• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday, 24 March 2016

    የማኅበረ ቅዱሳን ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ ቅድመ ዝግጅት ሒደት እውነታዎችና ቀጣይ ወቅታዊ ጥረቶች

    በታቀደው መርሐ ግብር የማካሔድ ጥረቱ ዛሬም ተጠናክሮ ይውላልዛሬ ከቀኑ 10፡00 በዋናው ማእከል ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣልየዝግጅቱ ቀጣይነት፣ ጊዜና ቦታ የሚታወቀው በሚሰጠው መግለጫ ነው


    ጳጉሜን 5 ቀን 2007 ዓ.ም. – የማኅበሩ የሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት፣ ማኅበሩ በአራት ዓመት ስትራተጅያዊ ዕቅዱ ያካተተውን የዐውደ ርእይ ልዩ ዝግጅት ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማሳሰቡን በመጥቀስ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍለት ጠየቀ፤

    ጳጉሜ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. – የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የዝግጅቱን መካሔድ ፈቅዶ፥ “ከዚኽ በፊት እንደተለመደው ኹሉ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ” በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም በመጠየቅ ለኤግዚቢሽን ማዕከል እና የገበያ ልማት ድርጅት የድጋፍ ደብዳቤ ጻፈ፤

    መስከረም 03 ቀን 2008 ዓ.ም. – የማኅበሩ ጽ/ቤት በዋና ጸሐፊው፣ የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ደግሞ በዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነትበስድስት አንቀጾች የተዘረዘረ የአገልግሎት ውል በመፈራረም የጠቅላላ ዋጋውን 35 በመቶ ብር 200 ሺሕ ቅድመ ክፍያ ፈጸመ፤

    ጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም.፡- የ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ ዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴ፣ በማኅበሩ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ተቋቋመ፤

    ከአንድ ሺሕ በላይ የሰው ኃይል በማቀፍ በአምስት ዋና ዋና ክፍሎች (የትዕይንት ዝግጅት፤ የማስታወቂያና ቅስቀሳ፤ የሥነ ሥርዓት፣ የአዳራሽ እና የቴክኒክ አካላት) የተዋቀረው ዐቢይ ኮሚቴ፣ ጊዜያዊ ጽ/ቤቱን በዋናው ማእከል አንደኛ ፎቅ ከፍቶ የድርጊት መርሐ ግብሩን በማጸደቅ ሥራውን ጀመረ፤

    ታኅሣሥ ወር 2008 ዓ.ም.፡- ዐቢይ ኮሚቴው የልዩ ዐውደ ርእዩን ዝግጅት ለብዙኃን መገናኛዎች እና እንደ ሐዊረ ሕይወት ባሉ የብዙኃን መድረኮች በሰፊው በማስተዋወቅ የመግቢያ ትኬት ሽያጭ ማካሔድ ጀመረ፤

    ጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- ዐቢይ ኮሚቴው፥ “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን: አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ!!” የሚለውን የዐውደ ርእዩን መሪ ቃል እና መለዮ(ሎጎ) በዋናው ማእከል ጽ/ቤት አዳራሽ ከ300 በላይ እንግዶችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አደረገ፤

    ጥር እና የካቲት፤ 2008 ዓ.ም.፡- ዐቢይ ኮሚቴው፥ የማኅበሩን የሥራ አመራር እና የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ እንዲኹም የዝግጅት ኮሚቴውን አባላት ጨምሮ ፍላጎቱ ያላቸው ተሳታፊዎች ኹሉ በተገኙበት፣ በየሳምንቱ ረቡዕ ባዘጋጀው የግምገማ መድረክ፣ የአራት ትዕይንቶችንና የልዩ ክውን ጥበባት መሰናዶውን ጠቅላላ ይዘትና አቀራረብ በተደጋጋሚ በማስተቸት ዝግጅቱን አጠናቀቀ፤

    መጋቢት ወር መባቻ ሳምንታት፡- ዐቢይ ኮሚቴው በአገልግሎት ውሉ መሠረት የአዳራሾች ዝግጅት እና የትዕይንት ክፍሎች ዐቅዱን (floor plan and partition design) ለኤግዚቢሽን ማዕከሉ አስተዳደር በማቅረብ የቴክኒክ ክንውኑን በጋራ ቀጠለ፤ የትዕይንቱን ቁሳቁሶችም ማጓጓዝ ተጀመረ፤

