• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday 2 March 2016

    ሰበር ዜና – መፍቀሬ ኢትዮጵያ ወገባሬ ሠናይ: የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐረፉ


    ሐራ ዘተዋሕዶ

    ሥርዓተ ቀብራቸው ከነገ በስቲያ በአሰላ ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ይፈጸማልበታኅሣሥ 1966 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቻንስለርኾነው ተሹመው ነበር“በሔዱበት ኹሉ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታቸውን ይጠብቃሉ፡፡ የሚኖሩት ግን ተዋርደው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እያሳፈረን ነው፡፡ በእውነት አባትህን ጠይቅ ይነግርሃል፤ ነው፡፡ አፍሪካውያን በሙሉ በቅኝ ግዛት ሲገዙ ኢትዮጵያውያን ለቅኝ ገዥዎች እጃቸውን ያልሰጡት በምን ምክንያት ነው ብለው የዛሬ ክርስቲያኖች በሙሉ ማጥናት አለባቸው፡፡” /ብፁዕ አቡነ ናትናኤል/

    *               *               *

    ነገ ቤተ ክርስቲያን ይከፍታል ብሎ ያሳደገኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የአቅሜን ያኽል ተምሬአለኹ፤ ቤተ ክርስቲያን አሳድጋኛለች፤ ባለውለታዬ ነች፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ውለታ አኹንም አልከፈልኩም፤ እስከሞት ቢኾን ውለታዋን ተሸክሜ ወደ መቃብር ከመግባት በስተቀር ውለታዋን አልከፈልኩም፤ ይኼን የምናገረው ከልቤ ነው፤ ኹሉም ውለታ አለበት፤ የቤተ ክርስቲያኑን ውለታ መመለስ አለበት(ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ፲፱፻፳፫ – ፳፻፰ ዓ.ም)

    “ነቢዩ ኤርሚያስ፥ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይለቅም፤ ይላል፤ ይህ ሊጠና ይገባል፡፡ እንባችንን እግዚአብሔር እስኪያብስልን ድረስ እኛ አባቶች ስንጸልይ የምናለቅሰው፥ ለነገዪቱ ኢትዮጵያና ለነገው ትውልድ ነው፤ በተለይ አኹን ያለው ትውልድ ያሳዝነኛል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ መለያየት ምን እንዳስከተለ ተረድቶት ይኾን? ከዚኽ ትውልድ መማር አለበት፡፡ እኛስ ይህን ዓለም እንሰናበተዋለን፤ ጥፋት እንዳይፈጸም፤ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊነቷን ደርዟን እንዳታጣ በእውነት እያለቀስኩ ነው፡፡” – ለሀገርና ለትውልድ በብዙ ከሚጨነቅ ልባዊ ስሜት የመነጨው የዚኽ ረቂቅና ጥልቅ ንግግር ባለቤት፥ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በላይ የአርሲ ሀገረ ስብከትን በተመሰገነ አባታዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት የመሩት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል ናቸው፡፡

    ብፁዕነታቸው፥“ኢትዮጵያውያን ኹልጊዜ ኢትዮጵያዊ መኾን አለብን፤ የኢትዮጵያን ጠባይ ይዘን መጓዝ አለብን፤” እንዳሉት፣ በሥጋዊ ዝምድና ሳያምኑ፤ “ውለታዋ አለብኝ” ያሏትን ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ንቃት በተመላበት ኹለገብነትና በብቃት ለማገልገል እንደጣሩ ተጋድሏቸውን ፈጽመዋል – ብፁዕነታቸው ትላንት፣ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡30 ገደማ ከዚኽ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡

    በአሰላ መኖርያ ቤታቸው በቅርብ በሚረዷቸው ወዳጆቻቸው እንደተከበቡ በሰላመ እግዚአብሔር ያረፉት ብፁዕነታቸው፣ ከኩላሊትና ስኳር ሕመም ጋር በተያያዘ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፤ ከሕመማቸው አገግመው በመልካም ጤንነት ላይ እንደነበሩ የተነገረ ሲኾን፣ ከዕረፍታቸው ሦስትና አራት ቀናት በፊት ምግብ መወሰድ አቁመው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

