ሐራ ዘተዋሕዶ
ክልላዊ መንግሥቱ፡-
“የጋምቤላ እና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ጳጳስ” ኾነው በአባትነት እንዲቀመጡ ጠይቋልበ2ሺሕ ካ.ሜ. መሬት መንበረ ጵጵስና እያስገነባ ሲኾን፤ የቤት መኪናም አዘጋጅቻለኹ፤ ብሏል“ሕገ መንግሥቱ እንደሚያዘው የሕዝብ ድምፅ ይከበርልን” ሲል ክልላዊ አቋም እንደኾነ ገልጧልለ7ኛ ጊዜ መጠየቁን አስታውሶ፣ “ሌላ ጳጳስ ቢመደብ ከባሮ ቆላ ከኤርፖርት አናሳልፍም” ብሏል
***
ርእሰ መስተዳደሩ ጋትሉዋክ ቱት ኮት፡-
“ከአባ ተክለ ሃይማኖት ውጪ ጳጳስ፣ አባት አንፈልግም፤ ሲኖዶስ በጫና ቢመድብብን የግንኙነት መስመራችን ይበጠሳል፤ ቢመጣም ከባሮ ቆላ ከኤርፖርት አናሳልፍም፤ አንቀበልም፡፡”
***
ጵጵስና፣ ክህነታዊ ማዕርግ በመኾኑቀኖናዊና መንፈሳዊ ሹመት እንጂ እንደ ሕዝባውያን በ“ድምፃችን ይከበር” ዓይነት ውትወታ(lobby) ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ የሥራ አስኪያጁ የአገልግሎት ፍሬዎችና የድጋፍ መሠረቶች፣ በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መሪነት ተረጋግጦ፤ ጥቆማውም፣ በደንቡ መሠረት መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በዛቻና በማስፈራሪያ መልክ የቀረበው የርእሰ መስተዳደሩ ጥያቄ ኢ-ሕገ መንግሥታዊና ኢ-ቀኖናዊ በመኾኑ ያለማመንታት መታረም ይኖርበታል፤ይህንንም በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችንንም ራሳቸውንም የማስከበሩ ቅድሚያ፣ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጀመር ይገባዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ “ይደልዎ፤ ይደልዎ” ተብሎ ለመሾም የሐቅ ምስክርነቱና ሥራቸው ብቻ በቂ ነውና! አልያ፣ በመለካዊ እጅ ጥምዘዛ አስገዳጅ ኹኔታ በመፍጠር ሹመቱን ለመሸመት በእጅ አዙር የቀረበ ጥያቄና ማስጠንቀቂያ ስላለመኾኑ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?
***
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በጋምቤላ ክልል የምታከናውነውን ልማት፣ መልካም አስተዳደርና የሰላም ግንባታ ለማስቀጠል፣ የሥራ አስኪያጁ የመጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ “መኖር አስፈላጊ ነው፤” ያሉት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ኮት፤ አባ ተክለ ሃይማኖት ኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾሙላቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩንና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን የጠየቁ ሲኾን፤ ሌላ አባት፣ ጳጳስ ኾኖ ቢመደብ እንደማይቀበሉም አስጠነቀቁ፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ፣ በቁጥር መ2/6384/አ28/1 በቀን 02/10/2008 ዓ.ም. በአድራሻ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፉትና፤ በግልባጭ ደግሞ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለፌዴራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴርባሳወቁበት ደብዳቤአቸው፤ ጥያቄውን ለሰባተኛ ጊዜ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይኸው አቋም÷ የክልሉ መንግሥት፣ የማኅበረ ካህናቱ፣ የሕዝቡ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሰንበት ት/ቤቶች ተማሪዎች ድምፅ እንደኾነ በማስታወቅም፣ “ሕገ መንግሥቱ እንደሚያዘው፣ የሕዝብ ድምፅ ይከበርልን፤” በማለት ነው አጽንዖት የሰጡት፡፡
