• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 18 January 2016

    ተሃድሶ ክፍል ፲፩

    ካለፈው የቀጠለ . . .

        “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።”         “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።” 

                ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ፩ኛ፡- ትንቢቱን እና ምሳሌውን ለመፈጸም፤ ፪ኛ፡- በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፤ ፫ኛ፡- በጥምቀቱ ጥምቀታችንን ለመቀደስ፥ በፈለገ ዮርዳኖስ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ጌታ ነፍስን እና ሥጋን ተዋህዶ በማዕከለ ዮርዳኖስ በቆመ ጊዜ፥ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወረደ፥ አብ የክብሩ መገለጫ በሆነ ደመና ሆኖ፡- በተዋህዶ ፍጹም ሰው የሆነውን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን፡- “የምወደው ልጄ ይህ ነው፤” አለ። በዚህ ዓይነት ምሥጢረ ሥላሴ በዮርዳኖስ በገሀድ ታየ። ማቴ፡ ፫፥፲፫-፲፭፣ ማር፡፩፥፱-፲፩፣ ሉቃ፡፫፥፳፩፣ ዮሐ፡፩፥፴፪-፴፱።                                      

    ጌታችን ከጥምቀቱ በኋላ ልዋል ልደር ሳይል ዕለቱኑ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ወረደ፥ በዚያም አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ጾመ። በባህርዩ ረሀብ የሌለበት አምላክ፥ ረሀብ የሚስማማውን የሥጋን ባህርይ ተዋህዶ፥ አንድ አካል አንድ ባህርይ በመሆኑ ተራበ። በዚህን ጊዜ፡- ቀዳማዊ አዳምን በመብል ያሳሳተ ሰይጣን፥ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስንም በመብል አሳስታለሁ ብሎ፥ “አሁን ርቦሃል፤ የእግዚአብሔር ልጅ (የአብ ልጅ ወልድ፣የአምላክ ልጅ አምላክ) ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝና ብላ፤” አለው። እርሱም መልሶ፡- “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአልና፤” አለው። በስስት ቢፈትነው በትዕግሥት ድል አደረገው። ማቴ፡፬፥፩-፭። ጌታችን፡- ስለጾመ ክብር የሚጨመርለት፥ ስላልጾመ ደግሞ ክብር የሚቀርበት አምላክ አይደለም። እርሱ እከብር አይል ክቡር፥ እጸድቅ አይል ጻድቅ ነው። ነገር ግን ለእኛ ምሳሌ፣ አብነት ሊሆነን፥ እንደ ሙሴ፣ እንደ ኤልያስ (ሥርዓተ ጾምን አክብሮ) አርባ ቀን አና አርባ ሌሊት ጾመ። “እስከ መጨረሻው በጾም በጸሎት ተወስናችሁ ብትኖሩ ጥንተ ጠላታችሁን ዲያብሎስን ድል ታደርጉታላችሁ፤” ሲለን ነው።ዘጸ፡፴፬፥፳፰፣፩ኛ፡ነገ፡፲፱፥፰።                     

