በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ሰዎችን ማክበር ትኩረታቸውን ለማግኘት ይረዳናል። እግዚአብሔርን የምናምንና ስላመነውም ምስክርነት የምንሰጥ ሰዎች ሁሉ ሁሉን ማክበር ይጠበቅብናል። ሽማግሌም ሆነ ወጣት፣ የታመመ ሆነ ጤነኛ፤ ድሃም ሆነ ባለጠጋ፤ የተማረም ሆነ ያልተማረ፤ ወንድም ሆነ ሴት፤ ጻድቅም ሆነ ኃጥእ ሁሉን ማክበር ይጠበቅብናል፡፡ እነዚህ ሰዎች አስቀድሞ የነበራቸው ልምድ ምንም ይሁን ምን፣ አመለካከታቸውና ሥነ ምግባራቸውም መልካምም ይሁን መጥፎ እንድናከብራቸው ይጠበቅብናል።
ሰዎችን የምናከብራቸው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፤ በቅድሚያ እግዚአብሔር በአምሳሉና በአርአያው ስለ ፈጠራቸው እናከብራቸዋለን። ስናከብራቸውም ያከበርነው የተፈጠሩበትን የእግዚአብሔርን አምሳልና አርአያ መሆኑን ማወቅ ይጠበቅብናል። ሰዎችን የምናከብርበት ሁለተኛው ምክንያት እግዚአብሔር ልጁን ለሰው ዘር ሁሉ መሥዋዕት ይሆን ዘንድ ስለሰጠ ነው። ይህን የማዳን ሥራ እግዚአብሔር ከፈጸመላቸው ታላቅ መሥዋዕትነትም ከከፈለላቸው ታዲያ ቢያንስ ይህ የተደረገላቸውን ሰዎች ማክበር አይጠበቅብንም ይሆን? ሦስተኛው ሰው ምንም ያህል ክፋት ወይም መጥፎነት ቢኖርበትም በውስጡ ግን መልካምነት ስለሚገኝበት ሰውን ልናከብረው ይገባል።
ሰውን ማክበር በውስጣችን የሚገኘውን መልካምነት መቀስቀሻ መሣሪያ ነው፤ ይህም ሰው ክርክርንና ራሱን መከላከልን ትቶ ለነገሮች ጆሮ ሰጥቶ ለመስማት ያበቃዋል። ማክበር ሰውን ሳናስገድድና ሳናስጨንቅ ለመስማት የሚችልበት ነጻነት እንድንሰጠውና በእግዚአብሔር ጸጋ በመታመን ወደ ምሥራቹ ወንጌል ለመጥራት ይረዳናል፤ ጥሪያችንን ካስተላለፍን በኋላ የምሥራቹን ወንጌል መቀበልም ሆነ አለመቀበል ግን የእያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው።
ክብር መስጠት ስንል የሰው የግል መብቱን ነፃነቱንና ምስጢሩንም ማክበርንም ያካትታል፤ ስለዚህ ምንም በቅርበት የምናውቃቸው እንኳ ብንሆን ሰዎችን ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ለማቅረብ የምናደርገው ጥረት የሚሳካው በግኑኝነታችን ወይም በንግግራችን ወቅት ክብር ሰጥተን በምንጓዘው መንገድ ርቀት ነው። ክብር መስጠት የሰውን ስሜት የሚጎዱ ቃላቶችን አለመጠቀምን ያካትታል። የሰዎችን ባሕል፣ እሴቶቻቸውን፣ የቀደመ ታሪካቸውን በአግባብ መረዳትና ማወቅ ክብራቸውን የሚጎዳ ስህተት ከመሥራት ይታደገናል። ይህም ማስተዋል የተሞላበት አካሄድ እግዚአብሔር በመንገዱ እንዲመራን ለመጠየቅና ለመጸለይ ይረዳናል፤ ምንም ብናውቅ ሰውን ሊያስቀይሙ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉና።
ጌታችን በማስተማር ዘመኑ ለእያንዳንዱ የሚገባውን ክብር መስጠቱን የሚያስረዱን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ። ሳምራዊቱን ሴት ሲያነጋግራት ዮሐ 4፣ ኒቆዲሞስንም ሲያስተምረው (ዮሐ ፫)፣ ሕፃናትን ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ እንዳይከለክሏቸው ሲናገር (ማቴ ፲፰)፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በቀኙ ለነበረው ወንበዴ መልስ ሲሰጥ (ሉቃ ፳፫)፣ ባለጠጋውን ባስተማረው ጊዜ ያሳየው አክብሮት ትዝ አይለንምን? (ሉቃ ፲፥፳፭-፵፪)። ክብር መስጠት ሰዎችን ማክበራችንን የሚገልጹ ቃላትን በመጠቀም ማነጋገር ብቻ ሳይሆን ማክበራችንን የሚገልጽ ሥነ ምግባር በማሳየት ማነጋገርም ነው። በተጨማሪም የሰዎችን ግላዊ መብታቸውንም ማክበር እንደሚጠበቅብን መዘንጋት የለብንም፡፡ ወንጌላዊነት (ቃለ እግዚአብሔርን መናገር) ለሌላው የመናገራችንን አጋጣሚ በመጠቀም ራሳችንን በሌላው ላይ መጫን አይደለም።