የክልሉ መንግሥት፣ ለመጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት መንበረ ጵጵስና ማሠርያ፣ 2ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት መስጠቱንና ግንባታውም በእምነቱ ተከታዮች፣ በሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች፣ በማኅበረ ካህናቱ፣ በሰንበት ት/ቤቶች ተማሪዎችና በአምስቱ ብሔረሰብ ተወላጆች ትብብር እየተከናወነ መኾኑን አቶ ጋቱሉዋክ ቱት ጠቅሰው፤ ለመንበረ ጵጵስናው የሚያገለግል የቤት መኪናም መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፣ በአኙዋና በኑዌር ዞኖች በሚነሣው ግጭት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ለክልሉ ሰላም በመታገል ሰላምን አረጋግጠዋል፤ ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፣ ይህም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባሉበት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምስክርነት የተሰጠበትና በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር “የሰላም ጀግና” ተብለው የነሐስ ሜዳልያ የተሸለሙበት፤ በክልሉም “የሰላም እና የልማት አምባሳደር” ተብለው የተሠየሙበት እንደኾነ በደብዳቤአቸው አስፍረዋል ‐ “በአኙዋሃ ዞንና በኑዌር ዞን በሚነሣው ጦርነት መሀል ገብተው ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ኮሾሮ በመብላት የክልላችንን ሰላም ያረጋገጡ በመኾኑ የሰላምና የልማት አምባሳደር በማለት ሠይመናል፡፡”
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ባለፈው ግንቦት አጋማሽ ክልሉን በጎበኙበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በክልሉ ልማት፣ መልካም አስተዳደርና የሰላም ግንባታ ዙሪያ “ወደርየለሽ ሥራ እየሠራች ነው፤” ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ “ይህን ለማስቀጠል እንዲቻል፣ የአባ ተክለ ሃይማኖት ከእኛ ጋር መኖር አስፈላጊ ነው፤”ማለታቸውን ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በወርኃ ግንቦት እትሙ ዘግቧል ‐ “ክልላችን በተለያዩ ጊዜአት ቅዱስ ሲኖዶስን የጠየቀው ጥያቄ ተግባራዊ እንዲያደርግልን በክልላችን መንግሥት ስም አኹንም ጥያቄ እያቀረብኹ ቅዱስነትዎ እንዲያስብበት እጠይቃለኹ፡፡”
መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖትን፣ ለኤጲስ ቆጶስነት ያበቋቸዋል ያሉትን ምስክርነት፣በ22 ነጥቦች ዘርዝረዋል፤ ርእሰ መስተዳድሩ በደብዳቤአቸው፡፡
ከምስክርነቱም መካከል፤ የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዝዳንት አቶ ኡሞድ ኡቦንግንና በርካታ የክልሉን ባለሥልጣናት ጨምሮ ከ7ሺሕ637 በላይ የአምስቱ ብሔረሰብ አባላት ማስጠመቃቸውን፤ 53 አብያተ ክርስቲያናትን ማሳነፃቸውንና ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋታቸውን፤ “የመናፍቃን መዶሻ”የሚል ቅጽል የተሰጣቸው ጸሎተኛና ወንጌላዊ መኾናቸውን፤ 13 ባለፎቅ ት/ቤቶችን ማስፋፋታቸውን፤ የክልሉን ብሔረሰብ ልጆች ሰብስበው በገዳም የሚኖሩ፤ በእምነቱ ተከታይና ከእምነቱ ውጭ ባሉት ተወዳጅ ከመኾናቸው በቀር አንድም የሥጋ ዘመድ የሌላቸው፤ ዘረኝነት፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት የማያውቃቸው፤ ለአገልግሎት ሲወጡ በየመቃብር ቤቱና በቤተ ክርስቲያን የሚያድሩ እንጂ በሆቴል የማያድሩና በሴት የማይታሙ ናቸው፤ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ኾኖም ርእሰ መስተዳድሩ፣ የሥራ አስኪያጁን አገልግሎትና ብቃት መዘርዘሩ በኤጲስ ቆጶስነት ለማሾም በቂ ኾኖ ያገኙትና የተማመኑበት አይመስልም፤ ከበድ ያለ ማሳሰቢያም መስጠታቸው አልቀረም፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በቅርቡ እንደሚያካሒድ በሚጠበቀው የአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት፣ ከሥራ አስኪያጁ መጋቤ አእላፍ አባ ተክለ ሃይማኖት ውጭ ሌላ አባት መመደቡን እንደ ጫና እንደሚቆጥሩትና እንደማይፈልጉ ርእሰ መስተዳድሩ በግልጽ አስፍረዋል፤ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጋር ያለው የግንኙነት መሥመር እንደሚበጠስም አስጠንቅቀዋል፤ “ተመድቦ ቢመጣም ከባሮ ቆላ ከኤርፖርት አናሳልፍም፤ አንቀበልም፤” ሲሉም ዝተዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና÷ በመኳንንት አማላጅነት ሢመተ ጵጵስናን መፈጸምን ያወግዛል፤ ኤጲስ ቆጶስ፣ በእምነቱና በእግዚአብሔር እንዲጸና እንጂ በዚኽ ዓለም መኳንንት ርዳታ እንዳይቆም ያዝዛል፤(ፍትሐ ነገሥት 176፤ ረስጠብ 21)፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ታምኖበት ሲወሰን እንደኾነ የሚደነግገው ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን፤ ለሢመቱ የሚለዩትም፣ ለዕጩነት የሚያበቋቸውን መስፈርቶች አሟልተው ሲገኙ እንደኾነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
