• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 26 June 2016

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፭

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

    ተዋዳጆች ሆይ! ክፍል አምስትን ሳላቀርብላችሁ ዘገየሁ፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡ ከዓቅሜ በላይ የኾነ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው፡፡

    † ቁስጥንጥንያ ከተማ †

    እስኪስለ ቁስጥንጥንያ ጥቂት እንበል! ከአንጾኪያ ይልቅ ቁስጥንጥንያ ከቤተ ክርስቲያናዊም ኾነ ከፖለቲካዊ ፋይዳዋ ከፍ ያለ ነው፡፡ መሥራቿ ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ነው፤ በ330 ዓ.ም.፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ሺሕ ኗሪ ነበራት፡፡ መንበረ ፓትሪያሪኩ ለቤተ መንግሥቱ በጣም ቅርብ ነው፤ ሃጊያ ሶፍያ (ቅድስት ጥበብ - መድኃኔ ዓለም በሉት፡፡ ጥበብ ክርስቶስ ነውና)፡፡ በከተማይቱ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡- በ381 ዓ.ም. ጉባኤ ቁስጥንጥንያ የተካሔደበትና ከሃጊያ ሶፍያ 150 ሜትር ገደማ የሚርቀው ሃጊያ ኢረነ (ቅድስት ሰላም)፣ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ የቅዱሳን ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በዮሐንስ መጥምቅ ምትረተ ርእስ የተሰየመ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ በቅዱሳን ስም ቤተ ክርስቲያንን መሰየም የቅርብ ዘመን ታሪክ እንዳልኾነ እያስተዋላችሁ ነውን?

                 
    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ዲያቆናዊት ኦሎምፒያስ

    ኦሎምፒያስማን እንደ ኾነች በቅርቡ በታተመው መጽሐፍ ይመልከቱ፡፡ አሁን ግን እዚህ መግለጽ ወደምንፈልገው እንመለስ፡፡ ከሃጊያ ሶፊያ ደቡባዊ አቅጣጫ የመነኮሳይያት መኖሪያ ነበር፡፡ እመምኔታቸውም ዲያቆናዊት ኦሎምፒያስ ነበረች፡፡ ድኾችን ትረዳለች፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን ታሳንጻለች፡፡ ለመንፈሳዊያን አባቶች በሚያስፈልጋቸው ነገር ኹሉ ትረዳቸዋለች፡፡ ለራሷ ግን ምንም እንኳን እጅግ በጣም ባለጸጋ ብትኾንም የትኅርምት ሕይወትን የምትኖር ነበረች፡፡ የቅዱስ ዮሐንስና የኦሎምፒያስ ሕይወት በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ የተማረች ነች፡፡ ዕለት ዕለት ቅዱሳት መጻሕፍትን ታነባለች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደዚሁ፡፡ እናም ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ቁስጥንጥንያ እንደ መጣ ከኦሎምፒያስ ጋር ተዋወቀ፡፡ መተዋወቅ ብቻ ሳይኾን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ልብሱን የምታጥብለት፣ በትኅርምት ለተጎዳ ሰውነቱ ተስማሚ ምግብን የምታዘጋጅለት እርሷ ነበረች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በቁስጥንጥንያ እንደ እርሷ የሚወደው የልቡንም የሚያጫውተው ሰው አልነበረም፡፡

    ለውጥ በቁስጥንጥንያ

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቁስጥንጥንያ እንደ መጣ ጊዜ አላጠፋም፡፡ እውነተኛ ትምህርቱን በመንበረ ቁስጥንጥንያም ወዲያው ቀጠለ እንጂ፡፡ የመጀመሪያ ተግባሩን ያደረገውም በሶሪያና በሮም ብሎም በእስክንድርያ የነበረውን ልዩነት መፍታት ነበር፡፡ በዚህም ለሊቀ ጳጳሳት መላጥዮስንና ፍላቭያንን ሳይኾን ለጳውሊኖስ ዕውቅናን ሲሰጡ የነበሩት ሮምና እስክንድርያ በቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ዕርቅን ፈጠሩ፤ ወደ አንድነት መጡ፡፡ ቁስጥንጥንያ ሔዶ የአንጾኪያን ችግር ፈታ፤ እጅግ የሚያከብረው ሊቀ ጳጳስ ፍላቪያንም በሮምና በእስክንድርያ ዕውቅና እንዲሰጠው አደረገ፡፡
    ይህንበድል አጠናቀቀ፡፡ አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ አዲሱ መንበረ ጵጵስናው አዞረ፡፡ ከላይ የገለጽነውን የአንጾክያ፣ የሮምና የእስክነድርያ ችግር እስኪፈታ ድረስ ለጥቂት ጊዜያት የቁስጥንጥንያን መንበረ ጵጵስና ታዝቦታል፡፡ መታዘብ ብቻም ሳይኾን አስቸኳይ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ተረዳ፡፡ ለውጡንም ከቤተ ክህነቱ ግቢ ጀመረ፡፡ የመጀመሪያው ለውጥ ያደረገውም ገንዘብ ነክ ነገሮችን ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የማይጠቅሙ አላስፈላጊ ወጪዎችን አስቀራቸው፡፡ በቤተ ክህነቱ ውስጥ የሚደረጉ ግብዣዎችንና ድግሶችን ቤተ ክርስቲያንንና ድኾችን እንደ መዝረፍ አድርጎ ተመለከተው፡፡ ኹሉንም አስቀራቸው፡፡ ድሮዉንስ ከዮሐንስ አፈወርቅ ከዚህ ውጪ ምን ይጠበቃል? ምንም እንኳን እንዲህ አጀብን በሚወዱ ወገኖች ባይወደድለትም የቤተ ክርስቲያን ወጪ ወደ ድኾችና ወደ እጓለ ማውታን ዞረ፡፡

    ፓትሪያሪኩ አሁንም ቀጠለ፤ ወደ ካህናት! ሥርዓት የለሾችንና ምግባረ ብልሹዎችን ሥርዓት እንዲይዙ አደረገ፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ ሊቁ እጅግ የሚወዳት ዲያቆናዊት ኦሎምፒያስንም መገሠጹ ነው፡፡ ለዚህስ አይደል፡- “መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ” የሚባለው? እናም ስትመጸውት አግባብ ባለው መልኩ እንድትመጸውት፣ ላልተቸገሩ ሰዎች ገንዘቧን እንዲሁ መስጠት እንደሌለባት እንዲያውም በራሱ አገላለጽ፡- “ጥቂት ውኃን ወደ ባሕር እንደ መጨመር” እንደ ኾነ ነግሯታል፡፡
    በመቀጠልምወደ ምእመናን ዞረ፡፡ ቅጥ ያጣ አኗኗራቸውን እንዲያስተካክሉ ገሠጻቸው፡፡ ከአንዳንዶች በስተቀርም ሕዝቡ በጣም እየወደደው መጣ፡፡ ሕዝቡ ብቻ ሳይኾን በቤተ መንግሥቱም ቢኾን እየተከበረ መጣ፡፡

    ስብከተ ወንጌሉንም በሃጊያ ሶፊያ፣ በሃጊያ ኢሬኔ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም የሰማዕታት ዓፅም ባረፉባቸው ቅዱሳን መካናት እየተዘዋወረ አስተማረ፡፡ ሕዝቡ በጣም እየወደደው መጣ፡፡ እንዲያውም ታሪክ ጸሐፊው ሶዜሜን እንደሚለው ብዙ ሰው እየተረገጠ ይጎዳ ነበር፡፡ የሊቁን ትምህርት ለመከታተል ይመጡ የነበሩት መናፍቃንም ጭምር ነበሩ፡፡ ምንምእንኳን በአንጾኪያ ካስተማረው ይልቅ በመጠኑ አነስ ያለ ቢኾንም አዳዲስ ትምህርቶችም ነበሩበት፡፡ ብዙዎቹ በዓላትን የተመለከቱ ስብከቶቹ፣ አብዛኛውን የሐዋሪያት ሥራ ማብራርያን፣ የተቀሩት የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ማብራሪያዎች እና ሌሎችም በዚህ ጊዜ ያስተማራቸው ናቸው፡፡ በከተማይቱ ብቻ ሳይኾን ወደ ገጠርም እየሔደ ያስተምራቸው ብሎም አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያንጹ፣ እሑድ እሑድ ወደ ቅዱስ ቁርባን እንዲቀርቡ ያበረታታቸው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕሙማንንና ድኾችንም በየጊዜው ይጎበኝ ነበር፡፡ ወደ ኤፌሶንና ጎትስ ወደ ተባሉ አሕዛብም ሔዷል፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና የአራቱ መነኮሳት ነገር

    የዚህጽሑፍ ዳራ ገድቦኝ በመኻል የዘለልኩት ብዙ ነገር አለ፡፡ አሁን ግን ወደ 401 ዓ.ም. ላምጣችሁ፡፡ በዚህ ዓ.ም. ወደ መኸር ወቅት በቁስጥንጥንያ ጎዳናዎች ላይ ወደ ኃምሳ የሚደርሱ መነኮሳት ታዩ፡፡ ከግብጽ የመጡ ናቸው፡፡ መሪዎቻቸው አራት ናቸው፡፡ ዲዮስቆሮስ፣ አውኖሚዮስ፣ አውሳብዮስና ኢዩትሚዮስ ይባላሉ፡፡ እንዲያውም ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ ነበር፤ ከአሌክሳንድርያ በደቡብ ምሥራቅ 60 ኪ.ሜ. በሚርቅ ቦታ! በኦርቶዶክሳዊ እምነታቸው በጣም የታወቁ ናቸው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ግን በፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ ኦሪገናውያን ተብለው ተከሰሱ፡፡ መከሰስ ብቻ ሳይኾን ከግብጽ ብሎም ከፍልስጥኤም ተባረሩ፡፡ ኦሪገናውያን ያስባላቸው “እግዚአብሔር ረቂቅ እንጂ እንደ ሰው ሰብአዊ ገጽታ የለውም” የሚለው እምነታቸው ነበር፡፡ ያም ኾነ ይህ በብዙ እንግልት ቁስጥንጥንያ ደረሱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን አገኙት፡፡ በጉልበቱ ሥር ወደቁ፡፡ ጉዳያቸውን አስረዱት፡፡ ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስን እንዲማልድላቸውም ለመኑት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጣም ተጨነቀ፡፡ በአንድ መልኩ ሲታይ ጉዳያቸው መታየት ያለበት በአገረ ስብከታቸው ሊቀ ጳጳስ ነው፤ በአሌክሳንድርያ፡፡ በሌላ መልኩ ሲታይ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ሊመልሳቸው ቢያስብ መነኮሳቱ ቴዎፍሎስን በንጉሡ ዘንድ ሊከሱት እንዳሰቡ ነግረዉታል፡፡ በመኾኑም ምን ማድረግ እንዳለበት በማሰብ ተጨነቀ፡፡ ነገሩ ወደ ንጉሡ ከሚሔድ ይልቅም ቴዎፍሎስን መጠየቅ የተሻለ እንደ ኾነ ወሰነ፡፡ ስለኾነም ይቀበላቸው ዘንድ እጅግ ትሕትናን በተመላ መልኩ መልእክት ላከበት፤ ወደ ቴዎፍሎስ፤ እንዲህ በማለት፡- “ልጅህና ወንድምህ ለምኾን ለእኔ ቸርነትህ ይደረግልኝ፡፡ እነዚህን ሰዎች መልሰህ ወደ ጥበቃህ ትወስዳቸው ዘንድ ቅዱስነትህን እማፀናለሁ፡፡” እስከዚያ ግን መጠለያ ሰጥቷቸዋል፡፡ ዋና ተንከባካቢያቸው ማን ሊኾን እንደሚችል ማወቁ ቀላል ነው፤ ኦሎምፒያስ ነቻ!

    ቴዎፍሎስ ግን ለቅዱስ ዮሐንስ ጥያቄ ሳይመልስ ዝም አለ፡፡ “እንዲያውም” ይላል ሶዞሜን “እንዲያውም በእስክንድርያ አከባቢ ቅዱስ ዮሐንስ እነዚህን መነኮሳት እንደ ተቀበላቸው፣ ከምሥጢራት እንዳካፈላቸው፣ ለእነርሱም ጥብቅና እንደ ቆመላቸው በማስመሰል ወሬ ተነዛ፡፡” ቅዱስ ዮሐንስ ግን ምንም ቢቀበላቸውም ከምሥጢራት አላካፈላቸውም፡፡ ክሳቸው ከከሰሳቸው ሰው መስማት ነበረበትና፡፡ ዳግመኛም በአንድ አገረ ስብከት የተከሰሰ ሰው በሌላ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሊፈታ አይችልምና፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም ኹለተኛ ደብዳቤ ላከለት፡፡ መነኮሳቱን ወደ እርሱ - ወደ ቴዎፍሎስ - እንዲመለሱ ቢጠይቃቸውም መመለስ እንደማይፈልጉ፣ እርሱ ራሱ (ቅዱስ ዮሐንስ) ነገሩን የማይፈታላቸው ከኾነም ወደ ንጉሡ ወደ አርቃድዮስ ሔደው ቴዎፍሎስን ሊከሱ እንዳሰቡና ነገሩ የተወሳሰበ እንዳይኾን መልካም ነው ብሎ በሚያስበው መንገድ ፈጥኖ መፍትሔ እንዲሰጠው የሚጠይቅ ደብዳቤ ነበር፡፡

    ፓትሪያሪክ ቴዎፍሎስ በዚህ ጊዜ ደብዳቤ ጻፈ፤ ጠብን የሚያነሣሣ አሳብም ተናገረ፤ እንዲህ በማለት፡- “በጉባኤ ኒቅያ የተወሰነውና በአንድ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተያዘን ክስ በሌላ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሊፈታ እንደማይገባው የምታውቀው አይመስለኝም፡፡ ብታውቀው’ማ ኖሮ ተመልሰህ እኔን ባልወቀስከኝ ነበር፡፡ ደግሞም መከሰስ ካለብኝ በግብጻውያን ነገሥታት ፊት እንጂ ከዚህ የሰባ አምስት ቀን መንገድ ርቀህ በምትኖር በአንተ ፊት አይደለም፡፡” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቴዎፍሎስ የተንኰል ሥራ ምን እንደ ኾነ ስለማያውቅ የሚያስደነግጥ ኾነበት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ማድረግ ያለበትን ኹሉ ስላደረገ ከዚህ በላይ ምንም ላለማድረግ ወሰነ፡፡

    መነኮሳቱምከዚህ በኋላ ወደ ንጉሡ ሔዱ፡፡ ሰኔ 402 ዓ.ም. በመጥምቁ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓል ላይም ክሳቸውን አቀረቡ፡፡ በተለይም ነገራቸውን እንድታይላቸው የፈለጉት ንግሥት አውዶክሲያን ነበር፡፡ ንግሥቲቱም የሚቻላትን ኹሉ እንደምታደርግላቸው ቃል በመግባት ወደ አሌክሳንድርያ መልእክት ላከች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሚመራው ጉባኤ ክሱ እንዲታይ ቴዎፍሎስን የሚጠራ ነበር፡፡ እንግዲህ ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው ነገሮች እንዴት እየተወሳሰቡ እንደሔዱ ተመልከቱ!

    ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቁስጥንጥንያ

    ኤላጲዮስ የተባለ መልእክተኛ ከላይ የጠቀስነው መልእክት ይዞ ወደ ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ ተላከ፡፡ ፓትሪያሪኩም መልእክቱን ተቀበለ፡፡ የታዘዘውን ከማድረግ ውጪ አማራጭ አልበረውም፡፡ ነገር ግን ነገሮች እርሱ እንደሚፈልጋቸው ኾነው እንዲሔዱ አንድ ዘዴ ዘየደ፡፡ እርሱን ደግፈው የሚቆሙ ሰዎችን ማሰባበሰብ! በመኾኑም ወደ ቁስጥንጥንያ መሔድን ዘገየ፡፡ ዘግይቶ ተነሥቶም ቀጥታ ከመሔድ ይልቅ በፍልስጥኤምና በታናሽ እስያ ዞረ፡፡ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እንደ ተናገርን እርሱን ደግፈው የሚቆሙ ሰዎችን ለማሰባሰብ እንጂ፡፡ በዚህ ጉዞዉም የቅዱስ ዮሐንስ ቀንደኛ ጠላቶች የኾኑ አራት ሰዎችን አገኘ፡፡ ሦስቱ ጳጳሳት ሲኾኑ አንዱ መነኮሴ ነው፡፡ አካኪዮስ፣ አንቲዮኮስ፣ ሰቨሪያን እና ይስሐቅ ይባላሉ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በምግባረ ብልሹነታቸው ክህነታቸውን የያዘባቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በልጅነቱ በአንጾኪያ እያለ ምን ዓይነት ጠባይ እንደ ነበረው እንዲመረምሩም አዘዛቸው፤ ቴዎፍሎስ፡፡

    ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ ሌላም ሴራ ጎነጎነ፡፡ ይህን ሊያደርገው ያሰበውም በቅዱስ ኤጲፋንዮስ አማካኝነት ነበር፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ የኦሪገን ትምህርቶችን ይጠላ ስለ ነበርና ቴዎፍሎስም ይህን ስለሚያውቅ በዚህ ጎኑ ሊጠቀምበት አሰበ፡፡ በመኾኑም በቁስጥንጥንያ ኦርቶዶክሳዊ እምነት እየተፋለሰ እንደ ኾነና የዚህ መሪዉም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደ ኾነ በመግለጽ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ፈጥኖ ሊመጣ እንደሚገባ የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈለት፡፡

    ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅንና የንጽህና እንጂ የነገር ሰው አልነበረምና ቴዎፍሎስን አመነው፡፡ መጋቢት 28 ቀን 403 ዓ.ም. በበዓለ ትንሣኤ ዕለትም ከቆጵሮስ ተነሥቶ ሚያዝያ አጋማሽ ላይ ቁስጥንጥንያ ደረሰ፡፡ መጀመሪያ የደረሰው ከላይ ስንጠቅሰው ወደ ነበረው ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ከእርሱ ጋር አብረው የመጡ ካህናት ነበሩና ቅዳሴ ሊቀድስ ፈለገ፡፡ አንድ ዲያቆንም ሾሞ ሥርዓተ ቅዳሴውን አከናወነ፡፡ ልብ በሉ! ይህን ኹሉ ሲያደርግ በአገረ ስብከቱ አይደለምና የቅዱስ ዮሐንስን ፍቃድ አልጠየቀም፡፡ በሌላ አገላለጽ ስናየው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ሊቀ ጳጳስነት አልቀበልም እንደ ማለት ነበር፡፡

    ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ወደ ቁስጥንጥንያ እንደሚመጣ ምንም መረጃ ያልነበረው ቅዱስ ዮሐንስ ከላይ የተናገርነውን እንደ ተከናወነ ሰማ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህ ለምን እንደ ተደረገ ስላላወቀ እንደ ጥንቱ ቅዱስ ኤጲፋንዮስን ጠራው፡፡ አገልግሎትና ጸሎት አብረው እንዲያከናውኑ፣ ማረፊያዉንም በመንበረ ጵጵስናው እንዲያደርግ ጠየቀው፡፡
    ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ግን ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ከግብጽ የመጡትን መነኮሳት አውግዞ ከቁስጥንጥንያ እስካላባረራቸውና የኦሪገንን መጻሕፍት እስካላወገዘ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሚያድርበት ቤት ውስጥ አላድርም፤ አብሬውም አልቀድስም አለ፡፡ በዚህም ቅዱስ ዮሐንስ የኦሪገንን መጻሕፍት ካላወገዘ በራሱ ጊዜ ኦሪገናዊነቱን ያሳያል ብሎ አስቦ ነው፡፡ ተመልከቱ! ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ወደዚህ ኹሉ ውስብስብ ነገር የገባው በቴዎፍሎስ ነገረኛ ዘዴ ነው፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጉባኤ ሊያደርግ እንዳሰበ፣ በዚያም እነዚያ ከግብጽ የመጡት መነኮሳት ኦሪገናውያን ስለ ኾኑ የተወገዙ እንደ ኾኑ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እነርሱን መልሶ ስላላባረራቸው ሊነቅፈው እንደ ተዘጋጀ ዐወቀ፡፡ ነገር ግን ነገሮችን በትዕግሥት ዐይቶ በሊቀ ዲያቆኑ አማካኝነት መልእክት ላከበት፤ እንዲህ ሲል፡- “ኤጲፋንዮስ ሆይ! ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ተቃራኒ የኾኑ ብዙ ነገሮችን አደረግህ፡፡ በመጀመሪያ በእኔ ሥር ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እኔ ሳላውቅ ክህነት ሰጠህ፤ ገብተህ አገለገልህ፤ ጉባኤም አደረግህ፡፡ በዚህም ላይ ልቀበልህ ስል እምቢ አልህ፡፡ ወደ እኛ ትመጣ ዘንድ ብትጋበዝም አልተቀበልህም፡፡ ኹሉንም ነገር በራስህ ውሳኔ ታደርጋለህ፡፡ አሁንም ያደረግኸውና ልታደርገው ያስብከው ነገር ሊያመጣ ለሚችለው ሁከት ተጠያቂ እንዳትኾንና ራስህንም አደጋ ውስጥ እንዳትከት ተጠንቀቅ፡፡

    ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ይህን ተግሣጽ እንደ ሰማ ወደ ቆጵሮስ ለመሔድ ጉዞ ጀመረ፡፡ ሶዞሜን እንደ ጻፈው መነኮሳቱ ቅዱስ ኤጲፋንዮስን አናግረዉት ነበር፡፡ ነገሩን ከእነርሱ ሲሰማም እየኾነ ያለውን ነገር ተረድቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዱስ ዮሐንስን፡- “በመንበርህ እንዳለህ አትሞትም” እንዳለውና ቅዱስ ዮሐንስም፡- “አንተም ከመንበረ ጵጵስናህ አትደርስም” የሚል መልእክት እንደተለዋወጡ የሚገልጽ መረጃ አለ፡፡ ኹለቱም ያሉት ደርሷል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ወደ መንበረ ጵጵስናው ሳይደርስ ግንቦት 12 ቀን 403 ዓ.ም. በባሕር ላይ ዐርፏልና፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ትንሽ ወረድ ብለን እናየዋለን፡፡

    †††
    ሊቁ በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፉ 11ኛው ድርሳኑ ላይ ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር፡- “ይህ ቅዱስ ሰው (ቅዱስ ጳውሎስ) ከደረሰበት ማዕርግ ጋር ፊት ለፊት ስገናኝ አንደበቴ እንደ ከባድ ጎርፍ ኾኖ መቈጣጠር አቃተኝ” እንዳለው እኔም ስለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስናገር መቈጣጠር አቅቶኛልና ከዚህ በላይ ብቀጥል እናንተን ማድከም እንዳይኾን በቀጣይ ክፍል ብንጨርሰው ይሻላል!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፭ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top