ይህን አስመልክቶ የወንጌሉ አለቃ ባለቤቱ የሰጠንን መመሪያ እስኪ እንመልከት። ‹እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከኔ ጋር ይበላል።› (ራእ ፫፥፳)። ጌታችን እርሱ የሁሉ ፈጣሪ፣ ፈራጅ፣ በፍጥረት ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው ቢሆንም እንኳ ያለ ሰው ሙሉ ፈቃደኝነት ፈጽሞ ወደ ሰው ደጅ የማይገባና የሰውንም ክብሩንና መብቱን የሚጠብቅለት እንደሆነ አረጋግጦልናል።
ክብር መስጠት ማለት ሃይማኖታቸው ምንም ያህል የሚያስከፋ ቢሆን የሰዎችን ሃይማኖት አለመስደብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት እንደ ብዙዎች እናት የምትቆጠር ስለሆነችና ማንም እናትህ አታምርም ታስጠላለች ቢሉት ተቃውሞውን ተቋቁሞ መስማት ስለሚያቅተው ነው። አስቀድመን የሰውን ሃይማኖትን መስደብ ወደኛ ለመሳብ የሚኖረንን ዕድል ያበላሻል። ስለዚህ ከስድብ ይልቅ በክርስትና (ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ) ሃይማኖታችን ያሉንን መንፈሳዊ ምግባራትና ሀብታት ብሎም ከነርሱ አንዱ የሆነውን አክብሮትን በመጠቀም በጎነትን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም በተለያዩ የ“ክርስትና” እምነት ተቋማት ወይም በአንዳንድ የክርስትና ድርጅቶች ታቅፈው ያሉትንም ይመለከታል። ምንም የሚያስነቅፍ ነገር እንዳለባቸው አጥብቀን ብናውቅ ሰውን ወደኛ ለመሳብ ስንል ድርጅቶቻቸውን ባንሰድብባቸው እጅግ የተመረጠ ነው፡፡ ይልቁ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እንደ መሠረታት እርሱ በመሠረተው እምነት፣ አምልኮትና ትምህርት ጉዞዋ ቀጥሎ እንዴት እስከዚህ እንደደረሰች በትሕትናና በእርጋታ እናስረዳቸው። ይህን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ - ኢትዮጵያዊ ስብከተ ወንጌል መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን እምነት፣ አምልኮትና ሥርዓት ሳትለውጠውና ሳታጠፋው እስከ ዛሬ ጠብቃ እንዴት እንዳቆየችው መንገርንም አንዘንጋ፡፡ በዚህም ዘዴ በመጠቀም ማስረዳት በርካታ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማወቅ የበለጠ ፍቅር እንዲያድርባቸውና ወደ ቤተ ክርስቲያናችንም እንዲመጡ ለማነሳሳት ይረዳል።
የቤተ ክርስቲያናችን የወንጌል አገልግሎት አንዱ ምሰሶ ቅዱስ ጳውሎስ ነው። ምንም እንኳን ጣዖትን የሚያመልኩ ቢሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን መንገዶች በመጠቀም “ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳል ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።” (ሐዋ ፲፯፥፳፪-፳፫) በማለት በአቴንስ የሰጠው ስብከት ምን ያህል የሚደነቅ ነው? ይህ አክብሮቱስ እንዴት ያለ አክብሮት ነው!።
ክብር መስጠት ሰዎች የነገርናቸውን ነገር የሚያስቡበት ጊዜ መስጠትንም ያካትታል። ምግብ ስንመገብ አስቀድመን እንጎርሳለን፣ ቀጥለን እናላምጣለን፣ በመጨረሻም እንውጣለን እንጂ ወዲያው አንውጠውም። ለሰዎችም አስቀድመን የሚጎርሱትን፣ ቀጥሎ የሚያላምጡትን በመጨረሻም የሚውጡትን እንስጣቸው። ይህንንም ስናደርግ በርጋታ እናድርግ እንጂ አንፍጠን። ገበሬ እህል ዘርቶ በየጊዜው የሚያስፈልገውን ያህል ውሃ ለዘሩ እንደሚያጠጣው ለዘሩም የሚያስፈልገውን ዓይነት ምግብ እንደሚመግበው እኛም ለእያንዳንዱ ሰው በየመጠኑ የምናደርግ እንሁን።
