• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 18 January 2016

    ነገረ ማርያም ክፍል ፲፯


    ቅዱስ ዳዊት፡- የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን፡- ሥርወ ልደት ሲናገር፥ “መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤” ብሎአል። መዝ፡፹፮፥፩። እግዝአብሔር፡- አምልኰት እንዲፈጸምባቸው፥ መሥዋዕት እንዲቀርብባቸ ው፥ በረድኤትም እንዲገለጥባቸው የመረጣቸውን ተራሮች እንደቀደሳቸው፡- ምስክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በሕገ ልቡና ዘመን፡- እግዚአብሔር፡- በሲና ተራራ ራስ፥ በእሳት ነበልባል አምሳል በረድኤት ተገልጦ፥ የሲናን ሐመልማል ሳያቃጥላት ተዋሕዶ፥ ወዳጁን ሙሴን ባነጋገረው ጊዜ፥ “ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ(ተራራዋ) የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ (አውልቅ)” ብሎታል። ዘጸ፡፫፥፭። ሙሴም፡- የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ፥ የተቀደሰችውን ተራራ አክብሮ ጫማውን አውልቆአል።   

                                                                                                                    

    የእስራኤልን ከግብፅ የባርነት ቤት መውጣት ስንመለከት፥ የነቢያት አለቃ ሙሴ፡- በእግዚአብሔር ኃይል በብዙ ተአምራት ሕዝቡን ከግብፅ አውጥቶ እየመራ፥ በሦስተኛው ወር ሲና ምድረ በዳ አደረሳቸው፥ ይላል። እግዚአብሔርም፡- በተቀደሰችው ተራራ ላይ ተገልጦ ሙሴን አነጋገረው። ሙሴም፡- ከእግዚአብሔር የሰማውን ለሕዝቡ ነገራቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- “ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘለዓለም እንዲያምኑብህ እነሆ በከባድ ደመና እመጣለሁ፤” አለው። በዚህም፡- ቅዱሳን በአማላጅነታቸው፥ በቃል ኪዳናቸው መታመናቸው፥ በአጸደ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለም መሆኑን መስክሮላቸዋል። በዚህን ጊዜ ሙሴ፡- ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው (እንደ አንድ ልብ መካሪ፥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው) “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤” ማለታቸውን፥ ለእግዚአብሔር ነገረው። እግዚአብሔርም፡- “ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ። ወሰንም ለሕዝቡ በዙሪያው አድርግላቸው፡- ወደ ተራራው እንዳትወጡ፥ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፥ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤” አለው። በተባለውም ቀን በረድኤት ተገለጠ።” ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምፅ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ፤” ይላል።” ዘጸ፡፲፱፥፩-፳፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ሙሴም እጅግ እፈራለሁ፥ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ፥ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበረ፤” በማለት አድንቆ የተናገረው ይኽንን ነው። ዕብ፡፲፪፥፳፩። እግዚአብሔር፡- ሙሴ የሚቆምበትን እና ሕዝቡ የሚቆሙበትን ስፍራ፡- ወሰን(ክልል) አበጅቶላቸው ነበር። ከዚህም፡- የቅድስናውን ስፍራ እንዴት አድርጐ እንደ አከበረውና እንደ አስከበረው እንረዳለን። በተጨማሪም ካህናት ብቻ የሚቆሙበትና የሚገቡበበት ስፍራ መወሰኑን እናስተውላለን። ይህም ለአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን፡- ሥርዓተ ቤተ መቅደስ ጥሩ ምሳሌ ነው። ልዩነቱ፡- በብሉይ ኪዳን በረድዔት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን በደሙ ፈሳሽነት ነው። በሕገ ኦሪት ደግሞ፥ በሙሴ እግር ለተተካ ለኢያሱ ወልደ ነዌም፡- በኢያሪኮ አጠገብ፥ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦለት፥ “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ(የሆንኩ) አሁን መጥቼአለሁ።” ባለው ጊዜ፥ ወደ ምድር ተደፍቶ ከሰገደለት በኋላ፥ “ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድነው?” ሲል ጠይቆአል። ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም፡-”አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን አውልቅ፤” ብሎታል። ኢያሱም፡- የመልአኩን ቃል ሰምቶ፥ የተቀደሰውንም ተራራ አክብሮ የታዘ ዘውን ፈጽሞአል። ኢያ፡፭፥፲፫። በአዲስ ኪዳን፡- በኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም ወደ ተቀደሰች ተራራ (ወደ ቤተክርስቲያን) ጫማ አውልቀን ለመግባታችን መሠረቱ ይህ ነው። ከፍ ብሎ የእግዚአብሔር ቀጥሎም የመላእክት ትእዛዝ ነው። በሌላ በኵል ደግሞ ተራሮች “የተቀደሰ፥የተቀደሰች” እየተባሉ በወንድም በሴትም አንቀጽ የተጠሩበት ምክንያት፥ ለቅዱሳን አበውም ለቅዱሳት አንስትም ምሳሌዎች በመሆናቸው ነው።   

