• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 11 February 2016

    ሰበር ዜና – ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የመምሪያ እና የኮሌጅ ሓላፊዎችን አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ


    ሐራ ዘተዋሕዶ እንደዘገበው 

    የማኅበሩ ሚዲያዎች ታግደው ክሥ እንዲመሠረትበት አቋም ለማስያዝ እየተቀሰቀሰ ነውልዩ ጸሐፊአቸው ንቡረ እድ ኤልያስ እና አባ ሰረቀ ብርሃን ግንባር ቀደም ቀስቃሾች ናቸውቋሚ ሲኖዶስ እና ብፁዓን አባቶች፣ ፓትርያርኩን ሲመክሩ እና ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋልፓትርያርኩ፥“ምን ሲኖዶስ አለና” በሚል የጠሩት ስብሰባ፣ ሕጋዊም መዋቅራዊም አይደለም

    ፓትርያርኩ እና ልዩ ጸሐፊአቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ

    ፓትርያርክ አባ ማትያስ፥ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችን ዋና እና ምክትል ሓላፊዎችን እንዲኹም የሦስቱን መንፈሳውያን ኮሌጆች የአስተዳደር ሓላፊዎችን፣ ዛሬ፣ የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸው ተሰማ፡፡

    በመንበረ ፓትርያርኩ አዳራሽ ከጠዋቱ 2፡30 ላይ የተጠራው አስቸኳይ ስብሰባው÷ ማኅበሩ በኮሌጆች ውስጥ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄስለሚገኝበት አሳሳቢ ኹኔታ በሚዲያዎቹ ማስነበቡን ተከትሎ፣ ፓትርያርኩ በክሥ እና በቅስቀሳ መልክ ያሳለፉትን መመሪያ የማጠናከር ዓላማ እንዳለው ተገልጧል፡፡

    መመሪያው፣ የተሐድሶዎችን ክሥ የሚያስተጋባና የእውነት ጠብታ እንደሌለው በመተቸት ማኅበሩ ባለፈው ሳምንት በሰጠው የጽሑፍ ምላሽ ክፉኛ ተበሳጭተዋል የተባሉት ፓትርያርኩ፣ በተለይም ከማኅበሩ አገልግሎት ጋር የሚገናኙ የሥራ ዘርፎችን በሚመሩ ሓላፊዎች በኩል ተጽዕኗቸውን ለማጠናክር የሚያስችል ‘የጋራ አቋም’ እንዲያዝማሰባቸው ተጠቅሷል፡፡

    በክትትል እና በቁጥጥር ስም ለአገልግሎቱ አካሔድ ቢሮክራሲዊ ጫናዎችንና ዕንቅፋቶችን ከመፍጠር በተጨማሪ የማኅበሩ መጽሔት እና ጋዜጣ/ሐመር እና ስምዐ ጽድቅ/ ታግደው ማኅበሩ በኮሌጆቹ የስም ማጥፋት ወንጀል ክሥ እንዲመሠረትበት ለማድረግ መታሰቡም ታውቋል፡፡

    በዚኹ ዓላማ አንፃር አቋም እንዲያዝ፣ ቅስቀሳውን በተሰብሳቢዎች ላይ በዋናነት ከሚያካሒዱትየፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እና የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ ዲን ተስፋዬ ሃደራ ይገኙበታል፡፡

    በአባ ሰረቀ ብርሃን የሚመራው የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ፥ የአብነት ት/ቤቶች፣ መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ የማሠልጠኛ ማእከላት፣ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችና ዘመናዊ ት/ቤቶች፥በወጥ የትምህርት ፖሊሲና ሥርዐተ ትምህርት ተልእኳቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስተባበርሓላፊነት ያለበት ነው፡፡ በራሳቸው በዋና ሓላፊው በቀረበ የመንፈቅ ዓመት ሪፖርት ግን፣ “ምንም አቅም የሌለው፤ በሞት እና በሕይወት መካከል እያጣጣረ የሚገኝ” በሚል ተብጠልጥሏል፡፡

    የመንፈሳዊ ኮሌጆቹም፥ የትምህርት ጥራት፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ የመምህራን አመዳደብ…ወዘተ እንዲስተካከል ኮሚቴ ቢዋቀርም በሥራ ላይ አለመዋሉን፤ የደቀ መዛሙርት የመግቢያ መስፈርትና የአቀባበል ሒደት መምሪያው ሳያውቀው እንደነበረው መቀጠሉን፤ ተመርቀው ከወጡት የሚበዙት ደቀ መዛሙርትም በየተመደቡበት እንደማይገኙ በሪፖርታቸው አረጋግጠው ነበር፡፡

    ዛሬ፣ እኒኽ ድክመቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለደረሰው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ የራሳቸው አስተዋፅኦ እንዳላቸው ግልጽ ኾኖ ሳለ፤ አባ ሰረቀ ግን ለመፍትሔው ከመትጋት ይልቅ ሓላፊነታቸውን ተገን አድርገው ከልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ እና ከኮሌጆቹ አንዳንድ ሓላፊዎች ጋር ዋና ከሣሽና የተቃውሞው አስተባባሪ ኾነው ተሰልፈዋል፡፡


    ከተሰብሳቢዎቹ የአብዛኞቹ ሓላፊዎች ተጠሪነት፣የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ አስፈጻሚውን አካል በበላይነት ለሚያስተዳድረው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ነው፤ የተወሰኑትም በተሻሻለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ የኾኑ አካላትን የሚመሩ እንደ መኾናቸው፣ በፓትርያርኩ የተላለፈው የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪመዋቅራዊ አግባብነት የለውም፤ ውሳኔዎቹም ሕጋዊ ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡

    ይልቁንም ስብሰባው፣ ፓትርያርኩ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔና አሠራር ከመፃረር አልፈው መሠረተ ህልውናውንም እስከ መጠየቅ ለደረሱበት ሰሞናዊ ዓምባገነናዊ እና ኢፍትሐዊ አካሔዳቸው ተጨማሪ ግልጽ ማሳያ ነው የሚኾነው፡፡ 

    ፓትርያርኩ ለኮሌጆቹ ያስተላለፉት መመሪያ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ አኳያየደቀ መዛሙርቱ ምልመላና ቅበላ፤ የመምህራኑ ሃይማኖትና ክህሎት፤ ሥርዐተ ትምህርቱ እና የማስተማርያ መጻሕፍቱ እንዲፈተሹ በተደጋጋሚ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መንፈስ ጋር እንደማይስማማ በመጥቀስ፣ በቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲኹም ብፁዓን አባቶች በተናጠል እና በጋራ በመኾን አካሔዳቸውን እንዲያጤኑት ሲመክሯቸውና ሲያስጠነቅቋቸውመሰንበታቸው ታውቋል፡፡

    ምክር እና ማስጠንቀቂያውን ተቀብለው ከመታረም ይልቅ፣ “ይህን ማኅበር አንድ ነገር አናደርገውም ወይ?” በማለት የተወሰኑትና የሚወተውቱት ፓትርያርኩ፣ አስፈላጊ ከኾነም ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራና ጉዳዩ በምልዓተ ጉባኤ እንዲታይ ሐሳብ ሲቀርብላቸው፣ “ምን ሲኖዶስ አለና!” እስከማለት ነው የደረሱት፡፡

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    1 comments:

    1. I do no if the will of the God this and that . Then the all fanishement key was in our God .

      ReplyDelete

    Item Reviewed: ሰበር ዜና – ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የመምሪያ እና የኮሌጅ ሓላፊዎችን አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top