ታሪክ የሚነግረን ተሐድሶዎች እንቅስቀሴው ሲጀመር ጀምሮ ማእከላቸውን አዲስ አበባ አድርገው ወደ ሌሎቹ የአገራችን ክፍሎች ኑፋቄያቸውን ያስፋፉት መሆኑን ነው፡፡ አዲስ አበባ ተሐድሶዎች በየአጥቢያው ተወካዮችን አስገብተው ብዙ ሥራ የሚሠሩበት፣ የተለያዩ የሥልጠና መስጫ ተቋማትን እና ኮሌጆችን ያቋቋሙበት፣ የቤት ለቤት ሥራዎችን በሰፊው የሚሠሩበት፣ የጽዋ ማኅበራትን በብዛት የፈጠሩበት፣ ከክፍለ ሀገር ለሚያመጧቸው ካህናትና ዲያቆናት ሥልጠና የሚሰጡበት ነው፡፡ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር የሚያስተላልፉት፣ አብዛኛው የተሐድሶ መናፍቃን መጻሕፍት የሚታተሙት፣ የገንዘብ ልገሳ የሚያደርጉላ ቸው የመናፍቃን ድርጅቶች የሚገኙት አዲስ አበባ ነው፡፡ ፕሮቴስታንታዊ የአምልኮ ሥርዓት የሚፈጸምባቸው የተሐድሶ አዳራሾች በስፋት የሚገኙትም እዚሁ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የሚያስችላቸውን መዋቅራቸውን የዘረጉትና ስልታቸውን የነደፉት አዲስ አበባን ማእከል አደርገው ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከአዲስ አበባ እየተነሡ ያልደረሱበት የአገራችን ክፍል የለም ማለት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ያላቸው መረብም ጠንካራና ሁሉንም አጥቢያዎች የሚያቅፍ ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ መሐል አዲስ አበባ አካባቢ ካሉት አጥቢያዎች ተነቅቶባቸው ሲባረሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወደሚገኙ አጥቢያዎች በመሔድ ተመሳስለው ገብተው የቅሰጣ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተልእኳቸውን ተረድታ በውግዘት የለየቻቸውና አጋልጣ ምእመናን እንዲያውቋቸው ያደረገቻቸው ተሐድሶዎች ከጀርባ ሆነው በየአጥቢያው የሰገሰጓቸው ተሐድሶ መናፍቃን ተልእኳቸውን ያፋጥኑላቸዋል፡፡
እንቅስቃሴው በግልም በቡድንም እንዲሁም በድርጅት ስም የሚካሔድ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ የተሐድሶ አቀንቃኞችን እገሌ ወእገሌ ማለቱ ባያቅትም ለአንባቢም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ጥቅም ካለመኖሩና እነርሱንም የበለጠ እንዲደበቁ ዕድል መስጠት ስለሚሆን ይህንን መጠበቅ የለብንም፡፡ ነገር ግን በብዙ ቦታዎች እንደሚታየው በዓላማ እንቅስቃሴውን የሚመራው አካል አንድ ወይም ጥቂት ነው፡፡ ሌላው ግን ምን እየተሠራ እንደሆነ እንኳን ሳያውቅ ሌሎቹ ስለሔዱ ብቻ የሚከተል ነው፡፡
በተደጋጋሚ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ካህናትን እያመጡ አዲስ አበባ ላይ ያሠለጥናሉ፡፡ በተለይ ከገጠር ለሥልጠና የሚያመጧቸው ካህናት ከጥቂቶቹ በስተቀር በየዋህነት ጉዳዩ ምን እንደሆነ ሳይረዱ የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ሴራዎች ያውም የቤተ ክርስቲያን ምንጮች ያልናቸው አብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ላይ ሓላፊነት ላላቸው ሰዎች ተሰጥቶ የፈለጉት ነገር አለመሳካቱን ስናይ የእግዚአብሔርን ጠብቆት እናደንቃለን፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የሚሰጡት ሥልጠናÂ ውጤት ማምጣት ያልቻለው በአንድ በኩል ከሠልጣኞች አቅም ማነስ የተነሣ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሚከተሉት ዓላማ የጥፋት በመሆኑ እግዚአብሔር እንዳይሳካላቸው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን በረድኤት ስለሚጠብቃቸው ነው ብለን እናምናለን፡፡ ተሐድሶዎችም