• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 18 January 2016

    ተሃድሶ ክፍል ፯

                          ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፤”      

                                  

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-“ፊተኛው ኪዳን፤”ያለው በኦሪቱ የተሰጠውን ነው። ኪዳን፡- ማለት፥ ውል ስምምነት ማለት ነው።ይህ ውል እና ስምምነት ተደርጐ የነበረው፥ በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ነው። የውሉ፥ የስምምነቱ ማሰሪያም ቃል ነው፥ቃል ኪዳን ይባላል። እግዚአብሔር ዓለምን እና ሕዝቡን የሚያኖረው በቃል ኪዳን ነው፤በዚህም መሠረት፥ እግዚአብሔር፡- ከጥንት ጀምሮ ለሰው ልጅ ሰጥቶት የነበረውን ቃል ኪዳን በዝርዝር እንመለከታለን። ፩ኛ፡-ኪዳነ አዳም ነው፤ እግዚአብሔር አዳምን፡- በገነት ካኖረው በኋላ፥“ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ።”ብሎት ነበር። ዘፍ፡፪፥፲፮። ለአዳም  የተሰጡት ሦስት ዓይነት ዕፅዋት ነበሩ፤ አንዱን ሊጠብቀው፥ አንዱን ሊመገበው፥ አንዱን ደግሞ ሺህ ዓመት እየኖረ ሊታደስበት ነበር። በምክረ ከይሲ  አትብላ የተባለውን ዕፅ በበላ ጊዜ ግን የሚታደስበትን ዕፅ አጥቶታል። የእግዚአብሔርን ቃል ባለ ማክበሩ የሞት ሞት ተፈርዶበታል ፤በሥጋው ወደ መቃብር፥ በነፍሱ ደግሞ ወደ ሲኦል የሚወርድ ሆኖአል። የተሰጠውን ዕፅ በልቶ ሊታደስ ፸ ዘመን ሲቀረው በ፱፻፴ ዓመቱ የሞትን ጽዋ ቀምሷል። ዘፍ፡፫፥፩-፳፬፣፭፥፭። በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚነቀፈው የአዳም አለመታዘዝ ነው።                                                                             

    አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት በተፈረደበት ፍርድ ከማዘን በቀር ሌላ ኅሊና አልነበረውም። ማዘኑም ከማዕርጌ ተዋረድኩ ከሥልጣኔም ተሻርኩ ብሎ ሳይሆን፥ፈጣሪዬን በደልኩ ብሎ  የንስሐ ነው። እግዚአብሔርም፡- አዳም በኃጢአቱ ምክንያት መጨነቁን አይቶ አዘነለት፥ በይቅርታውና በቸርነቱ ብዛት ያድነውም ዘንድ ወደደ። ቅዱስ ኤፍሬም፡- በሰኞ ውዳሴ ማርያም ላይ፥“ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ።” ያለው ለዚህ ነው።እርሱ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንዲት በሆነች ፈቃዱ፥ሞት ባመጣው ጨለማ ተግዘው፥ በሲኦል ምሽግነት ያሉ ነፍሳትን ሊያድን ወዶአልና ነው።በመሆኑም “ከሰማየ ሰማያት ወርጄ፥ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፥ በመስቀል ላይ ተሰቅዬ፥ ሞቼ፥ተነሥቼ አድንሃለሁ።”በማ ለት ቃል ኪዳን ሰጥቶታል። አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸምም፡-በቀራንዮ በመልዕልተ መስቀል ሥጋውን በመቍረስ፥ ደሙን በማፍሰስ፥ነፍሱንም አሳልፎ በመስጠት አድኖታል። በዕፀ ሕይወት ፈንታም የእርሱን ሥጋ ደም ተመግቦ የዘለዓለም ሕይወት ባለቤት እንዲሆን አድሎታል። ዮሐ፡፮፥፶፫።ይኸንን በተመለከተ ቅዱስ ኤፍሬም፡-በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ፥“ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፥ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን፤ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፥ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው።” ብሎአል።                                                                                  

