ፈቃዱን ለመስጠት ይመለከተዋል የተባለው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣“ለዐውደ ርእይ ፈቃድ የመስጠት አሠራር የለኝም፤ በእንግዳ ሕግ ፈቃድ ለመስጠት አልችልም፤” ብሏል፡፡ “ዝግጅቱን ለማካሔድ የሚያስፈልጉ ቅድመ ኹኔታዎችን በተሟላ መልኩ ኤግዚቢሽን ማዕከሉ ለአዘጋጆች ባለመግለጹና እንዲያሟሉ ባለማስቻሉ ዝግጅቱ በተያዘለት ፕሮግራም ሊካሔድ አልቻለም፡፡”/ማዕከሉ/በተፈጠረው ክፍተት ላይ ከማኅበሩ ጋር ተከታታይና ሰላማዊ ውይይት ማድረጉን የገለጸው ማዕከሉ፥ “ለማኅበረ ቅዱሳን፣ ለተሳታፊዎችና ለተመልካቾች ከፍተኛ ይቅርታ ይጠይቃል፤” በማለት የይቅርታ መልእክቱን በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች እያስተላለፈ ነው፡፡
የማኅበሩ ጽ/ቤት፣ የዐውደ ርእዩን ተለዋጭ ቦታ እና ጊዜ ገና አልወሰነም፡፡ጋዜጣዊ መግለጫው፣ በዋናው ማእከል ጽ/ቤት በዋና ጸሐፊው እየተሰጠ ነው፡፡
Thursday, 24 March 2016
ሰበር ዜና – ዐውደ ርእዩ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳይካሔድ የተከለከለው በመንግሥት ትእዛዝ ነው፤ “ላልተሟሉት ቅድመ ኹኔቻዎች” ማዕከሉ ሓላፊነቱን ወስዷል
የማኅበረ ቅዱሳን ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ ቅድመ ዝግጅት ሒደት እውነታዎችና ቀጣይ ወቅታዊ ጥረቶች
በታቀደው መርሐ ግብር የማካሔድ ጥረቱ ዛሬም ተጠናክሮ ይውላልዛሬ ከቀኑ 10፡00 በዋናው ማእከል ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣልየዝግጅቱ ቀጣይነት፣ ጊዜና ቦታ የሚታወቀው በሚሰጠው መግለጫ ነው
ጳጉሜን 5 ቀን 2007 ዓ.ም. – የማኅበሩ የሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት፣ ማኅበሩ በአራት ዓመት ስትራተጅያዊ ዕቅዱ ያካተተውን የዐውደ ርእይ ልዩ ዝግጅት ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማሳሰቡን በመጥቀስ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍለት ጠየቀ፤ጳጉሜ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. – የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የዝግጅቱን መካሔድ ፈቅዶ፥ “ከዚኽ በፊት እንደተለመደው ኹሉ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ” በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም በመጠየቅ ለኤግዚቢሽን ማዕከል እና የገበያ ልማት ድርጅት የድጋፍ ደብዳቤ ጻፈ፤
መስከረም 03 ቀን 2008 ዓ.ም. – የማኅበሩ ጽ/ቤት በዋና ጸሐፊው፣ የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ደግሞ በዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነትበስድስት አንቀጾች የተዘረዘረ የአገልግሎት ውል በመፈራረም የጠቅላላ ዋጋውን 35 በመቶ ብር 200 ሺሕ ቅድመ ክፍያ ፈጸመ፤
ጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም.፡- የ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ ዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴ፣ በማኅበሩ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ተቋቋመ፤