ምዕራባውያን ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ስውር ተልእኳቸውን ለማሳካት የበጀቱት ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንዳይቀርባቸው እንጂ ለጽድቅ ስለ ማይሠሩ ለሪፖርት ብቻ ሥልጠና ሰጥተው የሚልኳቸው ብዙዎችን ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መቦርቦርን እንጀራ ማብሰያ አድርገው የያዙት ብዙ የተሐድሶ ድርጅት አንቀሳቃሾች መናሃሪያቸው አዲስ አበባ ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ የተወገዙና ከሥልጣነ ክህነታቸው የተሻሩ ግለሰቦች ሳይቀሩ የክህነት ስማቸውን ተጠቅመው ዲያቆን፣ መሪ ጌታÂ እያሉ መጻሕፍት ያሳትማሉ፡፡ ሥልጠና የሚሰጡባቸው፣ ኑፋቄያቸውን የሚዘሩባቸው፣ በእነርሱ አነጋገር አምልኮት የሚፈጽሙባቸው፣ በሥውር ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ሴራ የሚጠነስሱባቸው፣ የቴቪዥን መርሐ ግብራትን የሚቀርጹባቸው፣ የግልና የኪራይ አዳራሾች አሏቸው፡፡ በእነዚህ አዳራሾች ሲያሻቸው ያስጨፍራሉ፣ ሲያሻቸው እንፈውሳለን ይላሉ፣ ሲያሻቸው ደግሞ እነርሱ ሳይማሩና የያዙት ወንጌል ሳይገባቸው ያስተምራሉ፡፡
የቤት ለቤት ቅሰጣ አልበቃ ብሏቸው በመገናኛ ብዙኀን ወደ ሕዝብ መድረስ ጀምረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ምእመናን ስለ ተሐድሶ ያላቸው ግንዛቤ እየጨመረ መምጣቱ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ከተሐድሶዎች ጋር እያደረጉት ያለው ትንቅንቅ መጎልበቱና ለምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብራት እየበረከቱ መምጣታቸው ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ከተሐድሶዎች እጅ ነፃ ለማድረግ ግን ሰፋ ያለና የተቀናጀ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡
አጥቢያቸው የሚገኘውን ሰንበት ትምህርት ቤት አፍርሰው ሌላ ሰንበት ትምህርት ቤት ለማቋቋም፣ አባላቱን ለሁለት ከፍለው አገልግሎቱ እንዳይካሔድ ለማድረግ የሚጥሩ ከተሐድሶ በሚገኝ ገንዘብ የሚደለሉ አንዳንድ አስተዳዳሪዎችና የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ዓላማችንን ያስፈጽሙልናል ያሏቸውን የሰንበት ተማሪዎች ሰብስበው የተለየ ትምህርትÂ ካስተማሩ በኋላ ተልእኮ ሰጥተው ተመልሰው ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሌላ ተልእኮ ይዘው ተመሳስለው የገቡትን የጥፋት መልእክተኞች አካሔድ አጢነው ሲያግዷቸው ለምን ታገዱ ብለው ሰንበት ትምህርት ቤቱን ለመዝጋት የሚነሡ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ምን ያህል ተመሳስለው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደገቡ ነው፡፡ ምእመናንም ሆኑ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንዲህ ዓይነት የጥፋት ተልእኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱትን ወገኖች ሲመለከቱ ማንነታቸውን የሚያሳይ መረጃ መሰብሰብ፣ ከማን ጋር እንደሚውሉ፣ ምን እንደሚሠሩ፣ አነጋገራቸው፣ አካሔዳቸው፣ ኦርቶዶክሳዊነታቸው ምን እንደሚመስል ማጣራት ይኖርባቸዋል፡፡
