• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday 27 February 2016

    ቅኔ እና እነ የኔታ


    መግቢያ

    ቅኔ ብሂል:- ቃሉ የግዕዝ ነው:: በርባታ ስያሜውም ጥሬ ዘር ይባላል:: ትርጉሙ ቃል በቃል “መገዛት” ማለት ነው:: ግብሩን በተመለከተ ከፈታነው ደግሞ ቅኔ ማለት “መገዥያ፣ ማምለኪያ፣ ማመስገኛ” ማለት ነው:: በአቀራረቡና በሌሎች አገሮች ካሉት ተመሳሳይ የግጥም ስልት ካላቸው ቅኔ መሰል ግጥሞች አንጻር ሲፈታ ደግሞ ቅኔ ማለት በጠቅላላ አቀራረቡ ሲታይ “ግጥም” ማለት ነው:: በቅኔ ምስጋና፣ ክብር፣ ደስታ፣ ኀዘን፣ ተገፍዖ፣ ተዋርዶ እና ታሪክ በአጠቃላይ በዓለም የሚታይና የሚከናወን ሕይወታዊ ገጽታ በባለ ቅኔዎች ይገለጽበታል::

    ቅኔ ልዩ የሆነ የምሥጢር ጎዳና፡ የፍልስፍና፡ የትምህርት፡ የርቃቄ መነሻ፤ የአእምሮ ማጎልመሻ፡ ወደ ሀገረ መጻሕፍት የሚያደርስ ምሕዋር፡ መገስገሻ፣ የጥበብ፡ የአእምሮ መንፈላሰሻ፡ ልዩ ሀብት ነው:: ኢትዮጵያዊ ቅኔ በመላው ዓለም ከሚገኙት የቅኔ የግጥም ባሕርያት የተለየ ባሕርይና ቅርጽ መልክ ያለው  የዕውቀት ጎዳና መሆኑን ነጩም ጥቁሩም ሊቅ ተስማምቶበታል:: ይህን በተመለከተ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የክቡር አቶ አለማየሁ ሞገስን “ሰዋሰወ ግእዝ” በመጥቀስ “ዝክረ ሊቃውንት” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ነበር ያሉት “ቅኔ በሌላ ሀገር የማይገኝ ግእዝ ወልዶ ያሳደገው በሽምግልናው ለአማርኛ ያስተዋወቀው… የሕሊና ስሜት፣ የአእምሮ ትፍሥሕት የድካም መድኃኒት፣ የኀዘን ማስረሻ፣ የፍልስፍና ማጎልመሻ ሲሆን ከልዑል እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ መድኃኒት ነው:: ልዩ ልዩ ልሳናትን ስንማር ምንአልባት እርሱን የመሰለ ጥበብ እንዳለ ለማለት በተቻለን መጠን ይልቁንም የግሪክና የእንግሊዝኛ ባለቅኔ የሚባሉትን የቅኔያችንን ጣዕም ጠልቆ ያልቀመሰ የሚያደንቀውን እና የሚያጋንነውን ግጥም ሁሉ ብናነብ እንደ ኮረንቲ ሽቦ ተጣምሮ የሚሄደውን የቅኔያችንን ምሥጢር… አገኛለሁ ማለት ከመሬት ቁጭ ብሎ በቀኝ እጅ ሰማይን ደግፎ በግራ እጅ ከዋክብትን መግፋት ሆነብን”[1]ብለዋል። ሊቁ እንዳሉ የኢትዮዽያ ቅኔ ከፈረንጆች “poem” ፍጹም ልዩ ነው:: አንድ የኢትዮዽያን ቅኔ ያጠኑ ሮማዊ ሊቀ ጳጳስ ስለ ቅኔያችን ሲናገሩ “የኢትዮጵያ ቅኔ ካልተማሩት በቀር ስለ እርሱ መናገር ይከብዳል። ስለ ቅኔ ላልተማረው ሰው ማስረዳት አይቻልም” ነበር ያሉት። እውነት ነው መንገዱ የዕውቀት መንገድ ነውና።