                                                  

    ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ደግሞ፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በደብረ ታቦር፡- በቅዱሳን ነቢያቱ በሙሴና በኤልያስ ፊት፥ እንዲሁም በቅዱሳን ሐዋርያቱ በጴጥሮስ በዮሐንስና በያዕቆብ ፊት፥ ግርማ መለኰቱን፣ ክብረ መንገሥቱን አቅማቸው በሚችለው መጠን በጥቂቱ ገልጦላቸዋል። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት ስለነበሩ ፍግም ፍግም እያሉ ወድቀዋል። ማቴ፡፲፯፥፩። ይኽንንም፡- የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ፡-“የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።ከገናናው ክብር (ከባህርይ አባቱ ከአብ)፡- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሏልና፤ (ከአብ ጋር ትክክል የሆነ ክብሩን ራሱ አብ መስክሮለታልና)፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ሰማን።” በማለት አስተምሮበታል። ፪ኛ፡ጴጥ፡፩፥፲፮።                                                                                                                                 

    ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የተቀደሱ ተራራች ያላቸው ወይም በተቀደሱ ተራሮች የመሰላቸው፥ ቅዱሳን እና ቅዱሳት የሆኑትን የእመቤታችንን የሥጋ ዘመዶች ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፡- “የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ፤“ ይለናል እንጂ፥የእናትና የአባቷን፡- እንኳን ታሪካቸውን፥ ስማቸውን እንኳ አይነግረንም። መቼም አለ እናትና አለ አባት አልተፈጠረችም።ይኽንን የምናገኘው ከአዋልድ መጻሕፍት (የመጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ከሚባሉ መጻሕፍት) ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ልጆች የተባሉበት ምክንያት፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የተጻፉ በመሆናቸውና መጽሐፍ ቅዱስንም ይበልጥ ስለሚያብራሩ ነው። አንድም፡- አባት በልጆቹ እንደሚታውቅ መጽሐፍ ቅዱስም ይበልጥ በእነርሱ ስለሚታወቅ ነው።አዋልድ መጻሕፍት ባይኖሩ ኖሮ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጐዶሎ ይሆን ነበር።   

                         የድንግል ማርያም ሥርወ ልደት፤

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- በአባቷ በኵል ከንጉሡ ከቅዱስ ዳዊት ወገን ስትሆን፥ በእናቷ በኵል ደግሞ ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን ናት። ይህ የሚያሳየን፥ እመቤታችን፡- ከቤተ መንግሥትም ከቤተ ክህነትም ወገን መሆኗን ነው።ምክንያቱም፡- በሚደነቅ እንጂ በማይመረመር በመንፈስ ቅዱስ ግብር፥ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ፥ በተዋህዶ ሰው ሆኖ፥ ከእርሷ የሚወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ንጉሥም ካህንም ነውና። በባህርይ አባቱ በአብ በኵል፥ በንጉሡ በዳዊትም በኵል ንጉሥ የንጉሥ ልጅ ነው። በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችው ድንግል ማርያምም፡-በምድርም በሰማይም ንግሥት ናት። “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፤” ይላል። መዝ፡፵፬፥፱። የምድር ነገሥታት ግብር አስገባሪዎች እርሱንም፡- እንደ ሰዉ ሊያስገብሩት በመጡ ጊዜ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ፡-“አዎን ይገብራል፤” ብሎ ነበር። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ፡- “ስምዖን ሆይ ምን ይመ ስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው ነውን ወይስ ከእንግዶች?” ሲል ጠየቀው። ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “የነገሥታት ልጆችማ ራሳቸው ነገሥታት ናቸው፥ ያስገብራሉ እንጂ አይገብሩም፥ የሚገብሩት እንግዶች ናቸው፤” አለ። በዚህን ጊዜ ጌታችን፡- “እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው፤” አለ። ይህንንም ያለው፡- ቅዱስ ጴጥሮስ ቸኵሎ፥ “አዎን ይገብራል፤” በማለቱ ነው። ነገር ግን ግብር ለመሰብሰብ የመጡ ሰዎች በዚህ ምክንያት እንዳይሰናከሉ ሲል፥ በእርሱ ትእዛዝ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ በአጠመደው ዓሣ ሆድ ውስጥ በተአምር የተገኘውን ሁለት እስታቴር፥ እንዱን በራሱ ስም ሁለተኛውን ደግሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ስም ገብሮአል።በዚህም፡- በሰውነቱ ሲገብር፥ በአምላክነቱ፣ በንጉሥነቱ ደግሞ፡- ባሕርን ዓሣ፥ ዓሣን ደግሞ እስታቴር አስገብሮአል። እዚህ ላይ በሰውነቱ፥ በአምላክነቱ ማለታችን፥ መለኰትንና ትስብእትን ነጣጥለን አይደለም፤ ሁሉም ነገር የሆነው በተዋህዶ ነው።ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በተዋህዶ፡- ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ሆኖአልና። 