ከአንድ ሺሕ በላይ የሰው ኃይል በማቀፍ በአምስት ዋና ዋና ክፍሎች (የትዕይንት ዝግጅት፤ የማስታወቂያና ቅስቀሳ፤ የሥነ ሥርዓት፣ የአዳራሽ እና የቴክኒክ አካላት) የተዋቀረው ዐቢይ ኮሚቴ፣ ጊዜያዊ ጽ/ቤቱን በዋናው ማእከል አንደኛ ፎቅ ከፍቶ የድርጊት መርሐ ግብሩን በማጸደቅ ሥራውን ጀመረ፤
ታኅሣሥ ወር 2008 ዓ.ም.፡- ዐቢይ ኮሚቴው የልዩ ዐውደ ርእዩን ዝግጅት ለብዙኃን መገናኛዎች እና እንደ ሐዊረ ሕይወት ባሉ የብዙኃን መድረኮች በሰፊው በማስተዋወቅ የመግቢያ ትኬት ሽያጭ ማካሔድ ጀመረ፤
ጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- ዐቢይ ኮሚቴው፥ “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን: አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ!!” የሚለውን የዐውደ ርእዩን መሪ ቃል እና መለዮ(ሎጎ) በዋናው ማእከል ጽ/ቤት አዳራሽ ከ300 በላይ እንግዶችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አደረገ፤
ጥር እና የካቲት፤ 2008 ዓ.ም.፡- ዐቢይ ኮሚቴው፥ የማኅበሩን የሥራ አመራር እና የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ እንዲኹም የዝግጅት ኮሚቴውን አባላት ጨምሮ ፍላጎቱ ያላቸው ተሳታፊዎች ኹሉ በተገኙበት፣ በየሳምንቱ ረቡዕ ባዘጋጀው የግምገማ መድረክ፣ የአራት ትዕይንቶችንና የልዩ ክውን ጥበባት መሰናዶውን ጠቅላላ ይዘትና አቀራረብ በተደጋጋሚ በማስተቸት ዝግጅቱን አጠናቀቀ፤
መጋቢት ወር መባቻ ሳምንታት፡- ዐቢይ ኮሚቴው በአገልግሎት ውሉ መሠረት የአዳራሾች ዝግጅት እና የትዕይንት ክፍሎች ዐቅዱን (floor plan and partition design) ለኤግዚቢሽን ማዕከሉ አስተዳደር በማቅረብ የቴክኒክ ክንውኑን በጋራ ቀጠለ፤ የትዕይንቱን ቁሳቁሶችም ማጓጓዝ ተጀመረ፤
መጋቢት 12 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- በተፈጸመው የአገልግሎት ውል የክፍያ ኹኔታ አንቀጽ 4 መሠረት ማኅበሩ ቀሪውን ብር 400 ሺሕ ያኽል የመጨረሻ ክፍያ ለኤግዚቢሽን ማዕከሉ አስተዳደር ፈጸመ፤
መጋቢት 14 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- በአገልግሎት ውሉ መሠረት፣ ዐውደ ርእዩ ከመጋቢት 15 – 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ክፍት ኾኖ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናት ለሥራ የሚያገለግለውን ጊዜያዊ ቢሮ ቁልፍ ዐቢይ ኮሚቴው ከማዕከሉ አስተዳደር ተረከበ፤
መጋቢት 14 ቀን ረፋድ 3፡50፡- የተረከቡትን ቢሮ ለሥራ ዝግጁ በማድረግ ላይ የነበሩ የዐቢይ ኮሚቴው የአዳራሽ እንዲኹም የቅስቀሳና ማስታወቂያ ክፍሎች ሓላፊዎች ወደ ማዕከሉ የዋና ሥራ አስኪያጅ ቢሮ በጸሐፊዋ አማካይነት በድንገት ተጠሩ፤
ሓላፊዎቹን ከኹለት ባልደረቦቻቸው ጋር የተቀበሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፥“በአካሔድ ላይ ክፍተቶች ስላሉ በአስቸኳይ ተሰብስበን መነጋገር ስላለብን ነው ያስጠራናችኹ፤” በማለት ዐውደ ርእዩን ለማካሔድ ፈቃድ ስለመኖሩ ጠየቁ፤ማኅበሩ ዕውቅና ከሰጠውና ተጠሪ ከኾነለት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የፈቃድ ደብዳቤ ማጻፉንና ከማዕከሉ ጋር ከሰባት ወራት በፊት ውል ተፈራርሞ አስፈላጊውን ክፍያ መፈጸሙን የጠቀሱት የዐቢይ ኮሚቴው ሓላፊዎች፣ ቀደም ሲል በማዕከሉ የተስተናገዱት ሦስት ዐውደ ርእዮችም በዚኹ አሠራር መሠረት መካሔዳቸውን በማስታወስበማኅበሩ በኩል የሰነድ ይኹን የአካሔድ ክፍተት እንደሌለ አስረዱ፤