በአንዳንድ አጥቢያዎች ገድላትና ድርሳናት፣ ተአምረ ማርያምና ስንክሳር እንዳይነበቡ የሚከለክሉ አስተዳዳሪዎች አሉ፡፡ የጠበል ቦታ አያስፈልግም ብለው ለጋራዥ በማከራየት ገንዘብ ከመመዝበር አልፈው ምእመናንን ከድኅነት የሚለዩና የተሐድሶ አጋርነታቸውን የሚገልጡ ወገኖች አሉ፡፡ ተሐድሶዎቹ ከእንደዚህ ያሉ የጫኑዋቸውን ተሸክመው ለማስፈጸም ከሚደክሙ አካላት ጋር በመመሳጠር ዐውደ ምሕረትን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ነገር ግን በሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በጠንካራ ምእመናን ተጋድሎ ዓላማቸው አልተሳካም፡፡ ሰባክያነ ወንጌልን የሚመድቡትና የማስተማር ሓላፊነት የተሰጣቸው አንዳንድ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች በዐውደ ምሕረት ላይ ወጥተው ሲያስተምሩ ስለ ቅዱሳን ማስተማር የኢየሱስን ማዳን ይሸፍናል ሲሉ ይሰማሉ፡፡ የሚጋብዟቸው መምህራን ደግሞ ኢየሱስን ብቻ እንሰብካለን የሚል መፈክር አንግበው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ያልገባቸው ወይም አውቀው ለማደናገር የሚጥሩት ስለ ቅዱሳን መስበክ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መስበክ መሆኑን ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ አጥቢያዎች አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ገና በመቃኞ እያሉ እና አጸዱ እንኳን ቅጥር ሳይኖረው ሁሉም ቁሳቁስ የተሟላለት ዘመናዊ አዳራሽ የሚሠሩም አሉ፡፡ ለምን ተብለው ሲጠየቁ ለወንጌል ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ስለሆነÂ የሚል መልስ ያቀርባሉ፡፡ በእውነቱ የሰው ልጅ ድኅነት ማግኘት ገድዷቸው ይህን ቢያደርጉ መልካም ነበር፡፡ የእነሱ ዓላማ ግን ሌላ ነው፡፡ ሰዎች ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ እንዲቀሩ ማድረግ፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን አሳንሶ አዳራሾችን ዘመናዊ አድርጐ መገንባት የተሐድሶዎች አንድ ስልት ተደርጎ እየተሠራበት ነው፡፡ ይህንን አካሔድ የሚቃወሙትንየወንጌል ጸሮች እያሉ ይሳደባሉ፤ ምእመናን እንዲጠሏቸው ያደርጋሉ፡፡ ለአካሔዳቸው እንቅፋት ይሆናሉ ያሉዋቸውን በሓላፊነት የሚገኙ አገልጋዮች ማባረር፣ ያላጠፉትን ይህን ጥፋት ፈጸሙ በማለት የሀሰት ስም መስጠት፣ ማብልጠልና ከምእመናን ጋር ማጋጨት በአዲስ አበባ የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም በየፖሊስ ጣቢያውና በየፍርድ ቤቱ ሲጓተቱ የሚውሉ አገልጋዮች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ይህ አካሔድ በቶሎ መፍትሔ ካልተሰጠው ከቅዳሴ በኋላ ዐውደ ምሕረት ላይ ተአምረ ማርያም ሳይነበብ ምእመናን ወደ አዳራሽ እንዲገቡ መደረጉ የማይቀር ነው፡፡ እነዚህ እና የመሳሰሉት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሽፋን ተደርገው የሚሠሩ የተሐድሶ ቅሰጣዎች ናቸው፡፡
ሌላው ደግሞ በግልጽ የሚሠራው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፍል ውኃ አካባቢ የሚገኝ ተስፋ ተሐድሶ የሚባል ድርጅት አለ፡፡ ይህ ድርጅት ላለፉት ሦስትና ዐራት ዓመታት ከተለያዩ ቦታዎች ለተውጣጡ የገዳማት አበምኔቶች፣ የአብነት ትምህርት ቤት መምህራን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግሉ ቀሳውስትና ዲያቆናት ሥልጠና እየሰጠ በሰርተፊኬት አስመርቋል፡፡ ከ፳፻ወ፮ ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ፍኖተ ሕይወት ማኅበረ መድኀኔዓለም የተስፋ ተሐድሶ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚባል ተቋም ከፍቶ በዲፕሎማ ማስመረቅ ጀምሯል፡፡ ድርጅቱ ነሐሴ ፲፰ ቀን ፳፻ወ፮ ዓ.