• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday 27 February 2016

    ዘወረደ


    /የዘወረደ እሁድ ትምህርትና ግጻዌ /

     

    በዐቢይ የጾም መግቢያ ላይ የሚገኘው እሁድ ዘወረደ ይባላል፤ ይህ ጾም ዐቢይ ጾም መባሉ መድኀኒታችን ስለ ጾመው ነው፡፡ ‹‹ሁዳዴ›› ጾምም የሚባለው ሑዳድ በሚባለው ጥንታዊ የእርሻ መሬት ስም ታላቅነቱን ለመግለጽ ነው፡፡

    በፍትሐ ነገሥት እንደተጻፈልን የጥንት ክርስቲያኖች ከጠዋት እስከ 11 ሰዓት ይጾሙት ነበር፤ ዛሬም ቢሆን በመጠኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ እስከ 7-9 ሰዓት ይጾሙታል፡፡ አንዳንድ አባቶችና እናቶችም እንደ ጥንቱ እስከ 11-12 ሰዓት ይጾሙታል፡፡ በጾሙም እንደ መድኃኒታችን ጠላትን ድል እንነሣበታለን፡፡  በባህረ ሐሳብ ቀመር ሲወርድ ከየካቲት 1 ቀን ሲወጣም ከመጋቢት 5 ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ትንሣኤ ዋዜማ ያለው 55 ቀን ዓቢይ ጾምና ሰሙነ ሕማት ይባላል፡፡

    1 ሰንበት (እሑድ) ዘወረደ ይባላል፡ በዚህ ቀን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር መውረድ የሰው ልጅ በትሕትና፣ በፈሪሃ አምላክ ስለ መኖሩ ይዘመራል፡፡ የዕለቱም ስያሜ የተወሰደው በዕለቱ ከሚዘመረው የያሬድ መዝሙር ነው፣ ከሰኞ ጀምሮ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሰው ለጾም ልቡን እንዲያዘጋጅ ትምህርት የሚሰጥበት በጾም ወቅት ሊኖረን ስለሚገባው ሕይወት የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡

    ማውጫ፡

    መዝሙርስ፡ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት

    (ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ)

    2.    በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች
    በገባሬ ሠናዩ ዲ/ን ያዕ 13፤7-17በንፍቅ ዲ/ን ያዕ 4፤6 እስከ ፍጻሜው

    በንፍቁ ቄስ የሐዋ ሥራ 25፤13 እስከ ፍጻሜው

    ምስባክ– 
    ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት
    ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ
    አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመአዕ እግዚአብሔር /መዝ 2፤11/

    አማርኛ–  ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ

    በረዓድም ደስ ይበላችሁ

    ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቆጣ

    ትርጉም፡ ለእግዚአብሔር በፍርሃት በመንቀጥቀጥ ተገዙ፣ በመገዛታችሁም ደስ ይበላችሁ ዋጋ ያለበት ስለ ሆነ፣ በፍቅር በመነጨ ፍርሃት ደስ ይበላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም ተገዙ ፥ ጥበብ ወልድን እመኑ ፣ ልጄን በሥጋ ብሰድላችሁ አላመናችሁበትም (አልተቀበላችሁትም) ብሎ እግዚአብሔር እንዳይፈርድባችሁ በልጁ እመኑ፡፡

    ወንጌል ፡- ዮሐ 3፣10-25

    ቅዳሴ፡- የጌታችን (ነአኲተከ)

    የዕለቱየትምህርትርእስ

    ፈሪሀ እግዚአብሔር

    1) ሥጋዊ ፍርሃት ከኃጢአት በኋላ ተከስቷል፣ በጥላቻና በመንቀጥቀጥ የሚሆነው የውስጥ ፍርሃት ሰው ሕገ አምላክን ሲተላለፍ ተጀምሯል፡፡ ይህ ዓቢይ ፍርሃት እና ረዓድ ወደ ዓለም ከኃጢአት በኋላ ስለመግባቱ (ዘፍ 3፤10፣ ምሳ 28፤1) ላይ እናነባለን፡፡ ክርስቲያን ግን የእግዚአብሔርን ፍቅር ስለሚያውቅ ከእንደዚህ ያለ ፍርሃት በክርስቶ ነጻ ወጥቷል፡፡ (ሮሜ 8፤15, 1ኛ 4፤18)

    2) ፈጣሪን ለማክበር እና በፍቅር ላይ የተመሠረተች ፈሪሃ እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት ከተፈጠረው ፍትሃት የተለየ ነው፤ ይህ ፍርሃት ከፍቅር፣ ከአክብሮት የመነጨ በመሆኑ ለምስጋና ለቅዳሴ የሚያተጋ በመሆኑ በገነት በነበረው ሰው ሕይወት ውስጥ ነበረ፣ ይህን ቅዱስ ጸጋ በጠላት ምክር ሲነጠቅ በድፍረት ኃጢአት ሠራ፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ናት (ምሳ 1፤7, ምሳ 9፤10) በመሆኑም ዳዊት ሊያስተምረን ፈቅዶ ‹‹ኑ ፈሪሃ እግዚአብሔር ላስተምራችሁ›› ይላል (መዝ 33፤1)