መጋቢት 14 ቀን ረፋድ 4፡40 – 6፡00፡– የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተጨማሪ የአስተዳደር ኮሚቴ አባላትን በመያዝ ከማኅበሩ አመራሮች እና አስፈጻሚዎች እንዲኹም ከዐቢይ ኮሚቴው አባላት ጋራ ባካሔዱት አስቸኳይ ስብሰባ፥ “ከአዲስ አበባ አስተዳደር ዐውደ ርእዩን ለማካሔድ የምትችሉበት የፈቃድ ደብዳቤ አምጡ፤” በሚል “የአካሔድ ክፍተት”ያሉትን አስታወቁ፤
ማኅበሩ ዐውደ ርእዩን ለማካሔድ ፈቃድ ማቅረብ ያለበት ዕውቅና ከሰጠውና ተጠሪ ከኾነለት አካል መኾኑን ጠቅሰው ማኅበሩም ይህንኑ የድጋፍ ደብዳቤ በወቅቱ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ አግኝቶ ያቀረበ በመኾኑ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ማጻፍ አለበት የተባለው ፈቃድ፥ በማዕከሉ አሠራር ያልተለመደ፣ በወቅቱ ያልቀረበ እና ጨርሶም ሕጋዊ አግባብነት እንደሌለው ተወካዮቹ አስረዱ፤የሚመለከታቸውን የከተማውን አስተዳደር ሓላፊዎች ለማነጋገር ከቀትር በኋላ በተደረገው ጥረትም፣ ለዐውደ ርእዩ ከአስተዳደሩ እንዲጻፍ ስለተጠየቀው የፈቃድ ደብዳቤ የሚያውቀው ነገር እንደሌለና አሠራሩም በአስተዳደሩ የሕግ ማህቀፍ እንደሌለውለማረጋገጥ ተቻለ፤ለሰላማዊ ሰልፍ እና ለስብሰባ ፈቃድ በመስጠት ከሚታወቀው የከተማው አስተዳደር አጽፉ፤ በሚል የተጠየቀው የፈቃድ ደብዳቤ አሠራር፣ አራት ዐውደ ርእዮችን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዕውቅና እና ፈቃድ ሲያካሒድ ለቆየው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ አካል ማኅበረ ቅዱሳን፥ ሊቀርብ የማይችል፤ በኤግዚቢሽን ማዕከሉ አሠራር ያልተለመደ መኾኑንና በማኅበሩ በኩልም አንዳችም የአካሔድ ክፍተት እንደሌለ ከማዕከሉ አስተዳደር ጋር መተማመንና መግባባት ላይ ተደረሰ፤
ይኹንና ተሲዓት በኋላ 9፡30 ገደማ፣ የኤግዚቢሽን ማዕከሉ አስተዳደር፣ በቁጥር ኤማ/1085-520-21/08 በዋና ሥራ አስኪያጅ ታምራት አድማሱ “አስቸኳይ” በሚል ለማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ ዛሬ ሊካሔድ የነበረው ዐውደ ርእይ “ከፈቃድ ጋር በተያያዘ ያልተሟላ በመኾኑ” በሚል ዝግጅቱን ለማካሔድ አስቸጋሪ በመኾኑ መሰረዙን አስታወቀ፤በልምድ ያልነበረንና በሕግም የማይታወቅን አሠራር ከጊዜው ውጭ በመጨረሻው ሰዓት የጠየቀውን ትክክለኛ አካል ማንነት በማወቅ፣ የመክፈቻ ጊዜው እክል የገጠመውን ዐውደ ርእይ በመርሐ ግብሩ መሠረት ለማስቀጠል በየፊናው ጥረት ሲያደርግ ያመሸው የማኅበሩ የሥራ አመራርና የሥራ አስፈጻሚ እንዲኹም የዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴው ለጋራ ምክክር አስቸኳይ ስብሰባ በመቀመጥ ሌሊቱን አጋምሷል፡፡
መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም.፡- ወራትን ባስቆጠረው መርሐ ድርጊት መሠረት ከብር 2 ሚሊዮን በላይ የቅድመ ዝግጅት ወጪ የተደረገበት ልዩ ዐውደ ርእዩ፥ ዛሬ፣ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በሚከናወነው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ለሕዝብ እይታ ክፍት የሚኾንበት ዕለት ነበር፤
