• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday 30 January 2016

    «ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡» ቅዱስ ያሬድ፡፡

    አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜንጥር 21-እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ

    «ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡» ቅዱስ ያሬድ፡፡
    ‹‹አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት፡፡›› ቅዱስ ዳዊት፡፡

    ‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ነይ!›› ጠቢቡ ሰሎሞን፡፡

    ከመጽሐፈ ተአምሯ

    እመቤታችን ከዚህ ዓለም ታልፍ ዘንድ የጸለየችው ጸሎት ይህ ነው፡- ‹‹ልመናዋ ክብሯ ለዘለዓለሙ በእውነት ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ይህ ነው፡- አምላክን የወለደች እመቤታችን በቤተልሔም ተቀምጣሳለች ‹አቤቱ ቸር ጌታዬ ሆይ! ከዚህ ሑከትና ኀዘን ከመላበት ዓለም ደገኛውን መልአክህን ልከህ ወደኝ› ስትል በጸለየች ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልተገለጸላት፡፡ እንዲህም እያለች ስትጸልይ ሰማይ ተከፈተ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ወደ እመቤታችን ወርዶ ‹ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ› በማለት የደስታ መልእክት ነገራት፡፡ ዳግመኛም ‹‹እነሆ ጸሎትሽ ከአንቺ ከተወለደው ከእግዚአብሔር ዘንድ ደረሰ፡፡ እንደፈቃድሽ ከዚህ በኃላፊው ዓለም ወደ ዘላለም ሕይወት ትሄጂ ዘንድ ልመናሽ ተሰምቶልሻል›› አላት፡፡

    እመቤታችንም ይህንን ነገር ከመልአኩ በሰማች ጊዜ ወደ በዓቷ ተመለሰችና ከዚያ የሚያገለግሏትን ደናግል ሰብስባ ‹አይሁድ ሁልጊዜ የልጄን መቃብር ይጠብቃሉና ስለዚህ የእኔን ከዚያ መገኘት አንድ ቀን ይገለጽላቸውና ከዚያ መግባት ይከለክሉኛል ብዬ ፈራሁ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ራሳችሁን ችላላችሁበሰላም ትኖራላችሁ እኔ ወደ ቤተልሔም እሄዳለሁና› አለቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ሁሉም በአንድነት ቃላቸውን አስተባብረው ‹ከአንቺ ጋር እንሄዳለን፡፡ ስለ አንቺ እናት አባታችንን፣ እኅት ወንድሞቻችንን ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሻልና እነሆ አሁንም አንቺ ከሄድሽበት እኛም አብረንሽ እንሄዳለን፣ ባለ ዘመናችን ሁሉ ከአንቺ አንለይም› አሏት፡፡ እመቤታችንም በዚያን ጊዜ ይዛቸው ወደ ቤተልሔም ሄደች፣ በዚያም ተቀመጠች፡፡ እንዲህም ያለቻቸው ስለአይሁድ ፍራቻ ሳይሆን ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሞት የመለየቷ ጊዜ ስለመድረሱ ነበር፡፡ እናንት የፍቅሯን ፈለግ የተከተላችሁና በፍቅሯ ቀምበር የተጠመዳችሁ የወንጌል ልጆች ሆይ እንግዲህ እመቤታችን በቤተልሔም ተቀምጣ ሳለች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከዚህ ዓለም በሞት የምትለይበትን ጊዜ በክብር እንደነገራት አስተውሉ፡፡ ልመናዋ ክብሯ ለዘለዓለሙ በዕውነት ይደርብን፡፡

    እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፡- በ50 ዓ.ም ገደማ በዕለተ እሑድ ጌታችን እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ ‹‹እናቴ ሆይ! ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፣ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?›› አለችው፡፡ ጌታችንም በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳያትና ‹‹እናቴ ሆይ! ሞትሽ ለእኒህ ቤዛይሆናቸዋል›› አላት፡፡ ለፍጥረታት ሁሉ እጅግ የምትራራ እመቤታችንም ‹‹እነዚህን ከማርክልኝስ ይሁን ልሙት›› አለችው፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ቅድስት ነፍስዋን ከክብርት ሥጋዋ ለይቶ በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ ‹‹እመቤታችሁን ቅበሩ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ይዘዋት ወደ ጌታ ሰማኔ ወሰዷት፡፡