      ፪ኛ፡-ኪዳነ ኖኅ ነው፤ኖኅ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ፥በትውልዱ ጻድቅና ፍጹም ሰው የነበረ፥አካኼዱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ፥ እግዚአብሔር የመሰከረለት ጻድቅ ነው። ዘፍ፡፮፥፰።“በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።” ብሎታል። ዘፍ፡፯፥፩።ሦስት ክፍል ያላት መርከብ በእምነት ሠርቶ፥ ራሱን እና ቤተሰቦቹን አድኖአል።እንዲሁም እንስሳትን፥ አዕዋፋትን እና አራዊትን ወንድና ሴት እያደረገ ወደ መርከቧ በማስገባት ለዘር አትርፎአል። ዘፍ፡፯፥ ፯-፳፬።ከጥፋት ውኃ በኋላም ንጹሕ መሥዋዕት ሠውቶ፥ እግዚአብሔርን በመማጸኑ፥ሁለተኛ  ምድርን በንፍር ውኃ እንደማያጠፋት ቃል ገብቶለት፥ የቃል ኪዳን ምልክት ቀስተ ደመናን ሰጥቶታል። በጻድቁ ቃል ኪዳን እንኳን የሰው ልጅ፥ እንስሳቱ፣ አዕዋፋቱ እና አራ ዊቱ ሳይቀሩ እስከ ዛሬ ተጠብቀው ይኖራሉ። ዘፍ፡፰፥፳፤፱፥፩-፲፱።በአዲስ ኪዳንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-“ኖኅ ገና ስለ ማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥በዚህም ዓለምን ኰነነ ፥በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።” በማለት መስክሮለታል። ዕብ፡፲፩፥፯።ሦስት ክፍል ያላት የኖኅ መርከብ፡- ንጽሐ ሥጋን፣ንጽሐ ነፍስን እና ንጽሐ ልቡናን፥ ሦስቱን አስተባብራ ይዛ ለተገኘች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት።እግዚአብሔር፡-መርከቧን ምክንያት አድርጐ፥ ኖኅን እና ቤተሰቦቹን እንደ አዳነ፥ እመቤታችንን የማዳን መሣርያ አድርጐ ዓለሙን በጠቅላላ አድኖአል። ምልክት ሆና የተሰጠች ቀስተ ደመናም የእመቤታችን ምሳሌ ናት።ምክንያቱም፡- እንደ ኖኅ ቀስተ ደመና ምልክት ሆና ለመላው ዓለም የተሰጠች፥ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤት ድንግል ማርያም ናት።ኢሳ፡፯፥፲፬።ሦስት ክፍል ማለትም፡-ቤተ መቅደስ፥ቅድስት እና ቅኔ ማኅሌት ላላት ፥በደሙ ለተመሠረተች ቤተ ክርስቲያንም የኖኅ መርከብ ምሳሌ ናት።የኖኅን መርከብ የተጠጉ ከሞተ ሥጋ እንደዳኑ፥ቤተ ክርስቲያንን ጥግ ያደረጉ (ሃይማ ኖት ይዘው፣ምግባር ሠርተው የተገኙ) ምዕመናን፥ከሞተ ነፍስ ይድናሉ።ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም እና ማኅደረ መለኰት ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ቢመሰሉም፥ከኖኅ መርከብ ይበልጣሉ፤ ምክንያቱም፡- ያቺ ድኅነት የተፈጸመባት ከሥጋ ጥፋት ሲሆን፥እነዚህ ግን ከነፍስ ጥፋት ነው።በመሆኑም ሥጋን ብቻ ታድን የነበረች የኖኅ ቃል ኪዳን ጉድለት ነበረባት ። መጉደሏም ፍጹም የምትሆንበት ጊዜ እስከሚደርስ ነበር።ቅዱስ ዳዊት፡-“እግዚአብሔር ሥራ የሚሠራበት ጊዜ አለ፤” ያለው ለዚህ ነበር።ጌታችንም በወንጌል፡- “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤” እያለ ደጋግሞ ተናግሮአል።ዮሐ፡፪፥፬፤፯፥፮ ፤ጊዜው ሲደርስ ግን፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤዛነቱ የጐደለውን ሁሉ ሙሉ አድርጐታል።                      