በተጨማሪም፣ ኤጲስ ቆጶስ የሚሾመው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ እንደኾነ በሥርዓታችን የተደነባ ሲኾን፤ ስለ ደግነቱና ትሩፋቱ፤ ስለ ንጽሕናውና ከነውር የራቀ ስለመኾኑ የማረጋገጫ ምስክርነት የመስጠቱ ድርሻ የሚሾምበት ሀገር ካህናትና ምእመናን እንደኾነ፤ ሹመቱ ሲፈጸምም፣ ካህናቱም ሕዝቡም ተገኝተው እየመሰከሩለት እንደሚሾምየተቀነነ ነው፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 5፣ አብጥሊስ 2፤ ረስጠብ 52)
ዕጩ ቆሞሳት ወይ መነኰሳት፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውና በግብረ ገብነታቸው፤ በአስተዳደር የሥራ ልምዳቸውና በሥራ አመራራቸው ያላቸው ችሎታና ብቃት የሚጣራው፣ በነበሩበት አካባቢ/የሥራ ቦታ/ ሲኾን፤ ይህም በክፍሉ/በሀገረ ስብከቱ/ ሊቀ ጳጳስ ርእሰ መንበርነት በሚሰበሰቡ ካህናትና ምእመናን ምስክርነት እንደሚረጋገጥበሕገ ቤተ ክርስቲያናችን የኤጲስ ቆጶሳት የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንብ፣ 2007(ቁ.8) ተገልጧል፡፡
በዚኽም መሠረት፣ የኤጲስ ቆጶሳት ሰማያዊና ክህነታዊ ሹመት እንደ ሕዝባውያን ምድራዊና ዓለማዊ ሹመት በ“ድምፃችን ይከበር” ዓይነት ውትወታ(lobby) ብቻ የማይወሰን ቀኖናዊ መለኪያዎችና አፈጻጸሞች እንዳሉት እንረዳለን፤ ፈቃደ እግዚአብሔር የሚጠየቅበትና በጸሎት የሚታገዝ መንፈሳዊ በመኾኑም ዛቻና ማስፈራራቱ አግባብነት እንደሌለው እናስተውላለን፡፡ በመኾኑም፣ በቀኖናው፣ በሕጉና በማስፈጸሚያ ደንቡ ዓይን፤ ርእሰ መስተዳደሩ የጠቀሷቸው የሥራ አስኪያጁ የሥራ ፍሬዎችና የድጋፍ መሠረቶች፣ በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መሪነት ተረጋግጦ ጥቆማውም በዚኹ መሠረት መከናወን እንዳለበት እናምናለን፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጻፉትን ደብዳቤ በሰፊ ልቡና ለመውሰድ ብንሞክርና የዘረዘሯቸውንም የመጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት አገልግሎትና ብቃት ብናምንበት እንኳ፤ በዛቻና በማስፈራሪያ መልክ መቅረባቸው ኢ-ሕገ መንግሥታዊና ኢ-ቀኖናዊ ብቻ ሳይኾን፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሉዓላዊነትና ብሔራዊነት የሚገዳደር በመኾኑ ያለማመንታት መታረም ይኖርበታል፡፡
ይህንንም በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችንን የማስከበሩ ቅድሚያ፣ ከራሳቸው ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጀመር ይገባዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ “ይደልዎ፤ ይደልዎ” ተብሎ ለመሾምየሐቅ ምስክርነቱና የዓመታት ሥራቸው ብቻ በቂ ነውና! አልያ፣ በመለካዊ እጅ ጥምዘዛ አስገዳጅ ኹኔታ በመፍጠር ሹመቱን ለመሸመት በእጅ አዙር የቀረበ ጥያቄና ማስጠንቀቂያ ስላለመኾኑ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?
የጋምቤላ እና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመኾን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት፣ መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፤ ከመቱ – ኢሉ አባ ቦራ የተገኙ፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የዲፕሎማ ምሩቅ ናቸው፡፡ የቀድሞው ዲያቆን አምሳሉ ንጉሤ፣ አባ ተክለ ሃይማኖትተብለው ምንኵስና የተቀበሉት በደብረ ሊባኖስ ገዳም እንደኾነ የተገለጸ ሲኾን፤ ከክልላዊ መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋር ባላቸው ጥብቅ ግንኙነት ጎልተው ይታወቃሉ፡:
0 comments:
Post a Comment