    ይኸንን፥ ጌታ፡- ዲያብሎስን ያሳፈረበትን ቃል ተፈጽሞ የምናገኘው በቅዱሳን ገድል ውስጥ ነው። ለአብነትም የጻድቁን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ገድል እንመለከታለን። የአባቱ ስም ስምዖን፥ የእናቱ ስም ደግሞ አቅሌስያ ይባላል። የተወለደው በደቡብ ግብፅ ከቆላው ሀገር ንኂሳ ነው። የተፀነሰውም የተወለደውም፥ ጌታ በተፀነሰበት እና በተወለደበት ዕለት ነው። (ፅንሰቱ መጋቢት ፳፱፥ልደቱ ታኅሣሥ ፳፱ ነው)። ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በተወለደበት ዕለት፡- ከእናቱ እቅፍ ወርዶ፥ ለሥላሴ ከሰገደ በኋላ፡- “ከጠባብ ማኅፀን ወደ ሰፊው ዓለም፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ስለ አወጣኸኝ አመሰግሃለሁ፤” ብሎአል። በዚህም ቅዱስ ዳዊት ተናግሮት በዕለተ ሆሣዕና የተፈጸመው ቃል፥ ዳግም ተፈጽሞአል። “ከሕፃናት እና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፤” ይላል። መዝ፡፰፥፪፣ ማቴ፡፳፩፥ ፲፮። ከዚህ በኋላ እናቱ አላቀፈችውም፥ ጡቷንም አልጠባም፥ከሦስት ዓመትም በኋላ፥ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ እግዚአብሔር በነገረው መሠረት፡- ወደ ገዳም ወሰደው፤ አበ ምኔቱንም፡- “ሕፃኑን ከበር አንሥተህ ካንተ ዘንድ አኑረው፥ ስለ ልብሱና ስለ ምግቡ አታስብ፥ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በመሆኑ ምግቡ መንፈሳዊ ነው፥በወንጌል እንደተነገረ፡- ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር እወቅ፤” አለው። አባ ዘመደ ብርሃን፡- መልአኩ እንደ ነገረው፡- ሕፃኑን ተቀብሎ ወደ በዓቱ አስገባው። የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እያስተማረም አሳደገው። ትምህርቱን እንደጨረሰም ከብፁዕ አቡነ አብርሃም እጅ ማዕርገ ዲቁና ተቀበለ። እንደ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም ጸጋን እና ሞገስን የተሞላ ሆነ። የሐዋ፡፮፥፭። ከዚህም በኋላ፡- ሥርዓተ ምንኵስናን ተቀበሎ ቀሰሰ። ከዕለታትም በአንዱ ቀን፡- ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ፥ በሕፃንነቱ ጊዜ እንደ አደረገው፥ ወደ ሰማይ አሳርጐ በጌታ ፊት አቆመው። ጌታም ከሰው ተለይቶ በምድረ በዳ(በበረሀ) ከአራዊት ጋር እንዲኖር ነገረው። ከዚህ በኋላ መልአኩ ወደ ቀደመ ቦታው መልሶት ድንቅ ድንቅ ተአምራት ያደርግ ጀመር። ጽሕሙና ጸጉሩም አድጐለት መላ ሰውነቱን ሸፈነው። ብፁዕ አባታችን፡- ጸጋውን ክብሩን እና ተአምራቱን ሰዎች እንደ አወቁበት በተረዳ ጊዜ፥ ጌታ እንደነገረው ከሰው ተለይቶ ኑሮውን በበረሀ አደረገ።                                                            

    ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፡- በበጋው ሐሩርና በክረምቱም ቍር እየተሰቃየ፥ በገድል እየተቀጠቀጠ ሲኖር ለሰውነቱ ልብስ አልነበረውም። በጾም፥ በጸሎት፥ በስግደትና በብዙ ትጋት በቀንም በሌሊትም ጽሙድ መሆኑ ሰማያውያን መላእክትን አስመስሎታል። ሥጋው እስኪደርቅ፥ ቍርበቱ ከአጥንቱ እስኪጣበቅ ድረስ፥ ከእንጨት ፍሬና ስራ ስር ወይም ከአትክልት ወይም ገዳማውያን ከሚመገቡት ከሌሎች ፍሬያት ምንም ምን የሚመገበው አልነበረውም። በእውነትም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፡- ቅዱሳን መላእክትን መሰለ። በዚህ በኃላፊው ዓለም ለመብል ለመጠጥ አላሰበም፥ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ተራበ ተጠማ፥ ይላል። ጌታ በወንጌል፡- “ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤” ያለው፥ለዚህ ነውና። ማቴ፡፭፥፮።                                    “ይህን ሾላ፡-ተነቀለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት ይታዘዝላችሁ ነበር።”                      

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ፡- መሰናክል(መከራ) ሳይመጣ እንደ ማይቀር፥ መሰናክሉን የሚያመጣ ሰው ወዮታ እንደ አለበት፥ ከታናናሾቹ አንዱን ከማሰናከል፡- የወፍጮ ድንጋይ በአንገት አስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስመጥ እንደሚሻል (ከባድ ቀኖና ተቀብሎ በዕንባ ባሕር ቢሰምጥ እንደሚጠቅ መው)፥ ወንድም ቢበድል መገሠጽ እንደሚገባ፥ በቀን ሰባት ጊዜም ቢሆን፡- ተጸጽቶ ከተመለሰ ይቅር ማለት እንደሚያስፈልግ፥ ነግሮአቸው ነበር። በዚህን ጊዜ፡- “እምነት ጨምርልን፤” ብለው ጠይቀውታል። እርሱም፡- “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል (ጥርጥር የሌለው) እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፡- ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት ይታዘዝላችሁ ነበር።” ሲል መልሶላቸዋል። ሉቃ፡፲፯፥፩-፮። ይኸንን የወንጌል ቃል በተግባር ተተርጉሞ የምናገኘው በቅዱሳን ገድል ውስጥ ነው። ለዚህም የብፁዕ አባታችንን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገድል እንመለከታለን።                           

    የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ፥የአናቱ ደግሞ እግዚእ ኀረያ ይባላል። የተወለደው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፩፺፯ ዓ.ም. ገደማ ነው፥ ስሙም ፍስሐ ጽዮን ተብሎአል። “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፤” እንዲል፡- በተወለደ በሦስተኛው ቀን፡- “አሐዱ አብ ቅዱስ፥ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፥ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤” እያለ ሥላሴን አመስግኖአል። ጣቱንም አመሳቅሎ እየባረከ፥ በረከት አትረፍርፎአል። ጸጋ ዘአብ ካህን ስለነበረ የቤተክርስቲያን ትምህርት እያስተማረ አሳድጐታል። በሰባት ዓመቱ ዲቁናን ከግብፃዊው ከአቡነ ቄርሎስ ተቀብሎአል። ከጓደኞቹ ጋር አደን ላይ እያለ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ጠራው፤ ጌታዬ ሆይ፥ የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ፥ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ፤” ብሎ ተከተለው።                                                                                 

    ሁሉን ትቶ ፈጣሪውን በተከተለ ጊዜ፥ በየዕለቱና በየሰዓቱ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በእርሱ ላይ መገለጥ ጀመረ። የተአምራቱም ዜና በዐራቱ ማዕዘን ተሰማ፥ ሰዎች ሁሉ እየመጡ በእርሱ ይባረኩ ነበር፥ በሽተኞችንም በፈጣሪው ኃይል ይፈውሳቸው ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ፥ ቸይ የሚባለውን ወንዝ ተሻግሮ ከተታ የምትባል አውራጃ ደረሰ። ሕዝቡንም፡- እግዚአብሔርን የማያውቁ ከእንስሳም የማይሻሉ ሆነው አገኛቸው፥ የሚያመልኩትን ቢጠይቃቸው፡- ዛፍ እንደሚያመልኩ፥ ከዛፉም፡- “ፈጣሪያችሁና አምላካችሁ እኔ ነኝ፤” የሚል ድምፅ እንደሚሰሙ ነገሩት። ወስዳችሁ አሳዩኝ ብሎአቸው ከዛፉ ሲደርሱ፥ በዛፉ ያደረው ሰይጣን፡- “እላንት የዚህች አገር ሰዎች፡- ከኔ ባሕርይ ልዩ የሆነ ምን አመጣችሁብኝ፥ ይኸውም በመካከላችሁ ያለ ተክለ ሃይማኖት ነው፤” እያለ ጮኸ። ሕዝቡም፡- “ፈጣሪያችን ስለጠላህ ወደ እኔ አታምጡብኝ እያለ በሩቁ እየጮኸ ነውና ሄደን እስክንለምነው ድረስ እባክህ ከዚህ ቆይ፥ ከለመንነው በኋላ ትመጣለህ አሉት።አባታችን ተክለ ሃይማኖትም፡- “እኔ ከሩቅ አገር ስለመጣሁ የሚጠላው እኔን አይደለም፥ እንዲያውም ጌትነቱ በእኔ ላይ እንዲገለጥ ደስ ይለዋል፥ ነገር ግን ከእናንተ መካከል የሚጠላው ሰው ካለ ፈልጉ፤” አላቸው። የሀገሩም ሰዎች፡- “ተክለ ሃይማኖት የምትባል አንተ ነህን? ከሆነ ጀምሮ በዚህ ስም የሚጠራ ሰው ሰምተን ስለማናውቅ እንግዳ ነገር ነው፥ አሁንም ፈጣሪያችን እንዳይቆጣን ከዚህ ቆይ፤” ብለውት፥ ሦስት ኪሎ ሜትር ከሚርቅ ቦታ ላይ ትተውት ሊሰግዱ ሄዱ።             

