• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 18 January 2016

    ተሃድሶ ክፍል ፲፪

    ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ስለ ቅዱሳን፤

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡-የእርሱን መልክ እንዲመስሉ የወሰነላቸውን ቅዱሳንን የመረጠ፥ ሥልጣንም የሰጠ እርሱ ነው። ማቴ፡፲፥፩፣ ዮሐ፡፲፭፥፲፮፣ ሮሜ፡፰፥፳፱።

    መጠራት እና መመረጥ፡-

    ጌታችን፡-በገሊላ ባሕር ማዶ ሲመላለስ፥ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን እና ወንድሙን እን ድርያስን፡- ሁለቱን ወንድማማቾች አገኛቸው። ዓሣ አሥጋሪዎች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕር እየጣሉ ነበር። “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁና ለግዜው በእግረ ሥጋ ተከተሉኝ ፥ለፍጻሜው ግን በግብር ምሰሉኝ፤” አላቸው። የሰውን ሕይወት እንደ ዓሣ፥ ወንጌልን እንደ መረብ፥ዓለምን እንደ ባሕር፥ ቤተክርስቲያንን እንደ መርከብ አድርጐ ሰጣቸው። ልዋል ልደር፥ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ፥ሁሉን ትተው ፈጥነው ተከተሉት። ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጆች ዮሐንስን እና ወንድሙን ያዕቆብን፡- ከአባታቸው ጋር፥መረባቸውን፡- ያደፈውን ሲያጥቡ፥ የተቆረጠውን ሲቀጥሉ አገኛቸውና ጠራቸው። እነርሱም ሁሉን ትተው ፈጥነው ተከተሉት። ማቴ፡፬፥፲፰-፳፪። ቅዱስ ማቴዎስንም፡- ቀራጭ ነበርና በመቅረጫው ተቀምጦ ባገኘው ጊዜ፥ ተከተለኝ (ለፍጻሜው በግብር ምሰለኝ) አለው፤ እርሱም ሁሉን ትቶ ተከተለው። ማቴ፡፱፥፱።                                  

                                                                                    

    እንግዲህ ጌታችን፡- እንዲያገለግሉት ቅዱሳኑን እንደጠራቸው ሁሉ፥ እኛም በአማላጅነታቸው እንዲያገለግሉን እንጠራቸዋለን። ጸሎቱ እና ምጽዋቱ ቅድመ እግዚአብሔር የደረሰለት ቆርኔሌዎስ፡- የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት በነገረው መሠረት፥ መልእክተኞችን ልኰ ቅዱስ ጴጥሮስን ወደ ቤቱ ጠርቶታል። ቅዱስ ጴጥሮስ በዚያን ዕለት ተገልጦለት ስለነበረው ራእይ፡- ሲያወጣ እና ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ ቅዱስ፡- “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና፥ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤” ብሎታል። የሐዋ፡፲፥፩-፳፫። ከዚህ የምነረዳው ትልቁ ቁም ነገር፥ ሰዎችን ወደ ቅዱሳን የሚልከው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ነው።                               

    ቅዱሳንን በአጸደ ሥጋ በነበሩበት ጊዜ ስንጠራቸው ይመጡ እንደ ነበረ፥ ከዚህ ዓለም ተለይተው ከሚኖሩበት ከአጸደ ነፍስ ስንጠራቸውም ይመጣሉ። ለዚህም አብነታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በደብረ ታቦር ሆኖ፥ ሙሴን እና ኤልያስን፡- በጠራቸው ጊዜ፥ መጥተው በግራውና በቀኙ ቁመው ሲያነጋግሩት ተሰምተዋል። ማቴ፡፲፯፥፩-፫። “እናንተም ብትጠሯቸው መጥተው፥ በአጠገባችሁም ቁመው ያነጋግሯችኋል፤” ሲለን ነው።                                                                                                           

    ለአማኞች፡- ከእምነታቸው ጋር፥ ቅዱሳን ያስፈልጉአቸዋል። ለምሳሌ፡-የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው፥ አምነው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠምቀው ነበር። የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለመቀበል ግን የቅዱሳን ጸሎት አስፈልጐአቸዋል። “በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰም ተው፥ ጴጥሮስን እና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው፥ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ።”ይላል።የሐዋ፡፰፥፲፬-፲፯።                                                                                                                                                   

    “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤”

