• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 20 June 2016

    በቁምስና የሰበኩለትን በጵጵስና ሊያጎርሱን ይኾን?

    ከወደ አሜሪካ የተሰማው ነገር ሥጋየን አልፎ አጥንቴ ድረስ ዘልቆ እጅግ አሳዘነኝ፡፡ ሰይጣን አንዱ ተልእኮው ተሳክቶለት ሲስቅ ከማየት በላይ ብሽቅ የሚያደርግ ምን አለ? መቼም እየተብከነከንም ቢኾን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለማንም የማይተው ነውና አርረን ተኮማትረን እስክናልቅ ድረስ አንተወውም፡፡ ጉዳዩ እንግዳ ስለኸነ አይደለም፡፡ ስንሰማው ባይኾን እያልን ስናሳስብበት የቆየነው እንጂ፡፡ በተለይም የአባ ወልደ ትንሣኤ ማዕረገ ጵጵስና የማግኘት ጉዳይ ከወሬ ያለፈ ስለ ነበር (ምንም እንኳ በምሥጢር የተያዘ ነው ቢባልም ቅሉ) እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይይለም፡፡ ኾኖ ሲታይ ግን እጅግ ልዩ መልክ ያመጣል፡፡ ያ መልክ ስለታየኝ እንዲህ አልሁ፡፡

    የእርቀ ሰላሙን ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተገኙትን ዕድሎች ሁሉ በማምከን የማበላሸት ሥራ እየተሠራ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንደ አክርማ እየተሰነጠቀች እንድትኖር የመሠረት ድንጋይ በማኖር በአባቶች ዘንድ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እየጠፋ ሄደ፡፡ ከእነዚህም አንዱ መሾም የሚገባ ቢኾን እንኳ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብ አንቅሮ የተፋቸውን ሰው የመሾሙ ፋይዳ በትኩረት ሊመረመር የሚገባው ነው፡፡ እውን ያ ሁሉ ቅሬታ በምድረ አሜሪካ አልተሰማም ነበርን? ከስህተት ወደ ስህተት የሚታደግበትስ መሠረተዊ ምክንያት ምን ይኾን?
    ከዚህ በፊት እልም ባለ ኑፋቄው በገጠመው ተቃውሞ የተነሣ ጨርቁን ጥሎ ለይቶለት የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መጋቢነትን (ፓስተር) ተቀዳጅቶ የነበረውን መልአኩ ባወቀን በማይኾን ሁኔታ ቅስና ሰጡ ተባለ ሰማን እና ዝም አልን፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሰው ተሳስቻለሁ ብሎ ወደ አባቶች እናቀርበው ዘንድ የመጣው ወደ እኛ ዘንድ ነበር፡፡ እናም ሁሉም ወግ እና ሥርዓት አለውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሊፈጸምለት የሚገባው እንዲደረግለት በደስታ ወደ አባቶች ይዘነው ቀረብን፡፡ ሁለት ነገሮች አንደሚጠብቁት ነገር ግን ቁም ነገሩ በእናት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ በመገኘቱ ምትክ የማይገኝለት ሀሴት እንዲሰማው ነገር ነው፡፡

    ከሚጠብቁት ሁለት ነገሮች አንዱ ጥፋቱን አምኖ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ እንዲጠይቅ እና ይህንንም በጽሑፍ እንዲያደርገው ሲኾን ሁተኛው ደግሞ በሚሰጠው ቀኖና መሠረት መኖር እንደሚገባው ነው፡፡ ሁለተኛውን በተመለከተ ቀኖናውን በአገባቡ ከፈጸመ ሊጠብቀው የሚችለው የመጨረሻው ውሣኔ ከማዕረገ ክህነት (ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት እያለ ዲቁና ነበረው) እንደሚሻር መኾኑን እርሱም አሳምሮ ያውቅ ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ በጣም ሲጠማዘዝ ሲጠማዘዝ ከረመ እንጂ ከሁለቱ አንዱን እንኳ አልፈጸመም፡፡ በዚያው የውኃ ሽታ ኾነ፡፡ ጥቂት ቆይቶ በአሜሪካ ምድር ተከሰተ ተባለ እና ቅስና ተሰጠው መባልን ሰማን፡፡

