Monday, 16 November 2015

የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ትርጓሜ


የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች፦

ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት

ክፍል 5 : የክርስቲያን ኑሮ (የክርስትና ሕይወት ኑሮ)

v  ከምዕራፍ 12 - ምዕራፍ 14

Ø  ምዕራፍ 12 የክርስቲያን ኑሮ ክፍል መጀመሪያ ምዕራፍ ነው::

Ø  የክርስትና ሃይማኖት የእምነት ነገር ብቻ ሳይሆን በኑሮአችንም ውስጥ እንዴት እንደምንመላለስ የሚያስተምረን የኑሮ መመሪያችንም ነው (1ተሰ 4፥1፤ 1ዮሐ 2፥6)

Ø  ስለዚህ በሚከተሉት በእነዚህ ሦስት ምዕራፎች ጽድቅን በእምነት የተቀበለ ሰው በኑሮው እንዴት መመላለስ እንደሚገባው እንማራለን:: በዚህም መሠረት:-

·         የክርስቲያን ኑሮ በእግዚአብሔር ዘንድ በምዕራፍ 12፤

·         የክርስቲያን ኑሮ በምድራዊ መንግሥት ዘንድ በምዕራፍ 13፤

·         የክርስቲያን ኑሮ በወንድሞች ዘንድ በምዕራፍ 14 ተመልክቶልናልና በትኩረት እንማረው ዘንድ ይገባናል:: በመሆኑም:-

§  በምዕራፍ 12 ሊኖረን ስለሚገባ መልካም ኅሊና (በጎ ልብ)፣

§  በምዕራፍ 13 በኑሯችን ውስጥ ማድረግ ስለሚገባን ነገር፣

§  በምዕራፍ 14 ደግሞ ማድረግ ስለማይገባን ነገር እንመለከታለን::

Ø  እስከ አሁን በተመለከትናቸው 11 ምዕራፎች የእምነት ነገር ምን እንደሆነ እየተረዳን መጥተናል:: አሁን ደግሞ በዚህ በምዕራፍ 12  እና በቀጣዮቹ ምዕራፎች የእምነት ተከታይ የሆነው የመልካም ሥራ ነገር እናያለን::

Ø  ይህም የክርስትናው ሕይወትና የመንፈሳዊውን ኑሮ ቅደም ተከተል በሚገባ የሚያስረዳን ነው:: ይኸውም ሰው አስቀድሞ በእምነቱ ይጸድቃል፣ ቀጥሎም በእምነት የተቀበለውን የጽድቅ ሕይወት መልካም ሥራን በመሥራት ይገልጣል::

Ø  ይህም በአፅንኦት የሚያስገነዝበን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በእምነት የተቀበለና በክርስቶስ የዳነ ክርስቲያን የመዳን ሕይወቱን የሚገልጥ መልካም አኗኗር ሊኖረው እንደሚገባ ነው::

v  ቁጥር 1- 2:-

Ø  “እንግዲህ” የተባለው ቃል ከምዕራፍ 3፥21 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 11 መጨረሻ ድረስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ርኅራሄ ይመለከታል::

Ø  በመሆኑም ሐዋርያው እስከዚህ ድረስ ባለው ትምህርት“የእግዚአብሔርን ርኅራሄ ከተረዳንና ከተቀበልን እንግዲህስ ራሳችንን ደስ የሚያሰኝና ሕያው መስዋዕት አድርገን ርኅራሄ ላደረገልን ለእግዚአብሔር እናቅርብ” በማለት ልመና አዘል ምክር ያቀርባል::

Ø  ይህም አቅርቦት መልካም ሥራችንን የተመረኮዘ ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር ርኅራሄ ወረታ ወይም ምላሽ እንጂ ምህረቱን ለማግኘት የሚደረግ ሥራ አይደለም::

Ø  እናስተውል! ከምእራፍ 3፥21 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 11 መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔር ያደረገልንን ቸርነትና ርኅራሄ ከማዳን ሥራው ጋር ተመልክተናል::

Ø  አሁን ደግሞ ለዚህ ቸርነቱ የምናቀርብለትን ወረታ ወይም የምላሽ ስጦታ እየተጠየቅን ነው::ለመሆኑ ምን ልንሰጠው ተዘጋጅተን ይሆን?

