• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 24 March 2016

    የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ባልታወቁ ታጣቂዎች የዘረፋ ስጋት ውስጥ ወድቋል


    በአመክሮ ላይ ካሉ ጥቁር ራሶች ጋር ውዝግብ በመፍጠር ደብድበዋቸዋልየደሴቶቹና የአካባቢው ኅብረተሰብ ኹኔታውን በንቃት እየተከታተሉ ናቸውየ740 ዓመት ገዳሙ፣ የበርካታ ጥንታውያን ብራናዎችና ቅርሶች ማዕከል ነው


    በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በጣና ሐይቅ ውስጥ ከሚገኙ የደሴት ገዳማት አንዱ የኾነው ጥንታዊው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም፣ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ ጀምሮ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የዘረፋ ስጋት ተደቅኖበት እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

    ምንጮች እንደገለጹት፣ ባለፈው ኃሙስ ምሽት ግለሰቦቹ በሦስት ጀልባዎች ከፎገራ አቅጣጫ በመምጣት ወደ ገዳሙ የደሴት ክልል ተጠግተው ያደሩ ሲኾን፤ ትላንት፣ መጋቢት 12 ቀን ምሽት 2 ሰዓት ላይ ደግሞ ጀልባዎቹ በቁጥር ጨምረውና ግለሰቦቹም በትጥቅ ተደግፈው መምጣታቸው ስጋቱን ከፍ አድርጎታል፡፡

    ኀሙስ ምሽት የመጡት ጀልባዎች ዓርብ ጠዋት ስፍራውን ለቀው ቢሔዱም ትላንት ምሽት ከተመሳሳይ አቅጣጫ በስምንት ጀልባዎች ተጓጉዘው የመጡት የታጠቁ ግለሰቦች በገዳሙ አቅራቢያ ማደራቸው በምንጮቹ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ዛሬ ጠዋት ድረስም፣ ከስምንቱ ጀልባዎች አምስቱ ከነታጣቂዎቹ በስፍራው እንዳሉ ተገልጧል፡፡

    አመጣጣቸው ዓሣ ለማስገር እንደኾነ በመግለጽ ኃሙስ ሌሊቱን ከገዳሙ አበምኔትና ከማኅበረ መነኰሳቱ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ያደሩት ግለሰቦቹ፤ ዓርብ ጠዋት በአመክሮ ላይ ከሚገኙ ጥቁር ራሶች አንዱን በመደብደብ ጉዳት ማድረሳቸው ታውቋል፡፡

    “የአካባቢው ነዋሪዎች እንኳ፣ ዓሣ እዚያ የማውጣት ልምድ የላቸውም፤”  ይላሉ ምንጮቹ፡፡ ስለግለሰቦቹ አመጣጥ ሲያስረዱም፥ ወቅቱ የጾም ወራት በመኾኑና ማኅበረ መነኮሳቱም ሱባኤ ላይ በመኾናቸው አጋጣሚውን ተጠቅሞ ዘረፋ ለማካሔድ የሚደረግ ሙከራ እንጂ ሌላ ሊኾን እንደማይችል ይናገራሉ፡፡

    ካለፈው ኃሙስ ምሽት ጀምሮ የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት ከሌሎች የደሴታቱ ገዳማት፣ በዙሪያውና ባሻገሩ ከሚኖረው ማኅበረሰብ ጋር በመደዋወል አካባቢውን በንቃት እየጠበቁ ቢኾንም የክልሉ መንግሥት የግለሰቦቹን ማንነት በመለየትና በመቆጣጠር አስቸኳይ ጸጥታዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

    ከዚኽ ቀደም የመነኮሳቱን አልባሳት በመልበስና ተመሳስሎ በመግባት ጭምር በገዳሙ ዕድሜ ጠገብና ውድ ቅርሶች ላይ ተደጋጋሚ የዘረፋ ሙከራዎች መደረጋቸውን ምንጮቹ አስታውሰው፤ ገዳማውያኑና የአካባቢው ማኅበረሰብ በንቃት መከታተላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፤ መረጃው የደረሰው የክልሉ መንግሥትም አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ የተጠየቀውን ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

    ከአትክልት ልማት ምንጣሮ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ጥር ወር በገዳሙ ተቀስቅሶ የነበረው የእሳት ቃጠሎ፤ በደሴያቱ ማኅበረ መነኮሳት፣ በአቅራቢያው ነዋሪዎች፣ ከባሕር ዳር ከተማ በጀልባ ተጓጉዘው በደረሱ አገልጋዮችና ምእመናን፣ በክልሉ መስተዳድር ሓላፊዎችና በጸጥታ ኃይሎች የጋራ ርብርብ ከቤተ ክርስቲያኑ መቶ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ መጥፋቱ ይታወሳል፡፡


    ከ740 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ጥንታዊው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም፣ በሐይቁ የደቡብ ምሥራቅ ገጽ ከባሕር ዳር ከተማ የኹለት ሰዓት የጀልባ ጉዞ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ለዘመናት የተካበቱ አያሌ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት ማእከል ከመኾኑም በላይ፤ በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የተሣለች ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል፣ የመሥራቹ የአቡነ ኂሩተ አምላክ መቋሚያ፤ የታወቁት ነገሥታት የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የዐፄ ሱስንዮስ፣ የዐፄ ፋሲልና የሌሎችም ነገሥታት አዕፅምት፣ የወግና የክብር ዕቃዎች/ዘውዶች፣ አልባሳት፣ ጎራዴ …/ ተጠብቀው ይገኙበታል፡፡

    የገዳሙ መነኮሳት የሚመገቡት ከዳጉሳ እህል የተዘጋጀ ዳቤ የሚመስል መኩሬታ የሚባል ምግብ ነው፤ መተዳደርያቸውም አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ሲኾን ሙዝ፣ ሸንኮራ፣ ሎሚ፣ ትርንጎ፣ ፓፓያ፣ ማሽላ ያመርታሉ፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ባልታወቁ ታጣቂዎች የዘረፋ ስጋት ውስጥ ወድቋል Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top