የማኅበሩ አመራርና ዐቢይ ኮሚቴው ይህንኑ መርሐ ግብር አስቀድሞ በታቀደው መሠረት ለማስቀጠል የሚያደርገውን ጥረት ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲኾን፤ ውሎውንና የደረሰበትን ውጤት ከቀትር 6፡00 ጀምሮ በማጠቃለልና በመገምገም አንድ ውሳኔ አድርጎ ከቀኑ 10፡00 ላይ በዋናው ማእከል ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ማኅበሩ፣ የልዩ ዐውደ ርእዩን እውንነት፣ ትክክለኛ ጊዜና ቦታም፤ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫው ለምእመኑ በይፋ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡
ለቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አስተህምሮ፣ ለኦርቶዶክሳዊነት ዓለም አቀፋዊነትና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲኹም ከቤተ ክርስቲያን ነባራዊና ወቅታዊ ተግዳሮቶች አንጻር ከምእመኑ ለሚጠበቀው ድርሻ ልዩ ትኩረት የሰጠው ልዩ ዐውደ ርእዩ፣ ከመቶ ሺሕ በላይ ተመልካቾች እንደሚጎበኙት ግብ የተያዘበት ነው፤ ከ40‚000 በላይ የመግቢያ ትኬቶችን አስቀድመው የገዙ ምእመናንም የመጀመሪያዎቹ ጎብኚዎች ለመኾን በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቁታል፡፡
የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ባልታወቁ ታጣቂዎች የዘረፋ ስጋት ውስጥ ወድቋል
በአመክሮ ላይ ካሉ ጥቁር ራሶች ጋር ውዝግብ በመፍጠር ደብድበዋቸዋልየደሴቶቹና የአካባቢው ኅብረተሰብ ኹኔታውን በንቃት እየተከታተሉ ናቸውየ740 ዓመት ገዳሙ፣ የበርካታ ጥንታውያን ብራናዎችና ቅርሶች ማዕከል ነው

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በጣና ሐይቅ ውስጥ ከሚገኙ የደሴት ገዳማት አንዱ የኾነው ጥንታዊው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም፣ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ ጀምሮ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የዘረፋ ስጋት ተደቅኖበት እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
ምንጮች እንደገለጹት፣ ባለፈው ኃሙስ ምሽት ግለሰቦቹ በሦስት ጀልባዎች ከፎገራ አቅጣጫ በመምጣት ወደ ገዳሙ የደሴት ክልል ተጠግተው ያደሩ ሲኾን፤ ትላንት፣ መጋቢት 12 ቀን ምሽት 2 ሰዓት ላይ ደግሞ ጀልባዎቹ በቁጥር ጨምረውና ግለሰቦቹም በትጥቅ ተደግፈው መምጣታቸው ስጋቱን ከፍ አድርጎታል፡፡
ኀሙስ ምሽት የመጡት ጀልባዎች ዓርብ ጠዋት ስፍራውን ለቀው ቢሔዱም ትላንት ምሽት ከተመሳሳይ አቅጣጫ በስምንት ጀልባዎች ተጓጉዘው የመጡት የታጠቁ ግለሰቦች በገዳሙ አቅራቢያ ማደራቸው በምንጮቹ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ዛሬ ጠዋት ድረስም፣ ከስምንቱ ጀልባዎች አምስቱ ከነታጣቂዎቹ በስፍራው እንዳሉ ተገልጧል፡፡
አመጣጣቸው ዓሣ ለማስገር እንደኾነ በመግለጽ ኃሙስ ሌሊቱን ከገዳሙ አበምኔትና ከማኅበረ መነኰሳቱ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ያደሩት ግለሰቦቹ፤ ዓርብ ጠዋት በአመክሮ ላይ ከሚገኙ ጥቁር ራሶች አንዱን በመደብደብ ጉዳት ማድረሳቸው ታውቋል፡፡
