• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 18 January 2016

    ተሃድሶ ክፍል ፲፫


             ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቅዱሳን፡-                             ካለፈው የቀጠለ. . .       

                                                                        

                        “አንተ ጴጥርስ (የዓለት መሠረት) ነህ፤”፩ኛ፡ጴጥ፡፲፮፥፲፰። 

                                         

    የዮና ልጅ ስምዖን፡- በፊልጶስ ቂሣርያ፡-ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የአብ የባህርይ ልጅ፤” መሆኑን፥ በመመስከሩ፥ “አንተ መሠረት ነህ፤”ተብሎአል። መሠረት በመባሉም፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለቅዱሳን የተሰጠ ጸጋ የማይናወጥ ጽኑዕ መሆኑን እንገነዘባለን። ጽኑዕ መሠረት ደግሞ እንኳን እርሱ ሊናወጥ፥ በእርሱ ላይ የተመሠረተ ቤት እንኳ አይናወጥም። “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን (የመሠረተን) ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፥ ጐረፍም መጣ፥ ነፋስም ነፈሰ፥ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለተመሠረተ አለወደቀም።”ይላል። ማቴ፡፯፥፳፬። ቤት የተባለው የሰው ሕይወት ሲሆን፥ በዝናብ በጐርፍ እና በነፋስ የተመሰለው ደግሞ መከራ ነው። እንግዲህ የጌታ ቃሉ ወንጌል፥ በመከራ መካከል ጸንተን ለመቆም እንደሚረዳን ሁሉ፥ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃም በመከራ መካከል ጽኑዕ መሠረት ይሆንልናል፥ማለት ነው።ምክንያቱም፡-ሁላችንም እንደምናውቀውና እንደምናምነው፥ እንደ ቃሉ የመኖር ፍጹማን አይደለንም። ብዙ፥ የብዙ ብዙ፥ የሚጐድለን ነገር አለ። ቃሉን እንናገረዋለን እንጂ አንኖረውም። ስለዚህ የሚያበረታን ያስፈልገናል። ስምዖን ጴጥርስ፡-“አንተ መሠረት ነህ፤ ”የተባለው ለግል ሕይወቱ ብቻ አይደለምና። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ፡- “በዚችም ዓለት ላይ  ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ (ምእመናንን እሰበስባለሁ፤)”ብሎታል።   

                         

    አንድን ታላቅ ሕንፃ፡- ሰማይ ጠቀስም ቢሆን አጽንቶ የሚያቆመው መሠረቱ ነው። በዚህ ምሳሌ መሠረት በክርስትና ሕይወት የሁሉ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።ይኸንንም ታላቁ  ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፡-“የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን አንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” በማለት ነግሮናል። ፩ኛ፡ቆሮ፡፫፥፲።ይህ ቃል በቤተክርስቲያን የታመነ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የእርሱን መልክ እንዲመስሉ የወሰነላቸውን ቅዱሳንን፥ (እርሱ ብርሃን ሲሆን፥ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፥ ያላቸውን ወዳጆቹን)፥ የቤተክርስቲያን መሠረት አድርጐአቸዋል። በመሆኑም ሃይማኖታቸው፥ ምግባራቸው፥ ቅድስናቸው፥ ገድላቸው፥ ተአምራቸው፥ ትምህርታቸው፥ ቃልኪዳናቸው፥ አማላጅነታቸው ሁሉ መሠረት ነው።                                                              

    “መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤”ብሎ ያስተማረ ሐዋርያ፥ቅዱስ ጳውሎስም፡- የቅዱሳንን  መሠረትነት በሚገባ አስተምሮአል። ምክንያቱም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸው ጸጋ ነውና፥ እርሱም ራሱ የዚህ ጸጋ ባለቤት ነው። በመሆኑም፡- “እንግዲያስ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰብእ ናችሁ እንጂ መጻተኞች አይደላችሁም። በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንፃ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።” ብሎአል። ኤፌ፡፪፥፳። ሰማያዊ ምሥጢር በራእይ የተገለጠለት ቅዱስ ዮሐንስም፡- ስለ መንግሥት ሰማያት በዝርዝር ሲናገር፥“ ለከተማዪቱም ቅጥር አሥራ  ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት (ኢየሱስ ክርስቶስ መሠረት ያደረጋቸው ሐዋርያት) ስሞች ተጽፈው ነበር።. . . ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፥ ከተማዪቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች። ፊተኛው መሠረት ኢያሰጲድ ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ አሥረኛው ክርስጵራስስ አሥራ አንደኛው ያክንት፥ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ።” ብሎአል። ራእ፡፳፩፥፲፬-፳። ከዚህም የምንረዳው ትልቁ ነገር፥ የቅዱሳን መሠረትነት በምድር በአጸደ ሥጋ ብቻ ሳይሆን፥ በሰማይም በአጸደ ነፍስም ጭምር መሆኑን ነው። እንግዲህ የቅዱሳን ነገር በምድርም በሰማይም እንዲህ ከሆነ፥ የመናፍቃን የጥላቻቸው ምንጭ፥ ከቅዱሳን ከሳሽ ከዲያብሎስ እንደሆነ እናስተውላለን።       