    ፫ኛ፡-ኪዳነ አብርሃም ነው፤አብርሃም፡-እግዚአብሔርን ፈልጐ ያገኘ፥ቃሉን ሰምቶ፡- ከዘመዶቹ ተለይቶ፥ከአገሩ ወጥቶ፥ወደ ከነዓን የተጓዘ የእግዚአብሔር ወዳጅ ነው።ከካራን ወጥቶ ወደ ከነዓን የተጓዘው እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ አምኖ ነው።“እግዚአብሔርም አብራምን አለው፡ -ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደ ማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብ(ብዙ ወገን) አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ (አገነዋለሁ፥ የብዙኃን አባት እንድትባል አደርግሃለሁ)፤ ለበረከትም ሁን፤ (ስምህ በሚጠራበት፥ መታሰቢያህ በሚደረግበት በረከት ይትረፍረፍ)፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ (የሚመር ቁህን እመርቃለሁ)፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ (የሚረግሙህን ሰዎች አጠፋለሁ)፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። (አብርሃምን ያከበረ ያክብርህ እያሉ በአንተ ስም ይመራረቃሉ)። ይላል። ዘፍ፡፲፪፥፩። አብርሃም ይኸንን  ቃል ኪዳን ተሸክሞ በስደት ብዙ መከራ ተቀብሎአል። ዘፍ፡፲፫፥፩። እግዚአብሔር በራዕይ እየተገለጠ ያነጋግረው ነበር። “ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋም አበዛዋለሁ።” ብሎታል። ዘፍ፡፲፫፥፲፬፤፲፭፥፭። ከዋክብት የተባሉት ከእርሱ ወገን የሚወለዱት ጻድቃን ሲሆኑ፥ አሸዋ የተባሉት ደግሞ ኃጥአኑ ናቸው። አብርሃም የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት የተገለጠለት፥ በድንኳኑም ያስተናገደ ሰው ነው።ሥላሴም ዘመን ከተላለፈው በኋላ ይስሐቅን እንደሚወልድ ነግረውታል። ፲፰፥፩-፲፩። የቃል ኪዳን ልጁን ይስሐቅን እንዲሰዋለት እግዚአብሔር ባዘዘውም ጊዜ፥ በፍጹም ሃይማኖት በመሠዊያ ላይ አጋድሞታል።ዘፍ፡፳፪፥፩-፲፰፣ ዕብ፡፲፩፥፲፯።                           

    ለአብርሃም በተሰጠው ቃል ኪዳን፥“የምድር አሕዛብ በአንተ ይባረካሉ፤” የሚለው፥ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመለከት ነው።ከአብርሃም ዘር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፥ ሕዝብንም አሕዛብንም እንደሚባርክ (እንደሚያድን) የተሰጠ ተስፋ ነበር። ቃሉ በደረሰ፥ ተስፋውም በተፈጸመ ጊዜ፥ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የአብርሃም  ልጅ ተብሎአል። ማቴ፡፩፥፩። የትውልዱንም ቍጥር ሲዘረዝር፡- “ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እሰከ ባቢሎን ምርኰ ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኰ እስከ ክርስቶስ ዐሥራ አራት ትውልድ ነው።”ይላል። ማቴ፡፩፥፲፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በበኵሉ፥ “የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም።” ብሎአል። ዕብ፡፪፥፲፮። በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ምን የሚነቀፍ አለው?                                                         