      

    ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፡-የጌታችንን የዘር ሐረግ ሲጽፍ፥“የዳዊት ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ፤” በማለት፡- ከአበ ብዙኃን ከአብርሃም እና ከንጉሡ ከዳዊት ወገን መሆኑን ተናግሮአል። ማቴ፡፩፥፩።በመዋዕለ ሥጋዌውም ሁለቱ ዓይነ ስዉራን እና ከነዓናዊቱ ሴት፥ ተአምራቱን ያየ ሕዝብም፡-“የዳዊት ልጅ፤” ብለውታል።ማቴ፡፱፥፳፯፤፲፪፥፳፫፤፲፭፥፳፪። ይኽንን ስም ያገኘው በእመቤታቸን በኵል ነው። እርሱም ራሱ ፈሪሳውያንን፡- “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል፥ የማንስ ልጅ ነው?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ፥ “የዳዊት ልጅ ነው፤” ብለውት ነበር። በዚህን ጊዜ፡- “እንኪያስ ዳዊት፡- ጌታ (እግዚአብሔር አብ)፥ ጌታዬን (እግዚአብሔር ወልድን) ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ (በመዝሙረ ትንቢት) ጌታ (ፈጣረዬ፣አምላኬ) እያለ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ (ፈጣሪ) ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል ?” በማለት መልስ አሳጥቶአቸዋል። ማቴ፡፳፪፥፵፩።                                                                      

    ቅዱስ ዳዊት፡-የፈጣሪ አባት የመባል ክብር ያገኘው፥ከእርሱ ወገን በተወለደች፥ በልጁ በድንግል ማርያም በኵል ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- ወደ ኋላ እሰከ አዳም ድረስ ያሉትን አባቶች ያስከበረች፥ ወደፊትም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚነሡትን የምታስከብር ክብርት ልዕልት ናት። አባ ሕርያቆስ፡- “የቀደሙ አባቶች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩብሽ ድልድይ ሆይ! ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል (አስቀድሞ ያዕቆብ በራዕይ ያየሽ አማናዊት መወጣጫ) ሆይ! የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ በአንቺ ታደሰ።” በማለት ያመሰገናት ለዚህ ነው።    

         

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- መሥዋዕት፥ መሥዋዕት አቅራቢ እና መሥዋዕት ተቀባይ፥ማለትም፡- በአንድ ጊዜ ሦስቱንም የሆነ ሊቀ ካህናት ነው። ቅዱስ ዳዊት፡- “አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ካህን ነው፤” በማለት አስቀድሞ የተናገረው ለዚህ ነው። መዝ፡፻፱፥፬፣ ዕብ፡፭፥፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- “እንግዲህ ወንድሞቻችን ሆይ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ወደ መቅደስ ለመግባት ባለሟልነት አለን። በሥጋው መጋረጃ በኵል የሕይ ወትንና የጽድቅን መንገድ ፈጽሞ አድሶልናልና። በእግዚአብር ቤት ታላቅ ካህን አለን።” ብሎአል። ዕብ፡፲፥፲፱።                                                                                                      

                        ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፤

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- አባቷ ቅዱስ ኢያቄም ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፥ እናቷ ቅድስት ሐና ደግሞ ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን ናት። ለዚህም፡- በነገረ ማርያም ተጽፎ፥ መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ የሚያደርገውን የእመቤታችንን ታሪክ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ፡- ነገረ ክርስቶስን እንኳ አሟልቶ አይነግረንም።ይኸውም፡- ከቅዱሳን ሐዋርያት በኋላ የሚነሡ ሊቃውንት የተቀረውን ጽፈው በረከት እንዲያገኙ ነው። ለምሳሌ፡- መጽሐፍ ቅዱስ፡- የጌታችንን ከግብፅ ስደት መመለስ እና በናዝሬት ማደግ፥ በአሥራ ሁለት ዓመቱም በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱን ይነግረናል እንጂ፥ እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ምን እንደሠራ አይነግረንም። ከዚያም በኋላ ሠላሳ ዓመት ሞልቶት እስኪጠመቅ ድረስ ያለውን ታሪኩን አልመዘገበልንም። ይህም የጌታችንን የነገረ ድኅነት ታሪክ ጐደሎ ያደርግብናል። ማቴ፡፩፥፳፫፣ ሉቃ፡፪፥፵፩። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ነበር ይመስለኛል።” ብሎአል። እንዲህም ማለቱ፡- እነርሱ በቃል ያስተማሩት፥ ነገር ግን በጽሑፍ ያላስቀመጡት ብዙ ነገር መኖሩን እና ተከታዮቻቸው፡- በአፍም በመጽሐፍም የተማሩትን አስፋፍተው እንደሚጽፉ ለመግለጥ ነው። ዮሐ፡፳፩ ፥፳፭።                                                                                                                  