                                                                                

    “በምድር ያሰራችሁትና የፈታችሁት በሰማይ የታሰረና የተፈታ ይሆናል፤”  

                                  

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ሁሉን ትተው ለተከተሉት፥ እስከ ሞት ድረስም ለታመኑት ቅዱሳን የሰጣቸው ጸጋ፥ በአንደበት ተነግሮ፥ በፊደልም ተቀርጾ የሚያልቅ አይደለም። ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ፥ በአጸደ ሥጋም በአጸደ ነፍስም የሚሠራ ነው። በአማናዊ ቃሉ፡-“እውነት እላችኋላሁ፥ በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” ያላቸው ለዚህ ነው። ማቴ፡፲፰፥፲፰። ይኽንን የመሰለ ቃል ለቅዱስ ጴጥሮስም ነግሮታል። ማቴ፡፲፮፥፲፰። በመሆኑም፡- እነርሱ በምድር የሚሠሩትን ሁሉ እርሱ በሰማይ ያጸናዋል፥ ማለት ነው። ይህ ጸጋ በዚህ ዓለም የሚቀር አይደለም፥ ይልቁንም ከዚህ ከክፉ ዓለም ተለይተው፥ ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር በሚቀርቡበት ጊዜ (በሰማይ ከእርሱ ጋር በሚኖሩበት ጊዜ) በዚያም ሥራ ይሠራል። የቅዱሳን ጸጋ ተከትሎአቸው እንደሚሄድ፥ በአጸደ ነፍስም እንደሚሠራ ምስክሩ መንፈስ ቅዱስ ነው። ራእ፡፲፬፥፲፫። ስለዚህ፡- ሊያስሩንም ሊፈቱንም በእኛ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ማመን ያስፈልጋል። ይህ ታላቅ ቃል ኪዳን የተሰጣቸው ቅዱሳን፡- በአማላጅነታቸው ከኃጢአት ማሰሪያ ይፈቱናል። ምክንያቱም ጸሎታቸው ኃጢአትን ያስተሰርያል። “የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፥ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል።. . . የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ፥ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች።”ይላል። ያዕ፡፭፥፲፭።     

                                                                                

    ይህ ሥልጣን ለቅዱሳን ብቻ የተሰጠ፥ በእነርሱም ብቻ የቀረ አይደለም፥ የእነርሱን ሃይማኖት ለያዙ፥ መንገዳቸውንም (ትምህርታቸውን) ለተከተሉ ካህናት ሁሉ ተሰጥቶአል። ጌታ እነርሱን  እንደ ሾማቸው፥ እነርሱም ተከታዮቻቸውን የሾሙት ለዚህ ነው። አድሮባቸው የሚኖር መንፈስ ቅዱስም በየጊዜው መመረያ ይሰጣቸው ነበር። “በአንጾ ኪያም ባለችው ቤተክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤. . . እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፡- በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ (ለክህነት አገልግሎት) ለዩልኝ አለ። በዚያን ጊዜ ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።” ይላል። የሐዋ፡፲፫፥፩። በዚህ አይነት፡- ዲያቆናት፥ ቀሳውስትና ጳጳሳት በመንፈስ ቅዱስ ተሹመዋል። የሐዋ፡፮፥፫፤ ፲፬፥፳፫፤ ፳፥፳፰። እስከ ዓለም ፍጻሜም ድረስ፥ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ይቀጥላል። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን፡- “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤” ያላቸው ለዚህ ነው። ማቴ፡፳፰፥፳።                                                                   

    ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በምድር ላሉ ምእመናን ብቻ አይደለችም፥ ገድላቸውን ፈጽመው ለሄዱ (በሰማይ ለሚኖሩ) ቅዱሳንም ናት። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን፡- በምድር ከክፉዎች የሥጋ ምኞቶች፥ ከአጋንንትም ጋር እየተዋጉ ያሉ ቅዱሳን እና ገድላቸውን ፈጽመው በሰማይ የሚኖሩ ቅዱሳን አንድነት ናት። ጌታችን፡- በአጸደ ነፍስ ያሉትን ሙሴንና ኤልያስን አውርዶ፥ በአጸደ ሥጋ የነበሩትን ደግሞ፡- ጴጥሮስን፣ ዮሐንስን እና ያዕቆብን ይዞ በደብረ ታቦር መታየቱ፥ ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው። ማቴ፡፲፯፥፮።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሃድሶ ክፍል ፲፫ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top