    ፬ኛ፡-ኪዳነ ዳዊት ነው፤ቅዱስ ዳዊት፡-በእግዚአብሔር ፈቃድ ከእረኝነት ቦታ ተጠርቶ ፥በነቢዩ በሳሙኤል እጅ ተቀብቶ፥ገና በብላቴናነቱ በእስራኤል ላይ የነገሠ ንጉሥ ነው። ፩ኛ፡ ሳሙ፡፲፮፥፲፫።ዙፋኑን ከመውረሱ በፊት፥ የመጀመሪያውን የእስራኤል ንጉሥ ሳኦልን በጋሻ ጃግሬነት (በጦር ዕቃ አንጋችነት) አገልግሎአል። ፩ኛ፡ሳሙ፡፲፮፥፲፰።የእስራኤልን አርበኞች ልብ ያሸበ ረውን ጎልያድን፥ የእግዚአብሔር ስም ኃይል ሆኖት፥ በወንጭፍ በተወረወረ ጠጠር ብቻ ግንባሩን መጥቶ የገደለ የልጅ አርበኛ ነበር። ፩ኛ፡ከሳሙ፡፲፯፥፵፭። ንጉሡ ሳኦል በጠላትነት ባሳደደው ጊዜ፡- በፍልስጥኤማውያን መካከል በስደት ተቀምጦ ችግሩን አሳልፎአል። ፩ኛ፡ሳሙ፡፳፥፳፩። ከጋሻ ጃግሬዎቹ ጋር ሆኖ በአዶላም ዋሻ የተሸሸገበት ጊዜም ነበረ። ፩ኛ፡ሳሙ፡ ፳፪፥፩።ቅዱስ ዳዊት፡- እግዚአብሔር ጠላቱን ሳኦልን በእጁ ላይ ቢጥልለት፥ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሳም፤” ብሎ ምሕረት አድርጐለታል።ጋሻ ጃግሬዎቹ ቢገፋፉትም አላደረገውም። ለምልክት እንዲ ሆነው፥ ንጉሡ ሳያውቅ የመጐናጸፊያውን ዘርፍ ቀድዶ ወሰደ። የሆነውን ሁሉ ሳያውቅ ከዋሻው የወጣውን ንጉሥ ሳኦልንም ተከትሎት ወጣ፥ ከፍ ባለ ድምፅም፡-“ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥” ብሎ ጮኸ ፤ወደ ምድር ተጐንብሶ እጅ ከነሣውም በኋላ፥“ዳዊት ክፉ ነገር ይሻብሃል፥የሚሉህን ሰዎች ቃል ለምን ትሰማለህ? እነሆ፥ ዛሬ በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ እንደ ሰጠህ ዓይንህ አይታለች፤አንተንም እንድገድልህ ሰዎች ተናገሩኝ፤እኔ ግን፡-በእግዚአብሔር የተቀባ ነውና እጄን በጌታዬ ላይ አልዘረጋም ብዬ ራራሁልህ፤ደግሞም አባቴ ሆይ፥የልብስህ ዘርፍ በእጄ እንዳለ ተመልክተህ እወቅ፤የልብስህንም ዘርፍ በቈረጥሁ ጊዜ አልገደልሁህም፤ ስለዚህም በእጄ ክፋትና በደል እንደሌለ፥አንተም ነፍሴን ልትወስድ ምንም ብታሳድደኝ እንዳልበደልሁህ ተመልክተህ እወቅ። እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መክከል ይፍረድ፥እግዚአብሔር አንተን ይበቀልልኝ፤እጄ በአንተ ላይ አትሆንም፤” አለው። ከትህትናውም ብዛት ራሱን በሞተ ውሻና በቍንጫ መስሎ፥ “እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ፤” አለ። ንጉሡም ጠላቴ ብሎ እንዳላሳደደው፥ “ልጄ ሆይ ዳዊት፥ይህ ድምፅህ ነውን?” ብሎ አለቀሰ።“እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፈንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ፤” በማለትም መሰከረለት።፪ኛ፡ሳሙ፡፳፬፥፩-፳፪።                                              