ም ደግሞ Integrated Theological Training and Skill Development for Africa ከሚባል ኮሌጅ ጋር በመተባበር የመጀመሪያ ዙር ዐሥር ተማሪዎችን በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ እና ዙሪያውን እንቅስቃሴ ስንመለከት በገንዘብ ጥማት ልቡናቸው በታወረ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ በተሐድሶ እንቅስቀሴ መረብ ውስጥ ባሉ ስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች እና በፕሮቴስታንት ድርጅቶች ጥምረት የሚካሔድ ነው፡፡ ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ለቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ደንታ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ባሉባቸው አጥቢያዎች እና ከተሐድሶዎች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ባሉባቸው አጥቢያዎች ዐውደ ምሕረቱ የሚፈቀደው ለኦርቶዶክሳውያን ሳይሆን ለተሐድሶ መናፍቃን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው እንቅስቃሴ በዚህ መልክ የሚቀጥል ከሆነ ከጊዜ በኋላ የተወሰኑ አጥቢያዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አይደለንም ማለታቸው የማይቀር ነው፡፡
ሰሜኑን ማእከል ያደረገ የተሐድሶ እንቅስቃሴ
ይህ እንቅስቃሴ የክርስትና መሠረት የተጣለበትን ሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ለማጥፋት ታቅዶ የሚካሔድ ነው፡፡ እንቅስቃሴው ጥንታውያን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በትምህርት ስም፣ በማኅበራዊ ልማቶች ስም፣ በእርቅና ሰላም ስም፣ ማረሚያ ቤቶችን እናግዛለን በሚል ስም ምእመናን እና ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ ፊታውራሪዎች ከሣቴ ብርሃን የተሐድሶ ድርጅት፣ መሠረተ ክርስቶስ ቸርችና የኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን መጥምቃዊት ቸርች ሲሆኑ በግለሰብ ደረጃ እንቅስቃሴው ውስጥ ታላቅ ሱታፌ ያላቸው ግለሰቦች አሉ፡፡
ከሣቴ ብርሃን ከመወገዙ በፊትም የትኩረት አቅጣጫው የነበረው ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ነበር፡፡ የከሣቴ ብርሃን ቅጥረኞቹ ጽጌ ሥጦታው፣ ሠረቀ ብርሃን ዘወንጌል፣ ጌታቸው ምትኩ፣ ባዩ ታደሰና ሙሴ መንበሩ ከአዲስ አበባ ተነሥተው በጎጃም በር ወጥተው ሥልጠና ሰጥተው፣ ቅኝት አድርገውና አዳዲስ ተከታዮች አፍርተው በሸዋ በር ይመለሳሉ፡፡ በ፳፻ወ፯ ዓ.ም ብቻ ሸኖ፣ አንጾኪያ፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር ሁለት ጊዜ እና አዲስ አበባ ላይ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና አብነት ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ በአጠቃላይ ከሁለት መቶ በላይ ለሚሆኑ ካህናትና የአብነት መምህራን ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ሥልጠናውን የሚወስዱት ሰዎች የሚመለመሉት በከሣቴ ብርሃን ቢሆንም ሥልጠናው የሚሰጠው በፕሮቴስታንት አዳራሾችና በፕሮቴስታንት ፓስተሮችም ነው፡፡