“የአካባቢው ነዋሪዎች እንኳ፣ ዓሣ እዚያ የማውጣት ልምድ የላቸውም፤” ይላሉ ምንጮቹ፡፡ ስለግለሰቦቹ አመጣጥ ሲያስረዱም፥ ወቅቱ የጾም ወራት በመኾኑና ማኅበረ መነኮሳቱም ሱባኤ ላይ በመኾናቸው አጋጣሚውን ተጠቅሞ ዘረፋ ለማካሔድ የሚደረግ ሙከራ እንጂ ሌላ ሊኾን እንደማይችል ይናገራሉ፡፡
ካለፈው ኃሙስ ምሽት ጀምሮ የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት ከሌሎች የደሴታቱ ገዳማት፣ በዙሪያውና ባሻገሩ ከሚኖረው ማኅበረሰብ ጋር በመደዋወል አካባቢውን በንቃት እየጠበቁ ቢኾንም የክልሉ መንግሥት የግለሰቦቹን ማንነት በመለየትና በመቆጣጠር አስቸኳይ ጸጥታዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከዚኽ ቀደም የመነኮሳቱን አልባሳት በመልበስና ተመሳስሎ በመግባት ጭምር በገዳሙ ዕድሜ ጠገብና ውድ ቅርሶች ላይ ተደጋጋሚ የዘረፋ ሙከራዎች መደረጋቸውን ምንጮቹ አስታውሰው፤ ገዳማውያኑና የአካባቢው ማኅበረሰብ በንቃት መከታተላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፤ መረጃው የደረሰው የክልሉ መንግሥትም አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ የተጠየቀውን ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ከአትክልት ልማት ምንጣሮ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ጥር ወር በገዳሙ ተቀስቅሶ የነበረው የእሳት ቃጠሎ፤ በደሴያቱ ማኅበረ መነኮሳት፣ በአቅራቢያው ነዋሪዎች፣ ከባሕር ዳር ከተማ በጀልባ ተጓጉዘው በደረሱ አገልጋዮችና ምእመናን፣ በክልሉ መስተዳድር ሓላፊዎችና በጸጥታ ኃይሎች የጋራ ርብርብ ከቤተ ክርስቲያኑ መቶ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ መጥፋቱ ይታወሳል፡፡

ከ740 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ጥንታዊው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም፣ በሐይቁ የደቡብ ምሥራቅ ገጽ ከባሕር ዳር ከተማ የኹለት ሰዓት የጀልባ ጉዞ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ለዘመናት የተካበቱ አያሌ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት ማእከል ከመኾኑም በላይ፤ በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የተሣለች ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል፣ የመሥራቹ የአቡነ ኂሩተ አምላክ መቋሚያ፤ የታወቁት ነገሥታት የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የዐፄ ሱስንዮስ፣ የዐፄ ፋሲልና የሌሎችም ነገሥታት አዕፅምት፣ የወግና የክብር ዕቃዎች/ዘውዶች፣ አልባሳት፣ ጎራዴ …/ ተጠብቀው ይገኙበታል፡፡
የገዳሙ መነኮሳት የሚመገቡት ከዳጉሳ እህል የተዘጋጀ ዳቤ የሚመስል መኩሬታ የሚባል ምግብ ነው፤ መተዳደርያቸውም አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ሲኾን ሙዝ፣ ሸንኮራ፣ ሎሚ፣ ትርንጎ፣ ፓፓያ፣ ማሽላ ያመርታሉ፡፡
Wednesday, 16 March 2016
ዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ ቅድስት“ !!