    የቅኔ ደራሲ:- የቅኔ ጀማሪ ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ አበው ተስማምተዋል:: የቅዱስ ያሬድ በስድ ንባብም በግጥምም መንገድ (መልክ) የተዘጋጁ በይዘታቸው “ጽድቅ” የሆኑ ቅኔያቱ በድርሰቶቹ መካከል እንደጌጥ አልፎ አልፎ ይታያሉ:: ቅኔዎቹም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመጻሕፍት የተጠቀሱ፣ ከአሁኑ ቅኔ የተለየ መልክ ያላቸው፣ የቅኔን ስያሜ ያስገኙ ቤት ያልመቱ ሰምና ወርቅ ወይንም ልዩ ልዩ የሆኑትን የቅኔ ጎዳናዎች ያልተከተሉ ቅኔዎች ናቸው:: በታሪክ ጥንታዊ በአካሄድ ዘመናዊ የሆነውን ቅኔ ደራሲ በተመለከተ አንዳንዶች “ዮሐንስ ገብላዊ” የሚባለው ሊቅ ነው የደረሰው ሲሉ ሌሎች ደግሞ “ደቀ እስጢፋ” ነው የደረሰው ይላሉ:: ያም ሆነ ይህ ቅኔ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው:: ሁለቱም ሰዎች በታሪክ እንደሚነገርላቸው ዕውቅ “የቅኔ” እና “የአገባብ” ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ነበሩ::

    የቅኔ መንገድ  ቅኔ ልዩ ልዩ መንገዶች አሉት:: ሁሉንም ለመዘርዘር ቢያዳግትም ጥቂቶቹን ብንጠቅስ “ሰምና ወርቅ” “ሰም ገፊ” “ውስጠ ወይራ” “አገናኝ” “አታላይ” “ጽድቅ” “አንጻር” “ሙሻ ዘር” “ንጽጽር” “ኅብር” “ጸጸት” “ሞይት” “ዝምዝም ወርቅ” “የወርቅ ተነጻጻሪ” “የወፍ እግር” “ስም ጥቅል” “ኃዳሪና ማኅደር” “ሠረዝ” “ድርብ ሠረዝ” “ጉት” “ፍና ተሳልቆ” “ውስጠ ዘ” እና ሌሎችም ብዙ የቅኔ መንገዶች አሉ:: ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ “ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት” በሚለው መጽሐፋቸው አንድ መቶ አሥራ ሰባት የቅኔ መንገዶችን ከነቅኔያቸው ሌሎች ዘጠና አራት የቅኔ መንገዶችን በስማቸው ብቻ ጠቅሰው በአጠቃላይ የሁለት መቶ አሥራ አንድ ቅኔ መንገዶችን ለትውልድ አስተዋውቀው ጽፈዋል:: ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት ገጽ ፻፹፪-፪፻፯ ይመልከቱ::

    የቅኔ ዓይነቶች /ክፍሎች/፦ የሚከተሉት ናቸው።ጉባኤ ቃና ዕዝልና ግእዝ፤ ዘአምላኪየ፤ሚበዝኁ፤ ዋዜማ፤ አጭር ዋዜማ፤ሥላሴ ፤ዘይዕዜ ፤ሣህልከ፤መወድስ (ፍታሕ ሊተ)፤ መወድስ (ኩልክሙ)፤ሕንፄሃ፤ግእዝ ክብር ይዕቲ፤ ዕዝል ክብር ይዕቲ፤ ዕጣነ ሞገር ግእዝ፤ዕጣነ ሞገር ዕዝል ናቸው::

     