ከ፳፻ወ፭ ዓ.ም ጀምሮ ብሔራዊ ተሐድሶን አመጣለሁ እያለ ሌሎችን የተሐድሶ ድርጅቶች ሲቀሰቅስና ሲያስተባብር የነበረው ይኸው ድርጅት ባለፈው ዓመት የወንጌል አገልግሎት ማኅበራት ኅብረት የሚባለው እናት የተሐድሶ ድርጅት እንዲቋቋም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡ ስሙን በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ስም ሠይሞ ስለሚንቀሳቀስ የቤተ ክርስቲያን አካል መስሎ የሚታያቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ያለ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅናና ፈቃድ ከተከፈቱት የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች በተጨማሪ ፳፻ወ፬ ዓ.ም ላይ የተወገዘው ከሣቴ ብርሃን የተሐድሶ ድርጅትም መጥቅዕ የተባለ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊጀምር ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
ሁለተኛው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተሐድሶ እንቅስቃሴ ፊታውራሪ የሆነችው መሠረተ ክርስቶስ ቸርች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰሜኑን በወንጌል እንወርሳለን የሚል ፕሮጀክት ነድፋ እየሠራች ሲሆን ፕሮጀክቱ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ፈሰስ እየተደረገ የሚሠራ ነው፡፡ መሠረተ ክርስቶስ እንደሽፋን ተጠቅማ ሰሜኑ ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሠራው ሁለት ፕሮጀክቶችን ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሰሜኑን በወንጌልና የማረሚያ ቤቶች አገልግሎት የሚባሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ዋና የትኩረት አቅጣጫ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ እንቅስቀሴዎችን ታደርጋለች፡፡
ሰሜኑን በወንጌል የሚባለው ፕሮጀክት በትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃምና ሸዋ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የተለያዩ አጥቢዎች፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ የምታገኘው ከተለያዩ የውጪ ድርጅቶች (የፕሮቴስታንት) ከሚላክ ገንዘብ፣ በሚያውቋቸው ሰዎች ከውጪ ከሚሰበሰብ እርዳታ እና ያሠለጠኗቸውን ሰዎች በቪሲዲ በመቅረፅና እርሱን በማሳየት ከደጋፊ ዎች በሚገኝ ገንዘብ ነው፡፡ የመሠረተ ክርስቶስ የልማት ድርጅት (Meserete Kirstos Church Relief Development) የታላቁ ተልእኮ አገልግሎት አጋር ስለሆነ ከዚህ ድርጅትም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ይደረግላታል፡፡
የዚህ እንቅስቃሴ ዓላማ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ካህናት፣ ዲያቆናትና መሪጌቶች በገንዘብ በማታለል፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ ማንነታቸውን መለወጣቸው እንኳን ሳይታወቃቸው የተሐድሶ እንቅስቃሴው አጋርና ቀኝ እጅ እንዲሆኑ በማድረግ በውስጥ ሆነው የተሐድሶ ሥራ እንዲሠሩ ተልእኮ መስጠት ነው፡፡ ሥልጠና የሚሰጡላቸው ደግሞ የተሐድሶውን እንቅስቃሴ ዓላማ ብለው የያዙት እነ ሠረቀ ብርሃን ዘወንጌል፣ ጽጌ ሥጦታው፣ አግዛቸው ተፈራ፣ የዕድል ፈንታ፣ ታምራት፣ ፓ/ር ሰሎሞን ከበደ፣ ወዘተ ናቸው፡፡
