Saturday, 27 February 2016

ዘወረደ


/የዘወረደ እሁድ ትምህርትና ግጻዌ /

 

በዐቢይ የጾም መግቢያ ላይ የሚገኘው እሁድ ዘወረደ ይባላል፤ ይህ ጾም ዐቢይ ጾም መባሉ መድኀኒታችን ስለ ጾመው ነው፡፡ ‹‹ሁዳዴ›› ጾምም የሚባለው ሑዳድ በሚባለው ጥንታዊ የእርሻ መሬት ስም ታላቅነቱን ለመግለጽ ነው፡፡

በፍትሐ ነገሥት እንደተጻፈልን የጥንት ክርስቲያኖች ከጠዋት እስከ 11 ሰዓት ይጾሙት ነበር፤ ዛሬም ቢሆን በመጠኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ እስከ 7-9 ሰዓት ይጾሙታል፡፡ አንዳንድ አባቶችና እናቶችም እንደ ጥንቱ እስከ 11-12 ሰዓት ይጾሙታል፡፡ በጾሙም እንደ መድኃኒታችን ጠላትን ድል እንነሣበታለን፡፡  በባህረ ሐሳብ ቀመር ሲወርድ ከየካቲት 1 ቀን ሲወጣም ከመጋቢት 5 ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ትንሣኤ ዋዜማ ያለው 55 ቀን ዓቢይ ጾምና ሰሙነ ሕማት ይባላል፡፡

1 ሰንበት (እሑድ) ዘወረደ ይባላል፡ በዚህ ቀን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር መውረድ የሰው ልጅ በትሕትና፣ በፈሪሃ አምላክ ስለ መኖሩ ይዘመራል፡፡ የዕለቱም ስያሜ የተወሰደው በዕለቱ ከሚዘመረው የያሬድ መዝሙር ነው፣ ከሰኞ ጀምሮ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሰው ለጾም ልቡን እንዲያዘጋጅ ትምህርት የሚሰጥበት በጾም ወቅት ሊኖረን ስለሚገባው ሕይወት የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡

ማውጫ፡

መዝሙርስ፡ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት

(ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ)

2.    በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች
በገባሬ ሠናዩ ዲ/ን ያዕ 13፤7-17በንፍቅ ዲ/ን ያዕ 4፤6 እስከ ፍጻሜው

በንፍቁ ቄስ የሐዋ ሥራ 25፤13 እስከ ፍጻሜው

ምስባክ– 
ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት
ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ
አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመአዕ እግዚአብሔር /መዝ 2፤11/

አማርኛ–  ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ

በረዓድም ደስ ይበላችሁ

ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቆጣ

ትርጉም፡ ለእግዚአብሔር በፍርሃት በመንቀጥቀጥ ተገዙ፣ በመገዛታችሁም ደስ ይበላችሁ ዋጋ ያለበት ስለ ሆነ፣ በፍቅር በመነጨ ፍርሃት ደስ ይበላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም ተገዙ ፥ ጥበብ ወልድን እመኑ ፣ ልጄን በሥጋ ብሰድላችሁ አላመናችሁበትም (አልተቀበላችሁትም) ብሎ እግዚአብሔር እንዳይፈርድባችሁ በልጁ እመኑ፡፡

ወንጌል ፡- ዮሐ 3፣10-25

ቅዳሴ፡- የጌታችን (ነአኲተከ)

የዕለቱየትምህርትርእስ

ፈሪሀ እግዚአብሔር

1) ሥጋዊ ፍርሃት ከኃጢአት በኋላ ተከስቷል፣ በጥላቻና በመንቀጥቀጥ የሚሆነው የውስጥ ፍርሃት ሰው ሕገ አምላክን ሲተላለፍ ተጀምሯል፡፡ ይህ ዓቢይ ፍርሃት እና ረዓድ ወደ ዓለም ከኃጢአት በኋላ ስለመግባቱ (ዘፍ 3፤10፣ ምሳ 28፤1) ላይ እናነባለን፡፡ ክርስቲያን ግን የእግዚአብሔርን ፍቅር ስለሚያውቅ ከእንደዚህ ያለ ፍርሃት በክርስቶ ነጻ ወጥቷል፡፡ (ሮሜ 8፤15, 1ኛ 4፤18)

2) ፈጣሪን ለማክበር እና በፍቅር ላይ የተመሠረተች ፈሪሃ እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት ከተፈጠረው ፍትሃት የተለየ ነው፤ ይህ ፍርሃት ከፍቅር፣ ከአክብሮት የመነጨ በመሆኑ ለምስጋና ለቅዳሴ የሚያተጋ በመሆኑ በገነት በነበረው ሰው ሕይወት ውስጥ ነበረ፣ ይህን ቅዱስ ጸጋ በጠላት ምክር ሲነጠቅ በድፍረት ኃጢአት ሠራ፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ናት (ምሳ 1፤7, ምሳ 9፤10) በመሆኑም ዳዊት ሊያስተምረን ፈቅዶ ‹‹ኑ ፈሪሃ እግዚአብሔር ላስተምራችሁ›› ይላል (መዝ 33፤1)

የጥበብ ሁሉ መጀመሪያው የተባለችበት ምክንያት ሰው እግዚአብሔርን ከፈራ እንደ አብርሃም የታዘዘውን ሁሉ ያደርጋል (ዘፍ 22፤12-23) እግዚአብሔርን ፈርቶ የሠራው ሥራም ሞገስ ይሆነዋል (ዘፍ 31፤42) አባታችን ዳዊት ኑ ላስተምራችሁ ያላቸውን ልጆቹን ሲያስተምር ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔርን በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይከባል ያድናቸውማል›› በማለት ፈሪሃ እግዚአብሔር በመላእክተ እግዚአብሔር እንደምታስጠብቀን ተናገረ፡፡ (መዝ 33፤7)

