Wednesday, 25 November 2015

ምሥጢረ ጥምቀት ክፍል-3


ሠ-በማን ስም ልንጠመቅ ይገባል

  ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ይሆኑ ዘንድ በሥላሴ ስም ታጠምቃለች፡፡ ይህም ጌታ ራሱ ለሐዋርያቱ ‹‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም  ያጠመቃችኋቸው፡፡››  (ማቴ. 28÷19) ብሎ የሰጠውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን አንስቶ በሥላሴ (በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ) ስም መጠመቅ የድኀነት በር ቁልፍ መሆኑን ስታስተምርና ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡

 ይህንን የወንጌል ቃል የሚያጣምሙ መናፍቃን በኢየሱስ ስም ብቻ መጠመቅ አለብን እንጂ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የለብንም ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን አነጋገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድ የምሥራቹን ቃል ድምጹን ከፍ አድርጐ ባሰማቸው ጊዜ ልባቸው ተነካ፡፡ ስለዚህም ‹‹ምን እናድርግ›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ንስሐ ግቡ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ አላቸው›› (የሐዋ ሥራ 2÷38)፡፡

 2006 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር በጎንደር

ሐዋርያው ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሎ ማስተማሩ ለምን ነበር? ለምን ጌታ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ያለውን ተከትሎ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ አላለም? የሚል ጥያቄ ለሚያነሣ ሁሉ ምክንያቱ እንደሚከተለው ነው፡፡በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ የተሰበሰቡት አይሁድ ከጥንት ጀምሮ በነቢያት አንደበት ይወርዳል ይወለዳል እየተባለ የተነገረለትን መሲሕን ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ ሐዋርያውም ያ የተስፋው ቃል ዛሬ መፈጸሙንና በተስፋው ቃል መሠረት ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ 33 ዓመተ ከ3 ወር በምድር ላይ ተመላልሦ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሰውን ልጅ በደሙ የዋጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት መሆኑን አምነው በሰው ካልተጠመቁ በስተቀር አብርሃም አባታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሚለው እምነት ብቻ አምነው ጌታን በሰቀሉት አይሁድ መንገድ የሚጓዙ ከሆነ እንደማይድኑ በመሲሕ አምነው በስሙም ከተጠመቁ ግን እንደ ሚድኑ ሊያስተምራቸው ስለፈለገ የጌታን ስም ለይቶ ጠራ፡፡ በዚህም የጌታን አዳኝነትና መሲሕነት አምነው እንዲቀበሉ በአጽንዖት መናገሩ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሐዋርያት ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ቤዛ የሆነልንን ጌታ ሰው ሁሉ አምኖ እንዲድን በየሄዱበት የጌታን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት አሰተምረዋል፡፡ የስብከታቸው ማዕከል የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክህደቱ ጸንቶ የነበረው በጌታ የባሕርይ አምላክነት ላይ ነበርና፡፡ በዚህ የተነሣ የእርሱን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት ለማሳመን ጌታን የስብከታቸው ማዕከል አደረጉ፡፡

ረ-አጥማቂው ማነው?

ሊያጠምቁ የሚገባቸው ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ሰዎች ማለትም ቄስ ወይም ጳጳስ መሆን እንዳለባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል፡፡ ግን ‹‹በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ካህን ነውና ሊያጠምቅ ሥልጣን አለው›› የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም የሚገባቸው ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ብቻ እንጂ ሥልጣነ ክህነት የሌላቸው ምእመናን ሊሆኑ አይገባም፡፡ አይሆኑምም፡፡

ሥልጣነ ክህነት በሌለው ሰው የተደረገ ጥምቀት አማናዊ ጥምቀት አይደለም፡፡ ከሥላሴም ልጅነትን አያሰጥም፡፡ምክንያቱም ጌታ ‹‹አጥምቁ›› ብሎ የላካቸው ከሌላው ሁሉ መርጦ የሾማቸውን ሐዋርያቱን እንጂ ያመኑትን ሁሉ አይደለም (ማቴ.28÷19፤ ማር.16 ÷16)፡፡

ሐዋርያት ሥልጣነ ክህነትን ከጌታ መቀበላቸው በወንጌል ተመዝግቧል፡፡ #ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ$ ይላል (ዮሐ. 2ዐ÷22)፡፡ ይህም ሥልጣነ ክህነት ለመሆኑ ማረጋገጫችን ‹‹ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፡፡ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው›› (ዮሐ.20÷23) በማለት ልጅነትን ሳይሆን ሥልጣነ ክህነትን እንደሰጣቸው ቅዱስ ወንጌል ያስተምረናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነት ኃጢአት ሊያስተሠርይ፣ ከኃጢአት ሊፈታ፣ ሊያስር፣ አይችልምና ነው፡፡ ሥልጣነ ክህነት ግን ኃጢአትን ሊያስተሠርይ፣ ከኃጢአት ሊፈታና ሊያስር ይችላል፡፡

ስለዚህ ለማጥመቅም ሆነ ሌሎችንም ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ለመፈጸም ሥልጣኑ ያላቸው ካህናት እንጂ ሁሉም ምእመን አይደለም፡፡ በዚህም የተነሣ ቤተክርስቲያን በምእመናን የሚፈጸመውን ጥምቀት እውነተኛ ጥምቀት አድርጋ አትቀበለውም፡፡

ሰ-ጥምቀት አንዲት ናት

ጥምቀት የማትደገም፣ የማትከለስ አንዲት ናት፡፡ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ልጅነትን የምናገኝባት ጥምቀት የማትደገምና የማትከለስ አንዲት ብቻ መሆንዋን ሲያስተምር ‹‹አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት…አለ›› ብሏል (ኤፌ.4÷5)፡፡ ሃይማኖታቸው የቀና 318ቱ ሊቃውንትም ‹‹ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡››

 ብለው አስተምረዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ኣርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ጊዜ ያጠመቀችውን ድጋሚ አታጠምቅም፡፡ ነገር ግን አማናዊቷን ጥምቀት ቀድሞም አልፈጸሙምና ከቤተ ክርስቲያናችን ውጪ በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ‹‹ተጠምቀን ነበር›› የሚሉትን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሲቀርቡ በሥርዓቷ መሠረት አስተምራ አሳምና ታጠምቃቸዋለች፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ቀድሞ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ተጠምቆ ኋላ ግን ወደ ሌላ እምነት ቢገባ ተናዞ (ንስሐ ገብቶ) በማየ ጸሎት (መጽሐፈ ቄደር ተደግሞለት) ይረጫል እንጂ ድጋሚ አይጠመቅም፡፡ቄደር የንስሐ እጽበት ነው፡፡ ያደፈ ልብስ እንደሚታጠብ ሁሉ ይህም ሰው ንጽሕት እምነቱን አሳድፏልና ከኃጢአቱ ለመታጠቡ ምልክት ይሆን ዘንድ በማየ ጸሎት ይታጠባል፡፡

ጥምቀት የማይደገምበት ምክንያት

ሀ. ጥምቀት ከእግዚአብሔር ዳግም የምንወለድበት ምሥጢር ነው፡፡

የሥጋን ልደት ስንመለከት ሰው ከእናቱ ማኀፀን የሚወጣው (የሚወለደው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔርም በእውነት አንድ ጊዜ ወልዶናል፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን፡፡