    መጋቢት 12 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- በተፈጸመው የአገልግሎት ውል የክፍያ ኹኔታ አንቀጽ 4 መሠረት ማኅበሩ ቀሪውን ብር 400 ሺሕ ያኽል የመጨረሻ ክፍያ ለኤግዚቢሽን ማዕከሉ አስተዳደር ፈጸመ፤

    መጋቢት 14 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- በአገልግሎት ውሉ መሠረት፣ ዐውደ ርእዩ ከመጋቢት 15 – 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ክፍት ኾኖ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናት ለሥራ የሚያገለግለውን ጊዜያዊ ቢሮ ቁልፍ ዐቢይ ኮሚቴው ከማዕከሉ አስተዳደር ተረከበ፤

    መጋቢት 14 ቀን ረፋድ 3፡50፡- የተረከቡትን ቢሮ ለሥራ ዝግጁ በማድረግ ላይ የነበሩ የዐቢይ ኮሚቴው የአዳራሽ እንዲኹም የቅስቀሳና ማስታወቂያ ክፍሎች ሓላፊዎች ወደ ማዕከሉ የዋና ሥራ አስኪያጅ ቢሮ በጸሐፊዋ አማካይነት በድንገት ተጠሩ፤

    ሓላፊዎቹን ከኹለት ባልደረቦቻቸው ጋር የተቀበሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፥“በአካሔድ ላይ ክፍተቶች ስላሉ በአስቸኳይ ተሰብስበን መነጋገር ስላለብን ነው ያስጠራናችኹ፤” በማለት ዐውደ ርእዩን ለማካሔድ ፈቃድ ስለመኖሩ ጠየቁ፤ማኅበሩ ዕውቅና ከሰጠውና ተጠሪ ከኾነለት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የፈቃድ ደብዳቤ ማጻፉንና ከማዕከሉ ጋር ከሰባት ወራት በፊት ውል ተፈራርሞ አስፈላጊውን ክፍያ መፈጸሙን የጠቀሱት የዐቢይ ኮሚቴው ሓላፊዎች፣ ቀደም ሲል በማዕከሉ የተስተናገዱት ሦስት ዐውደ ርእዮችም በዚኹ አሠራር መሠረት መካሔዳቸውን በማስታወስበማኅበሩ በኩል የሰነድ ይኹን የአካሔድ ክፍተት እንደሌለ አስረዱ፤

    መጋቢት 14 ቀን ረፋድ 4፡40 – 6፡00፡– የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተጨማሪ የአስተዳደር ኮሚቴ አባላትን በመያዝ ከማኅበሩ አመራሮች እና አስፈጻሚዎች እንዲኹም ከዐቢይ ኮሚቴው አባላት ጋራ ባካሔዱት አስቸኳይ ስብሰባ፥ “ከአዲስ አበባ አስተዳደር ዐውደ ርእዩን ለማካሔድ የምትችሉበት የፈቃድ ደብዳቤ አምጡ፤” በሚል “የአካሔድ ክፍተት”ያሉትን አስታወቁ፤

    ማኅበሩ ዐውደ ርእዩን ለማካሔድ ፈቃድ ማቅረብ ያለበት ዕውቅና ከሰጠውና ተጠሪ ከኾነለት አካል መኾኑን ጠቅሰው ማኅበሩም ይህንኑ የድጋፍ ደብዳቤ በወቅቱ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ አግኝቶ ያቀረበ በመኾኑ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ማጻፍ አለበት የተባለው ፈቃድ፥ በማዕከሉ አሠራር ያልተለመደ፣ በወቅቱ ያልቀረበ እና ጨርሶም ሕጋዊ አግባብነት እንደሌለው ተወካዮቹ አስረዱ፤የሚመለከታቸውን የከተማውን አስተዳደር ሓላፊዎች ለማነጋገር ከቀትር በኋላ በተደረገው ጥረትም፣ ለዐውደ ርእዩ ከአስተዳደሩ እንዲጻፍ ስለተጠየቀው የፈቃድ ደብዳቤ የሚያውቀው ነገር እንደሌለና አሠራሩም በአስተዳደሩ የሕግ ማህቀፍ እንደሌለውለማረጋገጥ ተቻለ፤ለሰላማዊ ሰልፍ እና ለስብሰባ ፈቃድ በመስጠት ከሚታወቀው የከተማው አስተዳደር አጽፉ፤ በሚል የተጠየቀው የፈቃድ ደብዳቤ አሠራር፣ አራት ዐውደ ርእዮችን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዕውቅና እና ፈቃድ ሲያካሒድ ለቆየው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ አካል ማኅበረ ቅዱሳን፥ ሊቀርብ የማይችል፤ በኤግዚቢሽን ማዕከሉ አሠራር ያልተለመደ መኾኑንና በማኅበሩ በኩልም አንዳችም የአካሔድ ክፍተት እንደሌለ ከማዕከሉ አስተዳደር ጋር መተማመንና መግባባት ላይ ተደረሰ፤