ፈሪሃ እግዚአብሔርም ሕይወትን ለሚፈቅድና በጎን ዘመን ለማየት ለሚወድ ጠቃሚ መሆኑን እያስገነዘበ ሲተረጉም እግዚአብሔርን የምትፈራ ከሆነ በጎ ዘመንንም ለማየት፣ በሕይወት መኖር ከፈለግህ፣ አንደበትህን ከክፉ ከልክል፣ ከንፈሮችህም ሽንግላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ፣ መልካምን አድርግ፣ ሰላምንም እሻ ተከተላትም፣ አለ (መዝ 33፤14) በፈሪሃ እግዚአብሔር የተጠቀመው ዳዊት ‹‹የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ እግዚአብሔርን ፍሩት›› አለ መዝ 33 ፣ 9-11 ። ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድ ሰው ምስጉን ነው፣ ዘሩም በምድር ላይ ኃያል ትሆናለች›› አለ ቁጥር 1፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎችም ከደፋሮች ይልቅ ክቡራን በመሆናቸውን እነሱንም የሚያከብር እንደሚከበር ሲናገር ‹‹ዘያከብሮሙ ለፈራህያነ እግዚአብሔር›› እግዚአብሔርን የሚፈሩትን የሚያከብር ይከበራል (መዝ 14፤4)፣ በእግዚአብሔር ድንኳን ያድራል አለ፡፡  ልጁ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም አክብር (ጠብቅ) አለ (ምሳ 8፤7)፣ እግዚአብሔርን የሚፈራው የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ጸሎቱ ተሰማለት ለአሚነ ክርስቶም በቃ (የሐዋ 10፤2)

አንባቢ ሆይ፡ እንግዲያውስ እኛም ወንጌልን እንዳልተቀበሉ በክርስቶስ እንዳላመኑ ለፍርድ እንደተጠበቁ ሰዎች ከድንጋጤና ከጭንቀት የሚፈጠረውን ፍርሃት አስወግደን (የሐዋ 6፤29 ። ዕብ 10 ፣ 26-30 ። ራዕ 21፤8) ከዚህ ዓይነቱ ፍርሃት ክርስቶስ ነጻ እንዳወጣን እየተገነዘብን የእግዚአብሔርን ፍቅር ቅድስናና ክብር ታላቅነት በሚገልጸው ፈሪሃ እግዚአብሔር እንቁም፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ›› ይላል (ፊልጵ 2፤12)  በዕብራውያን መልእክቱም ‹‹የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበት ጸጋ እንያዝ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና›› አለ (ዕብ 13፤7-17)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃትና በፍቅር ኑሩ›› ይላል (1ኛ ጴጥ 1፤17)

በመለኮታዊ ጥባቆቱ ከድፍረት ኃጢአት እግዚአብሔር እንዲያድነን እንጸልይ እንማፀነውም (መዝ 18፤13) ‹‹… ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ ። ለእነሱም መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል›› ብሎ የተናገረውን ተስፋ እንዲያወርሰን (ኤር 32፤40) ከፍቅር የተነሣ እንፍራው እናከብረው ፤ የአጋንንት ዓይነት ፍርሃት ሳይሆን አባታችን ስለሆነ ክብርን፣ ንጉሣችን ስለሆነ ፍርሃትን ይዘን ለእሱ በፍቅር እንገዛለት፡፡

‹‹ልጅ አባቱን ያከብራል፥ ባሪያም ጌታውን ይፈራል፥ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንኩ መፈራቴ ወዴት አለ?›› እንዳንባል (ሚልክ 1፣6-7)

ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ)

ሑር፥ እምድኅሬየ ሰይጣን፤ ጠላት ሆይ፥ ከኋላዬወግድ

የጾም ትርጉምና ዓላማ፦ሊቃውንት አባቶቻችን በፍትሕ መንፈሳዊ እንደተረጎሙት ጾም ማለት ለተወሰኑ ሰዓታት ከእህልና ከውኃ፤ እንዲሁም ለተወሰኑ ዕለታት ወይም ሳምንታት ደግሞ ሥጋን ደስ ከሚያሰኙና ከሚገነቡ ምግቦች መከልከል ነው። በመሠረቱ የጾም ዋነኛ ዓላማው የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ ፈቃድ ማስገዛት መቻል ነው።

የዐቢይ ጾም ጀማሪና ዓቢይ ያሰኘው ምክንያት፦ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት እንደሚመሰክሩት ጾም በሕገ ኦሪትም ሆነ በሐዲስ ኪዳን በሚገባ የታወቀና የተረዳ ሥርዓተ ሃይማኖት ከመሆኑም በላይ ከጥንት ጀምሮ ሕዝበ እግዚአብሔር ሲጠቀሙበት የኖረና ያለ ቀዋሚ መንፈሳዊ ሕግ ነው። ለጌትነቱ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢቱንና ምሳሌውንም ለመፈጸም ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሔድ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ የጽድቅና የመልካም ሥራ ሁሉ ተቃራኒ የሆነውን ክፉውን ጠላት ዲያብሎስን ፍጹም ድል በመንሣት በጥምቀቱ ሀብተ ልደትን ለሰጠን ለእኛም ጾም መንፈሳዊ የድል መሣሪያ እንዲሆን ባርኮልን በቃልና በተግባር በሚገባ አስተምሮናል። አካለ ክርስቶስ የሆነችውና በከበረ ደሙ የተዋጀችው ቤተ ክርስቲያንም አምላኳንና አዳኟን አብነት አድርጋ ዘወትር በጾምና በጸሎት በመትጋት ዘወትር የሚፈታተናትን ጠላት ሰይጣን እንደ ጌታዋ ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን፤ ጠላትሆይ፥ ከኋላዬ ወግድ እያለች ፈተናውን በአሸናፊነት በመወጣት ድል ስትነሣበት ኖራለች፤ ዛሬም ወደፊትም ድል ትነሣበታለች።

 