በዚህ በመጀመርያው ሳምንት ከመዝሙረ ዳዊት ላይ የሚሰበከው ምስባክ፦
በግዕዝ፦
እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ
አሚን ወሰናይት ቅድሜሁ
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ
በአማርኛ፦
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
ምስጋናና ውበት በፊቱ ነው፥
ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። (መዝ.፺፭(፺፮)፡፭
በዚህ የሁለተኛ የአብይ ጾም ሳምንት ስለ እግዚአብሔር ቅድስና ቤተ
ክርስቲያን ልጆቿን ታስተምራለች። እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ የተቀደሰ ነገርያስፈልገዋልና ሰው ሁሉ በቅድስና መንገድ በመመላለስ የክብሩ ባለቤት የመንግሥቱ ወራሽእንዲሆን እግዚአብሔር እኔ ቅዱሳን ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ በማለት ስለማስተማሩ ሰፊትምህርት ይሰጥበታል። ሰውም፤ መላእክትም፤ ቦታም፤ ዕለትም
ለእግዚአብሔር በእግዚአብሔር ተቀድሰዋል። ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎችየእግዚአብሔርን ቅድስና ተረድተው እግዚአብሔርን በማመስገን ሲተጉ ቅዱሳት ቦታዎችእና ዕለታት የቅዱሳኑ ነገር ሲታሰብባቸው፤ ጸሎት ሲደርስባቸው እና ለእግዚአብሔር እናእግዚአብሔር ለቀደሳቸው ቅዱሳን ስም መጠሪያ ሆነው ሲያገለግሉ ይኖራሉ።እግዚአብሔርን ማየት እና የእግዚአብሔር የሆነን ሥርዓት መከተል ስለሚያስችል ዕለትዕለት መልካም በማድረግ ቤተ መቅደስ ተብሎ የተነገረለትን ሰውነታችንን በመጠበቅለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዕቃ ሆነን መቅረብ እንደሚገባ
ይዘከርበታል። እግዚአብሔር አምላካችን ቅዱስ ነው እያልን በልባችን አምነን በአፋችን
መስክረን በተግባር ግን ከቅድስና ርቀን እንዳንኖር እግዚአብሔር እንደቀደሰን እናልጅነትን እንደሰጠን በማመን በተቀደሰ ሁኔታ መኖር ይገባናል። የእግዚአብሔርን ቅድስናእንዲሁም ደግሞ እግዚአብሔር ለሰዎች ቅድስናን እንደሚሰጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልየተለያዩ ክፍሎች እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፦
* እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ
መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም
ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን
ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥
ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ
ይጮኽ ነበር። የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም
ጢስ ሞላበት። ኢሳ.፮፡፩-፬
* በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ
ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ
እነርሱ እቀድሳለሁ። ዮሐ.፲፯፡፲፯-፲፱
* ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ
ሆይ፥ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን
የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፥ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ
አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን
ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ። ራእ.፭፡፫-፬
በዚህ በሁለተኛው ሳምንት በቅዳሴ ላይ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሙሉውምንባብ
ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፦
* እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ
ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ
እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን
እንመክራችሁማለን። በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ
ታውቃላችሁና። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤
ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት
አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ
ዘንድ እንዲያውቅ፤ አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥
ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ
ወንድሙንም አያታልል። ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።
እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር
የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ። እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ
ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም
ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤ እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት
ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ
ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥
እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም
እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች
ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው
ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ፩ተሰ.፬፡፩-፲፫
* ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ
ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። እንደሚታዘዙ ልጆች
ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን። እኔ ቅዱስ
ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ
በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ
ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት
ኑሩ። ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር
ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር
የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ
አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን
ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ
ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። ለእውነት እየታዘዛችሁ
ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደደ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ
በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ
ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ
ዘር ነው እንጂ። ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤
ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል።
በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው። ፩ጴጥ.፩፡፲፫-፳፭
* የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ
እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው
ወደ ኢዮጴም ላካቸው። እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥
ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። ተርቦም ሊበላ
ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት
ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤
በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት
የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም
ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች
ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ። ደግሞም ሁለተኛ።
እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።
ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም
ስላየው ራእይ። ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ
የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም
ከፍ አድርገው። ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን?
ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥
መንፈስ። እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም
ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው። ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ
ወርዶ። እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው?