Ø  ብዙ ጊዜ ሲሆን የምናየው እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት በስጦታነት የምናቀርበው ያለንን ገንዘብ አልያም ከእኛ ውጭ የሆነውን ነገር ነው::

Ø  ሐዋርያው የሚነግረን ግን:-

·         እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መስዋዕት ወይም ስጦታ ከእኛ ውጭ የሆነ ነገር ሳይሆን የራሳችንን ሰውነት ማለትም ልባችንን እንድንሰጠው ነው:: እርሱም:-

1.      ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችን፣

2.     በልባችን መታደስ የተለወጠ ማንነት እና

3.     ይህንን ዓለም ያልመሰለ አኗኗራችን ነው::

ማስገንዘቢያ :-

Ø  ብዙ ጊዜ በክርስትና ኑሯችን ተመላልሰን የቤተክርስቲያንን ቅጥሮች ወይም በሮች ስመን እና ጥቂት ሳንቲም ዘርዝረን ለድሆች ሰጥተን መምጣት አልያም ጥቂት ሰዓት በጸሎትና በጾም ቆይተን መመለሱ ብቻ በቂያችን እንደሆነ ስንገምት እንታያለን:: ይህ ነገር ለክርስቲያን አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ነገር ግን አይደለም:: ዋናውና ቀዳሚው ያለንን ሳይሆን ራሳችንን ለቅዱሱ አምላካችን ለእግዚአብሔር በቅድስና መስጠት ነው:: ራስን መቀደስ፣ መለየት!

v  ቁጥር 3-8:-

Ø  ይህ የአካልና የብልቶች ምሳሌ ዓይነተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ሆኖ በ1ቆሮ 12፥12-27፣ በኤፌ 4፥15-16 እና በቈላ 1፥18 ደግሞ ቀርቧል ወይም ይገኛል::

Ø  በዚህ ትምህርት ውስጥ ሐዋርያው በተለይ ስለመንፈሳዊ ስጦታዎችና ስለቤተክርስቲያን ሥራ ይናገራል:: ስለሆነም:-

·         ትንቢት :- ተብሎ በቁጥር 6 ላይ የተገለጠው ቃል የወደፊትን ነገር መናገር ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚደረገውን የወንጌል ስብከትም የሚያመለክት ነው:: (1ቆሮ 14፥1-5) ይህም የቀሳውስትን ሥራ የሚያመለክት ነው::

·         አገልግሎት :- ተብሎ የተገለጠው የዲያቆናቱን የተልዕኮ ሥራ የሚያሳይ ነው (ሐዋ 6፥1-6)

·         መምከር :- ደግሞ የንስሐ አባት ሥራ ነው (ቁጥር 8)

·         መማር :- ደግሞ በሽተኞችን የሚጠይቀውና የሚንከባከበው ወገን ሥራ ነው::

·         መግዛት ወይምማስተዳደር :-የዓለቃ ሥራ ነው::

Ø  እንግዲህ የክርስትና ማኅበር ወይም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እያንዳንዳቸው በተሰጣቸው ሙያ ሊተጉ ይገባል::

Ø  እያንዳንዳችን የተለያየ ስጦታ ተሰጥቶናልና (ኤፌ 4፥7)፤ ሁላችንም በተሰጠን ሥጦታ ሳንኮራ በመጨረሻው ቀን የጌታችንን ምስጋና እንቀበል ዘንድ በትጋት እናገልግል (ማቴ 25፥21-23)

v  ቁጥር 9-13

Ø  በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በቀዳሚነት የምንመለከተው ፍቅርን የሚያመለክቱ ሁለት ቃሎችን ነው

·         ፍቅር

·         መዋደድ የሚሉት ናቸው

Ø  ይህም አንደኛው እግዚአብሔር የሚያፈቅርበትን ከፍ ያለውን ነገር የሚገልጥ ሲሆን ሁለተኛው እርስ በእርስ ሊኖረን የሚገባውን መዋደድ የሚገልጥ ነው:: እነዚህ ቃሎች በ ዮሐ 21፥15-17 እየተፈራረቁ የተነገሩ ናቸው::