ሐዋርያዊት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በቀኖናዋ የታወቁ ሰባት አጽዋማት አሏት። ከእነዚህም መካከል ተቀዳሚው ዐቢይ ጾም ሲሆን ይህንንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአድኅኖት ሥራው መጀመሪያ በማድረግ እነሆ ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋ ሳያጥፍ፣ አንዳች እህልና ውኃ ሳይቀምስ የጾመው ታላቅ ጾም ነው። በመሆኑም ዐቢይ ጾም ይባላል። ይኸውም ታላቅና ደገኛ ጾም፤ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ሰው የሆነው አምላክ በፈቃዱ የጾመው ጾም ማለት ነው። ደገኛ ያሰኘውም ሥርዓተ ጾሙ የተመሠረተው ወልደ አብ፥ ወልደ ማርያም በሆነው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነና ጥንተ ጠላታችን የሆነውን ዲያብሎስን ጌታችን ፈጽሞ ድል የነሣበት ጾም በመሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ዐቢይ ጾም መክበበ አጽዋማት ነው። ከዚህም ጋር ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ጾም፣ ጸሎትና ስግደት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን ትጥቆች ናቸው። ስለሆነም እኒህ ትጥቆቻችን የጨለማው ገዥና የሐሰት አባት የተሰኘ ዲያብሎስን እንደ መምህራችን ክርስቶስ ተዋግተን ፍጹም ድል የምንነሣባቸው ልዩ መሣሪያዎቻችን መሆናቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ዛሬ ዓለም በልዩ ልዩ ሥልት ብዙዎችን ወደ ራሷ እየሳበች በመሆኗ እነዚህ የከበሩ መንፈሳውያን ሀብታት ከብዙ ሰዎች ሕይወት በመራቅ ላይ ይገኛሉ። ይህች ዓለም ያስፋፋችው ከንቱ ልማድም ለክርስቶስ ሰማያዊ ርስት ዜጎች የሆኑትን ነፍሳት ብዙም ሳይዋጉ በዚህ ዓለም ገዥ እንዲያው በቀላሉ እንዲማረኩ አድርጓል።

የጾም ጥቅም፦ቅዱሳን አበው ሊቃውንት እንዳስተማሩት ጾም የትዕግሥት መማሪያ፣ የአርምሞ መግኛ፣ የአንብዐ ንስሐ ምንጭና የመልካም ተጋድሎ ሁሉ መሠረት ነው። በመሆኑም በመጽሐፈ መነኮሳት የእግዚአብሔር ሰው ጾምየጸሎት እናት፣ የዝምታ እኅት፣ የእውነተኛ ንስሐ እንባምንጭ፣ የተጋድሎ ሁሉ መጀመሪያ ናት” በማለት ታላቅነቷን ይመሰክራል። እኛም መዝገበ በረከት ከሆነው አምላክ ዋጋ እንድናገኝ ጾማችን የልማድ ጾም መሆን የለበትም። ይልቁንም ጾማችን ፍጹም መንፈሳዊነትን የተላበሰና ሥርዓትን የጠበቀ እውነተኛ ጾም መሆን ይገባዋል።

እውነተኛ ጾም፦ በመሠረቱ ጾም ከእህልና ውኃ ብቻ  መከልከል አይደለም። ነገር ግን ጾም ማለት እግዚአብሔር አምላካችንን ከሚያሳዝንብን ተግባር መቆጠብ እንዲሁም ራስንና ሌላውንም ሰው ከሚጎዳ ማናቸውም አድራጎት ሁሉ መከልከል ማለት ነው። ስለሆነም ጾም ሁለንተናዊ የሕይወት ለውጥ ካልታየበት ረብ ጥቅም የለውም። ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅና የቅዱሳት መጻሕፍት መተርጉም የሆነው ቅዱስ ያሬድ ይጹም ዐይን፥ይጹም ልሳን፥ ዕዝንኒ ይጹም እሰሚዐ ሕሱምበተፋቅሮ፤ በፍቅር በመጽናት ዓይን ክፉ ነገርንከማየት ይጹም፣ አንደበትም ክፉ ከመናገር ይጹም፣ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም ሲል በጾመ ድጓው በአጽንዖት የዘመረው ለዚህ ነው። ከዚህም ትክክለኛ ጾም ማለት ሁለንተናዊ ሕዋሳትን ከክፉ አሳብ፣ ንግግርና ተግባር መከልከል መሆኑን እንገነዘባለን።

ክቡራን  ሆይ!

ከመድኃኒታቸን ከኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ጉዞ እንደምንረዳው በጾም ጊዜ ሁልጊዜ ፈተና አለ። ምክንያቱም ጾም መንፈሳዊ ሰልፍ ነውና። ይሁን እንጂ በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የጠላትን ፈተናዎች ሁልጊዜ በድል ይወጧቸዋል። እነሆ ፈታኙንም እንደ መምህራቸው ክርስቶስ ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን፤ጠላቴ ሰይጣን ከኋላዬ ሒድ ብለው ድል ይነሱታል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር ወዝንቱ ዘመድኢይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት ሲል የጽድቅ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በጾምና በጸሎት ኃይል ካልሆነ በቀር በሌላ ድል እንደማይነሳ በመግለጽ የጾምን ኃይል አስረድቷል። (ማቴዎስ 17፥21) ስለዚህ እኛም በውስጥም በውጭም ያለውን ጠላት ዘወትር ድል ለመንሳት እንድንችል እግዚአብሔር አምላካችን የሚወደውንና የሚፈቅደውን እውነተኛ ጾም ልንጾም ይገባል። (ኢሳይያስ 58)  www.kidusyared.org

ክርስቶሳውያን ምእመናንና ምእመናት!