    አዲስ ቅኔ፦ ቅኔ ሁልጊዜ አዲስ ታስቦ ወይም ተቆጥሮ ወይም ተዘርፎ ይቀርባል እንጂ ያደረ ቅኔ የደረቀ ቅኔ ወይም ክልስ ቅኔ ወይም የተውሶ ቅኔ የለም። ቅኔ ሁልጊዜ አዲስ ከአንድ ጊዜ በላይ ተደግሞ ለምስጋና የማይቀርብ ሁልጊዜ ትኩስ በሊቃውንት አእምሮ የሚመነጭና የሚፈልቅ የምስጋና ቃል ነው። ከላይ እንዳልኩት ቅኔ አይደገምም አይከለስም አይሰለስም፣ ቅኔ ሁልጊዜ አዲስና ትኩስ ነው። ባለቅኔውም በእግዚአብሔር ፊት አዲሱን ምሥጋናውን ከማቅረቡ በፊት ስለቅኔው ከጓደኛው ከመምህሩ ጋርም ቢሆን አይወያይም ቅኔውንም ለማንም አይነግርም። ለእግዚአብሔር ቅኔው ከመቅረቡ በፊት የቅኔ ሰዎች ቅኔአቸውን እንደሚደብቁ መናገሬ ነው እንጂ በደል ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም አንዳንዶቹስ ደህና የቅኔ ሰው አማክረው፣ አስተካክለው እንደ አቤል መስዋዕት የተዋበውን ቅኔ ያቀርባሉ።

    የቅኔ አገልግሎት፦በቅኔ ሃይማኖትን፣ ሥነ ምግባርን፣ ትሕትናን፣ ፍቅርን፣ ተዘክሮተ ሞትን፣ ትምህርተ ሕይወትን፣ አዝማነ መንግሥተ ሰማያትን፣ ጸሎትን፣ ተመስጦን አባቶቻችን ሲያስተምሩ ኑረዋል:: ዛሬም አሉ ያስተምራሉ:: በአጠቃላይ በቅኔ የፈለጉትን ማለት ይቻላል:: ሊቃውንት በቅኔ ብሶታቸውንም ይገልጹ ነበር:: ቅኔን ለምሥጋናም፣ ለዘለፋም፣ ለተግሣጽም፣ ለተምኔትም፣ ለአቤቱታም መግለጫ አድርጐ መጠቀም ይቻላል ተችሏልም:: አሁን ለምሳሌ ያህል በቅኔ እንዴት አባቶቻችን ሲያስተምሩ ሲመክሩ ስለ ሃይማኖታቸውም ሲከራከሩ ሐሳባቸውንም ሲገልጹ እንደኖሩ ከጥንት ቅኔዎችና በቅርቡ ከተደረጉት ቅኔያት አንዳንዶችን ለምሳሌ ለአንባቢያን ወደፊት በተከታታይ አቀርባለሁ:: ስለዚህ ዓለም ጥበብ ከንቱነት,የሃይማኖት አቋም መግለጫ ሊሆን ይችላል። ቅባት፣ ጸጋ እየተባባሉ ሊቃውንት በሃይማኖት በተለያዩበት ዘመን አንድ ባለቅኔዎች ተቃውሞአቼውንም ሆነ ድጋፋቸውን በቅኔ ያቀርቡ ነበር::ስለ ሥነ-ምግባር ስለ ፍቅር ጠቃሚነት,የቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ በቅኔ መግለጽ ይቻላል::  መምህራን በቅኔአቸው ኀዘናቸውን ይገልጹ ነበር። ለዚህም የታወቁት ሊቅ የኔታ ገብረ ጊዮርጊስ ዓይናቸውን ታመው በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም በእስቴ መካነ ኢየሱስ ሳሉ የዘረፉት ቅኔ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ደቀ መዝሙራቸው ስለነበሩ በቃላቸው ይዘው ያጻፉኝን ቅኔ እንደምሳሌ አቀርበዋለሁ:: በሚቀጥለው እትም ደግሞ የቅኔውን ትርጉምና ምስጢር አቀርባለሁ።

    መወድስ ቅኔ

    በመኑ አቀልል ክበደ ተገፎዖ ጽዋዐ ሕማም ወሞት ትህልፍ እምኔየ

    አምጣነ ክህደኒ ሥልሰ ሐዋርያ ብርሃን ዓይንየ

    ወሕፀተ ባሶር ሠረገላ መጽአ ከመ ይቅትለኒ ስናክሬም ደዌየ

    ሠራዊተ ባቢሎን አመ ርእየ

    እስመ ጸበበቶ ምድር ለኤርምያስ ሕሊናየ::

