• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 6 December 2015

    ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ክፍል 2


    5:- ወእቀውም ዮም በትህትና ወበ ፍቅር በዛቲ ዕለት ቅድመ ዝንቱ ምስጢር ግሩም: ዮምና በዛቲ ዕለት አንድ ወገን: ቀድሶ ያቆረበባት ቀን ናት: እንደጠሉኝ ልጥላቸው እንደናቁኝ ልናቃቸው ሳልል በፍቅር በትህትና ጸንቼ ግሩም በሚሆን በስጋው በደሙ ፊት እቆማለው::
    ሐተታ:- ስጋው ደሙን ምስጢር አለው ከአምስቱ አዕማደ ምስጢር አንዱ ምስጢረ ቁርባን ነውና:: አንድም ከሃጥያት ነጽቶ ቢቀበሉት በልሳነ ነፍስ ያናግራልና:አንድም ሲለወጥ አይታይምና: ለበቁትም ሰዎች ስንኳ ከተለወጠ በኋላ ነው እንጂ ሲለወጥ አይታይምና: አንድም የወድያኛውን ምስጢር ይገልጣልና ግሩም አለ: በሚገባ ቢቀበሉት ግሩም ጸጋ ያሰጣልና: በሚገባ ባይቀበሉት ግሩም ፍዳ ያመጣልና: አንድም ግሩማን መላእክት ከበውት ይቆማሉና አንድም ከሃጥያት ነጽቶ ቢቀበሉት ግሩም ምስጢርን ይገልጻልና: አንድም የአምላክ ስጋ የአምላክ ደም አይገርም ማን ይገረም: አንድም የሚወደድ ሲል ነው: ኢትርዓይ ግርማ ርእየቱ ለኤልያብ እንዲል አንድም ልዩ ሲል ነው: ግሩም ምክሩ እመጓለ እመ ህያው እንዲል::

    ወቅድመ ዝንቱ ማዕድ ወቁርባን ዐ ማእድም ያለው ስጋው ደሙ ነው: ሐተታ:- ማእድ አለው ማእድ ስጋዊን ከበው እንዲመገቡት ይህንም አእሩግ ህጻናት ከበው ይቀበሉታልና: አንድም ለማእድ ስጋዊ ሰው እንዲመረጥለት ለዚህም የበቃና ያልበቃ ይመረጥለታልና አንድም ማዕደ ነፍስ ነውና ቁርባን እንዳለፈው: አንድም ማእድ ጻህል ጽዋው ቁርባን ስጋው ደሙ ነው ::

    6:- በአማን ቁርባን ውዕቱ ዘእይክሉ ይጥዐሙ እምኔሁ ግሙናነ መንፈስ ልቦናቸውን ሰውነታቸውን በሃጥያት ያሳደፉ ሰዎች ሊቀበሉት የማይገባቸው መለኮት የተዋሃደው እውነተኛ ቁርባን ነው:

    ሐተታ:- ማን ይከለክላቸዋል ቢሉ ራሳቸው ፈርደው ይከለከላሉና አንድም ቄሱ ይከለክላቸዋልና አንድም እግዚአብሔር በምልዓት በልቡናቸው አድረው ይከለክላቸዋልና: ህዝቡ ያልበቁ ልዑካኑ የበቁ የሆኑ እንደሆነ የህዝቡን ለልዑካኑ ይደርብላቸዋል: ልዑካኑ ያልበቁ ህዝቡ የበቁ ይሆኑ እንደሆነ የልዑካኑን ለህዝቡ ይደርብላቸዋል ህዝቡም ልዑካኑም ያልበቁም የሆኑ እንደሆነ መልአክ ወስዶ በበርረሃ ለወደቁ ባህታውያን ያቀብላቸዋል: ምግብ ሁኑአቸው የሚኖር ቅሉ ይህ ነው: ያም አያውቅም ይህም አያውቅም ያ እንዳይታበይ ይህ ከቀቢጸ ተስፋ እንዳይደርስ ነው::

    አኮ ከመ መስዋእቶሙ ለቀደምት አበው ዘበደመ በግዕ ሐርጌ ወላህም:: በደመ በግዕ በደመ ላህም የቀደሙ ሰዎች ይሰውት እንደነበረ መስዋእት አይደለም: አንድም የቀደሙ ሰዎች በደመ ላህም በደመ በግዕ ይሰዉት እንደነበረ መስዋዕት አይደለም::