    አበው ‹‹እመቤታችን ሆይ! ሞትሽ ሠርግን ይመስላል›› እንዳሉት የእመቤታችን እረፍት እንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት ቅዱሳን መላእክት በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟት እንጂ፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለች፤ በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች›› በማለት ዘምሯል፡፡ የእመቤታችን ሥጋዋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን አስቀድሞ አባቷ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት ሲናገር ‹‹አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› በማለት ተንብዮዋል፡፡ መዝ 131፡8፡፡ ይህም ‹‹ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ›› ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ከኖረች በኋላ ነብሷ ከሥጋዋ ተለይቶ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ‹‹ታቦት›› ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡

    ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌ ሲናገር «ወደጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፣ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ መዐዛቸውንም ሰጡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ» አለ፡፡ መኃ 2፡10-14፡፡ ይህ ኃይለ ቃል ሲተረጎም በውስጡ ብዙ ምሥጢራዊ ነገሮችን ያያዘ ነው፡፡ «በክረምትና በዝናብ» የተመሰሉ የእመቤታችን መከራዎች ናቸው፡፡ የመከራሽ ጊዜ አልፏል ሲላት «አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ» ማለቱ ከልጅሽ እግር ሥር ቁጭ ብለው ተምረው ወንጌልንየተቀበሉ ሐዋርያት አንቺን በእናትነት የተረከቡ የሐዋርያት ድምፅ ወይም ስብከት በምድር ሁሉ መሰማቱን ያጠይቃል፡፡

    ጠቢቡ ሰሎሞን «የዜማ ጊዜ ደረሰ» ያለው የመከሩን ወቅት ነው፡፡ መከር የፍሬ ጊዜ እንደመኖኑ ሐዋርያት የዘሩት ዘር ማለትም ስብከታቸው ፍሬ አፈራና ክርስቲያኖች በዙ፤ «በለሱ ጎመራ» በጎ ምግባር የሌላቸው ሰዎች በሐዋርያት ስብከት ተምረው ምግባር መሥራት ጀመሩ፤ «ወይኖች አብበዋል መዐዛቸውንም ሰጥተዋል» በመላው ዓለም ያሉ ምዕመናን በሃይማኖት ማበብ፣ መዐዛ ምግባራቸውን ማቅረብ መስጠት ጀመሩ በማለት ሊቃውንት አባቶች ምሥጢሩን ያብራሩታል፡፡ በዚህ ትርጓሜ ‹‹ወደጄ ሆይ! ተነሽ›› እያለ የሚናገረው ተወዳጁ ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ድንግልማርያምን በመለኮታዊ ስልጣኑ ከሙታን ለይቶ ማስነሣቱን ሲያስረዳን ነው፡፡

    ስለዚህ ድንቅ ምስጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› (መዝ 131፡8) ብሎ የተናገረው ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍትና ትንሳኤ እንዲሁም ፍልሰት (ዕርገት) ከማሳየቱም በተጨማሪ የአምላክ እናት በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በክብር መኖሯንም በግልጽ ያስረዳል ያስገነዝባል፡፡ ‹‹በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› (መዝ 44፡9) የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ትንቢታዊ ቃል ሊቃውንት አባቶች በተለይም የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መተርጉማን ‹‹ንግሥተ ሰማይ ወምድር ድንግል ማርያም በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና›› ተሸልማና አጊጣ በሰማያዊው ዓለም በልጇ መንግሥት በክብር መኖሯን የሚያመለክት መሆኑን አስረግጠው አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሰማያዊው አባታቸውን እግዚአብሔርን ‹‹አቡነ ዘበሰማያት፤ በሰማያት የምትኖር አባታችን›› እያሉ ዘወትር ሲያመሰግኑ፤ በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊት እናታቸውን ድንግል ማርያምን ‹‹በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ፤ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ›› እያሉ ዘወትር ያከብሯታል ያመሰግኗታልም፡፡ ሉቃ 1፡28፡፡

    ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዘወትር በምንጸልየው የእሑድ የእመቤታችን ውዳሴ ላይ ‹‹ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር፣ ምልዕተ ውዳሴ የሆንሽ ድንግል ሆይ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልኝ ዘንድ ለአንቺ ይገባል፡፡ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ፤ ከቅዱሳን ነቢያት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት ከሰብዓ አርድእትም ትበልጫለሽ፡፡ ዳግመኛም ከሱራፌልና ከኪሩቤል ይልቅ የሚበልጥ የመወደድ የመፈራት ግርማ አለሽ፡፡ በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፡፡ ለሰውነታችንም ሕይወትን፣ ድኅነትን የምትለምኚና የምታማልጅን አንቺ ነሽ›› በማለት የእመቤታችን ልዕልናዋን የጸጋዋን ፍጹምነትና የክብሯን ታላቅነት በአጽንኦት ገልጾ መስክሯል፡፡