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቀኖቹ ክፉዎችናቸውና ዘመኑን ዋጁ” (ኤፌሶን 516) ሲል እንዳስገነዘበው ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን ከመቼውም በበለጠ አብዝታ ልትጾምና ልትጸልይ ይገባታል። ምክንያቱም አሁን ያለንበት ጊዜ መንፈሳዊነት እየተዘነጋ፣ ዓለማዊነት እየሰለጠነ ሰዎች በሥጋዊ ሐሳብና ስልት ብቻ እየተመሩ ያለበት ፈታኝ ወቅት ነው። ሰይጣን የሕይወት እንጀራ ክርስቶስን በዳቦ፣ የሥልጣናትና የኃይላት ጌታ ወልድን በትዕቢት፣ የዓለማትን ጌታ በኃላፊና ጠፊ ገንዘብ ከፈተነ በእኛ ላይ ልዩ ልዩ ፈተና ቢያመጣ ምን ያስደንቃል? ይህ ረቂቅ ጠላት ብዙዎችን ቢያስትና የፈተናዎቹንም ስልቶች እየለዋወጠ ቢታገላቸው ልንደነቅ አይገባም። ምክንያቱም ክርስቶስን በሁለንተናዊ ሕይወታችን ከመሰልነውና በኑሮአችንም ካከበርነው በክፉ ሰይጣናዊ ፈተና ድል አንነሣም። ከመ እንተ ብእሲ ለጸዊም በውስተገዳም ኃደረ። እምኀበ ዲያብሎስ ተመከረ በኃይለመለኮቱ መኳንንተ ጽልመት ሠዓረ፤ እንደ ሰው ሆኖለመጾም  መዓልት  ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስኖረ። ከዲያብሎስ ዘንድ በሦስት አርእስተ ኃጣውዕተፈተነ፥ ድል ይነሣልን ዘንድ።  ሺህ ከ፭ መቶ ዘመንሰልጥነው የኖሩትንና የጨለማ ገዥ የሆኑትንሠራዊተ ዲያብሎስን በጌትነቱ ሻረልን።”  እንዲል /አባ ዲዮስቆሮስ/። እንደሚታወቀው በዘመናችን ይህ ጠላት የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን በሐሰት ወሬ፣ በዓለማዊነት፣ በሥጋዊ ጥቅም፣ በሰላምና አንድነት እጦትና በመለያየት ክፉኛ እየተፈታተናት ይገኛል። ይሁን እንጂ እርሱንም ሆነ ማደሪያዎቹን ስምከሕያው ዘኢይመውት፤ ስምህ የማይሞትናየማይለወጥ ዘላለማዊ ነው” ተብሎ የተመሰከረለትንና መግረሬ ፀር የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕያውና ቅዱስ ስም ጋሻና መከታ አድርገን “ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን” እያልን ልንቃወማቸውና ፊት ልንነሳቸው ይገባል።

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን  ቀድሱ ጾመ፥ ወስብኩምሕላ፤ ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ። በሚለው የነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል ኃይለ ቃል መሠረት በመላው ዓለም የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችንን በእግዚአብሔር ቃል ለማጽናናትና በአንድነት አጽንቶ ለመጠበቅ ታላቅ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ዘርግታ፣ የሕይወት ማዕድ አዘጋጅታ ለሕዝበ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ሕይወት በእጅጉ የሚጠቅም ሥራ የመስራት መገፈሳዊ ልምድ አላት። ስለዚህ ጌታችን ሰው ከእግዚአብሔር አፍበሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” (ማቴዎስ 44) ሲል በአጽንዖት እንደተናገረው ሁላችሁም በትምህርተ ወንጌሉ ፍጹም ተጠቃሚዎች በመሆን በጾምና በጸሎት መትጋትና መበርታት ይገባችኋል። ይህ ከሆነ ደግሞ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ሕይወታችሁን አብዝቶ ይባርካል፣ እርምጃችሁን ያቀናል፣ ዓላማችሁንም ያሳካላችኋል። ክፉ የሚናገሩትን ሳይሆን በጎ የሚያስተምሩትን ስሙ፤ አፍራሾችን ሳይሆን የሚያንጹትን ተከተሉ። እኛ በልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ፈቃድ የምንኖር ስለሆነ ስለራሳችን በአንዳች አንጨነቅ። ይልቁንም የሁላችን እናት የሆነችው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ የአገራችንና የሕዝባችን ጉዳይ ግን ዕለት ዕለት ሊያሳስበን ይገባል።  ምክንያቱም የመንፈሳዊ ሕይዎት ጉድለት በምድራችን  ስለበዛ ነው። እነሆ በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን የሰማያዊት አገራችን የመንግሥተ ሰማያት አካል ናት። በመሠረቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስ አካል እንደ መሆኗ በኪሩቤል ላይ በዘላለማዊ ክብሩ ነግሦ ከተቀመጠው ንጉሣችን ጋር አንድ ሆነን ስደቱንና ፈተናውን የምንቋቋምባትና የምንጽናናባት መለኮታዊ ተቋም ናት። ስለዚህ በዓላማዋ እንድትጸና ልንተጋ ይገባል። ስለዚህ በታላቁ ሱባኤያችን ወቅት የዘወትር ምኞታችንና ጸሎታችን የሰላም አምላክ ለአገራችን ፍጹም ሰላምን፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሕዝባችን ፍቅርንና አንድነት እንዲሰጥ መሆን አለበት።

ይልቁንም በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተግተው ሊጸልዩ ይገባል።  መዕመናንም ሰለ አባቶች ተግተው ሊጸልዩ ይገባል።   እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ስሜት በነገሠበትና መደማመጥ በጠፋበት በዚህ ጊዜ ሁሉንም ወደሚሰማና ለጥያቄዎቻችን ሁሉ ተገቢውን መልስ ወደሚሰጥ አምላክ ከልብ ልንጸልይ ይገባል። ስለ አገራችን ሰላምና ስለ ሕዝባችን ሕይወት ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ማመልከት ተገቢ ነው። መድኃኒታችን ክብር ይግባውና በጾሙ ጊዜ ከጠላት ዲያብሎስ ለቀረቡለት ሦስት ፈተናዎች መልስ የሰጠው በቅዱስ ቃሉ መሆኑን ቅዱስ ወንጌል በሚገባ ይነግረናል። ይህም በጾማችንና በጸሎታችን ወቅት ለሚያጋጥመን ማንኛውም ፈተና ተገቢውን መልስ የምናገኘው ከእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያመለክታል። ክርስቶስ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጠቀሰ ለጠላት መመለሱ ለእኛ አርዓያና ምሳሌ ለመሆን ነው። ይኸውም በጾማችን ወቅት ቃለ እግዚአብሔርን አብዝተን ልናነብና በማስተዋል ልንሰማ እንደሚገባን ያስገነዝበናል።