    “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤” ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከዓለም(ከሰው) ለይቶ የጠራቸውን፥ የመረጣቸውንም ደቀ መዛሙርቱን፡-“እናንተ የዓለም(ለሰው ልጅ) ብርሃን ናችሁ፤” ብሎአቸዋል። ማቴ፡፭፥፲፬፣ዮሐ፡፰፥፲፪። ብርሃንነታቸውም ለሰው ልጅ ሁሉ መሆኑን ሲነግራቸው፡- “መልካሙን ሥራችሁን አይተው አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።” ብሎአቸዋል። ማቴ፡፭፥፲፮። በመሆኑም፡- ቅዱሳን በቤተክርስቲያን  ውስጥ፥ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያሳዩ ብርሃናት እንጂ፥ ክርስቶስ እንዳይታይ የሸፈኑ መጋረጃዎች አይደሉም።                                             

    “እንደ ፀሐይ ይበራሉ፤”

    የጽድቅ ፀሐይ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ፥ ነቢዩ ሚልክያስ ፡- “ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችው ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ። በምሠራበት ቀን በደለኞች ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና እናንተ ትረግጡአቸዋላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” በማለት ነግሮናል። ሚል፡፬፥፪። ጊዜው ሲደርስም፡- ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ከምሥራቀ ምሥራቃት ወጥቶአል። (ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም፡- ከሥጋዋ ሥጋ፥ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ፥ በተዋህዶ ሰው ኹኖ ተውልዶአል። ሉቃ፡፪፥፯። እርሱም በደብረ ታቦር፡- ፊቱ እንደ ፀሐይ በርቶ፥ ልብሱ እንደ ብርሃን በርቶ ታይቶአል።ማቴ፡፲፯፥፪።የእርሱን መልክ እን ዲመስሉ የወሰነላቸውን ቅዱሳንን ደግሞ፡-“በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ።”በማለት ተናግሮላቸዋል። ማቴ፡፲፫፥ ፵፫።በመሆኑም፡-ቅዱሳን ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያሳዩ ፀሐዮች ናቸው።                                                                                                                                               

    “የመንግሥተ ሰማያት ቍልፍ፤”

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፡-“ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤”በማለት ስለ መንግሥተ ሰማያት ነግሮናል።ማቴ፡ ፮፥፴፫። በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱም ላይ፡-“ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ(ከዓለም ተለይተው ፥ ከበረሀ ወድቀው፥ ድንጋይ ተንተርሰው፥ ጤዛ ልሰው፥ የሚኖሩ፤ ድምፀ አራዊትን፥ ግርማ ሌሊትን እና ጸብዓ አጋንንትን  ሳይሰቀቁ በገድል የሚቀጠቀጡ ቅዱሳን) ብፁዓን (ንዑዳን ክቡራን) ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፤”ብሎአል። ማቴ፡፭፥፲። ከዚህም አያይዞ፡- ይህች የምንኖርባት ሰማይና ምድር ከመኖር ወደ አለመኖር እንደምታልፍ አስቅድሞ ነግሮናል።ማቴ፡፭፥፲፰።በመጨረሻው ዘመን(በዕለተ ምጽአትም)፡- “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ከተፈጠረበት ጌዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤” ይለናል። ማቴ፡፳፭፥፴፬። የክርስቲያኖች ተስፋ ይህ ነው። ይኸንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፡-“በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቀዋለን።” በማለት ተናግሮታል። ሮሜ፡፰፥፳፬፣ ፪ኛ፡ቆሮ፡፬፤፲፰። በዓይነ ሥጋ የማይታየው ተስፋ ምን እን ደሆነ ሲናገር ደግሞ፡-“ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።” ብሎአል።፪ኛ፡ ቆሮ፡፭፥፩።ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” ብሎአል። ፪ኛ፡ጴጥ፡፫፥፲፫።ቅዱስ ዮሐንስም በበኵሉ፡-“አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም።” ብሎአል። ራዕ፡፳፩፥፩። የመንግሥተ ሰማያት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህን ቍልፍ ያስረከበው ለአገልጋዮቹ ለቅዱሳን ነው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ፥ አገልጋዩን ቅዱስ ጴጥሮስን፡- “የመንግሥተ ሰማይትንም ቍልፍ እሰጥሃለሁ፤” ብሎታል። ማቴ፡፲፮፥፲፱።                                                                                                              

                                                                    ይቀጥላል፤

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሃድሶ ክፍል ፲፪ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top