አላቸው። እነርሱም። ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም
ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ
ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት። እርሱም ወደ
ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር
ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ።
በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን
በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ
ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን። ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው
ነኝ ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው
አግኝቶ። አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ
እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው
ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ
ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ
እጠይቃችኋለሁ አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው። በዚች ሰዓት የዛሬ
አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ
ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና። ሐዋ.፲፡፯-፴
በዚህ በመጀመርያው ሳምንት ከመዝሙረ ዳዊት ላይ የሚሰበከው ምስባክ፦
በግዕዝ፦
እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ
አሚን ወሰናይት ቅድሜሁ
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ
በአማርኛ፦ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
ምስጋናና ውበት በፊቱ ነው፥
ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። (መዝ.፺፭(፺፮)፡፭
በዚህ በመጀመርያው ሳምንት የሚነበበው የወንጌል ክፍል፦
ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ
ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጦም፥
በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም
ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም
ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም
ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ
ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። የሰውነት መብራት ዓይን ናት።
ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ
ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥
ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም
አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንምይንቃል፤
ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ
በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ
ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ማቴ.፮፡፲፮-፳፭
Monday, 7 March 2016
ቅዱስ ሲኖዶስ: ፓትርያርኩ ሕግ አክብረውና መዋቅር ጠብቀው እንዲሠሩ አስጠነቀቃቸው፤ በሰላም ጉዳዮች ዛሬ መግለጫ ያወጣል
ሐራ ዘተዋሕዶ
በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው መመሪያዎችና የጠሯቸው ስብሰባዎች ሕገ ወጥ ተብለዋልቋሚ ሲኖዶስ፥ የስምዐ ጽድቅን የፀረ ተሐድሶ ጽሑፍ ጨምሮ የተደረጉ መጻጻፎችን ይመረምራልየፓትርያርኩ ጉዞዎች፥ ስፖንሰር ተገኘበሚል ሳይኾን በቋሚ ሲኖዶሱ ማስወሰን ይኖርባቸዋል

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ መዋቅር ጠብቀው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑና ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ በቅዱስ ሲኖዶስ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ከቀትር በኋላ ባካሔደው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጽሑፎች ላይ ቀርበዋል ለተባሉ አቤቱታዎች የነበራቸውን አያያዝ፣ የወሰዷቸውን አቋሞችና የሰጧቸውን ምላሾች ገምግሟል፡፡
ፓትርያርኩ አቤቱታዎቹን ለመመልከት በሚል በራሳቸው የጠሯቸው የኮሌጆችና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች ሓላፊዎች ስብሰባዎች፤ ማእከላዊ አሠራርን ያልጠበቁና አድሏዊ እንደነበሩ ጉባኤው ተችቷል፡፡ ከዚኽም ጋር በተያያዘ ፓትርያርኩ፣ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በተጻፉ ደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳንላይ ያስተላለፏቸው የክሥና የቅስቀሳ መመሪያዎችየቅዱስ ሲኖዶስን የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መንፈስ የሚፃረሩና ሕገ ወጥ መኾናቸውን ያረጋገጠ ሲኾን በስብሰባዎቹ ወጥተዋል የተባሉ የአቋም መግለጫዎችም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተገልጧል፡፡