    ንጉሥ ዳዊት፡-ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ ያስቸግሩ የነበሩ ፍልስጥኤማውያንን አሸንፎ ጸጥ ያደረገ፥ የእስራኤል ጎረቤቶችን አስገብሮ፡- በደቡብ፣በሰሜንና በምሥራቅ ድንበር ያሰፋ፥ኢያ ቡሳውያንን አሸንፎ ታቦቱንም አምጥቶ ኢየሩሳሌምን መንፈሳዊ ከተማ ያደረገ ታላቅ ንጉሥ ነው። ፪ኛ፡ሳሙ፡፭፥፲፰፣ ፪ኛ፡ሳሙ፡፰፤፲፪፥፳፮፣ ፪ኛ፡ ሳሙ፡፭፥፩፣፪ኛ፡ሳሙ፡፮፤ ፩ኛ፡ዜና፡፲፭፥፲፮።ታላቅና  ገናና ንጉሥ ከመሆኑ የተነሣ፥ ለክርስቶስ መንግሥት ምሳሌ ሆኖአል። ፪ኛ፡ሳሙ፡፯፥፰፣ኢሳ፡፱፥፯፣ ኤር፡፳፫፥፭፣ ሕዝ፡፴፬፥፳፫፤ ፴፯፥፳፬፣ ሆሴ፡፫፥፮። ንጉሥ ዳዊት፡- እግዚአብሔር፡- ከመጀመሪያው፥“እንደ ልቤ የሆነ፥ ፈቃዴን የሚያደርግልኝ፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤”ብሎ የተናገረለት ሰው ነው። የሰጠውም ቃል ኪዳን፡-“ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥትህንም አጸናለሁ።እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸና ለሁ። እኔም አባት እሆነዋለሁ፥እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤” የሚል ነበር። ፪ኛ፡ሳሙ፡፯፥፲፪።ይህም፡-ለጊዜው ለልጁ ለሰሎሞን የተነገረ ሲሆን፥ለፍጻሜው ግን፥ከእርሱ ወገን ከሆነች ከድንግል ማርያም ስለሚወለደው፥ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ ነው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ እመቤታችንን ባበሠራት ጊዜ፥“ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን (ባለሟልነትን) አግኝ ተሻልና አትፍሪ።እነሆ ትፀንሻለሽ፥ወንድ ልጅንም (ወልድን) ትወልጃለሽ፥ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ ።እርሱም ታላቅ (ዓቢይ እግዚአብሔር) ነው፥የልዑል እግዚአብሔር ልጅ (ተቀዳሚና ተከ ታይ የሌለው የአብ የባህርይ ልጅ) ይባላል።(በተዋህዶ ሰው ሆኖ መወለዱ፥ አምላክ የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚያስቀር አይደለም)።እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። ለያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለሙ ይነግሣል፥ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” ያለው ለዚህ ነው።ሉቃ፡፩፥፴። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊም፡-ወንጌሉን፥“የዳዊት ልጅ፥የአብርሃም ልጅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ፤” በማለት ጀምሮአል። ማቴ፡፩፥፩።ሁለቱ ዕውራን፥“የዳዊት ልጅ ሆይ፥ማረን፤” ብለውት ዓይኖቻቸውን አብርቶላቸዋል።ማቴ፡፱፥፳፮።ሕዝቡም፡- ዕውርና ዲዳ የነበረውን እስኪያይና እስኪናገር ድረስ በፈወሰው ጊዜ፥ እጅግ ተደንቀው፥“እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” ብለዋል። ከነዓናዊቷም ሴት ወደ እርሱ የጮኸችው፥ “ጌታ ሆይ ፥የዳዊት ልጅ ማረኝ፤” ብላ ነው። ማቴ፡፲፭፥፳፩።ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡-ፈሪሳውያ ንን፥“ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል፥ የማንስ ልጅ ነው?”ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ፥“የዳዊት ልጅ ነው፤”ብለውት ነበር።ጌታም ጥያቄውን በጥያቄ ሲመልስ፥“እንኪያስ ዳዊት፡-ጌታ ጌታዬን፡-(ጌታ እግዚአብሔር አብ፥ጌታዬን እግዚአብሔር ወልድን) ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ አስከ ማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል፥እንዴት በመንፈስ (በትንቢት) ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?” ብሎ መልስ አሳጥቶአቸዋል። መዝ፡፻፱፥፩፣ ማቴ፡፳፪፥፵፩። ቅዱስ ዳዊት በትንቢት፡-“ጌታ፤” ብሎ የጠራው፥ ከአንድ ሺህ ዘመን በኋላ የእርሱ ወገን ከምትሆን፥ከንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም የሚወለደው፥ወልደ አብ፣ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው።                                