    እመቤታችን በጥር ሃያ አንድ ቀን በታላቅ ክብር ካረፈች በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በፈቃደ እግዚአብሔር ከያሉበት መጥተው በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የፈጣሪያችን እናት ድንግል ማርያምን በጸሎትና በማዕጠንት አክብረው ገንዘው ጥልቅ በሆነ ኃዘን ሊቀብሯት ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና «ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተቀብሮ ሳለ ተነሣ እያሉ ሕዝቡን አስኮበለሉ አሁን ደግሞ እናቱን ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያውኩ ሥጋዋን እናቃጥል» በሚል የክፋት ምክር ተነሳሱ፡፡ በተለይም ደግሞ በእመቤታችን ላይ በክፋትና በተንኮል ከተነሳሱት ከእኒህ አይሁድ መካከል ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊአማናዊት ታቦተ እግዚአብሔር የሆነችው የድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ ያረፈበትን አልጋ ለመያዝ እጁን በድፍረት ዘረጋ፡፡ በዚህን ጊዜ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን (2ኛ ሳሙ 6፡6፤ 1ኛ ዜና 13፡7-10) ላይ የአሚናዳብ ልጅ ዖዛ እጁን በታቦተ ጽዮን ላይ በድፍረት በመዘርጋቱ ምክንያት ተቆጥቶ እንደቀጣው ታውፋንያንም ሰማያዊው መልአክ ሰይፍ እጆቹን ቀጣው ቆረጠው፡፡ «እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንም (1ኛ ሳሙ 26፡9) እንደተባለ እጆቹም አልጋው ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡

    ታውፋንያም ስለተቆረጡት እጆቹ ወደ እመቤታችን አምኖ ወደ እርሷ ቢጮህ ቢማጸናት፤ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካይኝነት እጆቹን እንደ ቀድሞ ሆነው ድነውለታል፡፡ በጌታችን ትእዛዝ መልአኩ የእመቤታችንን ቅዱስ ሥጋ ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር በክብር አኑሮታል፡፡ቅዱሳን ሐዋርያት ዮሐንስ ከተመለሰ በኋላ ‹‹እመቤታችን እንደምን አለች?›› አሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም «ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች» አላቸው፡፡ እነርሱም ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ጥር አርፋ በነሐሴ ወር ሁለት ሱባኤ ይዘው ሲጨርሱ በነሐሴ 14መልአኩ ቅዱስ ሥጋዋን ከገነት አምጥቶ ሰጥቷቸው በጸሎትና በምሕላ ቀብረዋታል፡፡ በዚህ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረም፡፡ በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ፣ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ያገኛታል፡፡ በዚህ ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው፣ ለእርሱ የቀረበት መስሎት አዝኖ ‹‹በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከደመናውለመውደቅ ተመኘ፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አጽናናችው፡፡ ከእርሱ በቀር ትንሣኤዋን ሌላ እንዳላየ ነገራው ለምስክር እንዲሆነው ሰበኗን/መግነዝሰጥታው ዐረገች፡፡

    ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ ክብርት እናቱ እመቤታችም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጇ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ ‹‹እንደ ልጅዋ ትንሣኤ›› ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያት ወዳሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ምስጢሩን ደብቆ ‹‹ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር›› አላቸው፡፡ ሐዋርያትም ‹‹አንተ ተጠራጣሪ ነህ›› ብለው መቃብሩን ሊያሳዩት ሲከፍቱ አጧት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹እመቤታችን ተነሥታ አርጋለች›› ብሎ ሁኔታውን ተረከላቸው፡፡ ‹‹ለምስክር ይሁንህ›› ብላ የሰጠቸውንም ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን አይተው ትንሣኤዋን አመኑ። ሰበኗን ቆራርጠው ለበረከት ተከፋፍለው ወደየሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል፡፡ ዛሬም በመጾር መስቀልና በካህናት እጅ መስቀላቸው ላይ የሚያስሯት‹‹መሀረብ›› የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡ በዓመቱም ሐዋርያት ‹‹ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እንዴት እኛ ይቅርብን!›› ብለው ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በነሐሴ 16 ቀንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ ሰማይ አሳርጎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቅዳሴ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገቷን በዓይናቸው አይተውና በሚገባ ተረድተው ዓለምን ዙረው አስተምረዋል፡፡ ልመናዋ ክብሯ ለዘለዓለሙ በዕውነት ይደርብን፡፡