    ለዓለም

    ኃይልየሂ ወልደ እሴይ ለእመ ረስአ ወበልየ

    ነግሠ በፈቃዱ አዶንያስ ሕማምየ

    ወአመ ትትገፈታዕ ሥልሰ ኢየሩሳሌም ሥጋየ

    ተንሥአ ለተሰዶ እንባቆም ልቡናየ:: /ትርጉሙንና ምሥጢሩን በሚቀጥለው እትም ይመልከቱ/

    በመግቢያው ላይ እንደገለጽኩት ቅኔ በቅጥነተ ሕሊና በርቀት ባለቅኔውን አክሎ ለተመለከተው ሰው ማራኪ የሚመስጥ ረቂቅ የጥበብ ጐዳና ሲሆን፡ ለሌላው ተርጉሞ ለማስረዳት ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ብዙ ሐተታ የሚያሻው በቅርብ የማይገኝ የምሥጢር ሩቅ ስለሆነ ለባለቅኔዎች እንጂ ለሌሎች በቀላሉ የሚደረስበት አይደለም:: ባለቅኔዎች አባቶቻችን ቅኔ እያሰቡ የት እንዳሉ በተመስጦ ያሉበትን ይረሱ ነበር:: ቅኔ እያሰቡ በላያቸው ላይ ዝናብ ቢወርድ አይሰሙትም ሰውም በፊታቸው ቢያልፍ ዓይናቸው እያየ አያዩትም ነበር:: ምክንያቱም በቅኔ ሐሳብ ይነጠቁ በምሥጢሩም ይጠልቁ ይራቀቁ ስለነበር ነው::

    እውቁ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ስለዚሁ ነገር ሲጽፉ እንዲህ ነበር ያሉት:: “ቅኔ ሕዋሳተ አፍዓን ሕዋሳተ ውስጥን ለሕሊና አስገዝቶ በተወሰነ ቁርጥ ሐሳብ የሚታሰብ ስለሆነ ቅኔ ተብሏል:: ይኸውም ሊታወቅ በቅኔ ምሥጢር ልቡ የተነካ ሰው ቅኔ በሚያስብበት ጊዜ በፊቱ የሚደረገውን ነገር እያየ አያይም፣ እየሰማ አይሰማም:: ከዚህም የተነሳ በጎንደሮች መንግሥት የቁስቋሙ አለቃ በእልፍኝ ውስጥ ምንጣፍን አስነጥፎ መጻሕፍቱን በፊቱ ደርድሮ ለበዓለ ቁስቋም የሚቀኜውን ቅኔ ሲያወጣና ሲያወርድ ንጉሡ ዘው ብለው ቢገቡ ልቡ ተመሥጦ ሊያያቸው ባለመቻሉ ቁጭ እንዳለ ቀረ:: ንጉሡም ነገሩ ደንቋቸው ፍጻሜውን ለማየት እሱን አልፈው ከአልጋው ላይ ተቀምጠው ሁኔታውን ይመለከቱ ጀመር:: ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ አእምሮው ሲመለስ ንጉሡ ተቀምጠው ቢያይ ደንግጦ ተነሥቶ እጅ ነሣ:: ንጉሡም ምነው ምን ሆነህ ነው ቢሉት ጃንሆይ ቁስቋምን ያህል ደብር አምነው ሹመውኛል ለበዓል የተሰበሰበው ሰው አለቃው ምን ይናገር ይሆን እያለ ዓይን ዓይን ሲያይ ያልሆነ ነገር ቢሰማ ደብሩን አዋርዳለሁ ጃንሆይን አሳማለሁ እኔም አፍራለሁ ብየ ቅኔ እቆጥር ነበር አለ ይባላል” ብለዋል:: በመሆኑም ቅኔ ልዩ የጥበብ፣ የትምህርት፣ የተመሥጦ ሀብት ስለሆነ ትውልዱ ሊያጠናው ያሉት አባቶች ሳሉ በስሙ ሊያውቀው በመልኩ ሊያየው በእጁ ሊዳስሰው በዐይነ አእምሮው በፍጹም ልቡም ሊከተለውና ሊያጠናው የሚገባው ልዩ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው::

    ይቀጥላል

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅኔ እና እነ የኔታ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top