    የተደረገው ሁሉ ኢ-ቀኖናዊ እና አሳፋሪ ቢኾንም እንደዚህ ያለውን ማንሣት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማወክ ይኾናል፡፡ ችለን አባቶች እንዲስማሙ እንጣር በሚል አልፈነው ቆየን፡፡ ከዚያም አልፎ አልፎ አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ የሚባሉ ሰው አንድ ጊዜ በጫማ መቅደስ መግባት ችግር የለውም፣ ሌላ ጊዜ የአሳማ ሥጋ መብላት ችግር የለውም፣ ቆይተውም ከአሳማ አልፈው ቁንጫ እና ቅማል መብላትም ችግር የለውም እያሉ ወንጌል ቢጠፋባቸው ሥርዓተ መብል ሰባኪ ኾነው አረፉት፡፡

    ለነገሩ እዚህም ሳሉ እንዲሁ ወጣ ገባ እምነት እና ውልግድግድ ቁመና በመያዝ ያስቸግሩ የነበሩ የውስጥ ሁከት ያለባቸው ሰው ነበሩ፡፡ በዐሥራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ገና ስወስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት ተማሪ ሳሉ ጀምሮ ይህንኑ የሞኝ ስብከት መስበክ ሥራየ ብለው ያዙት፡፡ በተለይም “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን” የሚል ጥቅስ እያነሱ መጽሐፍ ቅዱስ ያላለውን እጁን እየጠመዘዙ ለክህደት ስብከታቸው ማመቻመች ቀጠሉ፡፡ በኦርጋን መዘመርን የተለከፉበት አሜሪካ ከገቡ ሳይኾን ገና አገር ቤት ሳሉ ጀምሮ ነበረ፡፡ ስብከተ አሳማንም (ከዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ ልዋስና) እዚሁ ነበር አሐዱ ያሉት፡፡ ራሳቸው በፈቃዳቸው አብደው የፈቃድ እብደት እያሉ ያስተምሩ ነበር፡፡

    ያን ገጊዜ የት/ቤቱ ዲን ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያመ ወርቅነህ እንደነበሩ ልብ ይሏል፡፡ ያዳቆነ ሳያቀስ አይቀርም ማለት እንዲህ ነበር ለካ! በወቅቱ እሳት የኾኑ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ወጥረው ያዟቸው፡፡ ወዲህም ቢሉ ወዲያ ማምለጫ ሲያጡ ትቻለሁ ተመልሻለሁ የሚል ለቅሶ በየመድረኩ ማሰማት ቀጠሉ፡፡ የዛሬውን አያድርገው እና በዚያን ጊዜ አባ ብእሴ ሰላም ሳይቀር የአባ ወልድ ትንሣኤን አቋም ይቃወም አንደነበር በደንብ ዐውቃለሁ፡፡ በተለመደው የማሙለጭለጭ ቁመና ስብከተ ኦርጋን ሊነገር ቀርቶ ቀኖና ተቀብያለሁ ብለው በየዐውደ ምሕረቱ በመለፈፍ የሕዝበ ክርስቲያኑን ይቅርታ ለማግኘት በቁ፡፡ በቤተ ክርስቲያን መመህራንም ዘንድ መመለሳቸው እንጂ ትኩረት የተሰጠው ሌላ ነገር አልነበረም፡፡