    ሐተታ:-ሃርጌን ለበግ የቀጸሉ እንደሆነ ሙክት በላህም የቀጸሉ እንደሆነ ጊድር ማለት ነው::

    7:- አላ እሳት ውዕቱ:: መለኮት የተዋሃደው ቁርባን ነው እንጂ እሳት መለኮት የተዋሃደው ቁርባን ነው እንጂ:እሳት ማህየዊ ለርቱአነ ልብ ለዕለ ይገብሩ ፈቃዶ:: ለና ለ አንድ ወገን እሳትም ብዬ ብላችሁ አንድነቱን ሶስትነቱን አውቀው ህማሙን ሞቱን አምነው ሃጥያታቸውን ለመምህረ ንስሓ ነግረው መምህረ ንስሃ ያዘዘውን ሰርተው በሚገባ ለሚቀበሉ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው::
    ሐተታ:- እሳት በመጠን የሞቁት እንደሆነ የበሉት የጠጡትን ያስማማል: ደዌ ይከፍላል: ይህም ከሃጥያት ነጽቶ ቢቀበሉት ይህወተ ስጋ ህይወተ ነፍስ ይሆናል: ደዌ ነፍስ ያርቃልና::
    እሳት በላዒ ለአማጽያን ለእለ ይክህዱ ስሞ:: ለና ለ አንድ ወገን ነው እሳት ማህየዊም ብላችሁ ስመ አምላክነቱን ለሚክዱ ሰዎች የሚያቃጥል እሳት ነው::

    ሐተታ:- ስመ አምላክነቱን ከካዱ የማን ስጋ የማን ደም ብለው ይቀበሉታል ቢሉ ስመ ቁርባንነቱን ለሚክዱ ሰዎች::
    ሐተታ:- ስመ ቁርባንነቱንስ ከካዱ ምን ይረባናል ምን ይጠቅመናል ብለው ይቀበሉታል ቢሉ በግብሩ መካድ አለና::ከሃጥያት ሳይነጹ ቢቀበሉት በፍዳ ላይ ፍዳ የሚያመጣ ስለሆነ እሳት ነበልባሉ ከወረደው ፍህሙ ከመረተው ቀርበው ያለመጠን ቢሞቁት ያቃጥላል ይህም በማይገባ ቢቀበሉት ፍዳ ያመጣልና:: ወይእዜኒ ዘበልዖ ለዝንቱ ህብስት: ወዘሰትዮ ለዝንቱ ጽዋ እንዘ እይደልዎ ደይኖ ወመቅሰፍቶ በልዓ ለርእሱ መንሱትኬ ነሢአ ሥጋሁ በድፍረት ወተመጥዎ ደሙ ዘእንበለ ሃፍረት እንዘቦ ላዕሌሁ ነውረ ሃጥያት እንዲል::ከዚህም ስጋውን ከእሳተ ባቢሎን ደሙን ከማየ ግብጽ ምሳሌ አምጥተው ይናገራሉ: እሳተ ባቢሎን ሰልስቱ ደቂቅን ሳይነካ በአፍአ ያሉ የባቢሎንን ሰዎች አቃጥሎአቸዋል ስጋውም ከሃጥያት ነጽተው የሚቀበሉትን ያድናቸዋል ከሃጥያት ሳይነጹ የሚቀበሉትን ያጠፋቸዋልና ማየ ግብጽ በግብጻውያን ሲለወጥባቸው በእስራኤል አልተለወጠባቸውም ደሙም ከሃጥያት ነጽተው የሚቀበሉትን ያድናቸዋል ከሃጥያት ሳይነጹ የሚቀበሉትን ያጠፋቸዋልና ዛሬም ቀሳውስት ይህን ምሳሌ ይዘው የበደላችሁትን ሳትክሱ የቀማችሁትን ሳትመልሱ ከሃጡያት ሳትነጹ ሳትበቁ ብትቀበሉት ሥጋው ደሙ በነፍስ በስጋ ያስፈርድባችኋል እያሉ አዋጅ ይነግሩበታል::