እነሆ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን  በመላው ዓለም ለምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ሁሉ ዐቢይ የወንጌል ጉባኤ በወርሀ ጾም የመዘጋጀት ልማድ አላት። ስለዚህ በየአቅራቢያችሁ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ዘወትር በመገኘት ቃለ እግዚአብሔርን ልትማሩ ይገባል። በመላው ዓለም የተበተነው ውድ ሕዝባችንም ቤተ ክርስቲያኑን ነቅቶና ተግቶ ይጠብቅ ዘንድ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን  በየጊዜው የሚተላለፈውን መመሪያና መልእክት አክብሮ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ ለቤተ ክርስቲያን መስፋፋት ሁሉም ተባብሮ እንዲሠራ አደራ እንላለን። እግዚአብሔር አምላክ ቸርነቱ ባርኮ የሰጠንን ይህንን ወርቃማ የሥራ ጊዜ ሁላችንም በሚገባ እንጠቀምበት። ይልቁንም ጊዜው የጾምና የጸሎት ጊዜ ነውና በእውነት ለእውነት እንጹም፣ ለችግሮቻችን ሁሉ ተገቢውን መፍትሔ በወቅቱ ወደሚሰጠን አምላክ በአንድነት እንጸልይ። በመጨረሻም ነቢዩ ኢዩኤል እንደተናገረው ሁላችንም በያለንበት በእውነት ጾምን እንስበክ፥ ምሕላንም እናውጅ።

እግዚአብሔር አምላካችን ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን።

ቅኔ እና እነ የኔታ


መግቢያ

ቅኔ ብሂል:- ቃሉ የግዕዝ ነው:: በርባታ ስያሜውም ጥሬ ዘር ይባላል:: ትርጉሙ ቃል በቃል “መገዛት” ማለት ነው:: ግብሩን በተመለከተ ከፈታነው ደግሞ ቅኔ ማለት “መገዥያ፣ ማምለኪያ፣ ማመስገኛ” ማለት ነው:: በአቀራረቡና በሌሎች አገሮች ካሉት ተመሳሳይ የግጥም ስልት ካላቸው ቅኔ መሰል ግጥሞች አንጻር ሲፈታ ደግሞ ቅኔ ማለት በጠቅላላ አቀራረቡ ሲታይ “ግጥም” ማለት ነው:: በቅኔ ምስጋና፣ ክብር፣ ደስታ፣ ኀዘን፣ ተገፍዖ፣ ተዋርዶ እና ታሪክ በአጠቃላይ በዓለም የሚታይና የሚከናወን ሕይወታዊ ገጽታ በባለ ቅኔዎች ይገለጽበታል::

ቅኔ ልዩ የሆነ የምሥጢር ጎዳና፡ የፍልስፍና፡ የትምህርት፡ የርቃቄ መነሻ፤ የአእምሮ ማጎልመሻ፡ ወደ ሀገረ መጻሕፍት የሚያደርስ ምሕዋር፡ መገስገሻ፣ የጥበብ፡ የአእምሮ መንፈላሰሻ፡ ልዩ ሀብት ነው:: ኢትዮጵያዊ ቅኔ በመላው ዓለም ከሚገኙት የቅኔ የግጥም ባሕርያት የተለየ ባሕርይና ቅርጽ መልክ ያለው  የዕውቀት ጎዳና መሆኑን ነጩም ጥቁሩም ሊቅ ተስማምቶበታል:: ይህን በተመለከተ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የክቡር አቶ አለማየሁ ሞገስን “ሰዋሰወ ግእዝ” በመጥቀስ “ዝክረ ሊቃውንት” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ነበር ያሉት “ቅኔ በሌላ ሀገር የማይገኝ ግእዝ ወልዶ ያሳደገው በሽምግልናው ለአማርኛ ያስተዋወቀው… የሕሊና ስሜት፣ የአእምሮ ትፍሥሕት የድካም መድኃኒት፣ የኀዘን ማስረሻ፣ የፍልስፍና ማጎልመሻ ሲሆን ከልዑል እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ መድኃኒት ነው:: ልዩ ልዩ ልሳናትን ስንማር ምንአልባት እርሱን የመሰለ ጥበብ እንዳለ ለማለት በተቻለን መጠን ይልቁንም የግሪክና የእንግሊዝኛ ባለቅኔ የሚባሉትን የቅኔያችንን ጣዕም ጠልቆ ያልቀመሰ የሚያደንቀውን እና የሚያጋንነውን ግጥም ሁሉ ብናነብ እንደ ኮረንቲ ሽቦ ተጣምሮ የሚሄደውን የቅኔያችንን ምሥጢር… አገኛለሁ ማለት ከመሬት ቁጭ ብሎ በቀኝ እጅ ሰማይን ደግፎ በግራ እጅ ከዋክብትን መግፋት ሆነብን”[1]ብለዋል። ሊቁ እንዳሉ የኢትዮዽያ ቅኔ ከፈረንጆች “poem” ፍጹም ልዩ ነው:: አንድ የኢትዮዽያን ቅኔ ያጠኑ ሮማዊ ሊቀ ጳጳስ ስለ ቅኔያችን ሲናገሩ “የኢትዮጵያ ቅኔ ካልተማሩት በቀር ስለ እርሱ መናገር ይከብዳል። ስለ ቅኔ ላልተማረው ሰው ማስረዳት አይቻልም” ነበር ያሉት። እውነት ነው መንገዱ የዕውቀት መንገድ ነውና።