    ብፁዕ አባታችን ተክለ ሃይማኖትም፡- የእምነታቸውን ከንቱነት፥ የሥነ ምግባራቸውንም ጸያፍነት ተመልክቶ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጸለየ። “አቤቱ ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፡- የሃይማኖቴን ጽናት፥ የምግባሬንም ደግነት ተመልክተህ፥ በዚህ ሕዝብ ፊት ተአምራትህን ግለጥ፤” እያለ አጥብቆ ለመነ። ጸሎቱንም ከጨረሰ በኋላ፥ ፊቱን ወደ ዛፉ መልሶ፥ እንደ ወንጌሉ ቃል፡- “ሰይጣን በአንተ አድሮ እየተናገረ ሕዝቡን የሚያስትብህ አንተ ዛፍ፥ ሁሉም የፈጣሪዬን ኃይል ያዩ ዘንድ፥ ከስርህ ተነቅለህ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ፥ በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዤሃለሁ፤” አለው። በዚህን ጊዜ ሕዝቡ እያዩ ዛፉ ከስሩ ተነቅሎ ወደ አባታችን መጣ። ሰይጣኑም፡- “አንተ ክፉ ሰው እንግዲህ ከአንተ ወዴት እሸሻለሁ፥ መላውን የጽላልሽን አውራጃ የተውኩልህ አልበቃህ ብሎ ወገኖቼን ልትቀ ማኝ ከዚህ መጣህን?” እያለ ከመለፍለፍ አላቋረጠም ነበር። አባታችንም የሚከተለውን ዛፍ ባለህበት ጸንተህ ቁም ቢለው ጸንቶ ቆመ። በዛፉ ላይ ያደረውንም ሰይጣን፡- “እኔ ፈጠርኳችሁ እያልክ ሰውን ሁሉ ለምን ታስታለህ?” አለው። ሰይጣንም፡- “እኔ ሐሰተኛ የሐሰት ምንጭ እንደሆንኩ ከቶ አታውቅምን? በእኔ ለሚያምን ሁሉ እንደለመድሁ ሐሰት እነግረዋለሁ፥ አሁን ግን እባክህ ተወኝና ልሂድበት፥ ዳግመኛ ወደዚህች አገር እንደማልመለስ፥ አንተም ካለህበት ቦታ ፈጽሞ እንደማልደርስ እምልልሃለሁ፤” አለው። ብፁዕ አባታችን ተክለ ሃይማኖትም፡- እውነቱን እንዲናገር ሰይጣንን አስገደደው። ሰይጣንም፡- “ስግደትና አምልኰት የሚገባው፡- ለተክለ ሃይማኖት ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ፥ ለባህርይ አባቱ ለአብ እና ለባህርይ ሕይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ እንጂ ለእኔ አይደለም፤” ብሎ ሳይወድ በግድ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙት ተናገረ። ከዚህ በኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሰይጣንን፡- በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ቢገሥጸው፥ እንደ ጢስ በንኖ፣ እንደ ትቢያም ተበትኖ ጠፋ። በመጨረሻም ሕዝቡ፡- እግዚአብሔር በጻድቁ እጅ ያደረገውን ተአምራት አይተው፥ እግዚአብሔር እርሱ ፈጣሪ እንደሆነ አምነው በመጠመቅ ክርስቲያኖች ሆኑ። እንግዲህ እንዴት ነው፥ይህ የቅዱሳን ገድል የኢየሱስን ስም ሸፈነው የሚባለው?እኛ ግን የምናምነው፥ ቅዱሳን በገድላቸው ኢየሱስን ገለጡት፥ ኢየሱስም እነርሱን በምድርም በሰማይም ገለጣቸው ብለን ነው። ምክንያቱም ጌታችን በወንጌል፡- “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤” ያለው ለዚህ ነውና። ማቴ፡፲፥፴፪። በብሉይ ኪዳንም ዘመን ቢሆን፡-እግዚአብሔር፡-“አብርሃም ነቢይ ነው፥ስለ አንተ ይጸልያል፥ ትድናለህም፤” በማለት አብርሃምን ገልጦታል። ዘፍ፡፳፥፯።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሃድሶ ክፍል ፲፩ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top