    ከመጽሐፈ ስንክሳር፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመሞቷ በፊት በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለእመቤታችን ከዚህ ዓለም እንደምትለይ ነገራት፡፡ ጌታችንም በደብረ ዘይት ላሉ ደናግላን ነግሯቸዋልና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት መጡ፡፡ እርሷም መንፈስ ቅዱስ የነገራትን ለእነርሱ ነገረቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ እመቤታችን እንዲህ ብላ ጸለየች፡- ‹‹ልጄ ወዳጄ፣ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ልመናየን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚህች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም ሕያዋን የሆኑትን ሐዋርያትን ሁሉንም ነፍሶቻቸውን የለየሃቸውንም ሁሉ ወደ እኔ አምጣቸው፤ አንተ የሕያዋን አምላክ ነህና ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን›› አለች፡፡

    በዚያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ቅዱስ ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን አደረሰችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በፊቷ ሰገደላትና እንዲህ አላት፡-‹‹ሰላምታ ይገባሻል፣ ጌታችንን ፈጣሪያችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሽው ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ከዚህ ዓለም ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ትሄጃለሽና፡፡ ይህም ስሙ ክቡር ምስጉን የሆነ ጌታችንና ፈጣሪያችን ድንቅ ድንቅ ተአምራቶችን በአንቺ ላይ ከገለጠ በኋላ ነው›› አላት፡፡ እመቤታችንም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እግዚአብሔርንምእንዲህ ብላ አመሰገነችው፡- ‹‹ፈጣሪዬ ጌታዬ ላንተ ምስጋና ይሁን፣ የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና፡፡ አሁንም ነብሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊይሳርጓት ከሚመጡ ቅዱሳን መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ›› አለችው፡፡ በዚያም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ፡- ‹‹እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ፡፡ ሐዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ፡፡ ወዲያውም ሁሉም ሐዋርያት የሞቱት ከመቃብራቸው ተነሥተው በሕይወት ያሉትም ሁሉም ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት፡፡ ‹‹አምላካችን ከአንቺ የተወለደ ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ፣ እርሱ ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከእርሱ ጋር ያሳርግሻልና››አሏት፡፡

    በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በዐልጋዋ ላይ ተቀመጠችና ሐዋርያትን እንዲህ አለቻቸው፡- ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን ዐወቅሁ፡፡ ከዚህ ከሥጋዬ ወጥቼ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እሄዳለሁ፡፡ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ፣ እኔ ከዚህ ዓለም እንደምለይ ከወዴት ዐወቃችሁ?›› ብላ የጠቀቻቸው፡፡ በመጀመሪያ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚያም ሁሉም ሐዋርያት ‹‹ወደ አንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን፣ በደመና ላይም በተጫን ጊዜ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነን ደረስን›› አሏት፡፡

    እመቤታችንም ይህን ነገር ከሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፡- ‹‹ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈጽሜ አመሰግናለሁ፣ የእኔን የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል›› አለች፡፡ ጸሎቷንም ስትጨርስ ሐዋርያትን ‹‹ዕጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ጥሩት›› አለቻቸው፡፡ እነሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ፡፡ በዚያም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን እልፍ አእላፍ ቅዱሳን መላእክቱ አጅበው እያመሰገኑት መጣና እመቤታችንን አረጋጋት፡፡ ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት፡፡ በዚያም ጊዜ ድንቆቸ የሆኑ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ዓይነ ሥውራን ማየት ቻሉ፣ ደንቆሮች መስማት ቻሉ፣ ዲዳዎች ተናገሩ፣ ለምጻሞች ነጹ፣ ሐንካሶች መሄድ ቻሉ፣ ደዌ ያለበትም ሁሉ ዳነ፡፡ የብርሃን እናቱ ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ወደ አለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌአቸው ሁሉ ይፈወሳሉና፡፡