    8:-በአማን እሳት ውዕቱ ዘኢይክሉ ለኪፎቶ እሳታውያን እለ ነደ እሳት እሙንቱ ኪሩቤል ወሱራፌል ከእሳት ከነፋስ የተፈጠሩ ኪሩቤል ሱራፌል ሊይዙት የማይቻላቸው መለኮት የተዋሃደው እውነተኛ ቁርባን ነው ተፈጥሮዋቸው ከእሳት ከነፋስ ነውና:: ወሶበ ኢያእኮትኮ ለዘፈጠርከ እምነፋስ ወነድ ፈጠረ ህየንቴከ ሰንአ ዘማሬ እማይ ወእመሬት እንዲል::
    ሐተታ:- ከእለተ ሰሉስ አስቀድሞስ ግብር እም ግብር የተፈጠረ ፍጥረት የለም: የመላእክትም ተፈጥሮ እምሃበ አልቦ ነው: ግብራቸውን ሲያይ እሳት ነፋስ ሃያላን ረቂቃን ፈጣኖች ፈጻሚያነ ፈቃድ ናቸው: መላእክትም ሃያላን ረቂቃን ናቸውና: ለተልኮ ይፋጠናሉና: የፈጣሪያቸውን ፈቃድ ይፈጽማሉና::
    ሐተታ:- እሳት ሰብዓ ሰዶምን ደቂቀ ቆሬን አጥፍቷል ነፋስም ብእሲት ዘማን ጥቅመ ሰናኦርን ሃራ ጰራግሞንን አጥፍቷልና አንድም የባለሟልነት ስማቸው ነው: እገሌ ነደ እሳት ባለሟል ነው እንዲሉ::
    ታሪክ:- ዘኢይክሉ ለኪፎቶ አለ ንጉሱ ዖዝያን ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ይባላል በቀኙ ይቀመጣል: ምነው በቀኜ ትቀመጥብኛለህ ይለዋል ወካህን ይነብር በየማነ ንጉሥ እንጂ ይለኛል ይለዋል:: ከልብሰ መግስቱ ልብሰ ክህነቱ ይበልጣል ምነው ከኔ የበለጠ ልብስ ትለብሳለህ ይለዋል ካህናቲከ ይለብሱ ጽድቀ እንጂ ይለኛል ይለዋል:: ፍርዱን ይገስበታል ምነው ፍርዴን ትገስብኛል ይለዋል እምነ መንግስት የአቢ ክህነት እንጂ ይለኛል ይለዋል አድርጎ ቤተ መንግስትም እያረካከሰ ቤተ ክህነትን እያነጋገሰ እየጠቃቀሰ ቢያውከው በዚያም በዚያም ቢሉ ቀንቶበት ከቤተ መንግስትማ ቤተ ክህነት ከበለጠ እኔስ ባባቴ ከቤተ መንግስት ብወለድ በናቴ ከቤተ ክህነት እውለድ የለምን ብሎ ማእጠንተ ወርቁን ይዞ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊያጥን ገባ: ሲያጥን ጢሱ ቢያርፍበት ከግንባሩ ለምጽ ተቀረጸበት በሻሽ ሸፈነው: ከሻሹ ላይ ወጣበት ለምጻሙን በእስራኤል ስንኳንስ በቤተ መቅደስ በከተማ አያኖሩትምና: እሱን አውጥተው ልጁን አንግሰዋል በዘመኑ የነበረ ነቢይ ኢሣያስ ነው ፈርቶ ሳይገስጸው ቢቀር ለምጽ ወቶበት ሃብተ ትንቢት ተነስቶት 3 አመት ከመንፈቅ ያህል ኖሯል ወእምዝ በዓመተ ሞተ ዖዝያን ንጉስ ርኢክዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ብሩህ ወነዋህ እንዲል: ዖዚያን በሞተበት ወራት ጌታ በመንበረ ጸባኦት እንዳለ ሆኖ ለኢሳያስ ታየው ያ ታፍረው ታከብረው የነበረው ንጉስ ሞተ አልፈ እኔ ግን እልፈት ውላጤ የለብኝም ሲል ሊያድነው ቢሻ መነ እፌኑ ሃበ ህዝብየ እስራኤል ሁሉ ራሱ ጠበቀ አንገቱን ቀበረ ወደወገኖቼ ወደ እስራኤል በመምህርነት ማንን ልስደድ አለ:: እስመ ማዕከለ ህዝብ ዘርኩስ ከናፍሪሆሙ ሃሎኩ አነ እስራኤል ለምጽ ይጸየፋሉ: ደግሞም ትንቢት ተነስቶብኛል እንጂ እኔ አልፈራም ነበር አለው: ወተፈነወ አሃዱ እምሱራፌል ወነስአ ፍህመ በጉጠት ወአልከፎ ከናፍሪሁ ወይቤ አእተትኩ ለከ ሃጥያተከ እንዲል መልአኩን ከአለመ መላእክት ፍህሙን በጉጠት ወስደህ አጉርሰው አለው:: ሃጥያተከ ቢል ለምጹን አራቅሁልህ ሃጥያትከ ቢል ትንቢቱን መለስኩልህ ሲል ነው:: 
    ከዚህ በኋላ ለምጹ ድኖለት ትንቢቱ ተመልሶለት እንደገና አስተምሯልና: ይህም ምሳሌ ነው መልአኩ የቀሳውስት ጉጠት የስልጣነ እግዚአብሄር እሳያስ የምእመናን ለምጽ የፍዳ የመርገም ፍህም የስጋ ወደሙ :: አንድም ከናፍረ ኢሳያስ የምእመናን መልአኩ የዲያቆን ጉጠት የእርፈ መስቀል ፍህም የደሙ ምሳሌ:: መላእክት ስጋውን ደሙን የሚይዙበት ስልጣን የላቸውምና: ዘኢይክሉ አለ: ዘኢተገብረ ለመላእክት ተገብረ ለካህናት የሚያሰኘው ቅሉ ይሄ ነው: አባ መቃርዮስ እንዳየው ስለ ንጽህናው መልአኩ የቄሱን እጅ ይዞ ለማርቆስ ዘዮናኒ ግብጻዊ ሲያቀብለው አይቷል::