    ዋል አደር አሉና እንዲያውም ቤተ ክርስቲያንንም ሕዝበ ክርስቲያኑንም መካስ ይገባኛል በማለት መሰንቆ ተምሬ ስለ ኦርጋን ባስተማርሁበት አንደበቴ በመዘመር ካልወጣልኝ አሉ፡፡ ዘመኑ ሐራጥቃ ተሐድሶ በሙሉ ኃይሉ ቤተ ክርስቲያንን ለመነቅነቅ የሞት ሽረት ተጋድሎ የሚያደርግበት ስለነበር ያ ትምህርት ደግሞ ሌላ ድምጽ ስለነበረው ይህን አካሄድ በበጎነት በማየት ሰውየው እንዲማሩ ሁኔታዎች ተመቻቹ፡፡ ዘማሪ ይልማ ኃይሉ ለዚህ ዋና ተዋናይ ነበረና ከእርሱም መስማት ይቻላል፡፡ እነ ይልማም ቅዱስ ዑራኤል አካባቢ በሚገኙ ክርስቲያኖች ቤት ውስጥ መሰንቆ ማስተማራቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት ዘለሰኛ እንዳጠኑ መሰንቆ ይዘው ወደ መድረክ ብቅ በማለት ባለፈው አጥፍቻለሁ አሁን ያንን ለመካስ ይኸው በኦርጋን ፋንታ መሰንቆ ይዤ ቀርቤአለሁ እያሉ በፈቃዳቸው መናዘዝ ቀጠሉ፡፡ አዛኙ ሕዝብም በርኅራኄ ተቀበላቸው፡፡ ኦርጋንን ደጋግመው አወገዙ መሰንቆን ደጋግመው ሰበኩ፡፡

    በዚህ መካከል ተመርቀው ወደ ወለጋ ቢመደቡም የአዲስ አበባ ፍትፍት አላላውስ አላቸው (መናኝ እንዲህ ሲል ያማል)፡፡ እንደምንም ተሞዳሙደው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተመደቡ፡፡ እዚያም ሳሉ በሚሰጣቸው ደመወዝ እያጉረመረሙ፣ ደመወዛቸው አንድ ቦታ ለስብከት ሲሄዱ አንዳንድ ምእመናን ለኪስ ከሚሰጧቸው ጋር እያነፃጸሩ መንቀፍ ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደቆዩ ጉዞ ወደ አሜሪካ ከዚያም ውሻ ወደትፋቱ እንዲል መጽሐፍ ወደ ተፉት ተመልሰው እርሱኑ ሲልሱ ተገኙ፡፡ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ! የድሮውን አባብሰውም ከአሳማ እስከ ቁንጫ አበላል ማስተመር ቀጠሉ፡፡

    እኒህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብቸኛው የቁንጫ መምህር ማዕረገ ጵጵስና አግኝተው አቡነ በርናባስ ተባሉ ሲባል እንዴት ያሳዝናል፡፡ በእልህ እና በማን አለብኝነት ሊቀ ሥልጣናት አባ ወርቅነህ (አቡነ መልክ ጼዴቅ) የሚሠሩት ሥራ ነው፡፡ ትናንት የሰበኩለትን ዛሬ የአሳማ ሥጋ ዛሬ እንዲያጎርሱን ይኾንን? ታሪክ የቅር የማይለው ወንጀል በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ተሠርቷል፡፡ ለመኾኑ ጵጵስና አልፈልግም ሲል የነበረን ሰው መሾም ይገባልን? ለነገሩ አባ ወርቅነህም እንዲያ ነበሩ፡፡ ጀግናው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ተከላክለው ከሲመት አስቀሯቸው እንጂ እርሳቸውም በጊዜው አለፈልግም ብለው ትተውት የነበረውን ጵጵስና በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጊዜ ተመኝተውት ነበር፡፡ ቀኖናን አንድ ጊዜ የጣሰ ደግሞ ደጋግሞ ለመጣስ ምንም የሚጎድለው የለም፡፡ ከውስጥ የጎደለው ዋናው ነገር እምነት ነውና፡፡ የምን ምስክር ምን አደረጉት፡፡ የኦርጋን ሰባኪ የኦርጋን ጳጳስ የቁንጫ ሰባኪ የቁንጫ ጳጳስ፡፡ ያልበላንን የሚያክኩ ጤነኛውን የሚቧጭሩ እንደዚህ ጳጳሳት አንፈልግም፡፡ ቢሾሙም አንፈልግም፡፡ ስለተሾመ ይቀበላሉ ከኾነ አንቀበልም፡፡

    አባ ጽጌ ድንግልን ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ሳሉ ዐውቃቸዋለሁ፡፡ አሜሪካ ከገቡ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ባላውቅም ጸዋሚ ተሐራሚ፣ መምህረ ትህትና በሕማም በደቀቀው ሰውነታቸው ላይ ተጋድሎ የሚያበዙ የሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንንን ቃለ እግዚአብሔር እየተጎነጩ የኖሩ አባት ናቸው፡፡ ያን ጊዜም ግን አባ ወልደ ትንሣኤ ከእነርሱም ጋር በአስተሳሰብ አይስማሙም ነበረ፡፡ ብዙ ጊዜ ከእርሳቸው ጋር አባ ወልደ ትንሣኤን በተመለከተ የመነጋገር ዕድል ገጥሞን ነበር፡፡ አይደለም ከአባ ጽጌ ጋር በረከታቸው ይደርብን እና ሊቁ እና መናኙ አባት ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሁ ያሳስባቸው እንደነበር ዐውቃለሁ፡፡ እነዚህን አብሮ መሾም አደጋ መጥራት ነው፡፡ አባ ገብረ ሥላሴንም በጥቂቱ ዐውቃቸዋለሁ፡፡ ያኔ ሰባኬ ወንጌል ጠንካራ አቋም ያላቸው፣ ገራገር አባት እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡

    እርግጠኛ ነኝ በዚህ ጽሑፍ ቅር የሚላችሁ ጥቂቶች ትኖራላችሁ፡፡ ቆም ብለን እናስብ፡፡ እኔም ለቤተ ክርስቲያኔ አድልቼ እንጂ እንዲህ መናገሩ ሳያመኝ ቀርቶ አይምሰላችሁ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከችግር ወደ ችግር እየተሸጋገረች መቀጠል የለባትም፡፡ በእርግጥ የአንድ አባ ወልድ ትንሣኤ መሾም ብቻውን አያስቸግራትም ሊባል ይችላል፡፡ ግን እስከመቼ ተሸፋፍነን? ከመላኩ ሹመት ባለመማራችን እነ ትዝታው መጠለያ አገኙ፣ ከኦርጋን የስህተት ትምህርት መልሶ ሊዶለን ልዑለቃልን እና መሰሎቹን አሰማራ፡፡ ፊታውራሪው እኒሁ በቅድስት ሥላሴ የፀነሱት ኾኑ፡፡ ደግነቱ እነርሱ እንዳሉት ብቻ የሚነዳ ክርስቲያን የለም፡፡ የእነርሱ ክርስትና ከአንድ መንደር መሻገር ያልቻለ ነው፡፡ ስለኾነም እየሰማናቸcው ልንቀጥል በቸልታ ልናያቸው አይገባም፡፡ እኛ ስለ ቅዱስ ወንጌል እንጂ ስለ ቁንጫ እና ቅማል፣ ስለ ኦርጋን እና አሳማ የሚያስብልን አያስፈልገንም፡፡ ሥጋ ወደሙን በሚፈትተው እጅ ቁንጫ እና ቅማል መጉረስም አንፈልግም፡፡ ሥጋ ወደሙ ለሰው ልጆች መዳን የተሰጠ ሲኾን ቁንጫ እና ቅማል ግን ምግብነታቸው ለዝንጆሮ ነው፡፡ ካልገባችሁ የሰውን ልጅ እንዲህ እያቃለላችሁ ከፊታችን ልትቆሙ አትችሉም፡፡

    ስለዚህ በዚያ የምትገኙ አስተዋይ አባቶች ጠንካራ እርምጃ ልትወስዱ ይገባል፡፡ ከትናንትናው ስህተት የነገው ጥፋት ይብሳልና!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በቁምስና የሰበኩለትን በጵጵስና ሊያጎርሱን ይኾን? Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top