በ፳፻፮ ዓ.ም ብቻ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ለመጡ ከሃምሳ በላይ ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወረዳ ቤተ ክህነት፣ ሊቃነ ካህናት፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ሥልጠና ሰጥታለች፡፡ ሥልጠናው በተለያዩ ዙሮች መሐል ሜዳ፣ አዲስ አበባና ደብረ ዘይት ላይ የተካሔደ ነበር፡፡ ስለ እርቅና ሰላም አስተምራለሁ በሚል ሰበብ የማሠልጠኛ ሰነድ አዘጋጅታ የራሷን ዶክትሪን እያስተማረች ነው፡፡ ለዚሁ ዓላማ በ፳፻ወ፯ ዓ.ም የብርሃን ፍሬ የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁማለች፡፡ የበጎ አድራጎቱ መመሥረት ዋና ዓላማ በልማት ስም ምንፍቅናን ማስፋፋት ሲሆን «ወንጌልን ማስፋፋት ዋና ዓላማችን ቢሆንም በውስጠ ታዋቂነት የሚሠራ እንጂ ከመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አይቀመጥም» በማለት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተቀመጡት የበጎ አድራጎት ማኅበሩ «የማስመሰያ» ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.የቂም በቀል፣ ደም የመመለስ ወይም የጥቁር ደም፣ የነፍስ ግድያ ባህልና ግጭትን እንደ ጀግንነት የመቁጠር ልማድን ለኅብረተሰቡ በማስተማር ማስወገድ፣
2.ኋላ ቀር የሥራ ባህልን፣ ከአቅም በላይ መደገስንና አባካኝነትን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን፣ የትዳር መፍረስንና የቤተሰብ መበተንን፣ ለዕድገትና ለሰላም ጠንቅ የሆኑ አስተሳሰብ አመለካከትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ኅብረተሰቡን በማስተማርና በማማከር ማስወገድ፣
3.በልዩ ልዩ ሱሶችና መጥፎ ልማዶች ተጠምደው ጎጂ ልማደኛ ሆነው ጎዳና ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ካሉበት ሱስና መጥፎ ልማድ እንዲወጡ መርዳት፣
4.የአቅም ግንባታ የመልካም ሥራ ሠርቶ ማሳያ ልማቶችን መሥራት ናቸው፡፡
በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በእርዳታ ሰበብ በመግባት በሃምሳ ስድስት (፶፮) ማረሚያ ቤቶች ላይ የእምነት ማስፋፋት ሥራ እየሠራች ሲሆን ታራሚዎቹ ሲወጡ በሚሔዱበት ቦታ የራሳቸው «ቸርች» እንዲያቋቁሙ ተልእኮ ትሰጣለች፡፡ በሃያ አንዱ (፳፩) ማረሚያ ቤቶች ደግሞ መደበኛ ሠራተኞች ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ተቀጣሪዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዲቁናና በሰንበት ትምህርት ቤት ሲያገለግሉ የነበሩ ተሐድሶዎች ናቸው፡፡ ስውሩ የእምነት ማስፋፋት ሥራቸው እንዳይጋለጥ የተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች ላይ የልማት ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ የተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች ላይ ቤተ መጻሕፍትና ካፍቴሪያ ሠርተው ሰጥተዋል፡፡ ለታራሚዎች የልብስና የሳሙና እርዳታ ያደርጋሉ፡፡
መሠረተ ክርስቶስ ከእነዚህ ሁለት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በትምህርትና አቅም ግንባታ፣ በምግብ ዋስትና፣ በልማት፣ የተፈጥሮ አደጋን እና ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከል ስም በመግባት ምእመናንን የመቀሰጥ ሥራ ትሠራለች፡፡ አዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት፣ ሆለታ፣ ማርቆስ፣ ሜታ ሮቢ፣ መሐል ሜዳ፣ ጀልዱ፣ ቀዋ ገርባ፣ ወዘተ እነዚህ ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ የሆኑባቸውና ውጤት ያመጡባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ማንም ኢትዮጵያዊ አይቃወምም፣ ነገር ግን በልማት ስም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን በመንጠቅ፣ ከማንነቱ መለየትና ከርስት መንግሥተ ሰማያት በኣፍአ እንዲቀር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ እኛ የምንቃወመውም ርዳታውን እና ልማቱን ሳይሆን ከልማቱ በስተጀርባ ያለውንና ሰውን ከሃይማኖት መለየቱን ነው፡፡
የኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን መጥምቃዊት ችርች ደግሞ በትምህርት ዘርፍ ላይ ተሰማርታ ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሠራ ናት፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤት በመክፈት በቅናሽ ዋጋ እና ለወላጆች በሚደረግ ድጋፍ ስም የራሷን የእምነት ማስፋፋት ሥራ እየሠራች ነው፡፡ እስካሁን የእንቅስቃሴው አድማስ በሰሜን ሸዋ ዞን ዓለም ከተማ ወረዳ ላይ ቢሆንም ከተነደፈው ፕሮጀክትና ይዘውት ከተነሡት ግብ አንጻር በዚህ እንደማያቆም ግልጽ ነው፡፡
ሌላው መነሣት ያለበት ጉዳይ ባለፉት ቅርብ ዓመታት ትግራይ አካባቢ እየተካሔደ ያለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ማኅበረ ሰላማ መወገዙ የሚፈልገውን የቅሰጣ ተግባር ከመሥራት አልከለከለውም፡፡ እንዲያውም አድማሱን አስፍቶ ከምእመናን ወጥቶ በየዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎችን እና የቅዱስ ፍሬምናጦስ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትን በመሰብሰብ በሥውር ማሠልጠንና ማስተማር ጀምሯል፡፡ ከማኅበረ ሰላማ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት ትግራይ ተሐድሶ መንፈሳዊ ማኅበር (ቤተ ክርስቲያን) የሚባል የተሐድሶ ማኅበር ተመሥርቷል፡፡ ይህ ማኅበር ደንብ ቀርጾ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን እየተካሔደ ያለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ አድማሱ ምን ያህል ሰፊ እንደ ሆነና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ምን ያህል ትኩረት እንዳደረጉበት ነው፡፡
የአንድ አገር ልማትና ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ የሚደርሰው የሃይማኖት፣ የዘር፣ የቀለም ገደብ ሳይገድበው በተባበረ ክንድ ሲሠራ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ የአገሩን ልማትና የኅብረተሰቡን ዕድገት የሚጠላ አይሆንም፡፡ ሆኖም የልማቱ ተባባሪዎች ነን የሚሉ አካላት ፊት ለፊት ሰውን የሚያሳሱና መልካም የሚመስሉ ነገሮችን እያሳዩ ውስጣቸው ግን በማር የተለወሱ መርዞች ይዘውና ሌላ ተልእኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ልማቱም ልማት፣ ዕድገቱም የተሟላ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሕዝብ ለአገሩ ክብር፣ ለሃይማኖቱ ፍቅር፣ ለማኅበራዊ እሴቱ ዋጋ ከሌለው ማልማትም ማደግም አይችልምና፡፡
እስካሁን ያየናቸው በልማት ስም የተሠሩት ሥራዎች ደግሞ ውስጣቸው ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ሴራ ያነገቡ የራስን አስተሳሰብና እምነት በሌ ሎች ላይ ለመጫን ዓላማ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሔድ ግን ፍትሐዊም ሃይማኖታዊም አይደለም፡፡ ልማትን እንደ መሸፈኛ ተጠቅመው የቀረቡት ከላይ የጠቀስናቸው ተግባራትም በቤተ ክርስቲያን ላይ የተነጣጠሩ የጥፋት ተልእኮዎች እንጂ አማናዊ ልማቶች ስላልሆኑ ዝም ተብለው መታየት የለባቸውም፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጋዜጣ፣ 23ኛ ዓመት ቁጥር 3፣ ቅጽ 23 ቁጥር 331፣ ከጥቅምት 16-30 ቀን 2008 ዓ.ም
0 comments:
Post a Comment