    9:- ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ: ኦ ቃለ አክብሮ ቃለ አህስሮ ቃለ አራህርሆ ይሆናል: ቃል አክብሮ ኦ ድንግል ምልእተ ውዳሴ ብሎ የሚያመጣው ነው: ቃለ አራህርሆ ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ቃለ አህስሮ ኦ ሃናንያ ኦ አብዳን ሰብአ ገላትያ ነው:: በእንተዝ ያለፈውን አጠፈ እንደገና ብሎ መጽሃፍ ያለፈውንም የሚመጣውንም ማጠፍ ልማድ ነውና የሚመጣውን አጠፈ እመቤታችን ሆይ እናከብርሻለን እናገንሻለን::
    ሐተታ:- እኛ እሷን የምናከብራት የምናገናት ሆነን አይደለም ክብርሽን ገናንነትሽን እንናገራለን ሲል ነው::
    እስመ ወልድኪ ለነ መብልዓ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ህይወት ዘበአማን:: እውነተኛውን ምግብ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና ስላስገኘሽልን::
    ሐተታ:- ዘበአማን አለ ከመስዋዕተ ኦሪት ሲለይ ያ ስጋዊ ይህ መንፈሳዊ ያ አፍአዊ ይህ ውሳጣዊ ያ ምድራዊ ይህ ሰማያዊ ነውና:: አንድም የዚህ አለም ምግብ ጥዋት በልቶ ለማታ ማታ በልቶ ለጠዋት ያሻል ይህ ግን በሚገባ ከተቀበሉት በሃጥያት ካላሳደፉት ህማሙን ሞቱን ለማዘከር ነው እንጂአንድ ግዜ ከተቀበሉት በሌላ ግዜ አያሻምና:: አንድም የዚህ አለም ምግብ ሃሰር ይሆንል ይለወጥል በሱ ግን ይህ ሁሉ የለበትምና አንድም የዚህ አለም ምግብ ሞትን ያስከትላል ይህ ግን የዘላለም ህይወት ይሆናል አንድም ከማናዊት እመቤታችን ስለተገኘ መብልአ ጽድቅ ዘበአማን ውስቴ ህይወት ዘበአማን አለ:: ይቆየን .......ቸር ያቆየን!!!!!!

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    1 comments:

    1. ቅዳሴ ማርያም አንድምታዉን ጨርሱልንማ

      ReplyDelete

    Item Reviewed: ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ክፍል 2 Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top