    ይኹንና ተሲዓት በኋላ 9፡30 ገደማ፣ የኤግዚቢሽን ማዕከሉ አስተዳደር፣ በቁጥር ኤማ/1085-520-21/08 በዋና ሥራ አስኪያጅ ታምራት አድማሱ “አስቸኳይ” በሚል ለማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ ዛሬ ሊካሔድ የነበረው ዐውደ ርእይ “ከፈቃድ ጋር በተያያዘ ያልተሟላ በመኾኑ” በሚል ዝግጅቱን ለማካሔድ አስቸጋሪ በመኾኑ መሰረዙን አስታወቀ፤በልምድ ያልነበረንና በሕግም የማይታወቅን አሠራር ከጊዜው ውጭ በመጨረሻው ሰዓት የጠየቀውን ትክክለኛ አካል ማንነት በማወቅ፣ የመክፈቻ ጊዜው እክል የገጠመውን ዐውደ ርእይ በመርሐ ግብሩ መሠረት ለማስቀጠል በየፊናው ጥረት ሲያደርግ ያመሸው የማኅበሩ የሥራ አመራርና የሥራ አስፈጻሚ እንዲኹም የዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴው ለጋራ ምክክር አስቸኳይ ስብሰባ በመቀመጥ ሌሊቱን አጋምሷል፡፡

    መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- ወራትን ባስቆጠረው መርሐ ድርጊት መሠረት ከብር 2 ሚሊዮን በላይ የቅድመ ዝግጅት ወጪ የተደረገበት ልዩ ዐውደ ርእዩ፥ ዛሬ፣ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በሚከናወነው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ለሕዝብ እይታ ክፍት የሚኾንበት ዕለት ነበር፤

    የማኅበሩ አመራርና ዐቢይ ኮሚቴው ይህንኑ መርሐ ግብር አስቀድሞ በታቀደው መሠረት ለማስቀጠል የሚያደርገውን ጥረት ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲኾን፤ ውሎውንና የደረሰበትን ውጤት ከቀትር 6፡00 ጀምሮ በማጠቃለልና በመገምገም አንድ ውሳኔ አድርጎ ከቀኑ 10፡00 ላይ በዋናው ማእከል ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ማኅበሩ፣ የልዩ ዐውደ ርእዩን እውንነት፣ ትክክለኛ ጊዜና ቦታም፤ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫው ለምእመኑ በይፋ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡

    ለቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አስተህምሮ፣ ለኦርቶዶክሳዊነት ዓለም አቀፋዊነትና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲኹም ከቤተ ክርስቲያን ነባራዊና ወቅታዊ ተግዳሮቶች አንጻር ከምእመኑ ለሚጠበቀው ድርሻ ልዩ ትኩረት የሰጠው ልዩ ዐውደ ርእዩ፣ ከመቶ ሺሕ በላይ ተመልካቾች እንደሚጎበኙት ግብ የተያዘበት ነው፤ ከ40‚000 በላይ የመግቢያ ትኬቶችን አስቀድመው የገዙ ምእመናንም የመጀመሪያዎቹ ጎብኚዎች ለመኾን በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቁታል፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የማኅበረ ቅዱሳን ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ ቅድመ ዝግጅት ሒደት እውነታዎችና ቀጣይ ወቅታዊ ጥረቶች Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top