ለ. ጥምቀት ከጌታ ሞትና ትንሣኤ ተሳታፊ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡

‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ በጥምቀትም ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ›› (ቈላ.2÷12)፡፡ ጌታ የሞተውና የተነሣው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም እኛ ከእርሱ ጋር የምንቀበረውና የምነሣው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

ሸ - ለምን በውኃ እንጠመቃለን

1.  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በውኃ ነው እኛም እርሱን አብነት በማድረግ በውኃ 
       ልንጠመቅ ይገባናል (ማቴ.3÷13-16)፡፡

2. ጌታችን ለኒቆዲሞስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› ስላለ እኛም የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በውኃ እንጠመቃለን (ዮሐ.3÷5)፡፡

3. ሐዋርያት ከጌታ በተማሩት መሠረት ያጠመቁት በውኃ ነው፡፡ ጴጥሮስም መልሶ ‹‹እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ›› (የሐዋ.10÷46ና 47)፡፡ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ
        ወረዱ አጠመቃቸውም (የሐዋ.8÷28)፡፡

4.      ውኃ የሰውነትን እድፍ እንደሚያጠራ ሁሉ እንዲሁም ጥምቀት የነፍስን እድፍ  ያስወግዳል ያነጻል፡፡

5.      ውኃ መልክን ያሳያል እኛም በውኃ በመጠመቅ የሥላሴን ምሥጢር በዓይነ ኅሊናችን እናያለን፡፡

6.      በጥንተ ፍጥረት መንፈስ እግዚአብሔር በውኃ ላይ ረብቦ እንደነብር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል፡- ‹‹የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር›› (ዘፍ.1÷2)፡፡ እንዲሁም በውኃ፣ በሕይወትና በመንፈስ ያለውን ግንኚነት ማስተዋል ይገባል፡፡ ልዑለ ባሕርይ ጌታ በነቢዩ በኤርምያስ አንደበት እንዲህ ሲል ተናግራል ‹‹ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል…›› (ኤር.7÷13)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ አስተምሯል (ዮሐ.7÷39)፡፡ ለሳምራዊቷ ሴትም ‹‹እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፡፡ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት›› (ዮሐ.4÷14)፡፡

ከላይ በተገለጸው መሠረት ውኃ የሕይወት ምልክት ነው፡፡ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምናነበው ውኃ ለሰማያዊው መንግሥት፣ ለዘላለም ሕይወት ምሳሌ ሆኖ ተገልጿል፡፡ ‹‹እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር አንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል›› (መዝ. 1÷3) እና የመሳሰሉትን ሁሉ እናገኛለን (ራእይ.2÷16፣ 22÷1፣ 22÷17)፡፡

እንግዲህ ውኃ ከክፉ ኀሊና ለመንጻታችንና ለመቀደሳችን ማረጋገጫ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስተምሯል፡- ‹‹ከክፉ ሕሊና ለመነጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን፣ በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ›› (ዕብ.10÷22)፡፡

7.    ለንጊኖስ የተባለው ሐራዊ (ወታደር) የጌታን ቀኝ ጎን በጦር በወጋው ጊዜ ትኩስ ደምና ውኃ ባንድነት ፈሷል (ዮሐ. 19÷34)፡፡ደሙ ለመጠጣችን፣ ውኃው ለጥምቀታችን መሆኑን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ይህንንም ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ገልጾታል ‹‹በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም፡፡… የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም፡፡… የሚመሰክሩተ መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፡፡ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ›› (1ዮሐ.5÷6-8)፡፡

8.   ውኃ በሁሉም ቤት ይገኛል፡፡ በሀብታሙም በድኃውም ጥምቀትም ላመነ ሁሉ የተፈቀደ መሆኑን ለማጠየቅ በውኃ ሆኗል፡፡ ስለዚህም በውኃ ብቻ እንጠመቃለን፡፡ ሥርዓተ ጥምቀቱን የሚፈጽመው ካህን አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ሲባርከው ውኃው ተለውጦ በዕለተ ዓርብ ከጌታችን ቀኝ ጐን የፈሰሰውን ውኃ ይሆናል፡፡

ምንጭ: የዲ/ን መልአኩ አዘዘው ገጽ 

ምሥጢረ ጥምቀት- ክፍል-2


ሐ-የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን

ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት የዳኑባት መርከብ የአማናዊቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆንዋ በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠ ነው፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቡናቸው ያደረው ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት ሲድኑ እግዚአብሔርን ድምፅ ያልሰሙት የኖኀ ዘመን ለአማናዊው ጥምቀት ምሳሌነት እንዳለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲገልጽ (ሲያስተምር) #ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኀ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡

ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቡናቸው ያደረው ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት ሲድኑ እግዚአብሔርን ድምፅ ያልሰሙት የኖኀ ዘመን ለአማናዊው ጥምቀት ምሳሌነት እንዳለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲገልጽ (ሲያስተምር) ‹‹ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኀ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ›› 1ጴጥ.3÷20-12፡፡

ኖኀና ቤተሰቡ የዳኑባት መርከብ ምሳሌዋ በሆነው በአንዲቱ ቤተክርስቲያን የሚደረገው ጥምቀት ከፍዳ ያነጻናል ከዲያብሎስ ቁራኝነት ያላቅቀናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ድኀነት በጥምቀት መሆኑን ሲገልጽ ይህም ውኃ ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድናል ብሏል፡፡

2.             ግዝረት 

ግዝረት የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ምልክት ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁሉ የአብርሃም ልጅ አይባልም ነበር፡፡ ከሕዝቡም ተለይቶ እንዲጠፋ እግዚአብሔር አዝዞ ነበር (ዘፍ.17 ቁ. 14)፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም፡፡ ጽኑ ፍዳ ወዳለበት ገሃነም ይወርዳል እንጂ፡፡ ምክንያቱም መንግሥተ ሰማይ ካልገባ ያለው ምርጫ ገሃነም መጣል ነውና (ዮሐ.3÷3-6)፡፡ ስለዚህ ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር ግዴታ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም ለክርስቲያኖች ሊፈጽሙት የሚገባ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡

ግዝረት ሊመጣ ላለው ለጥምቀት ምሳሌው መሆኑን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ ‹‹በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣል ሰው ሠራሽ ያይደለ ግዝረትን የተገዘራችሁበት፤ በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ፣ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ›› ብሏል (ቈላ.2÷10-12)፡፡

ግዝረት ማለት ከአካል ላይ ሥጋን ቆርጦ መጣል እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም ሐዋርያው እንዳስተማረን የኃጢአትን ሰንኮፍ ከሕይወታችን ቆርጦ መጣል (ማስወገድ) ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ግዝረት በሰው አማካኝነት የሚፈጸም ሲሆን የኃጢአት ሥሩ ተቆርጠ ተመንግሎ የሚጣልባት ጥምቀት ደግሞ በካህናት አማካኝነት ይፈጸማል፡፡ ዳሩ ግን የኃጢአትን ሰንኮፍ ቆርጦ ከሕይወታችን የሚያስወግደው (የሚጥለው) በስሙ አምነን የተጠመቅንበት መድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ በሰው እጅ ያልተደረገ በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአት ሥር ተቆርጦ የሚወገድበት ግዝረት ጥምቀት ነው፡፡

 አንድ ሰው ሲገረዝ ከአካሉ ደም ይፈሳል፡፡ እደዚሁም ሁሉ በክርስቶስ ደም የተዋጀን ክርስቲያኖች ከኃጢአታችን የታጠብንበትን የጌታ ደም በጥምቀት እናገኘዋለን፡፡ ግዝረት ከአንድ ጊዜ በላይ እንደማይሆንና ሊደገምም እንደማይችል ሁሉ ጥምቀትም የማትደገም፣ የማትከለስ አንዲት ናት፡፡ ሁለት ጊዜ መጠመቅ አይቻልም (ኤፌ.4÷5)፡፡ መጠመቅ ከክርስቶስ ጋር በሞቱ መተባበር ነው (ሮሜ.6÷8)፡፡ ጌታ የሞተው አንድ ጊዜ ነውና ጥምቀትም አንድ ጊዜ ነው፡፡

3.             የእሥራኤልባሕረኤርትራንማቋረጥ

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እንዲህ ሲል ገልጦታል ‹‹ወንድሞች ሆይ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ፡፡ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፡፡ ሁሉም ሙሴ ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ›› (1ቆሮ.10÷1-12)፡፡

እሥራኤል ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር እንደተጠመቁ እኛም አንድነታችን በደሙ ከኃጢአታችን ካጠበን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲሆን እንጠመቃለን፡፡ እስራኤል ከዘመናት የባርነት ቀንበር የተላቀቁትና ነፃ የወጡት የኢርትራን ባሕር ተሻግረው ነው፡፡ ከኃይለኛው ከፈርዖን እጅ የዳኑትም የኤርትራን ባሕር ተሻግረው ነው፡፡ የኤርትራ ባሕር ለፈርዖንና ለሠራዊቱ ሞትን ሲያስከትልባቸው ለእስራኤል ግን ሕይወት፣ ደስታ፣ ነፃነትን አጎናጽፏዋቸዋል፡፡

እኛም ለርኵሳን አጋንንት ከመገዛትና ከፍዳ፣ ከመርገም፣ ከዘላለም ሞት፣ ነፃ ምንሆነው በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን ስንጠመቅ ነው፡፡ የኤርትራ-ባሕር ለፈርዖንና ሠራዊቱ መጥፊያ እንደሆነ በጥምቀትም አጋንንት ድል ይመታሉ፡፡ ለዚህ ነው በሥርዓተ ጥምቀታችን ተጠማቂው ከተጠመቀ በኋላ ከምዕራብ (ሲዖል) ወደ ምሥራቅ (ገነት) የሚዞረው፡፡

የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማን ከለምጹ የነጻው በዮርዳኖስ ወንዝ ታጥቦ ነው፡፡ በነቢይ በታዘዘው መሠረት በዮርዳኖስ ውኃ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ በማለት ታጥቦ ሥጋው እንደገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ንጹሕም ሆኖ መመለሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እናገኘዋለን (2ነገ.5÷8-14)፡፡

እኛም ከኃጢአት ደዌ የምንነጻውና ያረጀው ሕይወታችን ሊታደስ የሚችለው በጥምቀት ነው፡፡ ስንጠመቅ የክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን እንዳጠበን ማረጋገጣችን ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት እንዲህ ብሏል ‹‹በውኃም አጠብሁሽ፤ ከደምሽም አጠራሁሽ፤ በዘይትም ቀባሁሽ›› (ሕዝ 16÷9)፡፡

ለጊዜው ይህ አነጋገር በኃጢአት ለተመላችው ለኢየሩሳሌም የተነገረ ቢሆንም ፍጻሜው ግን በኃጢአት ለተበላሸው ለሰው ሁሉ ሕይወት የተነገረ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ‹‹ባንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ እነሆ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበር፡፡ እኔም መጎናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ፡፡ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም፡፡ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ አንቺም ለእኔ ሆንሽ፡፡›› (ሕዝ 16÷8)፡፡

እግዚአብሔር በምሕረቱ ሰውን በጎበኘበት ወቅት በፍጹም ፍቅሩ ስቦ ነው የሰውን ልጅ ያቀረበው፡፡ ጌታችንም እርቃኑን በመሰቀል የእኛን ከኃጢአት መራቆት አስቀርቶልናል፡፡ የክብር የሕይወት መጎናጸፊያ አጎናጽፎናል፡፡ ስለ እኛ መከራን ተቀበለ፡፡፡ የእርሱ አደረገን፡፡ ‹‹በውኃ አጠብሁሽ›› የሚለው ‹‹ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድን›› ያስረዳናል፡፡ ይኸውም በጥምቀት ነው፡፡ በጥምቀት ከዘላለም የኃጢአት ባርነት መላቀቃችንን ሲያስገነዝበን ‹‹ከደምሽም አጠራሁሽ›› ብሏል፡፡ በተጨማሪም ጥምቀት በቅብዐ ሜሮን ማኀተምነት እንደሚጸም ‹‹በዘይትም ቀባሁሽ›› በማለት አረጋግጦልናል፡፡ ‹‹አንቺም የእኔ ሆንሽ›› እንዳለው ሁሉ ተጠማቂውም በጥምቀት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ ሁሉ አግኝቶ የእርሱ ወገን መሆኑን ያስረዳል፡፡

መ-የሕፃናት ጥምቀት

አንዳንድ ሰዎች የሕፃናትን ጥምቀት ሲነቅፉና ትክክለኛ ጥምቀትም እንዳልሆነ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ተራ ትችት ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ነው፡፡ እነዚህ ክፍሎች ራሳቸው ከአእምሮአቸው አመንጭተው ላስተማሩት ሐሰተኛ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረው አስመስለው ለማቅረብ ሲሞክሩም ይስተዋላሉ፡፡

ለምሳሌ ያህል #ያመነ የተጠመቀ ይድናል$ የሚለውን በመጥቀስ ‹‹በመጀመሪያ እምነት ይቀድማል፡፡ ለማመን ደግሞ መማር፣ ማወቅ፣ ማገናዘብና አምኜአለሁ ተቀብያለሁ ሊባል ይገባል፡፡ ሕፃናት ግን የሚያውቁት ነገር ስለሌለ አላመኑም ስለዚህ ያላመኑ ሕፃናትን ማጥመቅ ተገቢ አይደለም›› ይላሉ፡፡ ዳሩ ግን ቤተክርስቲያን ወንዶችን በተወለዱ በ4ዐ ቀናቸው ሴቶችን በተወለዱ በ8ዐ ቀናቸው የምታጠምቀው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ ነው፡፡

ሀ. ሕፃናት የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኙ ወላጆቻቸው ናቤተክርስቲያን የሚሹት ነው፡፡

ያለ ጥምቀት ደግሞ ዘላለማዊ ሕይወት አይገኝም፡፡ ጌታ እንዳስተማረው #ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም$ (የሐ.3÷5)፡፡ ስለዚህ ሕፃናት በወላጆቻቸው እምነት የተነሣ የወላጆቻቸውን እምነት የእነርሱ እምነት በማድረግ ገና በሕፃንነት ጊዜያቸው ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጭ እንዳይሆኑ ታጠምቃቸዋለች፡፡ ዳሩ ግን ሳይጠመቁ ቢሞቱ ጌታ እንደተናገረው መንግስተ ሰማይን አያዩአትም፡፡ እንደ ጌታ ትምህርት የምንሄድ ከሆነ #ሰው$ ብሎ ባጠቃላይ ሕፃናትን አዋቂዎችን ሁሉ ጨምሮ ተናገረ እንጂ ከሕፃናት በስተቀር አላለም፡፡ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡

ለ. ሕፃናት በመጠመቃቸው የቤተ ክርስቲያን አባል ስለሚሆኑ የእግዚአብሔር ጸጋ ተከፋዮች ይሆናሉ፡፡

ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት ይለማመዳሉ፡፡ በዚህ ፈንታ ከሕፃንነታቸው ጊዜ ጀምረው ከእግዚአብሔር ጸጋ ተራቁተው የሚያድጉ ከሆነ ለመጥፎ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡

ሐ. ‹‹ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው››

እንዲሁም ጌታችን ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል›› ሲል በዚያን ዘመን ገና ወንጌል መስበክ በጀመረበት ላሉት ሰዎች የተነገረ ሲሆን ከክህደታቸውና ከጥርጥራቸው ተመልሰው የሚመጡ ሁሉ አምነው መጠመቅ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሕፃናት የእግዚአብሔር ልጆች ሊሆኑ እንደሚገባ ጌታችን ሲገልጽ ‹‹ሕፃናት

 ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተውአቸው አትከልክሏቸው መንግሥተ ሰማያት እንደ እነርሱ ላሉት ናትና›› ብሏል (ማቴ.19÷14)፡፡ በዚህ የጌታ ትምህርት መሠረት ቤተክርስቲያንም የመሪዋንና የመሥራችዋን የክርስቶስን ቃል መርሕ በማድረግ ወላጆቻቸው ታቅፈው ወደ ቤተክርስቲያን ይዘው በመምጣት ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጆች የቤተክርስቲያን አባላት እንዲሆኑ ሲያደርጉ እርሷ ከልካይ አትሆንም፡፡ ጌታ ተውአቸው ይምጡ ልጅነትን፣ ጸጋን፣ በረከትን ያግኙ ብሏልና፡፡

ሕፃናት ንጹሐነ አእምሮ መሆናቸውን ጌታ ሲያስተምር እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም ብሏል፡፡

መ. መጽሐፍ ቅዱስ ሕፃናት መጠመቃቸውን ያስተምረናል፤

የሚከተሉት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

1. በእሥር ቤቱ በተደረገው ተአምር የተደነቀውና ወደ ክርስትና እምነት የተሳበው የወኀኒ ጠባቂ ጳውሎስና ሲላስ ካስተማሩትና ካሳመኑት በኋላ ከነቤተሰቡ መጠመቁ ተገልጾአል፡፡ እግዲህ የተሰበከውና ያመነው የወኀኒ ጠባቂው ሲሆን የተጠመቁት ግን ሕፃናትን ጨምሮ መላው ቤተሰቡ ነው (የሐዋ.16÷33)፡፡

2. ልብዋን ጌታ የከፈተላትና ቃሉን አድምጣ ሕይወትዋን ለክርስቶስ የሰጠችው ልድያባመነች ጊዜ የተጠመቀችው ብቻዋን ሳይሆን ከመላው ቤተሰብዋ ጋር ነው፡፡ ከቤተሰቡ መካከል ሕፃናት መኖራቸው የማይቀር ነው (የሐዋ.16÷15)፡፡

3. ቅዱስ ጳውሎስ የእስጢፋኖስንም ቤተሰቦች ደግሞ አጥምቄያለሁ በማለት የእስጢፋኖስን መላ ቤተሰብ ማጥመቁን ገልኦአል (1ቆሮ.1÷16)፡፡ እነዚህ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ሁሉ ትላልቆች ብቻ ናቸውን? ሕፃናት የሉበትም ይሆን?

4. በሐዋ.ሥራ 2 ላይ እንደተገለጸው በበዓለ ሃምሳ ከ3ዐዐዐ ያላነሱ ሰዎች በጴጥሮስ ተሰበኩ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ ብዙዎቹ መጠመቃቸው ተገልጿል፡፡ የተጠመቁት ግን ዐዋቂዎች ብቻ መሆናቸውን የሚገልጽ ቃል የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሕፃናትን ጥምቀት የሚነቅፍ ባንዱም ክፍል ተጽፎ አናገኝም፡፡

እስከ አሁን እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ የሕፃናትን ጥምቀት ያልነቀፈ ሲሆን በብሉይ ኪዳን የጥምቀት ምሳሌ የነበሩትን ስንመለከት ይበልጥ የሕፃናትን ጥምቀት ትክክለኛነት ያረጋግጡልናል፡፡

ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናት በተወለዱ በስምንተኛው ቀን ይገረዙ ነበር (ዘፍ. 17÷12)፡፡ እንግዲህ ሕፃናቱ የሚገረዙት በወላጆቻቸው እምነት እንጂ እነርሱ ዐውቀው ግረዙን ብለው አይደለም፡፡

የእሥራኤል ቀይ ባሕርን ማቋረጥ የጥምቀት ምሳሌ መሆኑ በ1 ቆሮ.10÷2የተገለጸ ሲሆን ባሕሩን ያቋረጡት ዐዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናትም ጭምር ናቸው፡፡ ከባርነት ከፈርዖን አገዛዝ ነፃ የወጡት ሕፃናቱም ጭምር ናቸው፡፡

እሥራኤል ከበኲረ ሞት የዳኑበት የአንድ ዓመት ጠቦት በግ ደግሞ ምሳሌነቱ የጌታ መሆኑ የታወቀ ሲሆን በዚያን ጊዜ በበጉ ደም አማካኝነት ከሞት የዳኑት የታዘዙትን እሺ ብለው የፈጸሙት ዐዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የእነርሱ ልጆችም ጭምር ናቸው፡፡ እንግዲህ በወላጆቻቸው እምነት ሕፃናቱ መዳናቸውን ልናስተውል ይገባናል፡፡

ስለዚህ ሕፃናት በአእምሮ ባልበሰሉበትና ስለጥምቀታቸው አምነው ተቀብያዋለሁ ሳይሉ የሚደረገው ጥምቀት እውነተኛ ጥምቀት አይደለም የሚሉ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከላይ እንደተገለጸው ሁሉ መሳሳታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

እግዚአብሔር ሰውን ይመርጣል እንጂ ሰው እግዚአብሔርን አይመርጥም፡፡ ራሱ ባለቤቱ እንዳስተማረው ሁሉ #እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም$ ብሏል (ዮሐ.15÷16)፡፡ ድኀነት በእግዚአብሔር ቸርነት የሚገኝ እንጂ በሰው ትምህርትና ዕውቀት የሚሸመት ወይም የሚገበይ ዕቃ አይደለም፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ሕፃናትን ማጥመቋ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደሙት አበው ባገኘችው ትምህርት መሠረት ነው፡፡

ክፍል -3 ይቀጥላል - ይቆየን

ምንጭ: የዲ/ን መልአኩ አዘዘው ገጽ 

ምሥጢረ ጥምቀት


ክፍል-1

ሀ-አስፈላጊነት

መጠመቅ ማለት መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነት የሚሰጥበት እና የኃጢአት ሥርየት የሚገኝበት ምሥጢር ነው፡፡

1.      ድኀነትበጥምቀትነው፤

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ያልተጠመቀ ሰው አይድንም፡፡ የተጠመቀ ግን እንደሚድን በመዋዕለ ትምህርቱ እዲህ ሲል አስተምራል #ያመነ የተጠመቀም ይድናል$ ማር.16 ቁ 16፡፡ ያመነ ይድናል ብቻ አለማለቱን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ጥምቀት ለድኀነት ባያስፈልግ ኖሮ ጌታ ያመነ የተጠመቀም ይድናል ባላለ ነበር፡፡

2. በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንወለዳለን፤

ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ በሌሊት ወደ ጌታ ዘንድ ሊማር በሄደ ጊዜ ጌታ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› አለው፡፡ ይህ የጌታ ትምህርት ለኒቆዲሞስ ስለረቀቀበትና ስለተቸገረ ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኀፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

ዳሩ ግን ዳግም ልደት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መሆኑን ጌታችን እንዲህ ሲል አስተምሮታል ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም (ዮሐ. 3÷3-6)፡፡

ከጌታችን ትምህርት የምንገነዘበው በሚታይ ሥርዓት በውኃ በሚደረገው ጥምቀት አማካኝነት ከሥላሴ ልጅነት ካላገኘን በስተቀር እንኳን መንግሥተ ሰማያት ልንገባ ልናያትም እንደማንችል ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ከውኃና ከመንፈስ መወለድ›› ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡

ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ›› አለ እንጂ ‹‹መቼ ካልተጠመቀ›› አለ ብለው ለመከራከር ይከጅሉ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን አስተዋይ አእምሮ ያለው ሰው #ከውኃና ከመንፈስ መወለድ$ ማለት መጠመቅ ማለት እንደሆነ አይጠፋውም፡፡

 ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኀፀነ ዮርዳኖስ ዳግም የምንወለደው በጥምቀት ነው፡፡ መወለድ ከእናት ማኀፀን መውጣት እንደሆነ ሕፃኑም ከውኃው ጠልቆ ይወጣልና፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጥምቀት የሚገኘውን ጸጋና ክብር ለቲቶ ሲገልጽለት ‹‹ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደድ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም›› ብሏል (ቲቶ. 3÷5)፡፡ ‹‹ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብ›› ማለቱ ጥምቀትን ማለቱ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲሁም ለኤፌሶን ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ በጻፈው ክታቡ ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ…›› በማለት በጥምቀት አማካኝነት ምእመናን መንጻታቸውንና መቀደሳቸውን አስተምሯል (ኤፌ 5.26)፡፡

3. በጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ይገኛል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታን ከማሳደድ ተመልሶ የእርሱ ምርጥ ዕቃ ሊሆን በተጠራ ጊዜ ሐናንያ እንዲህ ብሎታል፡፡ ‹‹አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፡፡ ከኃጢአትህም ታጠብ›› (የሐዋ.22÷16)፡፡ በዚህ መሠረት መጠመቁም ተገልጾአል (ሐዋ.9÷15-16)፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን? ታላቁ ሐዋርያ ከኃጢአቱ የነጻውና የተቀደሰው በእምነቱ ብቻ ሳይሆን አምኖ ጥምቀትን በመፈጸሙ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ኃጢአቱ የተወገደለት ሐዋርያ እንዲሆን በተጠራ ጊዜ ሳይሆን ‹‹የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ በተጠመቀ$ ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ድኀነት የሚገኘው በጥምቀት መሆኑን እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከእናንተ አንዳንዶች እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል (1ቆሮ.6÷11)፡፡ በበዓለ ሃምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ልቡናቸው ከተመሰጠው አንዳንዶቹ ‹‹ምን እናድርግ?›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን ያሳውቃቸው ዘንድ በጠየቁት ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የመለሰላቸው ‹‹ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› የሚል መልስ ነው (ሐዋ.2÷37-38)፡፡

4. እምነት መሠረት ነው፡፡ ፍጹም የሚሆነው ግን በጥምቀት ነው፡፡

እምነት ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ ‹‹እመኑ ብቻ ኃጢአታችሁ ይሠረይላችኋል›› ባላቸው፣ እንዲጠመቁም ባላስገደዳቸው ነበር፡፡ በሃይማኖት ጸሎታችንም ‹‹ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› የምንለው በዚህ መሠረት ነው፡፡

5-በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አብረን እንሞታለን ከእርሱም ጋር እንነሣለን፡፡

ማንኛውም ክርስቲያን በማናቸውም ነገር ክርስቶስን ሊመሰል ይገባዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔን ምሰሉ›› ብሏልና፡፡ ስለዚህ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን ሮሜ.6÷ 8፡፡

በጥምቀት ከጌታ ጋር አብረን ልንሞትና ልንቀበር ያስፈልጋል፡፡ እንዴት? ቅዱስ ጳውሎስ የዚህን መልስ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› (ሮሜ.6÷3-4)፡፡ ወደ ቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱም ላይ ‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ›› ብሏል (ቆላ.2÷12)፡፡

ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት አንድንኖር እናምናለን ሮሜ.6÷8፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በጥምቀት ከጌታ ጋር መቀበራችንን ለማረጋገጥ አጥማቂው ካህን ተጠማቂውን በተጠራቀመ (ለመጠመቅ በተሞላ) ውኃ ውስጥ መላ አካሉን በማጥለቅ ነው የሚያጠምቀው፡፡

6-. በጥምቀት አዲስ ሕይወት ይገኛል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያረጋግጥ ‹‹እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› ብሏል (ሮሜ.6÷4)፡፡ የቀደመው በኃጢአት ምክንያት ያደፈ ሰውነታችን የሚታደሰው፣ የሚቀደሰውና አዲስ ሕይወትን የምናገኘው በጥምቀት ነው፡፡

7-. በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን ሲያስትምር ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና ገላ.3÷27፡፡ በጥምቀት በደሙ ከዋጀን ከፈጣሪያችን ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ በተጠመቅን ጊዜ አዲሱን ሕይወት እንጎናጸፋለን፤ ፈጣሪውን መስሎ በተፈጠረው በቀድሞው ሰው በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረውን ንጽሕናና ቅድስና እናገኛለን፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያደለውን አዲሱን ሰውነት የምንለብሰውና የክርስቶስ ተከታዮች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡

8-    በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባል እንሆናለን፡፡

በዘመነ ኦሪት የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመሆን መገረዝ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነበር፡፡ አሕዛብ በቁልፈት፣ እስራኤል በግዝረት ይለዩ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአብርሃም ልጆች ሁሉ በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ ሕግ የወጣው፡፡ ግዝረት ደግሞ ሊመጣ ላለው ለጥምቀት ምሳሌ ነው (ቈላ. 2÷11-13)፡፡

ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃል ኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደሆነ ሁሉ፤ ጥምቀትም በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሚገኘው ጸጋ ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆናችን ይረጋገጣል፡፡

ለ-የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን እንደነበሩት እንደ አይሁድና እንደ ዮሐንስ ያለ ጥምቀት አይደለም፡፡ አይሁድ ትዕዛዘ ኦሪትን ለጣሰ ሰው ይደረግ የነበረ የውኃ መታጠብ ነው፡፡ ከርኵሰት የሚነጻው በውኃ በመታጠብ ነበር (15÷1-18)፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ደግሞ የንስሐ ነበር (ማቴ.3÷5 እና 6)፡፡

ጌታ በዮሐንስ እጅ በባሕረ ዮርዳኖስ የተጠመቀው እንደ አይሁድ ሥርዓት ለመንጻት እንደ ዮሐንስም ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት አልነበረም፡፡ ዳሩ ግን ስለሚከተሉት ምክንያቶች ተጠምቋል፡፡

1ኛ. ትሕትናንለማስተማር

በአገልጋዩ (በፍጡሩ) በዮሐንስ እጅ መጠመቁ መምህረ ትሕትና መሆኑን ይገልጣል፡፡

2ኛ. ለእኛ አርአያ ለመሆን

ሁለተኛም በጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሔር ለምንወለድ ለእኛ አርአያ ለመሆን ሊጠመቅ በቅቷል፡፡

3ኛ. ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ ደብቆት የነበረውን የዐዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ፡፡

4ኛ. አንድነቱንና ሦስትነቱን ለማግለጥ

በብሉይ ኪዳን በተለያየ ኀብርና ምሳሌ የነበረውን አንድነቱንና ሦስትነቱን ለመግለጥ ጌታ ተጠምቋል፡፡ ‹‹ሰማያት ተከፈቱ›› የሚለው አነጋገር ሥውር የነበረው ይህ ምሥጢር መገለጡንና ገሃድ መውጣቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ የተዘጋ ቤት ሲከፈት በውስጥ ያለው የተሠወረው እንደሚታይ ሁሉ ከሰው ከእምሮ ረቅቆ የነበረው የሥላሴ ምሥጢርም በጌታ ጥምቀት መገለጡን ያረጋግጣል፡፡ በዚህም ጊዜ የክርስቶስ እውነተኛ አምላክነት በባሕርይ አባቱና በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ተመስሯል፡፡

ምንጭ: ዲ/ን መልአኩ አዘዘው ገጽ 

ሕይወት ዕድል ወይስ ምርጫ

ዕድል ሰዎች እንደሚሰጡት ትርጉም እነርሱን አድራሻ አድርጐ የሚመጣ፣ ያላሰቡትና ያልጠበቁት በረከት፣ በመንገዳቸው ፊት ለፊት የቆመ ማዕድ ማለት ነው፡፡ ሕይወት ግን በቋሚነት የተዋቀረችው በዕድል ሳይሆን በምርጫ ነው፡፡ ሕይወት ዕድል አይደለችም የምንለው፡-

1.             ማንኛውም ፍጥረት በአጋጣሚ ስላልተገኘ፣

2.            እግዚአብሔር ትእዛዝን ለሰው በመስጠቱ፣

3.            የሰው ልጅ ተጠያቂነት ያለውን ሕይወት በመቀበሉ፣

4.            እግዚአብሔር በሰው ጥፋተኝነት ላይ ብይን መስጠቱ ነው፡፡

1.          ማንኛውም ፍጥረት በአጋጣሚ አልተገኘም

በእግዚአብሔር ዕቅድና ዓላማ የሚታየውና የማይታየው ዓለም ተፈጥሯል፡፡ በስህተት የተገኘ፣ ቀስ በቀስም በማደግ ለዚህ የደረሰ ፍጥረት የለም፡፡ ፍጥረቱ በራሱ ላይ ካለው ዓላማ እግዚአብሔር በፍጥረት ላይ ያለው ዓላማ ይበልጣል፡፡ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ትርምስ የሚከሰተው በአጋጣሚ ያልተገኘውን ሕይወት በአጋጣሚ ስንኖረው ነው፡፡ ዕድል የምንለው አጋጣሚ፣ ራሱን በራሱ ለእኛ የናኘ ስጦታ ነው፡፡ እንዲህ የሚባል ቸር የለም፡፡ የስጦታ ሁሉ ባለቤት እግዚአብሔር ነው /ያዕ. 1÷17/፡፡ ሕይወትን ዕድል ስናደርጋት አጋጣሚ እናደርጋታለን፣ ከዚህ ሁሉ በላይ የእግዚአብሔርን ሰጪነት እንቃወማለን፡፡

2.         እግዚአብሔር ትእዛዙን ለሰው መስጠቱ

ሕይወት ረግጠን የምናያት ሳትሆን ዓይተን የምንረግጣት ናት፡፡ ዓይቶ ለመርገጥ ይረዳ ዘንድም እግዚአብሔር ትእዛዝን ለሰዎች ሰጥቷል፡፡ ሰዎች ጠጪነታቸውን፣ ሱሰኝነታቸውን ሳይቀር የ40ና የ80 ቀን ዕድሌ ነው ይላሉ፡፡ ጽድቅና ኃጢአት ግን ምርጫ እንጂ ዕድል አይደሉም፡፡ ሕይወት ወደ ወሰደችን የምንከተላት ሳትሆን ተምነን የምንጓዛት ናት፡፡ ለዚህም ትእዛዝ ተሰጥቶናል፡፡

3.         የሰው ልጅ ተጠያቂነት ያለውን ሕይወት መቀበሉ

ትእዛዝ የሚወጣው ሥልጣን ካለው አካል ነው፡፡ ሥልጣን ያለው አካል ደግሞ በትእዛዙ መሠረት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሔር ትእዛዝን ሰጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ተላላፊ የሆኑትን አዳምንና ሔዋንን እንዲሁም ቃየንን ጠይቋል፡፡ ሕይወት ዕድል ብትሆን ኖሮ ተጠያቂነት ባልኖራት ነበር፡፡ የመጣብን ነገር ነው፣ የማንለውጠው ምርጫ ነው እያልን በኃጢአታችን በተዝናናን ነበር፡፡ ሕይወት ግን ተጠያቂነት ስላላት በዘፈቀደ የምንጓዝበት ዕድል አይደለችም፡፡

4.         እግዚአብሔር በሰው ጥፋተኝነት ላይ ብይን መስጠቱ

ዕድል የሚባል የማንፈልገውን በረከት የሚያጥለቀልቀን፣ ዕድል የሚባል የማንፈልገውን ኃጢአት የሚያሸክመን ነገር የለም፡፡ እግዚአብሔር መርጠን የምንከተለውን ሕይወት ሰጥቶናል፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ለመልካም ሥራችንም ሆነ ለክፉ ሥራችን ብይን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ብይን የሚሰጠው ሕይወት ዕድል ሳትሆን ምርጫ ስለሆነች ነው፡፡

         ሕይወት የመዝራትና የማጨድ ሕግ ናት፡፡ ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው ሲባል ሁልጊዜ ለክፉ የምንጠቀምበት ነው፡፡ በመልካም ነገርም የምናጭደው የዘራነውን ነው፡፡ መልካም ነገርም ክፉ ነገርም ሁለቱም ዘር ነው፡፡ ዘር ከሆነ ሁለቱም ይታጨዳል፡፡ በመዝራትና በማጨድ ድንጋጌ ውስጥ ሦስት ቋሚ ሕጐች አሉ፡-

1.             የዘራነውን የሚመስል እናጭዳለን፡- ስንዴ ዘርተን በምንም መንገድ ገብስ አናጭድም፡፡ ስንዴ የዘራ የሚያጭደው ስንዴ ነው፡፡

2.            ከዘራነው በላይ እናጭዳለን፡- ኪሎ ስንዴ የዘራ ገበሬ በዓመቱ የሚያጭደው የዘራውን ያህል አይደለም፡፡ ከዘራው በላይ ያጭዳል፡፡ ምርት የተትረፈረፈ ነው፡፡ ቃሉ፡- “ነፋስን ዘርተዋል÷ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ” ይላል /ሆሴዕ 8÷7/፡፡

3.            ማንኛውም ዘር የአጨዳ ዘመን አለው፡- አንዳንዱ ዘር እንደ ወር ጎመን በወሩ፣ ሌላው እንደ ገብስ በ3 ወር፣ ሌላው እንደ ጤፍ በስድስት ወር ይታጨዳል፡፡ አንዳንድ ፍሬ ደግሞ በሃያ ዓመት፣ በስድሳ ዓመት ይደርሳል፡፡ መኸሩ ግን አይቀርም፡፡ አንዳንድ ሰው ሲያጠፋ በዕለት ይቀጣል፣ ሌላው ደግሞ ከሃያ ዓመት በኋላ መኸሩ ይደርስበታል፡፡

ሕይወት የመዝራትና የማጨድ ሕግ ከሆነ ሕይወት ዕድል አይደለችም፡፡ በባዶ ሒሳብ ላይ ቼክ ብንፈርም ወንጀል እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም ያላስቀመጥነውን መልካምነት መፈለግ ወንጀል ነው፡፡ የምናጭደው የዘራነውን የሚመስል መሆኑን ማሰብ አለብን፡፡

ጌታችን እግሩ ሥር ተቀምጠው ለሚማሩት ይሟገትላቸዋል፡፡ በሌሎች ዘንድ የሚታዩት ሥራን የሚሸሹ፣ ሥራ ፈት ተደርገው ነው፡፡ ማርታ ስለ እህቷ ስለ ማርያም ያለችው ይህን ነው፡፡ ጌታ ግን የሰጠው ምላሽ፡- “ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” የሚል ነው /ሉቃ. 10÷42/፡፡ በዚህ ምላሽ ውስጥ፡-

1.             የእግዚአብሔርን ነገር ወደን ካልጣልነው ማንም ሊወስድብን አይችልም፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፡- “ሰዎች ስምህን ሊያጠፉ ይችሉ ይሆናል፣ የራስህን ጠባይ የምታጠፋው ግን አንተ ብቻ ነህ” ብሏል፡፡ ጌታም የማይሰርቁብን መክሊታችን መሆኑን አባቶች ገልጠዋል፡፡

2.            መልካም ዕድል የምንመርጠው ነው፡፡ “መልካም ዕድል ፈልጐን የሚመጣ ሳይሆን የምንመርጠው ነው፡፡

ሕይወት ዕድል ሳትሆን ምርጫ ናት ብለናል፡፡ በሕይወት ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር የሚሰጠን መልካም የሥራ አጋጣሚ አለ፡፡ ጌታችን ይህን ሲገልጥ፡- “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች” ብሏል (ዮሐ.9÷4)፡፡ ጌታ ቀን ያለው የሥራ ጊዜን ነው፡፡ ጌታ መሥራት የሚቻልበትን ዘመን “ቀን” አለው፡፡ ያልፋል ማለት ነው፡፡ ቀን በሌሊት ይተካልና፡፡ አንድ ባለሥልጣን ፊት ሆኜ ይህን ጉዳይ አሳውቅልን አሉኝ፡፡ እኔም በእንዲህ ያለ ግንኙነት ከሹም ጋር መቀራረብ አልፈልግም፣ ወንጌሌን ያረክስብኛል አልኩኝ፡፡ የሰማሁት ድምፅ ግን፡- “መናገር በሚደመጡበት ዘመን ነው፣ አሁን እርሳቸው የሚሰሙት አንተን ነው” አሉኝ፡፡ አሳቡን ወደድኩት፡፡ አዎ መናገር በሚደመጡበት ዘመን፣ መሥራት በሚቻልበት ጊዜ ነው፡፡ ጆሮ የምንነፈግበት ዘመን ይመጣል፡፡

ለፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን ከተላለፈ የተስፋ ቃል አንዱ፡- “እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንም ሊዘጋው አይችልም” የሚል ነው (ራእ. 3÷8)፡፡ የተከፈተ በር የሥራ ዘመን፣ የምንማርከው ትውልድ ነው፡፡

አንድ በንጉሡ ዘመን የተጻፈ መጽሐፍ ላይ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፎቶ ሥር፡-

“አገሬ ኢትዮጵያ ጠንክረሽ ተማሪ

ሁልጊዜ አይገኙም ዕድልና መሪ” ይላል፡፡

ሁለቱ ገጥመው አይገኙም፡፡ ሁለቱ ከገጠሙ ብዙ ታላላቅ ሥራ ይሠራል፡፡

እግዚአብሔር በሕይወት ላይ ልዩ አጋጣሚዎችን ይሰጣል፡፡ እነርሱም፡-

1.             ንስሐ

2.            ትምህርት

3.            የሚመክሩን ሰዎች

4.            የዕረፍት ጊዜ

1-     ንስሐ፡- እግዚአብሔር በግብፅ ላይ ዐሥር መቅሰፍት ያወረደው ኃይሉን በመግለጥ ከፈርዖን ጋር ለመወዳደር አልነበረም፡፡ ለፈርዖንና ለግብፃውያን የንስሐ ዕድል እየሰጠ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የንስሐ ዕድል (መልካም አጋጣሚ) ይሰጣል፡፡ እርሱ ማንም ይጠፋ ዘንድ ፈቃዱ አይደለምና፡፡ ንስሐ ዕድል ከሆነ ይወሰዳል፡፡ ብዙ ሰዎች ንስሓን በማንኛውም ጊዜ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ንስሓ ግን ዕድል ነውና ይወሰዳል፡፡ ንስሓ የምንገባው የንስሓ መንፈስ ሲሰጠን ነው፡፡ እግዚአብሔር የንስሓ ድምፅ ሲያመጣ መንፈሱንም አብሮ ይልካል፡፡ ሰውዬው ወዲያው ታዝዞ ንስሓ ቢገባ መንፈሱ ያግዘዋል፡፡ ነገር ግን ከዘገየ መንፈሱ ይሄዳል ትእዛዙ ይቀራል፡፡ ደጋግመን የንስሓን ድምፅ ከገፋን በመጨረሻ እግዚአብሔር እንደ ፈርዖን ልባችንን በማጽናት ለቅጣት ያመቻቸናል፡፡

2-    ትምህርት፡- ስለ ትምህርት በተነሣ ቁጥር “የትምህርት ዕድል” የሚል ቃል አብሮ ይጠቀሳል፡፡ ትምህርት ዕድል ነው፡ እግዚአብሔር መንፈሳዊ መምህራንን ሲሰጠን ቃሉ እንደ ካፊያ ሲወርድ ይህ ትልቅ ዕድል ነውና መጠቀም ይገባናል፡፡ አሊያ ካልተጠቀምንበት ይወሰዳል፡፡

3-    የሚመክሩን፡- ምክር በብዙ ገንዘብ በሚሸጥበት ዘመን ላይ ያውም የሕይወት ምክር የሚመክሩን እግዚአብሔር የሰጠን ልዩ አጋጣሚ ነውና፡፡ ልንጠቀምባቸው ይገባናል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የአንድ ሽማግሌ ሞት የትልቅ ቤተ መጻሕፍት መቃጠል ነው እንደሚባለው በትምህርት ቤት የማይገኙ በጐ ዕውቀቶች የሚሰጡንን መምህራን ማክበርና መጠየቅ ይገባናል፡፡

4-   የዕረፍት ጊዜ፡- ብዙ ጊዜ ከ21 -30 ባለው ዕድሜ እግዚአብሔር የዕረፍት ዘመን ይሰጣል፡፡ ወጣቶች ትምህርት ጨርሰው ያለ ሥራ ያለ ወዳጅ የሚሆኑበት ጭው ያለ ጊዜ ይገጥማቸዋል፡፡ ጉዳዩ ምን እንደሆነ አይረዱም፡፡ ቀጣዩ ጉዞ ፌርማታው ረጅም የሆነ በረራ ነውና እግዚአብሔር የማንበብያና የጽሞና ጊዜ እየሰጣቸው እንደሆነ ስለማይረዱ በጭንቀት ያልፋሉ፡፡ የጽሞና ጊዜ ማጣት ከባድ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚነግረንን ምክር ተቀብለን ይህን የጽሞና ጊዜ ካላበጀን በስደት፣ በበሽታ፣ በእስር ቤት በመክተት ብቻችንን ያገኘናል፡፡

የእስራኤል ልጆች ከተሰጣቸው ትእዛዝ አንዱ ስድስት ዓመት ሠርተው በሰባተኛው ዓመት ማረፍ፣ ለምድሪቱ ሰንበት መስጠት ነው፡፡ እነርሱ ግን ይህን ትእዛዝ መጠበቅ አቅቷቸው በስስት ለ490 ዓመታት ያህል ባዘኑ ምድሪቱንም አላሳረፏትም፣ በስድስተኛው ዓመት በረከት ሰባተኛውን ዓመት የሚያኖረውን ጌታ ማየት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የባቢሎንን ምርኮ አመጣ፡፡ የባቢሎን ምርኰ 70 ዓመት ነው፡፡ የ490 ዓመታት ሰንበት 70 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ቃሉ፡- “በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፣ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሰንበትን አገኘች” ይላል (2ዜና 36÷21)፡፡

በሕይወታችን ማረፍ አቅቶን እኔ ስቆይ ሁሉም ነገር ይቆማል በሚል አሳብ እንቅበዘበዛለን፡፡ ምናልባት ዛሬ በእስር፣ በስደት፣ በበሽታ የምናልፈው የኖርነውና የምንኖረው በራሳችን ሳይሆን በእግዚአብሔር መሆኑን እንድናስተውል ነው፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር ብቻችንን ሊያገኘን ስለወደደ ነው፡፡ ወዳጅ የብቻ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ወዳጃችን ነውና የብቻ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በፍቅር ሲጠይቁን እምቢ ካልን ቆም አድርጎ ጊዜውን ይወስዳል፡፡

እንግዲህ ተፈጥሮ ለእኛ እንጂ እኛ ለተፈጥሮ አልተበጀንም፡፡ እግዚአብሔር የእኛና የተፈጥሮ አዛዥ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ስንታዘዝ ተፈጥሮ ይገዛልናል፡፡ ተፈጥሮ የምንለው ቀንና ታሪክን የሚጨምር ነው፡፡ ቀኑም ታሪኩም የእኛ እንዲሆን እግዚአብሔርን መያዝ ያስፈልገናል፡፡ ይልቁንም መንፈሳዊ ነገር ምርጫ እንጂ ዕድል ባለመሆኑ ጠንክረን ልንይዘው ይገባል፡፡

በርግጥ ብዙ ሰነፎች በሀብት ሲጥለቀለቁ ብዙ አረጥራጪዎች የከበረ ነገር ሲያገኙ እናያለን፡፡ አዎ እግዚአብሔር መሥራትም መማርም የሚቸገሩትን ይረዳቸዋል፡፡ ጐበዙ በጉልበቱ ሲቆም እግዚአብሔር ደግሞ ደካማውን ያግዛል፡፡ ዕድል የምንለው ብዙ ጊዜ ገንዘብን በመሆኑ ወይም ምድራዊ ነገር ብቻ በመሆኑ አስተሳሰባችን የወረደ ነው፡፡ ይህ ዓለም የተበጀው ለመንፈሳዊ ዓላማ ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊውን ነገር አክብረንና አልቀን መያዝ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ይህን ዓለም ከመፍጠሩ በፊት ያየው የከተሞችን ዕድገት ሳይሆን የቅድስና ኑሮአችንን ነው፡፡ እግዚአብሔር ያየልንን ስንኖር ቤታችን መሠራት ይጀምራል፡፡ ቤትን ጥረትና ምኞት ብቻ አይገነባውም፡፡ ቤተ ሠሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ እኔ ላንተ ቤት፣ አንተ ለእኔ ቤት ሥራ ልንል ይገባናል፡፡ ሕይወት ምርጫ ናትና አሁን እንምረጥ!   

የ36ቱ ቅዱሳት አንስት ስም ዝርዝርና የሚውሉበት ቀን

የ36ቱ ቅዱሳት አንስት
ስም ዝርዝርና የሚውሉበት ቀን

1. ኤልሳቤጥ የካቲት 16 ቀን
2. ሐና መስከረም 7 ቀን
3. ቤርዜዳን ወይም ቤርስት ታህሳስ 10 ቀን
4. መልቲዳን ወይም ማርና ጥር 4 ቀን
5. ሰሎሜ ግንቦት 25 ቀን
6. ማርያም መቅደላዊት ነሐሴ6 ቀን
7. ማርያም እንተ እፍረት እህተ አልአዛር የካቲት 6 ቀን
8. ሐና ነቢይት የካቲት 20 እና ጥቅምት 6 ቀን
9. ማርያም እሞሙ ለደቂቅ ዘብድዎስ ጥር 18 ቀን
10. ሶፍያ (በርበራ) ጥር 30 ቀን
11. ዮልያና (ዮና) ኅዳር 18 ቀን
12. ሶፍያ (መርኬዛ) ጥር 30 ቀን
13. አውጋንያን (ጲላግያ) ጥቅምት 11 ቀን
14. አርሴማ ግንቦት 11 ቀን
15. ዮስቲና ጥር 30 ቀን
16. ጤግላ ነሐሴ 6 ቀን
17. አርኒ (ሶፍያ) ኅዳር 10 ቀን
18. እሌኒ ጥር 29 ቀን
19. ኢዮጰራቅሊያ መጋቢት 26 እና ነሐሴ 2 ቀን
20. ቴዎክላ (ቴኦድራ) ጥር 4 ቀን
21. ክርስቲያና (አጥሩኒስ) ኅዳር 18
22. ጥቅሞላ (አሞና) ጥር 30 ቀን
23. ጲስ ጥር 30 ቀን
24. አላጲስ ጥር 30 ቀን
25. አጋጲስ ጥር 30 ቀን
26. እርሶንያ (አርኒ) ጥር 30 ቀን
27. ጲላግያ ጥር 30 እና ጥቅምት 11 ቀን
28. አንጦልያ (ሉክያ) የካቲት 25 ቀን
29. አሞን (ሶፍያ) ጥር 15 አና ነሐሴ 3 ቀን
30. ኢየሉጣ ነሐሴ 6 ቀን
31. መሪና ሐምሌ 27 ቀን
32. ማርታ እህተ አልአዛር ጥር 18 እና ግንቦት 27 ቀን
33. ማርያም የማርቆስ እናት ጥር 30 ቀን
34. ሣራ (ሶፍያ) የይሁዳ እናት ጥር 30 ቀን
35. ዮሐና (ዮላና) የኩዛ ሚስት ታህሳስ 26 ቀን
36. ሶስና ግንቦት 12 ቀን ናቸው፡፡

እነዚህ ጌታችንን ሲከተሉ ግማሾቹ በጉልበታቸው ግማሾቹ አብረው በማደርና አብረው በመዋል ከጌታችን ሳይለዩ አገልግለው በኋላም መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ጊዜ አብረው ስለነበሩ ግማሾቹ ከሐዋርያት ጋር ተከፋፍለው ተሰማርተዋል፡፡