ክብር መስጠት ስንነጋገር ተመጣጣኝ የሆነ ድምፅ (Tone) መጠቀምንም ያካትታል፡፡ በስብከት ሰዓት የብዙዎችን ትኩረት ለመሳብ ስንል ከፍተኛ ጉልበት (ኃይል) ያለው ድምፅ መጠቀም ሊያስፈልገን ይችላል፡፡ በግል ስናነጋግር ግን የተመጠነና የረጋ ድምጽ መጠቀም የተመረጠ ነው። በተጨማሪም በወንጌላዊነታችን ሁሉም ሰው የሚጠቀምበትንና የሚረዳውን ቋንቋ መጠቀምም ያስፈልገናል። ሰውን የምናከብረው ከሆንን በማይገባው ቋንቋ ከመጠቀም መቆጠብና ሊያገናዝበው ከሚችለው በላይ የሆነ መልእክትን ከማስተላለፍም መከልከል ይኖርብናል። ለምሳሌ፡-
፩፦ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የፍልስፍና መሠረት ያላቸው ቁልፍ ቃላቶችን በመጠቀም ከማነጋገርና ከማስተማር መቆጠብ፤
፪፦ ጎረምሶችን ስናናግራቸው ተራ የሆኑ እነርሱ የሚጠቀሙባቸው ቃላትን ከመጠቀም ይልቅ በአክብሮት ቀለል ያሉ
ለመረዳትምየማያስቸግሩ ቃላቶችንመጠቀም ማለት ነው።
አክብሮት ለሌሎች ጊዜ ክብር መስጠትንም ያካትታል። ሰዎች በርካታ ሥራዎችና ኃላፊነቶች ስላሉባቸው ምን ያህል ጊዜ እንደምንወስድባቸው መገንዘብ እና በጊዜ አጠቃቀማችን ጥንቁቅ መሆን ይጠበቅብናል። ከመደቡት በላይ ተጨማሪ ጊዜያትን ለመጠቀም ፈቃደኝነታቻውን መጠየቅና ሲስማሙበት ብቻ መቀጠል፣ ዝግጁ ካልሆኑም ወደ ጉዳያቸው ይሄዱ ዘንድ የምንተዋቸው ለመሆን መሰናዳት ይጠበቅብናል። እንግዲህ አጫጭር ትምህርቶችን እየሰጠን ጥያቄ ከመጠየቅ በቀር ለአንድ ሰው ረጅም ስብከት ከመስጠት እንቆጠብ፤ ጌታችን ረጃጅም መልእክቶችንን ያስተላለፈው በስብከቱ ነውና። ጌታችንም ሳምራዊቱን ሴት፣ ኒቆዲሞስን፣ ወይም ብሎም በወንጌል የተጠቀሱ ሰዎችን እንዴት አጫጭር መልእክቶችን እንዳሰተላለፈላቸው ጥያቄዎችንም እንደጠየቃቸው ረጃጅም መልእክቶችን ማስተላለፍም እንዳልወደደ እንረዳ።
አባቶቻችን ሐዋርያት፥ አምላካችን ያስተማራቸውን በመከተል የእግዚአብሔር አጋልጋዮች ይህን የተወደደ መንገድ እንዲከተሉ ምክንያት ሆነዋቸዋል። የእነርሱም ምሳሌነት ሳይደበዝዝና ሳይጠፋ እንደቀጠለ ዛሬም በሚገኙ አባቶቻችን ግልጽ ሆኗል፤ እነርሱም፡-
፩፦ ታላላቅ ሰዎች ቢጎበኛቸውም ተራ ሰዎችንና ሕፃናትን መቀበልን ለእነርሱ ማስተማርን አልዘነጉም። በተለያዩ ጊዜያትም ወጣቶች ከእነዚህ አባቶች ከተማሩ በኋላ በደስታ ተሞልተው ሲወጡ ተመልክተናል።
፪፦ ከእነዚህም አባቶች አንዳንዶቹ እንደ ስጦታ ይዘው የሚቀርቡትን ተቀብለው ለጎደለው በመስጠት አቅራቢዎቹ አገልግሎት የሰጡ ሆኖ እንዲሰማቸው በመመረቅ ይሸኙ እንደ ነበር ታሪካቸው ያስረዳል።
፫፦ እስላምና ክርስቲያኖች ሲገናኟቸው ለክርስቲያኖች በመስቀል ለሙስሊሞች በእጃቸው የፍቅር ሰላምታ በመስጠት የሚቀበሉም ስለ ነበሩ ሙስሊሞቹም በንግግራቸውና በድርጊታቸው እየተነኩ ደስታ እየተሰማቸው ይወጡ ነበር፤ አንዳንዴም መስቀላቸውን ወደ ግራ እጃቸው አድርገው ለሰላምታ ሲዘጋጁ እጃቸውን ከመስቀላቸው ጋር አብሮ በመያዝ ሙስሊሞችን መስቀል ለመሳም ያበቁ አባቶችም አሉ።
፬፦ አገረ ገዢዎችንም ሲጎበኙ ስጦታ ይዘው በመሄድ አክብሮታቸውን ከመግለፅ ጋር በሚሰጧቸው ስጦታ ኦርቶዶክሳዊ መልእክቶቻቸውን ያስተላልፉ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ጎዳና ተዳዳሪችንም ሲመለከቱ ወደነርሱ ሄደው ከአንድ ሰዓት በላይ አብረው ያሳልፉም እንደነበርም እናውቃለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወድንግል ማርያም ክብር!
ምንጭ፦ ቀሲስ ሰለሞን ሙሉጌታ፤ PDF
0 comments:
Post a Comment