    በፊት ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ መዓዛ ቅዱሳን ገብረ ሕይወት የሚባሉት ብፁዕነታቸው፣ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ከተሾሙት 13 ኤጴስ ቆጶሳት አንዱ ሲኾኑ ምድብ ሀገረ ስብከታቸውም በቀድሞው አጠራር ትግራይ ክፍለ ሀገር ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ከዐሥር ዓመት በፊት ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አብርሃም ቤት ዓምድ በሰጡት ቃለ ምልልስ፥ “በመንግሥት ሥራ የባህል ሚኒስቴር ሲቪል ሰርቫንት ኾኜ እየሠራኹ በመናኙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን ለጵጵስና ታጨኹ፡፡ እኔ ጵጵስና ለመሾም ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡ ያኔ የነበረኝ ዓላማ በመጽሐፍ መምህርነቴ ጉባኤ አስፍቼ እንዳስተምር ነበር የምፈልገው፡፡ ምንኵስናን ተቀብዬ እንኳ ለጵጵስና ጉጉቱም ፍላጎቱም አልነበረኝም፤” ብለዋል፤ለመምህርነት ሞያ ከፍተኛ ፍቅር እንደነበራቸው ሲያስረዱ፡፡

    “አንድ ዕድል አገኘኹና ቅድስት ሥላሴ መምህራን ማሠልጠኛ ገባኹ፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ በማሠልጠኛው ሳሉ፣ በአባ ሐና ጅማ አቅራቢነትና በቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ በተፈሪ መኰንን ት/ቤት የግብረ ገብ መምህር ኾነው ተቀጥረዋል፡፡ በመምህርነት የመጡ “ኢየሱሳውያን ሚሲዮናውያን” በት/ቤቱ ሥር ሰደው ከጠንካራ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ጋር ግጭት በመፍጠራቸው የተቀጠሩት ብፁዕነታቸው፣ ከ1949 እስከ 1954 ዓ.ም. ድረስ አስተምረዋል፡፡ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አንጋፋውን የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት ከመሠረቱት አባቶች አንዱ ለመኾን የበቁትም በዚኹ ሥራቸው ላይ ሳሉ ነው፡፡ በወቅቱ ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳምም ቋሚ ሰባኬ ወንጌልም ነበሩ፡፡

    “የዚያን ጊዜ ገና አልመነኰስኩም፤ ልጅ ነበርኩ፤ ሐዲሳቱንም በቃሌ ስለማውቅ እንደ ብርቅ ድንቅ ኾኜ ነበር የምቆጠረው፤ እውነትም መዓዛ ይሉኝ ነበር፤ መዓዛ የሚለው ስም የወጣልኝ ቅኔ ቤት እያለኹ ነው፡፡ እናቴ ያወጣችልኝ ስም ካሳዬ ነው፡፡ የዚያን ጊዜ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የዛሬው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ነበር፤ የአልጋ ወራሹም ግቢ እዚያው ምስካየ ኅዙናን አጠገብ፣ የልዑል መኰንን ቤትም በአቅራቢያው ነበር፤ ደጀ ጠኚውም በአጠቃላይ የሚመጣው ምስካየ ኅዙናን ነበር፤ ብዙ ሕዝብ ስለሚመጣ ለስብከቱም የተመቸ ነበር::”


    አንደበተ ርቱዕና ጥልቅ አሳቢው ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ቤተ ክርስቲያናችን በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ በነበራት ፕሮግራም ያስተምሩ ነበር፤ በሕይወት ዘመናቸው ካከናወኗቸው ተግባራትለምእመናን በሬዲዮ ስብከተ ወንጌልን በማስተላለፍ የሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ – ቤተ ክርስቲያናችን በሬዲዮው ለ12 ሰዓት ትምህርት ትሰጥ ነበር፡፡ እኔ በሳምንት አንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና ማኅበራዊ ኑሮ በቤተ ክርስቲያን በሚል የማስተላልፈው ዝግጅት ነበረኝ፤ ሬዲዮ ጣቢያውን ደርግ እስከወረሰው ድረስ የሰጠኹት አገልግሎት በሕይወቴ የተደሰትኩበት ነው፡፡”

    ዛሬ በየአድባራቱ የተስፋፉት ዘመናዊ ት/ቤቶችትልም፣ በብፁዕነታቸው ሐሳብ አመንጪነት የተቋቋመው የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ት/ቤት ነው፡፡ ሐሳቡን እንዴት እንዳመጡት ሲናገሩ፣“በወቅቱ በውጭ ሀገር የሚሰጠውን የትምህርት ዘዴና ዘመናዊ ት/ቤትን ከቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ የማቋቋም ብልሃት ቀስሜ ስለመጣኹ የምስካየ ኅዙናን ት/ቤት እንዲቋቋም ሐሳብ አቀርቤ የተምሮ ማስተማር እና የመድኃኔዓለም ጽዋ ማኅበርተኞች እንዲገናኙ አደረግኹ፤” ብለዋል፡፡

    እንደዚኹም ኹሉ በዘመናዊው ትምህርት ዐሥረኛ ክፍል ሲደርሱ በንጉሡ ጥያቄና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አስፈጻሚነት ወደ ኢየሩሳሌም አንግሊካን ሴንት ጆርጅ ኮሌጅ ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ተልከው ለኹለት ዓመት ተኩልየቤተ ክርስቲያን ታሪክና አስተዳደር ተምረው ዲፕሎማ ይዘው ተመልሰዋል፡፡ ዲፕሎማቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርበውና አስገምግመው ዕውቅና እንዲሰጣቸውና ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም እንዲተላለፍ በማድረጋቸው፣ “ለቤተ ክርስቲያኗ ትምህርት ዋጋ እንዲሰጠው በር ከፍቼ ነበር” ይላሉ፤ ብፁዕነታቸው፡፡

    ከዚኽ በኋላ ብፁዕነታቸው፣ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በካህናት አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ ኾነው በ1958 ዓ.ም. ቢሾሙም በካቴድራሉና ወደ ምስካየ ኅዙናን ገዳም በበጎ ፈቃድ እየተመላለሱ ማስተማራቸውን አላቋረጡም ነበር፤ ይህም ከብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ የስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ጋር ተደማምሮ በ1961 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ወደ እንግሊዝ ኦክስፎርድ ኦስሄትሮፕ ኮሌጅ ለከፍተኛ ትምህርት ተልከዋል፡፡ ትምህርታቸውን ለአራት ዓመታት ተከታትለው በ/Bachelor of Diginity Basic Philosophy Supermental and Developmental Psychology/ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተው ተመልሰዋል፡፡

    ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አቅራቢነት በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ በታኅሣሥ 1966 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ኾነው እንዲያገለግሉ በወቅቱ የጽሕፈት ሚኒስቴር ተሹመው የነበረ ቢኾንም ከተማሪው እንቅስቃሴና ከአብዮቱ ለውጥ ጋር ተያይዞ “ርእዮተ ዓለሙ አይፈቅድም” በመባሉ ወደ ቤተ ክህነቱ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡

    ቀደም ሲል የነበሩት የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ለውጡን ተከትሎ በመታሰራቸው በቦታቸው የተተኩት ብፁዕነታቸው፣ የሐዋርያዊ ድርጅት ሓላፊና የሰበታ ቤተ ደናግል የበላይ ሓላፊ እንዲኾኑ በጽሕፈት ሚኒስቴር ቢሾሙም የለውጡ ማዕበል በሥራቸው ለመቀጠል አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል – ስብከት ሳስተምር “ደርግ አረማዊ ነው ብሏል” በሚል ተከሠው ጉዳያቸው እስከ ጦር ፍ/ቤት ደርሶ ለአንድ ዓመት ከሥራ ውጭ መደረጋቸውን ያስታውሳሉ፤ “በእኔ ላይ በሐሰት የሚመሠክር በመጥፋቱ ተለቀቅኹ፤ እኔ ያስተማርኩት ለሰላም እንጸልይ እያልኩ ነበር፤ ልታሰር የሚገባኝ በሥራ ፈትነቴ እንጂ በትምህርቴ አልነበረም” የሚሉት ብፁዕነታቸው፣ በሐዋርያዊ ተልእኮ መፈተን አይቀሬ መኾኑንና ይህም ከሐዋርያት በረከት እንደሚያሳትፍ ይመክራሉ፡፡

    ሰው ችግር አይገጥመውም አይባልም፤ ፈተናም አይጠፋም፡፡ ጠንካራ ማርክሲስቶች ነበሩ፡፡ እነርሱም ቤተ ክርስቲያንን ለመጣል ይታገሉ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እንዳትወድቅ፤ ሕዝቡም ሃይማኖቱም እንዲጠበቅ ትግል ውስጥ ነበርን፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ሐዋርያዊ ግዴታዬ ስለነበር እንደ ችግር አላየውም፤ ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት ከደረሰባቸው ጽዋ መካፈል ስለነበረብኝ ነው፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሰበር ዜና – መፍቀሬ ኢትዮጵያ ወገባሬ ሠናይ: የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐረፉ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top