    ከዚህም በኋላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጇን ‹‹በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሣ ከእሳት ባሕርም የተነሣ እፈራለሁ›› ባለችው ጊዜ እርሱም ‹‹እናቴ ሆይ ከእነርሱ ለማንም በአንቺ ላይ ሥልጣን የለውም›› አላት፡፡ ከሥጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትንና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት፡፡ እመቤታችንም እጇን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ጌታችን ቅድስት ንጽሕት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጎናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት። ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው፤ወደ ጌቴ ሰማኒ ተሸክመው እንዲወስዷ ሐዋርያትን አዘዛቸው፡፡ ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃን እያየች ነበር፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችንም ‹‹እንግዲህ ሥጋሽን ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ፡፡ ዳግመኛም ሥጋሽን ከነፍሽ ጋር አዋሕጄ አስነሥቼ መላእክት በፊትሽ ሆነው በሚያመሰግኑበት አምሳያ በሌለው ተድላ ደስታ ባለበት መኖሪያ አኖርሻለሁ›› አላት፡፡

    እመቤታችንም እንዲህ አለች፡- ‹‹አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሠራህ አመሰግንሃለሁ፤ ሁለተኛም ልመናየን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ በስሜ ወደአንተ የሚለምነውን ሁሉ፤ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወደ አንተ የሚለምነውን ከመከራም ሁሉ አድነው፤ በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሃሊ ነህና መታሰቢያየን በውስጧ የሚያደርጉባትን ቦታ ሁሉ ባርክ፣ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መሥዋዕታቸውን ተቀበል›› አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት፡- ‹‹የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ ደስ ይበልሽ፣ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህ ዓለምም በወዲያኛው ዓለምም ከቶ አይጠፋም›› አላት፡፡ እመቤታችንም በታላቅ ክብር ካረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሊወስዷት ሐዋርይት ገንዘው ተሸከሟት፡፡ አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊይቃጥሉ ወጡ፡፡ ከእርሳቸውም አንዱ ከምድር ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ፡፡ ያን ጊዜም ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋው ላይ ጠንጠለጠሉ፡፡ ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ፡- ‹‹የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ሆይ! አንቺ በእውነት ድንግል ይሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ አለምንሻለሁ፡፡›› በሐዋርይትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ፡፡

    ሐዋርያትም እመቤታችንን በቀብሯት ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ፣ ዕረፍቷም የሆነው እሑድ ቀን ጥር ወር በ21 ቀን ነበረ፡፡ ጌታችንም ብርሃናውያን መላእክትን ላከ፣ እነርሱም ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሯት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲያሳርጓት እመቤታችንን አገኟት፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ‹‹ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርይም ና እጅ ንሣ›› አሉት፡፡ እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ፡፡ እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንዳረፈችና እንደ ቀበሯት ነገሩት፡፡ ቶማስም ‹‹ሥጋዋን እስከማይ አላምንም›› አላቸው፡፡ ሥጋውንም ያሳዩት ዘንድ ወደ መቃብሯት ባደረሱት ጊዜ በመቃብሩ ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም፤ እነርሱም ደንግጠው እያደነቁ ሳለ ያን ጊዜ ቶማስ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችን እንዳገኛት ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን ዕርገቷን ስላላዩ እጅግ አዘኑ፡፡ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም በተስፋ እስከ ነሐሴ 16 በተስፋ ኖሩ፡፡የሕይወት የድኅነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ በጸሎቷም ከከፉ ነገር ይጠብቀን፣ በረከቷ ከእኛ በአማላጅነቷ ከምንታመን ከተዋሕዶ ልጆች ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

    ስለ እመቤታችን ዕረፍትና ዕርገት ቊጥሩ ከ72ቱ አርድዕት አንዱ የሆነው ቅዱስ ኢቮዲየስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ስለነበረ በጥር 21 ቀንና በነሐሴ 16 ቀን የተከናውን የእመቤታችንን ዕረፍትና በዓለ ዕርገቷን በዐይኖቹ የተመለከተውን ጽፎልናል፡፡

