• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday 2 March 2016

    የዐቢይ ጾም ጾም ስያሜዎችና ትርጉም


    ይህ ጾም የተለያዩ ስሞች አሉት፡፡

    1. ዓቢይ ጾም ይባላል፡- ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የዓርባ ቀን ጾም በመሆኑ እንዲሁም ዓቢይ እግዚአብሔር ወብዙኃ አኮቴቱ ዓቢይ እግዚአብሔር ወዓቢይ ኃይሉ የተባለ ጌታ የጾመው ስለሆነ መዝ. 47፡1፣ መዝ. 146፡5 ፡፡

    2. ሁዳዴ ጾም ይባላል፡- ሁዳድ ማለት ሰፊ የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥራ ሁሉ ሁዳዴ የሚባል ሲሆን፤ የሁዳዴ ጾም የተባለውም በጾም ቀናት 55 ቀናት ስለሚጾምና ጾሙንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመው ነው፡፡አሞ. 7፡1

    3. በዓተ ጾም ይባላል፡- ይህም ማለት የጾም መግቢያ፣ መባቻ ወይም ጾሙ የሚሰፍርበት በዓት ማለት ነው፡፡

    4. ጾመ አርባ ይባላል፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓርባ ቀን ስለ ጾመው ነው፡፡ ማቴ. 4፤1

    5. ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡- ይህም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ ጹሙ ብሎ ስላዘዘን

    6. ጾመ ሙሴ ይባላል፡- ይህ ደግሞ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ሰኞ ዕዝል ከመዝ ይቤ ሙሴ . . . ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት . . . እያለ በጾመ ድጓው ስለ ዘመረ ነው፡፡
    ዓቢይ ጾም መሠረቱ ጌታችን የጾመው 40 ቀን ሆኖ ከመነሻው በፊት አንድ ሳምንትና ከመጨረሻው በኋላ ደግሞ አንድ ሣምንት ታክሎበት /ተጨምሮበት/ 55 ቀኖች የምንጾመው ጾም ዓቢይ ጾም ይባላል፡፡ የመጀመሪያው አንድ ሳምንት የዝግጅትና የመለማመጃ ጊዜ ሲሆን፣ የመጨረሻው አንድ ሳምንት ደግሞ የጌታችን ሕማማት ሳምንት ለማስታወስ ነው፡፡ በሌላ በኩል የመጀመሪያው ሳምንት ሕርቃል ከተባለ ንጉሥ ጋር በማያያዝ ጾመ ሕርቃል የሚባል ስም መሰጠቱ የተለመደ ነው፡፡

    ጾም፡- ጾመ፤ ጦመ፤ እህል ውሃ ሳይቀምስ ዋለ፤ ከሥጋ ከቅቤ ተከለከለ ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ ያለው ሲሆን፤ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህልና ውኃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ /ዘጸ. 34፤28/ በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ ዮናስ 2፤7-10
    በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥራው መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡ /ማቴ. 4፤2፣ ሉቃ. 4፤2/ ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር መንፈስ ርኩስ ሰይጣን፤ በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ /ማቴ.17፡21፣ ማር. 9፡2 ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም በየጊዜው ከመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾም እና በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር፡፡ /ሐዋ.ሥራ 13፤2/ ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስትም የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ /የሐዋ. ሥራ 13፤3፣ 14፤23/ እነ ቆርኔሌዎስ ያላሰቡትን ያዩና ያገኙ የነበረው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ለምነው ነው፡፡
    በጾም ወራት ላምሮት፣ ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ፤ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ ሥጋና የሚያሰክሩ መጠጦችን /ዳን. 10፤2-3/ ቅቤና ወተት /መዝ. 108፤24/ ማራቅ እንዳለብን ታዝዟል፡፡ ባልና ሚስት በጦም ወራት በአልጋ አይገናኙም፡፡ /1ኛ ቆሮ. 7፤5፣ 2ኛ ቆሮ. 6፤6/ በጾም ወራት ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ዓይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፤ ጆሮ ክፉ ከመስማት መቆጠብ እንደሚገባ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው፤ ይጹም ዓይን፣ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሡም በተፋቅሮ ሲል ይገልጽልናል /ያስረዳናል፡፡/