Ø  ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤

·         ይህ ቃል እግዚአብሔርን የምናፈቅርበት ፍቅር ሲሆን ምልክቱም :-

-       ክፉ ነገርን መጸየፍ እና ከበጎ ነገር ጋር መተባበር ነው

Ø  በወንድማማች መዋደድ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፤

·         ይህ ደግሞ የአንድ አባት ልጆች የሆንን (ዕብ 2፥10-11) ክርስቲያኖች ሊኖረን የሚገባውን መዋደድ የሚያመለክት ነው::: ምልክቱም:-

-       በ1ጴጥ 4፥8 ላይ የተገለፀው የሌላውን ኃጢአትና ድካም በመሸፈንና በመቻቻል እንዲሁም በመከባበር የሚገለጥ ፍቅር ነው::

Ø  ከ11-13 ባሉት ቁጥሮች የምናስተውላቸው ደግሞ ለመልካሙ የክርስትና ኑሯችን መሠረታዊ ሆነው የቀረቡትን ነገሮች  ነው:: እነርሱም:-

·         ለመልካም ሥራ አለመለገም /ዳተኛ አለመሆን/፤

·         በመንፈስ መቃጠል /ለመንፈሳዊ ነገር መቅናት/፤

·         ለጌታ መገዛት /ክርስቶስን ብቻ ማምለክ/፤

·         በተስፋ ደስ መሰኘት /የጌታን መምጣት መናፈቅ/፤

·         በመከራ መታገስ /የክርስትናውን ፈተና አለማማረር/፤

·         ቅዱሳንን መርዳት /ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ማገዝ/::

Ø  እዚህ ጋር ልብ ልንላቸው የሚገቡና በዓለም ሰዎችና በውጭ ባሉ ጠላቶች ዘንድ የምናደርጋቸው ሦስት ወሳኝ ነገሮች ናቸው::

1.      በተስፋ ደስ እንዲለን :- ተስፋ ምን እንደሆነ በምዕራፍ 8፥16-25 አይተናልና::

2.     በመከራ እንድንታገስ :- የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን በዚህ በሰይጣን ግዛት ውስጥ መከራ እንደሚገጥመን የታወቀ ስለሆነ  (1ዮሐ 4፥4-6፣ ገላ 4፥29፣ ዮሐ 15፥18)

3.     በጸሎት እንድንጸና :- ጸሎት ተስፋችን ላይ እንድናተኩርና በመከራችን እንድንበራታ ስለሚያደርገን

v  ቁጥር 14-21

Ø  በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በዋናነት የሚከተሉትን ቁም ነገሮች እንማራለን

1.      መከራ ለሚያደርሱብን መጸለይ ከጌታ የተማርነውና የበለጠ ክብር የሚያመጣልን እንደሆነ (ሉቃ 23፥34)

2.     ከደስተኞች ጋር ደስታቸውን መካፈል፤ ከመከረኞች ጋር አብሮ መቸገር:: ይህም ሕይወት ከጌታችን የተማርነው ነውና:: ጌታችን እርሱ :-

§  “በመከራቸው ሁሉ ጨነቀው” (ኢሳ 63፥9)

§  በድካማችን ይራራል (ዕብ 4፥15)

§  የኃዘንተኞችን ሐዘን ተካፈለ (ዮሐ 11፥33-35)

§  በሠርግ ቤት ታደመ (ዮሐ 2፥1-2)

3.     የትዕቢትን ሐሳብ ትተን የትህትናን ነገር መሥራት:: ይህም ከጌታችን የተማርነው ስለሆነ እናስተውለው:: ጌታችን እርሱ:-

§  ከድሆች ተወለደ፤

§  ከተዋረዱት ጋር ተቀመጠ፤

§  የተማሪዎቹን እግር ሊያጥብ ተንበረከከ (ዮሐ 13፥4-5)

4.     ክፋትን በክፋት አለመመለስና በፈንታው መልካም የሆነውን ማሰብ:: ይህም:-

§  በዓለም ካሉትና ካልዳኑት ሰዎች የምንለይበት ብቸኛው የክርስቶስ ሕይወት ነው::

5.     በቀልንና ፍርድን ለእግዚአብሔር መስጠትን:: ይህም:-

§  በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፍርድ ማመንና መደገፍን የሚያመለክት ነው::

“እግዚአብሔር በእኔና ባንተ መካከል ይፍረድ” 1ሳሙ 24፥12-13

No comments:

Post a Comment