ፓትርያርኩ ዛሬ ለተጀመረው ዐቢይ ጾም ባለፈው ሳምንት ዓርብ መግለጫ በሰጡበት አጋጣሚ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው አማካይነት በጠራው በዚኹ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በኃይለ ቃል ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፤ ማኅበሩንም በተመለሱ ጥያቄዎችና በአሉባልታዎች ወንጅለዋል፡፡ “የማኅበሩ አባላት ናችኹ፤ ሒዱ ስላላችኹ ነው የመጣችኹት” በማለት የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ማኅበሩንም “ሀብታሞች ኾነዋል፤ ከመንግሥትም ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ መንግሥት ይረዳቸዋል፤” እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡
ተንኮል የተሸረቡባቸውንና በክፋት የተሞሉ መረጃዎችን ሳያጣሩና ሳይመዝኑ እንደተነገራቸው የሚያስተጋቡት ፓትርያርኩ፣ እኒኽን ኃይለ ቃላት የተናገሩበት የረፋድ ወኔ ግን አብሯቸው አልዘለቀም፡፡ ስብሰባው ከቀትር በኋላ ሲጀመር አንሥቶ ከፍተኛ መደናገጥ ታይቶባቸዋል፡፡ ማእከላዊ አሠራርን ሳይጠብቁ የፈጸሟቸውን መተላለፎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ለጉባኤው ያሰሙ ሲኾን በማኅበሩ ላይ ለሰነዘሯቸው ክሦችም ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል፤ የማኅበሩ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ የአባላቱ አስተዋፅኦ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ በሒሳብ አሠራሩም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከማኅበሩ ብዙ የሚማረው እንዳለም አልሸሸጉም፡፡
ለመዋቅራዊ መተላለፋቸውም ኾነ ከማኅበሩ አንጻር ለቀረቡላቸው የተጨባጭነት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያልሰጡት ፓትርያርኩ፣ ማእከላዊ አሠራርን ባለመጠበቅ በፈጸሟቸው ተግባራት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “አዋረዱን፤ አፈርንብዎ” እስከመባል የደረሰ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል፤ በከፍተኛ ደረጃም ተገሥጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ከመዓርገ ክብራቸው አኳያ ከመሰል የደብዳቤ መጻጻፎች እንዲታቀቡ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ በኮሌጆች የሚገኝበትን አስከፊነት አስመልክቶ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዳሰሳ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ያወጣውን ጽሑፍ ተከትሎ ፓትርያርኩ የሰጧቸው መመሪያዎችና ከማኅበሩ ጋር የተመላለሷቸው ደብዳቤዎችም በቋሚ ሲኖዶሱ እንዲመረመሩ በጉባኤው ተወስኗል፡፡ በይቀጥላልም ጉባኤው፣ ፓትርያርኩ በመሰል ጉዳዮች አስፈጻሚ የአስተዳደር አካላትን በቀጥታ መሰብሰባቸው ስሕተት በመኾኑ፣ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተነጋገሩና በቋሚ ሲኖዶስ እየመከሩ ሕጉን አክብረውና መዋቅሩን ጠብቀው ከአድልዎ የጸዳ አመራር መስጠት እንደሚኖርባቸውም በጥብቅ አሳስቧቸዋል፡፡

ግለ ታሪካቸውን ከማበላሸት አልፎ በክፉ ምክሮችና በሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ቤተ ክርስቲያንን እያሳጣና እያስነቀፈ የሚገኘው የልዩ ጽ/ቤታቸው አሠራርብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በእጅጉ አሳስቧል፤ የልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና የክፋት ተባባሪዎቹ ጉዳይም አስቸኳይ እልባት እንደሚያስፈልገው ከድንገተኛ ልዩ ስብሰባው በተጓዳኝ በስፋት የተመከረበትና አቋም የተያዘበት ወቅታዊ ነጥብ ኾኗል፡፡
የፓትርያርኩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ጉዞ፣ ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ እያወቀው በዕቅድ መከናወን ያለበት ቢኾንም “የራሳችንን ወጪ ሸፍነን ቅዱስነታቸውን እናጅባለን” በሚሉ አማሳኝ ግብረ በላዎች ጭምር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ያለዕቅድ እየወጣ የሚባክንበት፤ ፓትርያርኩ እንደ ርእሰ መንበር ሐዋርያዊ ተልእኳቸውንና አባታዊ ሓላፊነታቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመወከል በሚያበቃ መልኩ የሚወጡበት ከመኾን ይልቅ“ስፖንሰር ተገኘ” በሚል ብቻ ከፍተኛ ስሕተት(የፕሮቶኮልም) የሚፈጸምበትና ክፋት የሚመከርበት እየኾነ እንደመጣም በጉባኤው ታይቷል፡፡
በመኾኑም ማንኛውም የፓትርያርኩ ጉዞዎችና የሚመደቡ ልኡካን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ሲወሰን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንተ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲኹም የመንበረ ፕትርክናውን ፕሮቶኮል በጠበቀ ደረጃ እንዲፈጸም ጉባኤው አሳስቧል፡፡
ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሚመለከታቸው አህጉረ ስብከት በሚመደቡ ልኡካን ተጨማሪ ማጣራት እንዲካሔድና አስፈላጊው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲደረግ የወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአገራችን ወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይም የመከረ ሲኾን በዛሬው ዕለትም በድንገተኛ ልዩ ስብሰባው ቃለ ጉባኤዎች ላይ በመፈራረም መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡




