• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 7 March 2016

    ቅዱስ ሲኖዶስ: ፓትርያርኩ ሕግ አክብረውና መዋቅር ጠብቀው እንዲሠሩ አስጠነቀቃቸው፤ በሰላም ጉዳዮች ዛሬ መግለጫ ያወጣል


    ሐራ ዘተዋሕዶ

    በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው መመሪያዎችና የጠሯቸው ስብሰባዎች ሕገ ወጥ ተብለዋልቋሚ ሲኖዶስ፥ የስምዐ ጽድቅን የፀረ ተሐድሶ ጽሑፍ ጨምሮ የተደረጉ መጻጻፎችን ይመረምራልየፓትርያርኩ ጉዞዎች፥ ስፖንሰር ተገኘበሚል ሳይኾን በቋሚ ሲኖዶሱ ማስወሰን ይኖርባቸዋል


    ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ መዋቅር ጠብቀው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑና ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ በቅዱስ ሲኖዶስ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡

    ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ከቀትር በኋላ ባካሔደው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጽሑፎች ላይ ቀርበዋል ለተባሉ አቤቱታዎች የነበራቸውን አያያዝ፣ የወሰዷቸውን አቋሞችና የሰጧቸውን ምላሾች ገምግሟል፡፡

    ፓትርያርኩ አቤቱታዎቹን ለመመልከት በሚል በራሳቸው የጠሯቸው የኮሌጆችና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች ሓላፊዎች ስብሰባዎች፤ ማእከላዊ አሠራርን ያልጠበቁና አድሏዊ እንደነበሩ ጉባኤው ተችቷል፡፡ ከዚኽም ጋር በተያያዘ ፓትርያርኩ፣ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በተጻፉ ደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳንላይ ያስተላለፏቸው የክሥና የቅስቀሳ መመሪያዎችየቅዱስ ሲኖዶስን የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መንፈስ የሚፃረሩና ሕገ ወጥ መኾናቸውን ያረጋገጠ ሲኾን በስብሰባዎቹ ወጥተዋል የተባሉ የአቋም መግለጫዎችም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተገልጧል፡፡

    ፓትርያርኩ ዛሬ ለተጀመረው ዐቢይ ጾም ባለፈው ሳምንት ዓርብ መግለጫ በሰጡበት አጋጣሚ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በብፁዕ ዋና  ጸሐፊው አማካይነት በጠራው በዚኹ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በኃይለ ቃል ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፤ ማኅበሩንም በተመለሱ ጥያቄዎችና በአሉባልታዎች ወንጅለዋል፡፡ “የማኅበሩ አባላት ናችኹ፤ ሒዱ ስላላችኹ ነው የመጣችኹት” በማለት የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ማኅበሩንም “ሀብታሞች ኾነዋል፤ ከመንግሥትም ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ መንግሥት ይረዳቸዋል፤” እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡

    ተንኮል የተሸረቡባቸውንና በክፋት የተሞሉ መረጃዎችን ሳያጣሩና ሳይመዝኑ እንደተነገራቸው የሚያስተጋቡት ፓትርያርኩ፣ እኒኽን ኃይለ ቃላት የተናገሩበት የረፋድ ወኔ ግን አብሯቸው አልዘለቀም፡፡ ስብሰባው ከቀትር በኋላ ሲጀመር አንሥቶ ከፍተኛ መደናገጥ ታይቶባቸዋል፡፡ ማእከላዊ አሠራርን ሳይጠብቁ የፈጸሟቸውን መተላለፎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ለጉባኤው ያሰሙ ሲኾን በማኅበሩ ላይ ለሰነዘሯቸው ክሦችም ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል፤ የማኅበሩ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ የአባላቱ አስተዋፅኦ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ በሒሳብ አሠራሩም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከማኅበሩ ብዙ የሚማረው እንዳለም አልሸሸጉም፡፡

    ለመዋቅራዊ መተላለፋቸውም ኾነ ከማኅበሩ አንጻር ለቀረቡላቸው የተጨባጭነት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያልሰጡት ፓትርያርኩ፣ ማእከላዊ አሠራርን ባለመጠበቅ በፈጸሟቸው ተግባራት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “አዋረዱን፤ አፈርንብዎ” እስከመባል የደረሰ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል፤ በከፍተኛ ደረጃም ተገሥጸዋል፡፡