የቅኔ ደራሲ:- የቅኔ ጀማሪ ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ አበው ተስማምተዋል:: የቅዱስ ያሬድ በስድ ንባብም በግጥምም መንገድ (መልክ) የተዘጋጁ በይዘታቸው “ጽድቅ” የሆኑ ቅኔያቱ በድርሰቶቹ መካከል እንደጌጥ አልፎ አልፎ ይታያሉ:: ቅኔዎቹም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመጻሕፍት የተጠቀሱ፣ ከአሁኑ ቅኔ የተለየ መልክ ያላቸው፣ የቅኔን ስያሜ ያስገኙ ቤት ያልመቱ ሰምና ወርቅ ወይንም ልዩ ልዩ የሆኑትን የቅኔ ጎዳናዎች ያልተከተሉ ቅኔዎች ናቸው:: በታሪክ ጥንታዊ በአካሄድ ዘመናዊ የሆነውን ቅኔ ደራሲ በተመለከተ አንዳንዶች “ዮሐንስ ገብላዊ” የሚባለው ሊቅ ነው የደረሰው ሲሉ ሌሎች ደግሞ “ደቀ እስጢፋ” ነው የደረሰው ይላሉ:: ያም ሆነ ይህ ቅኔ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው:: ሁለቱም ሰዎች በታሪክ እንደሚነገርላቸው ዕውቅ “የቅኔ” እና “የአገባብ” ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ነበሩ::

የቅኔ መንገድ  ቅኔ ልዩ ልዩ መንገዶች አሉት:: ሁሉንም ለመዘርዘር ቢያዳግትም ጥቂቶቹን ብንጠቅስ “ሰምና ወርቅ” “ሰም ገፊ” “ውስጠ ወይራ” “አገናኝ” “አታላይ” “ጽድቅ” “አንጻር” “ሙሻ ዘር” “ንጽጽር” “ኅብር” “ጸጸት” “ሞይት” “ዝምዝም ወርቅ” “የወርቅ ተነጻጻሪ” “የወፍ እግር” “ስም ጥቅል” “ኃዳሪና ማኅደር” “ሠረዝ” “ድርብ ሠረዝ” “ጉት” “ፍና ተሳልቆ” “ውስጠ ዘ” እና ሌሎችም ብዙ የቅኔ መንገዶች አሉ:: ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ “ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት” በሚለው መጽሐፋቸው አንድ መቶ አሥራ ሰባት የቅኔ መንገዶችን ከነቅኔያቸው ሌሎች ዘጠና አራት የቅኔ መንገዶችን በስማቸው ብቻ ጠቅሰው በአጠቃላይ የሁለት መቶ አሥራ አንድ ቅኔ መንገዶችን ለትውልድ አስተዋውቀው ጽፈዋል:: ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት ገጽ ፻፹፪-፪፻፯ ይመልከቱ::

የቅኔ ዓይነቶች /ክፍሎች/፦ የሚከተሉት ናቸው።ጉባኤ ቃና ዕዝልና ግእዝ፤ ዘአምላኪየ፤ሚበዝኁ፤ ዋዜማ፤ አጭር ዋዜማ፤ሥላሴ ፤ዘይዕዜ ፤ሣህልከ፤መወድስ (ፍታሕ ሊተ)፤ መወድስ (ኩልክሙ)፤ሕንፄሃ፤ግእዝ ክብር ይዕቲ፤ ዕዝል ክብር ይዕቲ፤ ዕጣነ ሞገር ግእዝ፤ዕጣነ ሞገር ዕዝል ናቸው::

 

አዲስ ቅኔ፦ ቅኔ ሁልጊዜ አዲስ ታስቦ ወይም ተቆጥሮ ወይም ተዘርፎ ይቀርባል እንጂ ያደረ ቅኔ የደረቀ ቅኔ ወይም ክልስ ቅኔ ወይም የተውሶ ቅኔ የለም። ቅኔ ሁልጊዜ አዲስ ከአንድ ጊዜ በላይ ተደግሞ ለምስጋና የማይቀርብ ሁልጊዜ ትኩስ በሊቃውንት አእምሮ የሚመነጭና የሚፈልቅ የምስጋና ቃል ነው። ከላይ እንዳልኩት ቅኔ አይደገምም አይከለስም አይሰለስም፣ ቅኔ ሁልጊዜ አዲስና ትኩስ ነው። ባለቅኔውም በእግዚአብሔር ፊት አዲሱን ምሥጋናውን ከማቅረቡ በፊት ስለቅኔው ከጓደኛው ከመምህሩ ጋርም ቢሆን አይወያይም ቅኔውንም ለማንም አይነግርም። ለእግዚአብሔር ቅኔው ከመቅረቡ በፊት የቅኔ ሰዎች ቅኔአቸውን እንደሚደብቁ መናገሬ ነው እንጂ በደል ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም አንዳንዶቹስ ደህና የቅኔ ሰው አማክረው፣ አስተካክለው እንደ አቤል መስዋዕት የተዋበውን ቅኔ ያቀርባሉ።

የቅኔ አገልግሎት፦በቅኔ ሃይማኖትን፣ ሥነ ምግባርን፣ ትሕትናን፣ ፍቅርን፣ ተዘክሮተ ሞትን፣ ትምህርተ ሕይወትን፣ አዝማነ መንግሥተ ሰማያትን፣ ጸሎትን፣ ተመስጦን አባቶቻችን ሲያስተምሩ ኑረዋል:: ዛሬም አሉ ያስተምራሉ:: በአጠቃላይ በቅኔ የፈለጉትን ማለት ይቻላል:: ሊቃውንት በቅኔ ብሶታቸውንም ይገልጹ ነበር:: ቅኔን ለምሥጋናም፣ ለዘለፋም፣ ለተግሣጽም፣ ለተምኔትም፣ ለአቤቱታም መግለጫ አድርጐ መጠቀም ይቻላል ተችሏልም:: አሁን ለምሳሌ ያህል በቅኔ እንዴት አባቶቻችን ሲያስተምሩ ሲመክሩ ስለ ሃይማኖታቸውም ሲከራከሩ ሐሳባቸውንም ሲገልጹ እንደኖሩ ከጥንት ቅኔዎችና በቅርቡ ከተደረጉት ቅኔያት አንዳንዶችን ለምሳሌ ለአንባቢያን ወደፊት በተከታታይ አቀርባለሁ:: ስለዚህ ዓለም ጥበብ ከንቱነት,የሃይማኖት አቋም መግለጫ ሊሆን ይችላል። ቅባት፣ ጸጋ እየተባባሉ ሊቃውንት በሃይማኖት በተለያዩበት ዘመን አንድ ባለቅኔዎች ተቃውሞአቼውንም ሆነ ድጋፋቸውን በቅኔ ያቀርቡ ነበር::ስለ ሥነ-ምግባር ስለ ፍቅር ጠቃሚነት,የቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ በቅኔ መግለጽ ይቻላል::  መምህራን በቅኔአቸው ኀዘናቸውን ይገልጹ ነበር። ለዚህም የታወቁት ሊቅ የኔታ ገብረ ጊዮርጊስ ዓይናቸውን ታመው በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም በእስቴ መካነ ኢየሱስ ሳሉ የዘረፉት ቅኔ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ደቀ መዝሙራቸው ስለነበሩ በቃላቸው ይዘው ያጻፉኝን ቅኔ እንደምሳሌ አቀርበዋለሁ:: በሚቀጥለው እትም ደግሞ የቅኔውን ትርጉምና ምስጢር አቀርባለሁ።

መወድስ ቅኔ

በመኑ አቀልል ክበደ ተገፎዖ ጽዋዐ ሕማም ወሞት ትህልፍ እምኔየ

አምጣነ ክህደኒ ሥልሰ ሐዋርያ ብርሃን ዓይንየ

ወሕፀተ ባሶር ሠረገላ መጽአ ከመ ይቅትለኒ ስናክሬም ደዌየ

ሠራዊተ ባቢሎን አመ ርእየ

እስመ ጸበበቶ ምድር ለኤርምያስ ሕሊናየ::

ለዓለም

ኃይልየሂ ወልደ እሴይ ለእመ ረስአ ወበልየ

ነግሠ በፈቃዱ አዶንያስ ሕማምየ

ወአመ ትትገፈታዕ ሥልሰ ኢየሩሳሌም ሥጋየ

ተንሥአ ለተሰዶ እንባቆም ልቡናየ:: /ትርጉሙንና ምሥጢሩን በሚቀጥለው እትም ይመልከቱ/

በመግቢያው ላይ እንደገለጽኩት ቅኔ በቅጥነተ ሕሊና በርቀት ባለቅኔውን አክሎ ለተመለከተው ሰው ማራኪ የሚመስጥ ረቂቅ የጥበብ ጐዳና ሲሆን፡ ለሌላው ተርጉሞ ለማስረዳት ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ብዙ ሐተታ የሚያሻው በቅርብ የማይገኝ የምሥጢር ሩቅ ስለሆነ ለባለቅኔዎች እንጂ ለሌሎች በቀላሉ የሚደረስበት አይደለም:: ባለቅኔዎች አባቶቻችን ቅኔ እያሰቡ የት እንዳሉ በተመስጦ ያሉበትን ይረሱ ነበር:: ቅኔ እያሰቡ በላያቸው ላይ ዝናብ ቢወርድ አይሰሙትም ሰውም በፊታቸው ቢያልፍ ዓይናቸው እያየ አያዩትም ነበር:: ምክንያቱም በቅኔ ሐሳብ ይነጠቁ በምሥጢሩም ይጠልቁ ይራቀቁ ስለነበር ነው::

እውቁ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ስለዚሁ ነገር ሲጽፉ እንዲህ ነበር ያሉት:: “ቅኔ ሕዋሳተ አፍዓን ሕዋሳተ ውስጥን ለሕሊና አስገዝቶ በተወሰነ ቁርጥ ሐሳብ የሚታሰብ ስለሆነ ቅኔ ተብሏል:: ይኸውም ሊታወቅ በቅኔ ምሥጢር ልቡ የተነካ ሰው ቅኔ በሚያስብበት ጊዜ በፊቱ የሚደረገውን ነገር እያየ አያይም፣ እየሰማ አይሰማም:: ከዚህም የተነሳ በጎንደሮች መንግሥት የቁስቋሙ አለቃ በእልፍኝ ውስጥ ምንጣፍን አስነጥፎ መጻሕፍቱን በፊቱ ደርድሮ ለበዓለ ቁስቋም የሚቀኜውን ቅኔ ሲያወጣና ሲያወርድ ንጉሡ ዘው ብለው ቢገቡ ልቡ ተመሥጦ ሊያያቸው ባለመቻሉ ቁጭ እንዳለ ቀረ:: ንጉሡም ነገሩ ደንቋቸው ፍጻሜውን ለማየት እሱን አልፈው ከአልጋው ላይ ተቀምጠው ሁኔታውን ይመለከቱ ጀመር:: ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ አእምሮው ሲመለስ ንጉሡ ተቀምጠው ቢያይ ደንግጦ ተነሥቶ እጅ ነሣ:: ንጉሡም ምነው ምን ሆነህ ነው ቢሉት ጃንሆይ ቁስቋምን ያህል ደብር አምነው ሹመውኛል ለበዓል የተሰበሰበው ሰው አለቃው ምን ይናገር ይሆን እያለ ዓይን ዓይን ሲያይ ያልሆነ ነገር ቢሰማ ደብሩን አዋርዳለሁ ጃንሆይን አሳማለሁ እኔም አፍራለሁ ብየ ቅኔ እቆጥር ነበር አለ ይባላል” ብለዋል:: በመሆኑም ቅኔ ልዩ የጥበብ፣ የትምህርት፣ የተመሥጦ ሀብት ስለሆነ ትውልዱ ሊያጠናው ያሉት አባቶች ሳሉ በስሙ ሊያውቀው በመልኩ ሊያየው በእጁ ሊዳስሰው በዐይነ አእምሮው በፍጹም ልቡም ሊከተለውና ሊያጠናው የሚገባው ልዩ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው::

ይቀጥላል

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እየተደረገ ያለው ድራማዊ መሸላለም፥ “ወይኖ አረሰው ወይኖ ጎረሰው” ዓይነት ነገር ነው /ዜና ቤተ ክርስቲያን/


የማነ ዘመንፈስ ቅዱስና መሰሎቹ በወርቅ ሐብላትና በወርቅ ብራስሌት ‘ሽልማቶች’ምይበዘብዛሉፐርሰንት አስከፍያለሁ ብሎ በ5 ወራት ብቻ የእጅ ሰዓት፣ የወርቅ ሐብላትና ብራስሌት ሰብስቧልከየአጥቢያው በኃይልና በግድ ፻ሺሕዎች ለ‘ሽልማት’ እየተሰበሰበ እርስበርሳቸው ይሞጋገሱበታልከንፋስ ስልክ ላፍቶ አጥቢያዎች ብቻከብር 300ሺሕ በላይ ተሰብስቦ ወርቃወርቅ ተሸላልመዋልራስን ለማጋነኛ እና ቦታ ለማግኛ የሚካሔዱ መደለያዎች ናቸው፤ ችግሩ በመሸላለም አይፈታም

/ታዛቢ የክፍላተ ከተማ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች/

*           *          *

ከምስክር ወረቀት ባለፈ ወርቃወርቅ እና ቁሳቁስ መሸላለሙ ወደ ሙስና ሊመራ ይችላልበድርቅ ለተጐዱት ርዳታ በማሰባሰብ ላይ እያለን በየምክንያቱ መሸላለም ከትዝብት ይጥላልገባእተ ነግሁ ብዙ ሠርተው ቤተ ክርስቲያንን ለገባኡተ ሠርኩ ያስረከቧት ያለመሸላለም ነው“የሚገባችኹን ሠርታችኹ የሚገባንን እንጂ ከሚገባን በላይ አልሠራንም በሉ”ተብለን ታዘናል

/ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ጥር እና የካቲት ፳፻፰ ዓ.ም./

*           *          *

(ርእሰ አንቀጽ)

መሸላለሙ ወደ ሙስና እንዳያመራ

… ዜና ቤተ ክርስቲያን ለሀገረ ስብከቱ የሚያሳስበው ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር፣ ሀገረ ስብከቱ መኪናዎችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የድካማቸውን ዋጋ በማሰብ በጉዳይ አስፈጻሚነት የመደባቸውን የራሱን ሠራተኞች እንደ ውጭ ሠራተኞች እንደ ውጭ ስፖንሰሮች ሊቆጥራቸውና ሊያጋንናቸው አይገባም፡፡ እንዲኹም በሥራ ብልጫ ላሳዩ አካላት የማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት መስጠት ሌላውን ለሥራ የሚያነሣሣ ቢኾንም ለተሸላሚውም ኾነ ለሸላሚው አካል ከምስክር ወረቀት ባለፈ ወርቃወርቅና ሌላም የቁሳቁስ ሽልማት መሸለሙ ወደ ሙስና ሊመራ ይችላል፡፡ መንግሥት የሚሸልመው አምራችና አትራፊ አካላትን እንጂ አክሳሪ አካላትን አይደለም፡፡

በተለይ በክፍላተ ከተሞች የተደረገውን መሸላለም በተመለከተ መጽሐፍ “ይወድስከ አፈ ነኪር”ማለትም የሌላው አፍ ያመስግንኽ፤ ይላል፡፡አመስጋኞችም እነርሱ፣ ተመስጋኞችም እነርሱ፤ ሽልማቱ የተዘጋጀው በእነርሱ፣ ተሸላሚዎችም እነርሱ፣ “ወይኖ አረሰው ወይኖ ጎረሰው” ዓይነት ነገር ነው፡፡ ወይም ማታ ማታ በቴሌቭዥን ከምናያቸው ድራማዎች ሌላው አዲስ ድራማ ነው፡፡“ሙስና እየተዳከመ ሔዷል” ተብሎ በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተነገረውንም ዐረፍተ ነገር ፈጽሞ ይሽረዋልና በዚኽ ጉዳይ ላይ ወደፊት ሀገረ ስብከቱ አጥብቆ ሊያስብበትና ለሽልማቱ ገደብ ሊያበጅለት ይገባዋል፡፡

በአኹኑ ጊዜ በሀገራችን በተከሠተው የድርቅ አደጋ ምክንያት በአንድ በኩል በድርቅ ለተጐዱ ወገኖቻችን ርዳታ በማሰባሰብ ላይ እያለን በሌላ በኩል በየምክንያቱ ስንሸላለም መታየቱ ቤተ ክርስቲያንን ከትዝብት ላይ የሚጥል እንዳይኾን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ገባእተ ነግሁ ብዙ ሥራ ሠርተው ያለፉትና ቤተ ክርስቲያንን ለገባኡተ ሠርኩያስረከቧት ያለአንዳች መሸላለም ነውና፡፡ ጌታችንም“የሚገባችኹን ሠርታችኹ የሚገባንን እንጂ ከሚገባን በላይ አልሠራንም በሉ” በማለት በቅዱስ ወንጌል አዞናልና፡፡

(ምንጭ፡- ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ርእሰ አንቀጽ፤ ጥር እና የካቲት ፳፻፰ ዓ.ም.