    ነገረ ማርያም ለነገረ ክርስቶስ መነሻ መሠረት በመሆኑ የግድ መብራራት አለበት። ምናልባት ከክርስቶስ ከጀመርን ይበቃል፥ የሚሉ ይኖራሉ፤ በእርግጥም አሉ። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ፥ ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፡- ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ያለውው ሠላሳ ስድስት ትውልድ ለመቍጠር አይደክምም ነበር። ማቴ፡፩፥፩-፲፮። ቅዱስ ሉቃስም፡- ከክርስቶስ ጀምሮ ወደ ላይ እስከ አዳም ድረስ ሰባ ስምንት ትውልድ ለመቍጠር አይቸገርም ነበር። በመጨረሻም አዳምን የእግዚአብሔር ልጅ ብሎታል። ሉቃ፡፫፥፳፫-፴፰። በመሆኑም ነገረ ማርያምን እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታለን። ቴክታና በጥሪቃ የሚባሉ፥ እጅግ ባዕለ ጸጋ የሆኑ ባልና ሚስት ነበሩ። ባዕለጸግነታቸውም የብር፥ የወርቅ ፥የወንድ እና የሴት አገልጋዮች፥የፈረስና የበቅሎ፥ የላም፣ የበግና የፍየል ነበር። በአጠቃላይ ይህ ቀራቸው የማይባሉ፥ ሁሉ የተሟላላቸው ሰዎች ነበሩ።በጥሪቃ፡- ከዕለታት በአንዱ ቀን፥ ከዕቃ ቤቱ ገብቶ ስፍር ቍጥር የሌለውን ሀብቱን ካየ በኋላ፥ ወራሽ ልጅ ስለሌው እጅግ አዘነ። ባለቤቱን ቴክታንም፡- “ከአንቺ በቀር የምወደው እንደሌለኝ አምላከ እስራኤል ያውቀዋል፥ ነገር ግን ልጅ የለንም፤”አላት። እርሷም፡- “ለልጅማ እኔ ምንድር ነኝ? ወደ እግዚአብሔር እናመልክት እንጂ፤” አለችውና በጾም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ።                                                

              እግዚአብሔር የሁለቱንም ቅንንት አይቶ፥ ለቴክታ በህልም ገለጠላት። ነጭ እንቦሳ ከማኅጸንዋ ስትወጣ ፥እንቦሳዋም እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ሲደርሱ፥ ስድስተኛይቱ እንቦሳ ጨረቃን ስትወልድ፥ ጨረቃይቱም ፀሐይን ስትወልድ አይታ ለበጥሪቃ ነገረችውና ወደ መፈክረ ሕልም (ሕልም ወደሚፈታ ሰው) ላከችው። ሕልም ፈቺውም፡- በእንቦሳ ምሳሌ ያየችው ልጅ መሆኑን እና ደግ ልጅ እንደሚወልዱ፥ “የጨረቃንና የፀሐይን ምሥጢር ግን፡- ጊዜ ይፍታው እንጂ ለእኔ አልተገለጠልኝም፤” አለው። ይኽንንም ለባለቤቱ ወስዶ ነገራት። ከዚህ በኋላ ቴክታ ፀንሳ ወለደችና ስሟን ሄሜን አለቻት፥ ሄሜን ደርዲዕን ወለደች፥ ደርዲዕ ቶናህን ወለደች፥ ቶናህ ሲካርን ወለደች፥ ሲካር ሄርሜላን ወለደች፥ ሄርሜላም ቅድስት ሐናን ወለደች። ቅድስት ሐና ደግሞ ከነገደ ይሁዳ የሆነውን ቅዱስ ኢያቄምን አግብታ ለጊዜው በመሀንነት ኖረች።ነገሥታት የሚሾሙት ከነገደ ይሁዳ ነበር፤ ምክንያቱም፡- ያዕቆብ አሥራ ሁለት ልጆቹን በመረቀ ጊዜ፥ “ይሁዳ፥ ወንደሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ልጄ ሆይ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል? በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስከሚመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል፤”ብሎ ነበር። ዘፍ፡ ፵፱፥፰። 

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ነገረ ማርያም ክፍል ፲፯ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top