    እግዚአብሔር ቃል የተገባባው፥ውል የተዋዋለው ከወደዳቸውና ከመረጣቸው ጋር ነው ።ይኸንንም በቅዱስ ዳዊት አንደበት፥”ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ፡- ዘርህንም ለዘላለም አዘጋጃለሁ፥ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ።” በማለት ተናግሮአል። መዝ፡፹፰፥፫። እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ለቅዱሳን የሰጠውን ቃል ኪዳን ያላሰበበት ያልፈጸመበትም ጊዜ የለም። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- እሳተ መለኰትን በማኅፀኗ ተሸክማ፥“ብላቴናውን እስራኤልን ተቀበለ፤(እስራኤላዊት ብላቴና የምሆን የእኔን ሥጋና ነፍስ በማኅፀን ተዋሀደ)፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ እንደተናገረው ምሕረቱን አሰበ።” ያለችው ለዚህ ነው። ሉቃ፡፩፥፶፫።ጻድቁ ካህን ዘካርያስም፡-አድሮበት የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ሲያናግረው፥“ለአባቶቻችን ለአብርሃምም የማለውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤በእርሱም ከጠላቶቻችን (ከአጋንንት) እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት (በአጋንንት እጅ የተወረወረ ጦር፥ የተጣለ ጠጠር ያጠፋናል ብለን ሳንፈራ) በቅድስና እና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግል ሰጠን። (ነፍስ የተለየውን፥ መለኰት የተዋሀደውን ሥጋውን እና ደሙን ሰጠን)” ብሎአል።ሉቃ፡፩፥፸፭።           

    ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚመሰክሩት፥የኪዳናት ሁሉ ፍጻሜ፥እመቤታችን ቅድስት ድን ግል ማርያም ናት።ኪዳናቱም የምሕረትና የይቅርታ በመሆናቸው፥ኪዳነ ምሕረት ተብላለች። ቅዱሳን አበው፡-በምሳሌ ኦሪት፥ቅዱሳን ነቢያት ደግሞ በትንቢት እያይዋት፥እርስዋን ተስፋ አድ ርገው የኖሩት በዚህ ምክንያት ነበር።ምክንያቱም የሚያድናቸው፥በተዋህዶ ሰው ሁኖ ከእርስዋ የሚወለደው ነበርና።አባ ሕርያቆስ፡-በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፥“ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነበርሽ።”ያለው ለዚህ ነው።እንግዲህ በዝርዝር እንደተመለከትነው፥ጻድቁ ካህን ዘካርያ ስም እንደ መሰከረው፥ኪዳናቱ ቅዱሳት ናቸው።ታዲያ፥“ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ለሁለ ተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።”ለምን አለ? ዕብ፡፰፥፯።                                                                         ይቀጥላል . . .

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሃድሶ ክፍል ፯ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top