    ዐቢይ ጾምን በተመለከተ ቀደም ሲል ወንጌላውያን የጻፉትን የጌታችን ጾም እንደሚከተለው እናያለን፡፡ /ማቴ. 4፡1-11፣ ሉቃ. 4፡1-13/ ኪዘያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፡፡ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ፡፡ ከተጠመቀ በኋላ መሄዱ እናንተም ተጠምቃችሁ ሳትውሉ ሳታድሩ ዕለቱን ጽኑ ሥራ ሥሩ፣ ለገድል ለትሩፋት ተዘጋጁ በማለት ለአብነት ለማስተማር ዕለቱን ሂዷል፡፡ ወደ ገዳም መሄዱም በብቸኝነት ባለበት በገነት አዳም ድል ተነስቶ ነበርና እርሱም በብቸኝነት ገዳም ውስጥ ተገኝቶ ዲያብሎስን ድልን ለመንሳት ነው፡፡ /ማቴ. 12፤29/

    ዘወረደ፡- 
    የዓቢይ ጾም መግቢያ የሆነው የሰኞ ዋዜማ እሁድና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ያለው የሚቀጥለው ሳምንት “ዘወረደ” ይባላል፡፡ ዘወረደ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መውረዱን የሚያመለክተው የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ስለሆነ ነው፡፡
    ያ በሰማያት የሚኖረው በእሳትና መብረቅ፣ በከባድ ደመናና ነጎድጓድ፣ በበረታ የቀንደ መለከትም ድምፅ ወደ ምድር የወረደውና በሙሴ መሪነት በምድረ በዳ ለሚጓዙት ለእስራኤል ልጆች በሲና ተራራ የተገለጠው እግዚአብሔር ብለን የምንጠራው ፈጣሪና የማይታየው አምላክ በመጨረሻ ዘመን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ሰው ሆኖና በበረት ተወልዶ፣ የመስቀል መከራን ተቀብሎና ሞቶ ተቀብሮና ተነስቶ ፍጥረተ ዓለሙን ከዲያብሎስ አገዛዝ ከኃጢአት ቀንበርና ከሞት ፍዳ ሊያድን ከሰማየ ሰማያት ወረደ ማለት ነው፡፡
    እንዲሁም ሙሴ በኢየሱስ ክርስቶስና በድንግል ማርያም ምሳሌ ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ቃላት፣ ትእዛዛትና / ጽላት/ ይዞ ከሲና ተራራ ወደ እስራኤል ሕዝብ የመውረዱን ዝክረ ነገር ለማስታወስ ዘወረደ ተባለ፡፡
    አምላክ አዳምን ለማዳን ከሰማይ መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱንና በመስቀል መስቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡ /ዘፀ. 3፤9፣ ዮሐ. 3፤11/ ሙሴኒም ይሉታል፡፡ ስለ ሙሴ ሕግና ጾም ሙሴን እየደጋገመ ስለሚያነሳ ነው፡፡
    በዚህም መሠረት የዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ተባለ፡፡

    ጾመ ሕርቃል፡-
    ይህ ሳምንት በሕርቃል ስም የተጠራበት ምክንያት በ714 ዓ.ም ሕርቃል የኤራቅሊዮስ/ የቤዛይንታን ንጉሥ በነበረበት ዘመን፤ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታችንን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደ ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡

     

    ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም ብለው ሥርዓት ሠርተው ነበርና እርሱም ጾሙን ፈርቶ ነበርና በኢየሩሳሌም የነበሩ ምዕመናን ይህን ሀሳብ ደግፈው የአንድ ሰው እድሜ ቢበዛ ሰባ ሰማንያ ነው፡፡ ጠላታችንን አጥፋልን እንጂ ጾሙን እኛ ተከፋፍለን እንጾማለን ባሉት መሠረት አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለው ጹመውለታል፡፡ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጹመው ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጹመውታል ብለው ሥርዓት አድርግው በዓመት በዓብይ ጾም መጀመሪያ ላይ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ ሰይማ እንዲጾም አድርጋዋለች፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የዐቢይ ጾም ጾም ስያሜዎችና ትርጉም Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top