    ዳግመኛም ዛሬ የመሐግሉ አቡነ ቀውስጦስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ እርሳቸውም የአቡነተክለ ሃይማኖት የቅርብ ዘመድ ሲሆኑ አርሲ ፈንታሌ ተራራ ላይ ሠሪቲ ለምትባል ጠንቋይ እየተላላኩ ሕዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ 470300 (አራት መቶ ሰባ ሺህ ሦስት መቶ) አጋንንትን በጸሎታቸው እሳት ከሰማይ አውርደው ተራውንን ደምስሰው አጋንንቱን ያቃጠሉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የታናሽ ወንድማቸው የዐፄ ይኩኖ አምላክ ልጅ ዐፄ አምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር የአባቱንእቁባት በማግባቱ አቡነ ቀውስጦስ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ሄደው ንጉሡን ስለገሠፁት በግዞት ወስዶ ጎናቸው በጦር ወግቶ ገድሏቸዋል፡፡ ጻድቁ ልደታቸውምሆነ ዕረፍታቸው ከእመቤታችን ጋር የተባበረላቸው ናቸው፡፡ ግንቦት አን ተወልደው ጥር 21 ዐርፈዋል፡፡  በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡

    ዳግመኛም ዛሬ የዘርዐ ቡሩክ ታላቅ ወንድም የሆኑት ዋሸራን ገዳምን የመሠረቱት በሱባኤ ስለ ዋሸራ ሕዝብ ታላቅ ምሥጢር የተነገራቸው አቡነ ተስፋ ኢየሱስ ዕረፍታቸው ነው፡፡

    የኑሲሱ አቡነ ጎርጎሪዮስም የዕረፍቱ መታሰቢያ ዛሬ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ሀገሩ ቂሳርያ ሲሆን በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ከሃድያንን የተከራከረ፣ ሲቀድስ ጌታችን በርግብ ምሳሌ ሲወርድ ያይ የነበረ፣ እመቤታችንም ተገልጣለት ‹‹ዕረፍትህ በዕረፍቴ ቀን ነውና ተዘጋጅ›› ብላው ቀድሶ ሲወጣ በግል ጸሎት ላይ እንዳለ ያረፈ ነው፡፡ በሐይቅ ሲያጥኑ የማዕጠንታቸው ሽታ እስከ ጣና ቂርቆስ ድረስ ይሸት ስለነበር ቅዱሳን ሲሸታቸው አባ ኤልያስ ዛሬ ቅዳሴ ገባ ይሏቸው የነበሩትና በሞትማረፋቸውን የሚያጥንባት ጽንሐቸው አፍ አውጥታ የተናገረችላቸው የመርጦው አቡነ ኤልያስም ዕረፍታቸው ዛሬ ነው፡፡

    የደብረ ጽላልሽዋ ቅድስት ማርያም ክብራም ዕረፍቷ ነው፡፡ ይህችውም ቅድስት የመስፍን ልጅ ብትሆንም በአቡነ ሕፃን ሞዐ እጅ መንኩሳ ዜና ማርቆስ ገዳም የገባች ሲሆን ሰይጣን በሰው ተመስሎ መጥቶ ሊያስታት ሲል በበትረ መስቀል መቋሚያዋ ያባረረቸው  ኤርናት፡፡

    ነቢዩ ኤርምያስም መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ በሰማዕትነት የሞተ በዋሻ የሚኖር የቅዱስ ኒቆላዎስም መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡የሮሜው አገር ንጉሥ ልጅ የሆነችው ቅድስት ኢላርያም ዕረፍቷ ነው፡፡

    በመናፍቁ ንጉሥ በመርቅያን ዘመን መኮንኑ ጳውሎስና ቀሲስ ሲላስ ምስክር ሆነው በዚህች ዕለት ዐርፈዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን የዕረፍቷ በዓል ዕለት በጌቴሴማኒ ከምእመናን ጋር ሆነው ተሰብስበው ሳሉ መኮንኑ መጥቶ በዚያ ካሉት አንድም ሰው ሳያስቀር ገደላቸው፡፡የእነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውን ቅዱሳን የሁሉንም ታሪካቸውን በሌላ ‹‹post›› እመለስበታለሁ፡፡

    የቅዱሳኑ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡ የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ ከበዓሏ በረከት ትክፈለን፣ በጸሎቷ ታስምረን!!! የልጇንና የእሷን ሞት በሚመስል ሞትሞተን ትንሣኤያቸውን በሚመስል ትንሣኤ እንተባበር ዘንድ ትርዳን በእውነት፡፡

    (ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርሃ ጥር፣ ተአምረ ማርያም፣ ድርሳነ ኪዳነ ምሕረት፣ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰ/ት/ቤትና የማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማዕከል መካነ ድር፣ የቅዱሳን ታሪክ)

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: «ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡» ቅዱስ ያሬድ፡፡ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top