    የጥበብ ሁሉ መጀመሪያው የተባለችበት ምክንያት ሰው እግዚአብሔርን ከፈራ እንደ አብርሃም የታዘዘውን ሁሉ ያደርጋል (ዘፍ 22፤12-23) እግዚአብሔርን ፈርቶ የሠራው ሥራም ሞገስ ይሆነዋል (ዘፍ 31፤42) አባታችን ዳዊት ኑ ላስተምራችሁ ያላቸውን ልጆቹን ሲያስተምር ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔርን በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይከባል ያድናቸውማል›› በማለት ፈሪሃ እግዚአብሔር በመላእክተ እግዚአብሔር እንደምታስጠብቀን ተናገረ፡፡ (መዝ 33፤7)

    ፈሪሃ እግዚአብሔርም ሕይወትን ለሚፈቅድና በጎን ዘመን ለማየት ለሚወድ ጠቃሚ መሆኑን እያስገነዘበ ሲተረጉም እግዚአብሔርን የምትፈራ ከሆነ በጎ ዘመንንም ለማየት፣ በሕይወት መኖር ከፈለግህ፣ አንደበትህን ከክፉ ከልክል፣ ከንፈሮችህም ሽንግላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ፣ መልካምን አድርግ፣ ሰላምንም እሻ ተከተላትም፣ አለ (መዝ 33፤14) በፈሪሃ እግዚአብሔር የተጠቀመው ዳዊት ‹‹የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ እግዚአብሔርን ፍሩት›› አለ መዝ 33 ፣ 9-11 ። ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድ ሰው ምስጉን ነው፣ ዘሩም በምድር ላይ ኃያል ትሆናለች›› አለ ቁጥር 1፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎችም ከደፋሮች ይልቅ ክቡራን በመሆናቸውን እነሱንም የሚያከብር እንደሚከበር ሲናገር ‹‹ዘያከብሮሙ ለፈራህያነ እግዚአብሔር›› እግዚአብሔርን የሚፈሩትን የሚያከብር ይከበራል (መዝ 14፤4)፣ በእግዚአብሔር ድንኳን ያድራል አለ፡፡  ልጁ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም አክብር (ጠብቅ) አለ (ምሳ 8፤7)፣ እግዚአብሔርን የሚፈራው የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ጸሎቱ ተሰማለት ለአሚነ ክርስቶም በቃ (የሐዋ 10፤2)

    አንባቢ ሆይ፡ እንግዲያውስ እኛም ወንጌልን እንዳልተቀበሉ በክርስቶስ እንዳላመኑ ለፍርድ እንደተጠበቁ ሰዎች ከድንጋጤና ከጭንቀት የሚፈጠረውን ፍርሃት አስወግደን (የሐዋ 6፤29 ። ዕብ 10 ፣ 26-30 ። ራዕ 21፤8) ከዚህ ዓይነቱ ፍርሃት ክርስቶስ ነጻ እንዳወጣን እየተገነዘብን የእግዚአብሔርን ፍቅር ቅድስናና ክብር ታላቅነት በሚገልጸው ፈሪሃ እግዚአብሔር እንቁም፡፡

    ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ›› ይላል (ፊልጵ 2፤12)  በዕብራውያን መልእክቱም ‹‹የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበት ጸጋ እንያዝ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና›› አለ (ዕብ 13፤7-17)፡፡

    ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃትና በፍቅር ኑሩ›› ይላል (1ኛ ጴጥ 1፤17)

    በመለኮታዊ ጥባቆቱ ከድፍረት ኃጢአት እግዚአብሔር እንዲያድነን እንጸልይ እንማፀነውም (መዝ 18፤13) ‹‹… ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ ። ለእነሱም መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል›› ብሎ የተናገረውን ተስፋ እንዲያወርሰን (ኤር 32፤40) ከፍቅር የተነሣ እንፍራው እናከብረው ፤ የአጋንንት ዓይነት ፍርሃት ሳይሆን አባታችን ስለሆነ ክብርን፣ ንጉሣችን ስለሆነ ፍርሃትን ይዘን ለእሱ በፍቅር እንገዛለት፡፡

    ‹‹ልጅ አባቱን ያከብራል፥ ባሪያም ጌታውን ይፈራል፥ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንኩ መፈራቴ ወዴት አለ?›› እንዳንባል (ሚልክ 1፣6-7)

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ዘወረደ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top