    ፓትርያርኩ ከመዓርገ ክብራቸው አኳያ ከመሰል የደብዳቤ መጻጻፎች እንዲታቀቡ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ በኮሌጆች የሚገኝበትን አስከፊነት አስመልክቶ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዳሰሳ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ያወጣውን ጽሑፍ ተከትሎ ፓትርያርኩ የሰጧቸው መመሪያዎችና ከማኅበሩ ጋር የተመላለሷቸው ደብዳቤዎችም በቋሚ ሲኖዶሱ እንዲመረመሩ በጉባኤው ተወስኗል፡፡ በይቀጥላልም ጉባኤው፣ ፓትርያርኩ በመሰል ጉዳዮች አስፈጻሚ የአስተዳደር አካላትን በቀጥታ መሰብሰባቸው ስሕተት በመኾኑ፣ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተነጋገሩና በቋሚ ሲኖዶስ እየመከሩ ሕጉን አክብረውና መዋቅሩን ጠብቀው ከአድልዎ የጸዳ አመራር መስጠት እንደሚኖርባቸውም በጥብቅ አሳስቧቸዋል፡፡


    ግለ ታሪካቸውን ከማበላሸት አልፎ በክፉ ምክሮችና በሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ቤተ ክርስቲያንን እያሳጣና እያስነቀፈ የሚገኘው የልዩ ጽ/ቤታቸው አሠራርብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በእጅጉ አሳስቧል፤ የልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና የክፋት ተባባሪዎቹ ጉዳይም አስቸኳይ እልባት እንደሚያስፈልገው ከድንገተኛ ልዩ ስብሰባው በተጓዳኝ በስፋት የተመከረበትና አቋም የተያዘበት ወቅታዊ ነጥብ ኾኗል፡፡

    የፓትርያርኩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ጉዞ፣ ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ እያወቀው በዕቅድ መከናወን ያለበት ቢኾንም “የራሳችንን ወጪ ሸፍነን ቅዱስነታቸውን እናጅባለን” በሚሉ አማሳኝ ግብረ በላዎች ጭምር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ያለዕቅድ እየወጣ የሚባክንበት፤ ፓትርያርኩ እንደ ርእሰ መንበር  ሐዋርያዊ ተልእኳቸውንና አባታዊ ሓላፊነታቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመወከል በሚያበቃ መልኩ የሚወጡበት ከመኾን ይልቅ“ስፖንሰር ተገኘ” በሚል ብቻ ከፍተኛ ስሕተት(የፕሮቶኮልም) የሚፈጸምበትና ክፋት የሚመከርበት እየኾነ እንደመጣም በጉባኤው ታይቷል፡፡

    በመኾኑም ማንኛውም የፓትርያርኩ ጉዞዎችና የሚመደቡ ልኡካን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ሲወሰን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንተ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲኹም የመንበረ ፕትርክናውን ፕሮቶኮል በጠበቀ ደረጃ እንዲፈጸም ጉባኤው አሳስቧል፡፡

    ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሚመለከታቸው አህጉረ ስብከት በሚመደቡ ልኡካን ተጨማሪ ማጣራት እንዲካሔድና አስፈላጊው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲደረግ የወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአገራችን ወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይም የመከረ ሲኾን በዛሬው ዕለትም በድንገተኛ ልዩ ስብሰባው ቃለ ጉባኤዎች ላይ በመፈራረም መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    2 comments:

    1. ደስ የሚሉ ብጹአን አባቶች አሉን ደስ ብሎናል!እግዚአብሔር ይመስገን

      ReplyDelete
    2. ቃለ ህይወት ያሰማቹህ የድንግል ማርያም ምልጃ አይለያቹህ።

      ReplyDelete

    Item Reviewed: ቅዱስ ሲኖዶስ: ፓትርያርኩ ሕግ አክብረውና መዋቅር ጠብቀው እንዲሠሩ አስጠነቀቃቸው፤ በሰላም ጉዳዮች ዛሬ መግለጫ ያወጣል Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top